Sunday, October 28, 2018

ሀገር አፍራሽ እንጅ ሀገር ገንቢ ስልጠና አያስፈልገውም

ይህን ጽሁፍ ከጻፍኩት ሰንበት ብሏል። ምናልባት የእኔ እይታ ሚዛናዊነት ይጎድለው ይሆን? የሚል ሃሳብ ብልቤ ይመላለስ ስለነበር ከብዙ ሰዎች ሃሳብ ለመውሰድ ሞክሬያለሁ ይሁን እንጅ ተመሳሳይ ስሜቶች ለማየት ስለቻልኩ ምናልባት ለሚመለከተውን አካል ጥቆማ መስጠቱ ከጉዳቱ ጥቅሙ ያመዝን ይሆናል በሚል ሃሳቤን ለመግለጽ ሞክሬያለሁ።

ከወር በፊት በተለያዩ ሚዲያዎች ይንጸባረቅ የነበረው ሃሳብ የብዙዎችን ቀልብ የሳበ ነበር። አህያውን ፈርቶ ዳውላውን እንዲሉ በቡድን በተደራጀ መልኩ የሰው ህይዎትና ንብረት  ሲያጠፉ የነበሩ ወገኖች ሊሰጣቸው ይገባ የነበረውን የስነ ባህርይ ትምህርት ስለ ሀገር ሰላምና አንድነት ዘብ የቆሙ የአዲስ አበባ ወጣቶችን መንግስት ሰብስቦ በማሰር ስልጠና እየሰጠሁ ነው የሚል መግለጫ ሲሰጥ ስንሰማ ይህ ነገር ከበስተጀርባው የምንፈውራ ችግር ይኖር ይሆንን? ለማለት ተገደናል? አንድ ጤነኛ የሆነ ሰውን ለህመምተኛ የሚታዘዝ መድኃኒት ቢሰጡት ከጥቅሙ ጉዳቱ የከፋ ነው። መድኃኒት የሚያስፈልገው ለበሽተኛ  ነው። ለጤነኛው ቢሰጡት በውስጡ በሽታውን ካላገኘ ሌላ የስሜት ህዋሱን ይጎዳና ለሌላ ችግር ይዳርገዋል።

በጎና ክፉ ቃላት የተናጋሪዎቹን ማንነት በጉልህ የሚያሳዩ በመሆናቸው ልንደነቅ አይገባም።

ሰዎች የሚናገሩትና የምንሰማው ሁሉ ወደ ተግባር የሚለወጥ ቢሆን በህይዎት መኖር የሚችል ፍጥረት ይኖራል ብሎ ማሰብ አይቻልም ነበር። በዓለም ላይ የተናገሩትን መፈጸም የቻሉ ሰዎች በመብራት ፈልጎ ማግኘት ከባድ ነው። በበጎም ሆነ በክፉ ሃሳብ ውስጥ ሆነው ብዙ ተናግረው ነገር ግን አንዱንም መፈጸም ያልቻሉ ብዙ ሰዎችን እናውቃለንና ምስክሮች ነን። ይህን ማድረግ የሚቻለው እግዚአብሔር ብቻ ነው። እስመ አልቦ ነገር ዘይሰአኖ ለእግዚአብሔር ሉቃ 1፥37  

የህይዎት ጉዞውን ለእግዚአብሔር መስጠት ያልቻለ ሰው ከስህተትና ከመሰናክል ሊያመልጥ አይችልም። አንዳንድ ጊዜ ከአቅም ጋር ያልተገናዘቡ ነገሮችን እሽ ብሎ መቀበል እራስን ለፈተና ማጋለጥ ነው። ብዙ ቅዱሳን አባቶቻችን ከእግዚአብሔር ያዘዘ ሹመት ስመጣላቸው ሀገር ጥለው የሸሹ እንደነበር ቅዱሳት መጻህፍት ምስክሮች ናቸው። ምክንያቱ ደግሞ እራሳቸውን ከፈተና ይጠብቁ ዘንድ ነው። እራሱን ከፍ የሚያደርግ  ሁሉ ይዋረዳል ራሱንም የሚያዋርድ ሁሉ ከፍ ይላል ማቴ 23፥ 12 - ሉቃ 14፥11

ቤተክርስቲያን በእግዚአብሔር ፈቃድ እንጅ በፕሮፓጋንዳ አትፈርስም አትሰራም።

ሰሞኑን በሶሻል ሚዲያ እየተናፈሰ ያለውን የአንድ ግለሰብ አመለካከትን የሚያንጸባርቅ ንግግር ብዙዎች ትኩረት በመስጠት ሲቀባበሉት ተመልክተናል። አቶ ጃዋር መሐመድ የሚባል የፖለቲከኝነትና የዘረንነት እንዲሁም የሃይማኖት አክራሪነትን በማንጸባረቅ የሚታወቅ ግለሰብ እንዳለ ግልጽ ነው። ይህንንም ዓላማውን በተለያዩ መድረኮች ባገኘው አጋጣሚ ሲያንጸባርቅ እንደነበር የሚያውቁት ሁሉ ምስክሮች ናቸው።  ታዲያ አሁን ምን አዲስ ነገር ተሰማና ነው ሽብር እየተነዛ ያለው? በጆሮየ ባልሰማውም ቤተክርስቲያን ይፍረስ ብሎ ተናግሯል በሚል ነው መወያያ የሆነው። ጌታ በወንጌል ‘’ከእሾህ ወይን ከኩርንችትስ በለስ ይለቀማልን ማቴ 7፥16’’ ብሎ እንደተናገረው በእኔ መረዳት ከእሱ ንግግር ይልቅ የእሱን እኩይ ዓላማ ለደጋፊዎቹ በማሰራጨት ላይ ያለነው እኛ ነን ቤተ ክርስቲያንን እየጎዳን ያለነው። በረከታቸው ይደርብንና ታላቁ የቤተክርስቲያናችን አባት ብፁዕ አቡነ ጎርጎርዮስ በሁሉ ዘንድ የሚታወቅ ንግግር/ አባባል አላቸው ’’ሥራህን ሥራ” ይህ አባታዊ ምክር ብዙዎችን አንጿል። ዛሬ በየሚዲያው የቤተክርስቲያን ጠላቶች የሆኑ አካላት የሚሰነዝሩትን ቃላት ከምንሰነጥቅ ሥራችንን ብንሰራ መልካም ነው። ቤተክርስቲያን እንኳን ጃዋር የመሃመድ ልጅ መሃመድ እራሱም ቢነሳ አትሸበርም። ጃዋር ስለተናገረ ቤተክርስቲያን ይፈርሳል ብሎ የሚደነግጥ ካለ ጠባቂዋ እግዚአብሔር መሆኑን መዘንጋት ነው።
ጃዋር በጠባብ መንግድ ውስጥ ባገኘው አጋጣሚ ተልእኮውን እየፈጸመ ነው። እኛ ደግሞ እለት እለት የ

Wednesday, September 12, 2018

ሰውና ማንነቱ

ሰው መሆን ከምንም በላይ ክብር የሚገባው ልዩ ማንነት ነው። ቅዱስ መጽሐፍ እንደሚነግረን ምድራዊ ህይዎታችን ጊዜያዊ ነው። ይህም በመሆኑ በምድር ያለው ሁሉ ኃላፊ ነው። ( ድንኳን የሚሆነው ምድራዊ መኖሪያችን ቢፈርስ፥ በሰማይ ያለ በእጅ ያልተሠራ የዘላለም ቤት የሚሆን ከእግዚአብሔር የተሠራ ሕንጻ እንዳለን እናውቃለንና። በዚህ ውስጥ በእውነት እንቃትታለንና፥ ከሰማይም የሚሆነውን መኖሪያችንን እንድንለብስ እንናፍቃለንና 2ኛ ቆሮ 5፥1)  በቋንቋው የሚመካ ካለ ሞኝ ነው። በዓለም ላይ እንግሊዝኛ የሚናገሩ በቢሊዮን የሚቆጠሩ ህዝቦች አሉ ማንነታቸው ግን አይደለም። እምነቱን መሰረት አድርጎ ሌላውን በመግፋት የግል ማንነት እንዲኖረው የሚፈልግ ካለ መንፈሱና ሥጋው የተጣሉበት ማስተዋል የተነሳው መሆን አለበት። አንተ የምታምነው አምላክ የሁሉ ፈጣሪ እንጅ የአንተ የግል ንብረት አይደለም። የትውልድ አካባቢውን መሰረት በማድረግ የነገሌ ዘር ነኝ ብሎ እራሱ ከሌላው ለመለየት አጥር የሚያጥር ካለ በዓለም ውስጥ የተሸነፈ ሰው ነው። ይህ ውሳኔ የሰው ሳይሆን የእግዚአብሔር ነው። ማንም በራሱ ላይ አንዳች ማድረግ የሚችል የለም። ጌታ በወንጌል እንዲህ ብሎ እንደተናገረው   ( ከእናንተ ተጨንቆ በቁመቱ ላይ አንድ ክንድ መጨመር የሚችል ማን ነው? ማቴ 6፥27) 

Friday, August 17, 2018

"ላለፈ ክረምት ቤት አይሰራም"

ዛሬ ላይ ብዙዎች ኢትዮጵያን የመሰለች እናት እያላቸው ማንነት ፍለጋ የሚዋትቱት  በገዛ ሀገራቸው እንደ ባይተዋር በመታየታቸው እንደሆነ ግልጽ ነው። "ላለፈ ክረምት ቤት አይሰራም" እንዲሉ ስላለፈው መጥፎ ነገር ጊዜ ማጥፋት ሞኝነት ነው። መፍትሄው። ያለፈውን በታሪክነቱ መማሪያ አድርጎ ለወደፊቱ  ይህን ክፉ ተግባር የሚፈጽሙ ወገኖችን እድል በመንሳት ታግሎ እኩልነት ማምጣት ብቻ ነው ። አባቶቻችን "በሀገርና በእናት ቀልድ የለም" ይላሉ ታዲያ እግዚአብሔር የኢትዮጵያ ልጆች አድርጎን በሰዎች ምክንያት እንዴት በእናታችን እንደራደራለን?

በግልጽ መታወቅ ያለበት የግል ማንነትና የጋራ ማንነት የተለያዩ ናቸው። በኢትዮጵያ ምድር ለተገኘን ሁላችን ወደድንም ጠላንም ኢትዮጵያዊነት ማንነታችን ነው። ይኽን ማንነት ደግሞ ሰዎች የሰጡን ማንነት ሳይሆን ከእግዚአብሔር ያገኘነው ነው። ይኽን ማንነት በተልካሻ ምክንያት የሚጥል የተሸናፊዎች ሁሉ ተሸናፊ ነው። እናት አንድ ጊዜ ትወልዳለች ለሁልጊዜ እናት ትባላለች። የወለደች እናት እያለች በምንም መስፈርት ሌላዋ እናት ልትባል አትችልም።

ስለዚህ እኛ ዛሬ ከእናታችን ጉያ ለመውጣት የምንፈራገጥ ሁላችን ነገ ምንደኛ ሆነን ለመኖር እየታገልን እንደሆነ እናስብ። እኔ በግሌ ሁልጊዜ ጸሎቴ ኢትዮጵያዊ የሆነ ሁሉ ወንድሜም እህቴም እንደሆነ የማስብበት ህሊና ፈጣሪ አምላክ እግዚአብሔር  እንዳይነሳኝ ነው። ለሁላችንም አስተዋይ ልቦና ያድለን።

Tuesday, August 14, 2018

እኛና እነሱ እየተባባልን እንዴት እንደመር?

አባቶቻችን ስለ ነገሩን ብቻ ሳይሆን ሀገር በተግባሯ እናትን ትመስላለች። የተፈጥሮን ህግ ጥለን እንደ እንስሳት እንሁን ካላልን በቀር የአንድ እናት ልጆች ወንድማማቾች፣ እህትማማች ይባላሉ። ይህን መቀበል የማይፈልግ ትውልድ የአንድ እናት ልጅ ወይም የአንድ ሀገር ህዝብ ሊባል ከቶ እንዴት ይችላል? ብዙ ጊዜ በጎውን ደጋግመን እያወራን ክፉው ነገር አስተዋይ በማጣቱ ከአቅም በላይ እያደገ የመጣ ይመስላል። ጤናማ ያልሆኑ ሃሳቦችን እውነት ነው እያልን ስንቀበል በመኖራችን ዛሬ ላይ ያለነው ትውልዶች የራሳችንን ስንፍና ወደ ጎን በመተው፤ ህይዎታቸውን ያለ ስስት ለሀገራቸው በመስጠት ሀገር ያስረከቡንን አባቶቻችንን ሽቅብ የምንራገም ተስፋ አልባ፣ ወደ ኋላ እንጅ ወደፊት ማየት የማንችል ትውልዶች ሆነናል። Where is Ethiopia?

Monday, August 6, 2018

ፈጥኖ ደራሽ መንግሥት እንዲኖረን እመኛለሁ

ይህን ጽሁፍ ስጽፍ የዶ/ር አቢይን ጥረትና ድካም ከንቱ በማድረግ እንዳልሆነ እንዲታወቅልኝ አደራ እላለሁ። በሱማሌ ክልል የደረሰውን አሰቃቂና ዘግናኝ ድርጊት በማየትና በመስማት ይህን ጻፍኩ።  በሀገራችን ለምን ተመሳሳይ ስህተቶች እንደሚሰሩ እስከ አሁን በግሌ የተረዳሁት ነገር የለም። የትላንቱን እየኮነንን ለምን ዛሬ ከትላንቱ የባሰ ጥፋት እንዲጠፋ እድል እንደምንሰጥም አልገባኝም። በኢትዮጵያ ምድር የሰው ህይዎት ክቡር መሆኑ ታምኖ ጥበቃ ሲደረግለት ማየት በጣም ነው የናፈቀኝ።

Wednesday, May 30, 2018

ከቀድሞው ይልቅ ያሁኑ ይደንቃል።


የሰው ሃሳብና የእግዚአብሔር መንገድ የተራራቁ በመሆናቸው ብዙ ጊዜ የምንጠብቀው ሳይሆን ያልተገመተው ሲሆን ማየት የተለመደ ነው። እግዚአብሔር ሁሉን አድራጊ በመሆኑ የሚሳነው የለም ነገር ግን ሁሉን የሚያደርግበት ጊዜ አለው። ዛሬ ላይ ሆኘ ምነው አሁን እያየንና እየሰማን ያለነው ነገር ከጥቂት ዓመታት በፊት ሆኖ ቢሆን ለማለት አሰብኩና የእግዚአብሔርን ድንቅ ሥራ አለማስተዋል ነው ብየ እራሴን ወቀስኩ። ያለፈው ኃዘን ባይኖር የዛሬው ደስታ የለም። ትላንት መስዋእት የሆኑ ሰዎች ባይኖሩ የዛሬው ሰላም ትልቅ ቦታ አይሰጠውም ነበር። ሁልጊዜም አንዱ እየቀለጠ ለብዙዎች ማብራቱ የተለመደ ነው። ለለወደፊቱ አንዱ እየሞተ ሌላው የሚኖርባት ሀገር እንዳትኖረን በጋራ ማሰብ አለብን።

ካለፉት ጥቂት ወራት ወዲህ የሰላም መልእክት በሀገራችን እየጎረፈ ነው።  ይህ የሰላም መልእክት የናፈቀው ህዝብ ሰላምን መስበክ ከናፈቀው መሪ ጋር ሲገናኝ ሰኔና ሰኞ ሆነ ማለት ይህ አይደል? አሁን እየታየ ያለውን የሰላም መንፈስ በቁመተ ሥጋ ሆነው ሳያዩ ላለፉ ወገኖች እጅግ እናዝናለን። የሰላም መንገድ ተሰውራ ብዙዎች አጥፊ ብዙዎች ተጎጅ ሆነው አልፈዋል። ማለፍ የማይቀር ቢሆንም ሰላምን አጥቶ ማለፍ ለየትኛውም ወገን ቢሆን አሳዛኝ ነው። ልበ አምላክ ቅዱስ ዳዊት" "፤ ከክፉ ሽሽ መልካምንም አድርግ፤ ሰላምን እሻ ተከተላትም። " (መዝ 34: 14) እንዳለው ሰላምን ከሁሉ አስቀድሞ መፈለግ ይገባል። አሁንም ለኛ የሚሆን ብዙ ሰላም አለ። ብዙ በረከት የሚገኝበት ሰላም በፍቅርና በመተሳሰብ የሚመጣ በመሆኑ ያለፈውን ክፉ ሃሳብ አስወግደን ወደ ፍቅር እንምጣ። ባለፈው ብዙዎችን አጥተናል ከዚያም አልፎ የሀገሪቱ ህልውና አደጋ ላይ ስለነበር ብዙ ተጨንቀን ነበር። ካጣነው ሁሉ በላይ የሀገር መኖር ከሁሉ ይበልጣልና እግዚአብሔር ይመስገን። ከሰላም እርቀን በነበርንበት ዘመን ያጣነውን ነገር በገንዘብ መተመን አይቻልም። የሰው ህይዎት በገንዘብ አይተመንምና። 

Saturday, May 19, 2018

የጥፋት ርኵሰት በማይገባው ስፍራ ቆሞ ብታዩ፥ አንባቢው ያስተውል ማር 13፥14


አባቶቻችን በአድዋ የፈጸሙትን ጀግንነት እያወሳን የደም ዋጋ የተከፈለበትን ማንነት እየጣልን የምንሄድ ከሆነ አደራ በላ ትውልድ ተብለን በታሪክ እንመዘገባለን። የኛ ትውልድ ይህን ድንበር መጠበቅ ካልቻለ ያለፉት አባቶቻችን በመንፈስ የሚመጣው በግልጽ በመመስከር እንደሚያዝኑብን ለማመን ከባድ አይሆንም። በኛ ዘመን የተበላሸውን ታሪክ የሚወዳደር ዘመን አለብሎ መናገር ዋሾ ያሰኛል። ኢትዮጵያ የሚጠበቅ ታሪክ ያላት ሀገር እንጅ አዲስ ታሪክ የሚሰራላት አይደለችም። የነበራትን ክብር ማስጠበቅ ባለፈው ከተሰራው የጀግንነት ታሪክ ያላነሰ ክብር የሚያሰጥ ተግባር ነው። ይሁን እንጅ የአሁኑ ትውልድ የሚማርክ ሳይኖር በፈቃዱ እጁን እየሰጠ ይመስላል። የሰሞኑ መወያያ ርእስ የሆነው ጉዳይ ጆሮን ጭው የሚያደርግ፣ ኢትዮጵያን ከክብሯ የሚያዋርድ ለብዙዎች መርዶ የሆነ ዜና እየሰማን ነው። የሀገር እድገት፣ የዘመን ስልጣኔ  ሀገራችን ገብቶ ከድህነት ተላቀን በርኃብና በበሽታ የሚያልቀው ወገናችን እግዚአብሔርን አመስግኖ የሚቀምሰው ምግብ ያገኛል ስንል በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ እንዲሉ ሰዶምና ገሞራን በእሳት እንዲጠፉ ምክንያት የሆነው የኃጢአት ርኩሰት ያለምንም ከልካይ አዲስ አበባን እያዳረሳት እንደሆነ እየተሰማ ነው። ችግራችን ዘርፈ ብዙ እንዲሆን ብዙ የሰሩ አካላት ያሰቡት ሁሉ እንደተሳካላቸው እየሆነብን ያለው ነገር በቂ ማሳያ ነው።



Monday, May 14, 2018

የዶ/ር ዓቢይና የስርዓቱ ፍጥጫ

የተስተካከለ መንገድ ካለ በአግባቡ መጓዝ ይቻላል። ወጣ ገባና ኮረኮንች የበዛበት መንገድ እንደ ልብ ሊያራምድ አይችልም። ሥርዓት ሰዎችን ካልጠቀመ ችግር አለበት ማለት ነው። ሥርዓት ያስፈለገው የሰው ልጆችን እኩልነት ለማስፈን መሆኑ የታወቀ ነው። ይህም ሆኖ ሥርዓት አስከባሪ እስካልተገኘ ድረስ ፋይዳ የለውም። ሥርዓት ካለ የሚበደል ሰው መኖር የለበትም። በየስፍራው ሰዎች የመኖር ህልውናቸው የሚገፈፍ ከሆነ ሥርዓቱ ጤነኛ አይደለም ማለት ይቻላል።ሌላው ሥርዓት መኖሩ የሚታወቀው ገዥና ተገዥ ውዴታና ግዴታቸውን ማወቅ ሲችሉ ነው። በሥርዓት ለመምራት ህዝቡን ሥርዓት ማስተማር ተቀዳሚ ተግባር ሊሆን ይገባዋል። ህዝቡ የማያውቀውን፣ ያልተቀበለውን፣ እምቢ እያለ በኃይል የተጫነበትን ተከፋፍሎ የመኖር ሥርዓት ለማስተካከል ጊዜ ባይወሰድ ከሁሉ የተሻለ መልካም ነው። መንግሥት ይህን ማድረክ ከቻለ ግዴታውን ተወጣ ሊባል ይችላል። 

Tuesday, May 1, 2018

"ክፉውን ስለ ክፉ ፈንታ አትመልሱ"


ስለ ክፋት ታሪካዊ አመጣጥ በመጠኑ ለመጠቆም አሰብኩና ምናልባት የክፋት ሰዎችን ቅር ያሰኝ ይሆን የሚል ሀሳብ ጎበኘኝ ነገር ግን ክፋት ምንጊዜም በጎ አያስብምና ወደ ኋላ ትቶ እውነቱን ማሳየቱ የክፋትን ጎጅነት ብዙ ሳይረዱ የክፋት ሰላባ የሆኑ ወገኖቻችን ማንቃት ይገባልና የግል ሃሳቤን ላካፍል ወደድኩ። 

ሰዎች በባህሪያቸው ክፉ ናቸው ከማለት ይልቅ የአንዳንድ ሰው ባህርይ የክፋት አባት ለሆነው ለዲያብሎስ ምቹ ሆኖ ስለሚገኝ የሰይጣን ፈረስ ሊሆን ይችላል ማለቱ ይቀላል። በቅዱስ መጽሐፍ ከሰውም ከእንስሳም ተንኮለኛ የተባሉ አሉ። ነገር ግን ባህርያቸው ሆኖ ሳይሆን የክፋት አባት ለሆነው ለዲያብሎስ ምቹ ሆነው በመገኘታቸው ነው። ለምሳሌ ይሁዳን ብንወስድ; በፊቱ ካለው በረከት ይልቅ ለማይጠቅም ለሚጠፋ ገንዘብ ልቡን ስለከፈተ፦  "፤ ሰይጣንም ከአሥራ ሁለቱ ቍጥር አንዱ በነበረው የአስቆሮቱ በሚባለው በይሁዳ ገባ፤  (ሉቃ22: 3)" ይላል።  እንዲሁም አስቀድሞ በሰው ልጅ ላይ ዲያብሎስ ሞትን ሲያመጣ በእባብ ተመስሎ እንደሆነ አይዘነጋም። "፤ እባብም እግዚአብሔር አምላክ ከፈጠረው ከምድር አውሬ ሁሉ ይልቅ ተንኰለኛ ነበረ። ዘፍ 3: 1)"

Tuesday, April 24, 2018

የሚሰማ መሪ

ከፍጥረታት ሁሉ አወቂና ክቡር ሆኖ የተፈጠረ እንደ ሰው ያለ ፍጡር አልተገኘም። ይህን ክቡርና አዋቂ የሆነ ፍጡር ለመምራት በእውቀትም  ሆነ በችሎታ ልቆ መገኘት ይጠይቃል። ከስነፍጥረት ጀምሮ ያለውን ታሪክ ስናነብ መሪዎች ነበሩ። ምንም እግዚአብሔር መርጦ መሪ ቢያደርጋቸውም በአስተሳሰባቸው ከሚመሩት ህዝብ በታች ሆነው በመገኘታቸው ፍጻሜያቸው ያላማረ ብዙዎች ናቸው። ብዙ ምሳሌ ማንሳት ይቻል ነበር  ነገር ግን በሰው ሁሉ ዘንድ የታወቀ ስለሆነ ወደ ዋናው ሃሳቤ ልግባ።

የተነሳንበት ርእስ የተለያዩ ትርጉሞች ሊሰጥ የሚችል ቃል ስለሆነ በማጥበቅና በማላላት እንዲሁም በመተርጎም ፍሬ ሃሳቡን ማግኘት እንችላለን። ስናጠብቀው ሁሉ የሚሰማው, ሁሉ እሽ በጄ የሚለው እንዲሁም የሚደመጥ ወ ዘ ተ ማለት ሲሆን ስናላላው ደግሞ የሚሰማ,የሚያዳምጥ, ለሃሳቦች ቦታ የሚሰጥ ወ ዘ ተ ልንለው እንችላለን።

Friday, April 6, 2018

በትንሳኤ ላይ ትንሳኤ

ክርስቶስ አንድ ጊዜ ሞቶ የሰውን ልጆች ነጻ ካወጣ በኋላ በክብር ተነስቷል። በዚህም ምክንያት በእርሱ ያመኑ ክርስቲያኖች የትንሳኤውን እለት በየዓመቱ ያከብሩታል። ሞቱን ስናስብ ሞተን እንደነበር እናስባለን ትንሳኤውን ስናከብር ሞተን እንደማንቀር በክብር እንደምንነሳ እንናገራለን። ስለዚህ በእርሱ ያመኑ ሁሉ ሞቱንና ትንሳኤውን ያስቡ ዘንድ ይገባል።

የክርስቶስን ትንሳኤ ከውድቀት ከመነሳት ጋር ብናከብረው እውነተኛ ትንሳኤ ይሆናል። እኛ ሳንነሳ እሱ ተነሳ ብንል ትርጉሙ አልገባንም ማለት ነው። ከክፋት፣ከተንኮል፣ ከምቀንነት፣ ከዘረንነት ወንበር ላይ ተነስተን የፍቅርና የሰላም ዓርማ የሆነውን መስቀሉን ይዘን የክፋት ሁሉ ባለቤት የሆነውን ሰይጣን ዲያቢሎስን ከእግራችን በታች መጣል ካልቻልን የክርስቶስ ትንሳኤ ተካፋዮች እንዴት ልንሆን እንችላለን? ስለዚህ በየደረጃው ያለን ሁላችን አንዱ ጌታ ስለሁላችን ሞቶ ትንሳኤን እንዳጎናጸፈን ከያለንበት የክፋት ባርነት መንፈስ ተላቀን ለመነሳት የሰላምና የፍቅርን ጋሻ ጦር እንልበስ።

Wednesday, April 4, 2018

ክፉ ምክር

እንበለ ደዌ ወህማም እንበለ ፃማ ወድካም አመ ከመ ዮም ያብጽሃነ ያብጽህክሙ ለብርሃነ ትንሳኤሁ በፍስሃ ወበሰላም አሜን። አይሁድ በጌታችን በመድኃኒታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ላይ የሞት ፍርድ ለመፍረድ የመጨረሻውን ምክር ያደረጉት ረቡእ እንደ ሆነ በቅዱስ  መጽሐፍ ተጽፏል። ይሁን እንጅ ከዚያም በፊት በተለያዩ ጊዜያት በእርሱ ላይ ምን እንደሚያደርጉ ሲማከሩ ነበር። በህዝቡ ፊት ያደርገው የነበረው መልካም ነገር ምክንያት አሳጥቷቸው እንጅ ሊይዙት ሲፈልጉ ቆይተዋል። 

የአይሁድ ክፉ ምክርና ጥላቻ ከቅንዓት የመጣ እንደሆነ እስከ ሀገረ ገዥው ጲላጦስ ድረስ የታወቀ ነበር።በዚህም ምክንያት ለሞት አሳልፎ ላለመስጠት ብዙ ሞክሯል። ይሁን እንጅ የእነሱን ፈቃድ ለመፈጸም ሲል እያወቀ አሳልፎ ሰጥቷቸዋል። ትልቁ በደል እንኳን ለሞት የሚያበቃ ለክስ የሚሆን መረጃ እንደሌላቸው እያወቀ ሁከት ስላበዙ እራሱን ነጻ ለማድረግ እጁን ታጥቦ ጌታን ግን አሳልፎ ሰጥቷቸዋል። 

Monday, April 2, 2018

'ነጻነት ከመንግስት ለህዝብ የሚበረከት ስጦታ አይደለም' (ዶ/ር አቢይ አህመድ)

ከእግዚአብሔር ለሰው ልጆች ከተሰጡት ጸጋዎች አንዱ የንግግር ስጦታ ሲሆን በተለይ ለመሪዎች አስፈላጊ መሆኑ አይካድም። ብዙ የእግዚአብሔር ሰዎች ለሰውም ለእግዚአብሔርም የሚመች ንግግር ከአንደበታቸው በመውጣቱ የተጣመመውን ማቅናት ችለዋል። በተሰጠን ጸጋ በአግባቡ ከተጠቀምንበት ዋጋ ይገኝበታል። ብዙዎች ግን ይህን ታላቅ ጸጋ ለክፉ ተግባር ሲጠቀሙበት አይተናል። 

ዶ/ር አቢይን በሚዲያ ስንተዋወቃቸው  ቃል ይገድላል ቃል ይተክላል ብለውን ነበር። በዚህም ምክንያት አብዛኛው የኢትዮጵያ ህዝብ እንዲህ ዓይነት መሪ በሰጠን እያለ ሲመኝ ሰንብቷል። ምኞቱም አልቀረ ቃሉን የተናገሩት መሪ ሆነዋል። በመጀመሪያ የፓርላማ ንግግራቸውም ያንኑ የንግግር ጸጋቸውን ተጠቅመው ተስፋ እርቆት የነበረውን የኢትዮጵያ ህዝብ ተስፋው እንዲለመልም አድርገዋል።

Saturday, March 31, 2018

ፍቱና አምጡልኝ



ወንጌላዊው ማቴዎስ እንደጻፈው ጌታችን አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ወደ ቤተመቅደስ ገብቶ በዚያ የሚሸጡትንና የሚለውጡትን ከመገሰጹ በፊት ከደቀመዛሙርቱ ሁለቱን ልኮ በእስራት ላይ ያሉ አህያና ውርንጭላዋን ፈትተው እንዲያመጡ አዞ ነበር። አትፍቱ የሚላችሁ ቢኖር ለጌታ ያስፈልጉታል በሉ የሚል መመሪያም ሰጥቷቸው ነበር። የሰው ልጆችን ሁሉ ከእስራት ሊፈታ እንደመጣ ሲያጠይቅ ይህን ተናገረ። ለምን ትፈታላችሁ የሚላችሁ ቢኖር ለጌታ ያስፈልጉታል በሉ አላቸው።  እነሱም እንደታዘዙት ለጌታ ያስፈልጉታል ብለው ፈትተው አምጥተውለታል።  ቃሉም እንዲህ ይነበባል " ወደ ኢየሩሳሌምም ቀርበው ወደ ደብረ ዘይት ወደ ቤተ ፋጌ ሲደርሱ፥ ያንጊዜ ኢየሱስ ከደቀ መዛሙርቱ ሁለት ላከ፥እንዲህም አላቸው፦ በፊታችሁ ወዳለችው መንደር ሂዱ፥ በዚያን ጊዜም የታሰረችን አህያ ውርንጫም ከእርስዋ ጋር ታገኛላችሁ፤ ፈትታችሁ አምጡልኝ።ማንም አንዳች ቢላችሁ፦ ለጌታ ያስፈልጉታል በሉ፤ ወዲያውም ይሰዳቸዋል።ለጽዮን ልጅ፦ እነሆ፥ ንጉሥሽ የዋህ ሆኖ በአህያ ላይና በአህያይቱ ግልገል በውርንጫይቱ ላይ ተቀምጦ ወደ አንቺ ይመጣል በሉአት ተብሎ በነቢይ የተነገረው ይፈጸም ዘንድ ይህ ሆነ።ደቀ መዛሙርቱም ሄደው ኢየሱስ እንዳዘዛቸው አደረጉ፥ ማቴ 21፥1"

Friday, March 30, 2018

"ባደርገውም እሞታለሁ ባላደርገውም አልድንም"

ህዝበ እስራኤል በምርኮ ሳሉ በባቢሎን የምትኖር ከእስራኤል ወገነ የሆነች ሶስና የምትባል አንዲት ሴት ነበረች። ይህች ሴት ከልጅነቷ ጀምሮ ህገ እግዚአብሔርን እየተማረች ነበር ያደገችው። እግዚአብሔር ይገድላል እንዲሁም ያድናል የሚለው ጽኑ እምነት የነበራት እና  በምግባሯም እጅግ የተወደደችና የተከበረች ሴት ነበረች። ከዚህም ሌላ እጅግ መልከ መልካምና ማራኪ ውበት ነበራት።  ባሏ ኢዮአቄም የሚባል ከሁሉ የተከበረና ባለ ፀጋ ነበር። በመሆኑም ከአይሁድ ወገን ብዙዎች ለጉዳያቸው ወደ እርሱ ይመጡ ነበር። ከባቢሎን ኃጢአት እንዲጠበቁ ህዝቡን እንመክራለን የሚሉ ሁለት የተሰወረ ተንኮል ያለባቸው ሁለት የአይሁድ መምህራን ነበሩ። እነዚህ ክፉ መምህራን ለኢዮአቄም ባለሟል ነበሩና ሶስናን እለት እለት እየተመለከቱ በዝሙት ፍቅር ወደቁ። አንዱ ለሌላው በልቡ ያለውን ሳይነግር አሳቻ ቦታ እየፈለጉ ሳለ ከቤቷ አቅራቢያ በሚገኘው የአትክልት ስፍራ እንደ ሥርዓቱ ለመታጠብ በሄደች ጊዜ ከሷ ቀድመው ወደ አትክልቱ ስፍራ በመግባት ተሰውረው ስለነበር አገልጋዮቿን አሰናብታ ለመታጠብ ስትዘጋጅ ከተደበቁበት ወጥተው በዝሙት እንድረስብሽ አሏት። ህገ እግዚአብሔርን ጠንቅቃ የምታውቅ በመሆኗ ይህን ኃጢአት እንደማትፈጽም ነገረቻቸው። እነሱ ግን በዝሙት አይናቸው ታውሮ ይህን ካልፈጸመች ያለበደሏ በሀሰት አስመስክረው እንደሚያስገድሏት ነገሯት። እሷም እኒያ አስመሳይ መምህራን ይህን ክፉ ኃጢአት እንድትፈጽም ባስጨነቋት ጊዜ እንዲህ አለች "ባደርገውም እሞታለሁ ባላደርገውም አልድንም" ይህን ብላ ድምጿን አሰምታ ጮኽች በዚያ የነበሩ ሰዎች ሲሰበሰቡ እነዚያ ተንኮለኞች መምህራን አስቀድመው እንደተናገሩት የሀሰት ቃል መናገር ጀመሩ ህዝቡም የመምህራኑን ቃል በመስማት በድንጋይ ተወግራ መገደል አለባት በማለት ተስማሙ። ሊገድሏት ሲሄዱ ያመነችው አምላክ ህፃን ልጅ ልኮ የነዚያን ተንኮለኞች መምህራን ስውር ሴራ ገልጦ በማውጣት የሷን ሞት እነሱ እንዲሞቱ አድርጓል። ያ ሶስናን ከሞት የታደገ ወጣት ነቢዩ ዳንኤል ነበር።  መ. ሶስና ቁ 5

Tuesday, March 20, 2018

እናንተን የጣለ እኔን ይጥላል ሉቃ 10፥16

በኛ ዘንድ የተዋረደውን ሳይሆን ያልተዋረደው ምንድነው ብሎ መጠየቅ ሳይሻል አይቀርም። ኢትዮጵያዊነት ከተኮነነ ሰነባበተ። ለኢትዮጵያ ትልቅ ውለታ ያበረከተችው ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ከተናቀች ውሎ አደረ። መቼም ይህን እውነት አለመናገር በሰውም በእግዚአብሔርም ዘንድ ያስጠይቃል። የትኛው በደል ይሆን ይህን ሁሉ ነገር በአንድ ወቅት ያመጣብን? ሰው ይበድላል። እግዚአብሔር ሊያስተምር እንደሚቀጣም እናምናለን እኛ ግን እየተማርን አይደለም። ሊያስተምረን ያመጣውን መከራ ለጥፋት እያደረግነው ይመስላል።  ኢትዮጵያ የሚለውን ስም መጥራት የማይፈልግ ትውልድ ምድራችን አብቅላ አየን። ሁሉን እንደራሷ ልጆች አድርጋ ፊደል አስቆጥራ፣ መጠለያ ሰጥታ፣ በጎ ምግባር አስተምራ ሀገርን ከነሙሉ ታሪኩ ለዛሬው ትውልድ ያስረከበች ቤተክርስቲያን አንደበታቸው የስድብ አፍ በተመላ ክፉ ትውልዶች ተሰደበች ይህ ያመጣው መርገም ለብዙዎች ተርፎ ሰላም ከራቀን ሰነባበተ።




Saturday, February 10, 2018

እያሰሩ መፍታት



ስለ ዘመናችን የስልጣኔ ደረጃ ስናነሳ ሁላችንም የምንገነዘበው ነገር አለ። ኃያላን መንግሥታት ቀድሞ ከነበራቸው አመለካከት ይልቅ የአሁኑ የተሻለ በመሆኑ የስልጣኔ መሪዎች ይባላሉ። ቀድሞ በኃይል ሁሉን ማሸነፍ የሚችሉ ይመስላቸው ስለነበር የሌሎችን መብት በመግፈፍ በጭቆና ይገዙ ነበር። ዛሬ ላይ ያንን አመለካከት ከመጥላታቸውም በላይ በየጊዜው ሲያወግዙ እንሰማቸዋለን። ምድራዊ ገዥዎች ምንጊዜም ከስህተት የማይርቁ ቢሆኑም የሰውን ልጅ መብት ለማስከበር በየሀገራቸው የሚጥሩ መሪዎች በመኖራቸው በደልና ስቃይ ጎልቶ እንዳይወጣ ለማድረግ ችለዋል።

Monday, January 22, 2018

በሥጋ እየሞትን በመንፈስ እየኖርን እግዚአብሔርን እናመልካለን።



ትላንት የተከበረው የጥምቀት በዓል በሀገራችን በኢትዮጵያ እና በሌችም ሀገራት የነበረው ገጽታ ደስታም ሀዘንም የቀላቀለ ነበር። የበዓሉን አከባበር በተለያዩ መገናኛዎች ስንመለከት በደስታ አክብረው ወደ ቤታቸው የተመለሱ እንዳሉት ሁሉ ህይዎታቸውን ያጡና በሀዘን በለቅሶ ላይ ያሉ ወገኖቻችን እንዳሉ ለማየት ችለናል። የሚገርመው ከዚህ ቀደም የክርስቲያኖች ደም ሲፈስ የነበረው በአረቡ ሀገራት ነበር። የአሁኑ ግን የተገላቢጦሽ በአረብ ኢምሬትስ በሰላምና በደስታ በድምቀት ሲያከብሩ ባየንበት ዓይናችን የክርስቲያን ደሴት በተባለችው ኢትዮጵያ የወጣቶች ደም ሲፈስ፣ የእናቶች እንባ ሲረጭ፣ የቃልኪዳኑን ታቦት በተሸከሙ ካህናት ላይ የአድማ መበተኛ ጭስ ሲወረወር ለማየት በቃን።

ይህ ነገር በእኔ መረዳት የቤተክርስቲያንን ሥም ለማጉደፍ የተሰራ ተንኮል እንደሆነ ይሰማኛል። በየእለቱ ስለ ዓለም ሰላም የምትጸልይና የምታስተምር ቤተክርስቲያን ሰላም አስከባሪ ምን ያደርግላታል?። ሰበብ ተፈልጎ የንጹሃንን ደም ለማፍሰስ ታስቦ የተደረገ ይመስላል። እኛ ስናውቅ የኢትዮጵያ ፓሊሶች በጥምቀት እለት እንኳን መሳሪያ ተኩሰው ሰው ሊገድሉ ይቅርና በራሳቸው ያለ ኮፍያ አውልቀው ከህዝቡ ጋር የሚዘምሩ ነበሩ። ታቦት የተሸከሙ ካህናት ላይ የሚተኩስ ኢትዮጵያዊ እያፈራን ነው ማለት ነው? እንንኳን ከርስቲያኑ ሙስሊሙ ለእግዚአብሔር ታቦት ክብር ይሰጥ እንደነበር እናውቃለን።