Saturday, May 19, 2018

የጥፋት ርኵሰት በማይገባው ስፍራ ቆሞ ብታዩ፥ አንባቢው ያስተውል ማር 13፥14


አባቶቻችን በአድዋ የፈጸሙትን ጀግንነት እያወሳን የደም ዋጋ የተከፈለበትን ማንነት እየጣልን የምንሄድ ከሆነ አደራ በላ ትውልድ ተብለን በታሪክ እንመዘገባለን። የኛ ትውልድ ይህን ድንበር መጠበቅ ካልቻለ ያለፉት አባቶቻችን በመንፈስ የሚመጣው በግልጽ በመመስከር እንደሚያዝኑብን ለማመን ከባድ አይሆንም። በኛ ዘመን የተበላሸውን ታሪክ የሚወዳደር ዘመን አለብሎ መናገር ዋሾ ያሰኛል። ኢትዮጵያ የሚጠበቅ ታሪክ ያላት ሀገር እንጅ አዲስ ታሪክ የሚሰራላት አይደለችም። የነበራትን ክብር ማስጠበቅ ባለፈው ከተሰራው የጀግንነት ታሪክ ያላነሰ ክብር የሚያሰጥ ተግባር ነው። ይሁን እንጅ የአሁኑ ትውልድ የሚማርክ ሳይኖር በፈቃዱ እጁን እየሰጠ ይመስላል። የሰሞኑ መወያያ ርእስ የሆነው ጉዳይ ጆሮን ጭው የሚያደርግ፣ ኢትዮጵያን ከክብሯ የሚያዋርድ ለብዙዎች መርዶ የሆነ ዜና እየሰማን ነው። የሀገር እድገት፣ የዘመን ስልጣኔ  ሀገራችን ገብቶ ከድህነት ተላቀን በርኃብና በበሽታ የሚያልቀው ወገናችን እግዚአብሔርን አመስግኖ የሚቀምሰው ምግብ ያገኛል ስንል በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ እንዲሉ ሰዶምና ገሞራን በእሳት እንዲጠፉ ምክንያት የሆነው የኃጢአት ርኩሰት ያለምንም ከልካይ አዲስ አበባን እያዳረሳት እንደሆነ እየተሰማ ነው። ችግራችን ዘርፈ ብዙ እንዲሆን ብዙ የሰሩ አካላት ያሰቡት ሁሉ እንደተሳካላቸው እየሆነብን ያለው ነገር በቂ ማሳያ ነው።




በየአዳራሹ የዋሁ ህዝብ በጠንቋዮችና  በአጋንንት መንፈስ አቅሉን ሲጥል እያየን የሚመለከታቸው አካላት መፍትሄ ይሰጡ ይሆናል በሚል በዝምታ ማለፍ ግድ ሆነብን። በአጥማቂነትና በብህትውና ሰበብ እግዚአብሄርን አገኛለሁ ብሎ ወደ ቤተክርስቲያን የሚመጣውን ህዝብ ጨርቁን እያስነጠፉ በእልልታና በጭብጨባ ሲራመዱ ማየታችን እውነት የኛ ቤተክርስቲያን አካላት ናቸውን? እስክንል ድረስ  ታዝበን አለፍን። እነዚህ ሁሉ አካላት ይህን ሰይጣናዊ ተግባር የሚፈጽሙት ከበላይ አካላት እውቅና ተሰጥቷቸው ለመሆኑ ጥርጥር የለውም። በነጻነት ሰበብ ህዝብን የሚጎዳ ሀገርን ባህልን የሚያጎድፍ ተግባር እየተጤነ የሚፈቀድ ካልሆነ ለስልጣኔ እሩቅ ለሆነ ህዝብና ሀገር መጥፊያ ነው የሚሆነው።  

ግብረ ሰዶም ለኢትዮጵያ ከነአሜሪካም በላይ እጅግ አጸያፊ ተግባር ነው። ምግብና ልብስ አልሟላ ብሎት በየእለቱ እሮሮ ለሚያሰማ ህዝብ በጥጋብ የሚወረስ ኃጢአትን ማለማመድ ከእንስሳም በታች እንደማየት ይቆጠራል። ይህን የፈቀደም ሆነ ሲሆን አይቶ ዝም ያለ የኢትዮጵያን ጥፋት ከሚመኙ ተለይቶ ሊታይ አይችልም። የኢትዮጵያ ህዝብ ቢርበው፣ ቢጠማው፣ ቢራቆት በእግዚአብሔር ላይ ባለው እምነት ችግሩን ተቋቁሞ ይኖራል። አሁን እየተሴረበት ያለው እየራበው፣ እየጠማው፣ እየተራቆተ ተመስገን ብሎ የሚኖርበትን ኃይሉን ለመግፈፍና ተስፋ ለማስቆረጥ ይመስላል።  መንግሥት ሀገር እጠብቃለሁ ሲል ዓይን እየፈረጠ እጅ እየተቆረጠ እያየ ለዚህ ዘብ የማይቆም ከሆነ ሀገር እንዴት ነው የሚጠብቀው? ትላንት ከነባህሏ፣ ከነሥርዓቷ የተቀበላትን ሀገር ከነሙሉ ክብሯ ለቀጣዩ ትውልድ ማስረከብ ካልቻለ ኃላፊነቱን አልተወጣም። ትላንት ዳርድንበር ለማስከበር ደማቸውን ያፈሰሱ ወገኖቻችን ሀገርን የሚደፍር፣ ባህልን የሚበርዝ፣ ማንነትን የሚያሳጣ ጠላት መጣ ብለው እኮ ነው። እኛ ዛሬ ይህን ክፉ ነገር እንዲሆን ከፈቀድን አባቶቻችንን ለምን እንዘክራለን? በሌላው ዓለም እንዲህ ዓይነት አዲስ ነገር ሲከሰት የህዝብ ፈቃድ ተጠይቆ ነው የሚፈቀደው እኛጋ የሆነው ግን ህዝብ ምን አገባው የተባለ ይመስላል። ትላንትና ሀሁ ፊደል አስቆጥራ፤ ወንጌል አስነብባ፣ ዳዊት አስደግማ መልካም ትውልድን ለሀገር ታስረክብ የነበረች ቤተክርስቲያን አጸያፊው ግብረ ሰዶም በይፋ ትውልድን እያረከሰ እያየች ዝም ማለቷ እውነትም ልጆቿ ያልተረዱላት ችግር ውስጥ እንዳለች ማሳያ ነው። ዛሬ ያልጮኸች ቤተክርስቲያን መቼ ነው ድምጿን የምታሰማው? አባቶቻችን እባካችሁ ለራሳችሁና ለመንጋው አስቡ።  








No comments:

Post a Comment