Thursday, March 13, 2014

አሜሪካንን ለማታውቋት

በዓለማችን ብዙ ሰው በተለያየ መንገድ ወደ አሜሪካ ይመጣል። የማያውቁት ሃገር አይናፍቅም የሚለው ተረት ለአሜሪካ አይሰራም። ከሚያውቃት ይልቅ የማያውቃት የሚናፍቃት ሃገር አሜሪካ ነች ቢባል አይጋነንም። የሃገር መሪዎች፣ የሃይማኖት መሪዎች፣    የፖለቲካና የኢኮኖሚ ስደተኞች፣   በልዩ ልዩ መንገድ የሚገቡ ምሁራንና ተማሪዎች፣ እንዲሁም በስራና በንግድ በህክምና በመሳሰለው ምክንያት ወደዚች ምድር ይመጣሉ። በተለይ እኛ ኢትዮጵያውያን ወደ አሜሪካ ለመግባት ስናስብ አስቀድመን ሰፋ ያለ መረጃ ለማግኘት እንቸገራለን። እንድንመጣ የሚረዳን ቤተሰብም ብዙ ገንዘብ ከፍሎ ከሃገራችን እንድንወጣ እንጅ የሚጥረው በሃገራችን ያለ አሜሪካ ውስጥ የሌለ ነገር እንዳለ  አይነግረንም። ሁልጊዜ እኛ እራሳችንን ድሃ ብለን መቁጠር ይቀናናል። እርግጥ ነው በሃገራችን ብዙ ድሆች ይኖሩ ይሆናል፥ ነገር ግን አሜሪካም ጥቂት ድሆች እንዳሉ ልናውቅ ይገባል። ጠንክሮ ካልሰሩ ባግባቡ ኑሮን መምራት ካልቻሉ አሜሪካ ውስጥ ድሃ ብቻ አይደለም የሚኮነው ወንጀለኛም ነው።


በአሜሪካ ማንኛውም ሰው ለሚጠቀምበት ነገር በአግባቡ መክፈል ካልቻለ ተአማኒነት ስለማይኖረው የህይወት ታሪኩ ይበላሻል። ዳግመኛ ሰርቶ ለማግኘት አስቸጋሪ ይሆንበታል። በዚህ የተነሳ በረንዳ አዳሪ ይሆናል። የትም ቦታ ስራ ተቀጥሮ መስራት አይችልም። በሃገራችን አንድ ሰው ሰርቶ ካልተሳካለት ድሃ ይሆናል። ነገር ግን የሰላም እንቅልፍ ይተኛል። ድሃ የሚሆነው ምናልባት በመብል በመጠጥ ወይንም በልብስና በመጠለያ ሊሆን ይችላል። ነገር ግን በተስፋ ድሃ አይሆንም። አንድ ቀን ሰርቼ ያልፍልኛል ብሎ ተስፋ የማይቆርጥ ከሆነ ሰርቶ ማግኘት ይችላል።
 
 አሜሪካ እንኳን ድሃው ሃብታሙ እንቅልፍ የለውም። ያለውም ሆነ የሌለው ለመረጃ ቅርብ ስለሆነ ክፉ ነገር ሳይሰማ አይውልም። በዚህ የተነሳ አእምሮ ሰላም አያገኝም። ለዚያ ነው ብዙ ሰዎች በጭንቀት ተይዘው እድሜያቸው የሚያጥረው። አሜሪካ ያላት ብዙ በጎ ነገር አለ። በተቃራኒው መጥፎ የሚባሉ ብዙ ነገሮች አሏት። የአሜሪካ ኃያልነት ዘርፈ ብዙ ነው። እምቢ ያለውን በኃይል የወደዳትን በፍቅር የምታንበረክክ ሃገር ነች። ወደ አሜሪካ ለመግባት ያለውን ውጣ ውረድ ያክል ከአሜሪካ ለመውጣትም ችግር ነው። ብዙዎች ሃብት አፍርተው ወደ ሃገራቸው ተመልሰው ቀሪ ዘመናቸውን በሰላም ለማሳለፍ ይፈልጋሉ ነገር ግን የሚሳካላቸው ጥቂቶች ናቸው። አሜሪካ በብልሃት ለኖረባት እንቁላል ሳሩን አይቶ ገደሉን እንደረሳው በሬ በጭፍን ለሚጓዘው ደግሞ ኩስ የምታሸክም ዶሮ ነች። ብዙዎች የሚስቁባት ፣ ብዙዎች የሚያለቅሱባት ፣ ብዙዎች የሚያተርፉባት፣ብዙዎች የሚከስሩባት፣ ወ ዘ ተ ባጠቃላይ ማግኘትና ማጣት የሚፈራረቁባት ሀገር ነች። 
 
አሜሪካንን ብዙዎች ከምድረ ከነዓን ሲመስሏት ብዙዎች ደግሞ ከዲያቢሎስ እርስት ከገሃነመ እሳት የሚመድቧትም አሉ። እሷ ግን ሁለቱንም አይደለችም ምንም ከማለት አሜሪካ ብሎ ማለፉ ይሻላል። ብዙ መልካም ስራ የሚሰሩ ሰዎች አሉባት። በተቃራኒው ደግሞ የኃጢዓት ወገን የተባለው ሁሉ በህጋዊ መንገድ ይሰራባታል።  የፈረጅ ችግረኛና ድሃ እንዳለ  የሚታወቀው አሜሪካ ነው። ወረቀት የሌላቸው ብዙ የአውሮፓ ነጮች ከአፍሪካውያን ጋር ዝቅተኛ ስራ በመስራት የሚተዳደሩ አሉ። ድሮ ድሮ ነጭ ሁሉ ባለጸጋ ይመስለን ነበር።  እድሜ ለአሜሪካ የጥቁርን እጅ ጠብቀው የሚኖሩ ነጮችንም እንድናይ አድርጋናለች። በተቃራኒው በሃብትም ሆነ በዝና እጅግ የላቁ ጥቁሮች የሚኖሩባትም ሃገር አሜሪካ ነች።
 
በስራቸው ብዙ ሰራተኞችን የሚያስተዳድሩ ኢትዮጳያውያን ባለሃብቶችና ምሁራን አሉ። እንደ አንድ እናት ልጆች ከመተያየት ይልቅ በየምክንያቱ ሲካሰሱ ሲወነጃጀሉ ማየት የተለመደ ነው። ለምን እንደሆነ መልሱ አልተገኘም።
 
የአሜሪካ ህጎቿ ጥብቅ ቢሆኑም አንዳንዱ ግራ ያጋባል። እርግጥ ነው ተጠንቅቀው ከኖሩ ያለገደብ የፈለጉትን ማግኘት ይቻላል። ነገር ግን አንዳንዴ የአንዱን መብት ለሌላው አሳልፎ የሚሰጥ ህግም አላት። ለምሳሌ የወላጆችን ለልጆች፣ የባልን ለሚስት፣ የባለ ንብረትን ለሌባ፣ የሟችን ለገዳይ ወዘተ በጥቅሉ አሜሪካን ለማያውቋት ሰዎች ሲገቡባት እንግዳ ነገሮችን በየእለቱ የሚያዩባት ሀገር ነች። በሃገራችን እንደሚታየው በየጊዜው ዘረፋና የነፍስ ግድያ ወንጀሎችም ይሰማሉ። ልዩነቱ የዚህ ሃገር ሌባ የሚሰርቀው የሚበላው የሚጠጣው አጥቶ ተርቦ tx,ምቶ ሳይሆን በአጉል ሱሶች እየተጠመደ ነው። ይህ በብዙ ቦታዎች አይታይም። አብዛኛው ሰው ሰርቶ መብላትን ባህሉ አድርጎ ይኖራል። ልዝረፍ ቢልም ሰርቶ ከሚያገኘው የተለየ ስለማይሆን ሰርቶ መብላትን ይመርጣል። በሃገራችን ያሉ ሌቦች ሌብነትን እንደ አማራጭ የሚይዙት ሰርተው ከሚያገኙት የተሻለ ስለሚሆን ይመስለኛል።  ብዙ ማለት ይቻላል ለጊዜው ይህችን ታህል ከጠቆምኩ በተለይ እኛ ኢትዮጵያውያን ከሚታዩብን  ችግሮች ጥቂቶቹን ላስታውስ።

በምኖርበት ከተማ ሰፊውን ጊዜየን የማሳልፈውን  መንፈሳዊ አገልግሎት በመስጠት ነው። በአገልግሎት ወቅት ብዙ ተመሳሳይ ችግሮች ያጋጥሙኛል። በኔ ግምት ሰዎች ለተመሳሳይ ችግር የሚጋለጡት ስለችግሩ ቀድሞ መረጃ ካለማግኘት ይመስለኛል። የችግሩ ተጋላጮች አስቀድመው ሳይሆን ወደ ቤተክርስቲያን የሚመጡት ችግሩ ከደረሰባቸው በኋላ ነው። በሃገሪቱ ያለው ያለገደብ ነጻነት ብዞችን ያታለላቸው ይመስላል። ብዙዎች ትዳራቸውን በመተው ለብቻ መኖርን ይመርጣሉ። ነገር ግን ከበፊቱ የባሰ ፈተና ይገጥማቸዋል። በአሜሪካን ሀገር ህግ ሁሉም ሰው ጉዳዩን ማስፈጸም የሚችለው በህጋዊ ጠበቃ በኩል ነው። ሰለዚህ ጠበቆቹ የስራ መስካቸው እንዳይቀዘቅዝ ስለሚፈልጉ ትዳራቸውን ለማፍረስ ወደ እነሱ ለሚመጡ ተጓዳኞች መጥፎነቱን አይነግሩም። በልጆች ላይ የሚፈጥረውንም የስነልቦና ጉዳት መፍትሄ እንደሚፈልጉለት ተስፋ ይሰጧቸዋል። ስለዚህ ትዳራቸውን በቀላሉ ያፈርሱታል። ነገር ግን በዚህ ሲጎዳ እንጅ ሲጠቀም የታየ ሰው የለም።

እንደሚታወቀው ብዙዎች ወደ አሜሪካ ሲመጡ ከሃገራቸው የተሻለ ነገር እንደሚያገኙ እርግጠኞች በመሆን በሃገራቸው የሚኖራቸውን ንብረት ሸጠው ለውጠው በጣም ጥቂቶች አደራ ሰጥተው ነው።  ነገር ግን እንዳሰቡት የሚሳካላቸው   ጥቂቶች ናቸው። ብዞዎቹ ከሁለት ያጣ በመሆን ላልተፈለገ ችግር ይጋለጣሉ።

አንዳንዶች ትዳራቸውን ትተው መጥተው ሲመለሱ ፈርሶ ያገኙታል። አንዳንዶች ንብረታቸውን አደራ ሰጥተው ሲመለሱ በወገኖቻቸው ክህደት ይፈጸምባቸዋል። በዚህ የተነሳ ለከፍተኛ የአእምሮ ህመም ይጋለጣሉ። አንዳንዶች ለልጆቻቸው ሲሉ ሃገራቸውን ትተው የተሻለ ነገር እናገኛለን በማለት ይሰደዳሉ። ነገር ግን ልጆቻቸው እንደጠበቁት ሳይሆን ባልተፈለገ መንገድ ይጓዙባቸዋል በዚህ የተነሳ ወላጆች ዘመናቸውን በሃዘን ያሳልፋሉ።

ሌላው ችግር ብዙ ኢትዮጵያውያን ወጣቶች ቤተሰቦቻቸውን ለመርዳት ካላቸው ፍላጎት የተነሳ በወጣትነት እድሜያቸው ወደ ትዳር የሚወስደውን መንገድ ወደ ጎን ትተው ረጅም ሰዓት ሥራ በመስራት ጊዜያቸውን ያሳልፋሉ። ቤተሰብ መርዳታቸው ባልከፋ ነገር ግን የቤተሰብም ምክር ስለማይታከልበት የወደፊት ኑሮዋቸውን ይዘነጉታል። ቤተሰቦችም በየወሩ የሚላክላቸውን ገንዘብ ተስፋ በማድረግ እንዲህ አይነቱን ጥያቄ ማንሳት አይፈልጉም። እንደውም የሚያስብ ወይም የምታስብ ከሆነች ሌላ ፈተና ነው የሚገጥመው(ት) ሁሉም በጊዜው ትዝ ማለቱ አይቀርምና ወደ ትዳር ለመሄድ ሲያስቡ ሌላ ፈተና ይገጥማቸዋል። ቀድሞ እንኳን ልጅህን ለልጄ  በሚባልበት ዘመን ለመተጫጨት ጊዜ አለው እድሜ ካለፈ ችግር ነው። በዚህ የተነሳ የማያውቃትን የማታውቀውን ወደ ሃገራቸው ሄደው አግብተው ያመጣሉ። ወደ አሜሪካ የሚመጡትም የሚኖራቸው መረጃ ስለ ሌለ አሜሪካ ልሂድ እንጅ ብለው የልቦናቸውን ደብቀው ይመጣሉ። እዚህ ሲመጡ ግን ዙሪያው ገደል ይሆንባቸዋል። ከራሳቸው አልፈው ለሌላው ችግር ይሆናሉ። በዚህ የተነሳ እስከ ህይዎት መጠፋፋት የደረሱ ብዙዎች ናቸው። አንዳንዶች ኢትዮጵያ ትዳርና ልጆቻቸውን አስቀምጠው ራሳቸውን በመደበቅ አግብተው ይመጣሉ። ከዚህ የሚሄዱትም ሰፊ ጊዜ ስለማያገኙ ግፋ ቢል ሁለት ወር ሶስት ወር ነው ይዘው የሚሄዱት ። በዚያ ጊዜ ደግሞ ሰውን አጥንቶ የኋላ ታሪኩን ለማወቅ ያስቸግራል። ስለዚህ ገበያ ወጥቶ ሸቀጥ የመግዛት ያክል ትዳር ሸምተው ይመለሳሉ፥ ከዚያ በኋላ አስቀድመው የተመኙት ነገር በሙሉ ህልም ይሆንባቸዋል። በዚህ የተነሳ ወደ ተስፋ መቁረጥ ይደርሳሉ። 

ሌላው እንደሚታወቀው ማንኛውም ሰው ወደ አሜሪካ ገብቶ ለመኖር ወይንም ጎብኝቶ ለመመለስ ሲያስብ የማይቆፍረው ጉድጓድ የለም። የመግቢያ ቪዛ (VISA) ለማግኘት የማለፊያ መስፈርቱ በውል የማይታወቅ በመሆኑ ብዙዎች ,, የምትሆነውን ለመሆን የማትሆነውን ትሆናለህ ,, የሚለውን ዘይቤ ይጠቀማሉ። ሌላውን ልተወውና ካህናት ሳይሆኑ ካህናት ነን፣ ሳይመነኩሱ መነኮሳት ነን፣ በማለት የሚመጡ አሉ። እዚህ ያለው ህዝበ ክርስቲያን አብዛኛው ኑሮው ሩጫ በመሆኑ ይህን አይመረምርም። የአገልጋይ እጥረት ስላለበት የመጣውን ተቀብሎ ይገለገላል። ከታች እስከ ላይ ያለው የቤተክርስቲያን መዋቅር የጸና ባለመሆኑ እንዲህ አይነት ሰዎችን ለመቆጣጠር አልተቻለም። በዚህ የተነሳ ትልቁ የቤተክርስቲያናችን የቅድስና ማዕረግ ክህነትና ምንኩስና እየተናቀ መጥቷል። ስርዓተ ቤተክርስቲያን በብዙ መንገድ ሲፋለስ ይታያል። ይህን እንደስህተት ቆጥሮ እንዲስተካከል የሚጥር አይኖርም። ቢኖርም የሚቀበለው አያገኝም። ከሃገር ቤት የሚመጡ የሃይማኖት አባቶችም ሆኑ የመንግስት አካላት የራሳቸው ፕሮጀክት ይዘው ስለሚመጡ በተቻለ መጠን የራሳቸውን ዓላማ ለማሳካት ይጥራሉ እንጅ ኢትዮጵያዊው ባህሉና ማንነቱ የመዘንጋቱ ነገር ብዙም አያሳስባቸውም።

በአሜሪካ ከዲቁና እስከ ጵጵስና እንዲሁም በሃገራችን የሚታወቁት ልዩ ልዩ ማዕረጋት የስም እንጅ የክብር ልዩነት የላቸውም። እኩልነት የሚለው ህጋቸው ብዙ ችግር ያለው ይመስላል። መቼም እድሜ የሚያመጣው ለውጥ በራሱ አስተማሪ መሆን ነበረበት ብሎ ማሰብ ይቻላል። ቅደም ተከተል የሌለው ነገር መነሻና መድረሻውን ለማወቅ ያስቸግራል። ለዚህም ነው የሁሉ አስገኝ እግዚአብሔር ለሁሉም ነገር መነሻና መድረሻ ያበጀለት።
 
በአሜሪካ ዲያቆኑ ከፈለገ ቤተክርስቲያን ከፍቶ ይመራል። እንኳን ዲያቆኑ አንድ ተራ ምዕመንም እንደዚሁ ሊያደርግ ይችላል። አቶዎች፣ ወይዘሮዎች በስማቸው ቤተክርስቲያን ከፍተው፥ ካህን እየቀጠሩ ያስገለግላሉ። ህግና መመሪያ የሚያወጡት ለራሳቸው በሚመቻቸው መንገድ ነው። ህዝቡ ቤተክርስቲያን የሚለውን እንጅ ስርዓት ተፋለሰ፣ ተበላሸ የሚያውቀው ነገር የለም።  ካህኑም ስለሚከፈለው ደመወዝ እንጅ ስለ ስርዓተ ቤተክርስቲያን መፋለስ ግድ አይለውም። ይህ ትክክል እንዳልሆነ ከትልልቅ አባቶች ጀምሮ ከላይ እስከታች ይታወቃል። እንደውም ይህንን ስርዓት አልባ አገልግሎት ያስፋፋፉት ከሊቃነ ጳጳሳቱ ጀምሮ ያሉት የቤተክርስቲያን አካላት ነን የሚሉ እንደሆኑ በሰፊው ይነገራል። ወደ አሜሪካ ሊመጣ ያሰበ አገልጋይ አሜሪካ ሄጄ ሰርቼ ያልፍልኛል ሳይሆን የሚለው ቤተክርስቲያን ከፍቼ ገንዘብ እሰበስባለሁ ብሎ ነው። ይህ የሚያሳየው ምን ያህል የተሳሳተና የተበላሸ መረጃ ይዘን እንደምንመጣ ነው። በአሜሪካ ከዚህ ይልቅ ብዙ ፍሬያማ ልንሆንባቸው የሚያስችሉ እድሎች አሉ። ነገር ግን አንጠቀምባቸውም። የመረጃ ልውውጥ የማድረግ ችግራችንም የጎላ ነው። ይህ በአብዛኛው የሚታየው በእኛ በኢትዮጵያውያን ዘንድ ነው። እንደኛ በተለያየ ችግር ምክንያት ከሃገራቸው ተሰደው በዚህ የሚገኙ ብዙ ህብረተሰቦች አሉ። ባህላቸውንና እሴቶቻቸውን ለሌላው ለማሳወቅ ሲጥሩ ይታያሉ። እንደኛው የተለያየ ሃይማኖትና ቋንቋ ያላቸውም አሉ። ነገር ግን በሃገራቸውና በበባህላቸው ሁሉም አንድ አቋም ይታይባቸዋል። በኛ በኩል ጥቂቶች ሲሞክሩ ይታያሉ። ነገር ግን ሌላው የቤት ስራ ስለሚበዛብን ውጤታማ አንሆንም።  አሜሪካ ለእንደዚህ አይነቶቹም ህብረተሰቦች የተመቸ ስርዓት አላት። የአሜሪካንን ህግ እስካከበረ ድረስ፥ማንኛውም የራሴ አለኝ የሚለውን ባህል፣ ሃይማኖት፣ ቋንቋ ወ ,ዘ ተ ይዞ  ለመኖር እንዲችል ፈቃድ ሰጥታለች።
 
በአሜሪካ የህግ የበላይነት አለ ብሎ መናገር ይቻላል።  አንድ ሰው የፈለገውን መሆን ይችላል። ያንን የሚቃወም ወንጀለኛ ተብሎ ሊቀጣ ይችላል። ማንኛውም ዜጋ ከህጻንነቱ ጀምሮ የሚያውቀው ነገር መብትና ግዴታውን ነው። በአሜሪካ ውስጥ ተወልዶ ያደገ ሰው ወንጀል ሲሰራ አስቀድሞ ምን እንደሚደርስበት ያውቃል። ያንን አምኖ ነው ወንጀል የሚሰራው።  

አንድ ኢትዮጵያዊ ወደ አሜሪካ ሲመጣ ምናልባት ስለፖለቲካም ሆነ ስለ ሃይማኖት በቂ ግንዛቤ ባይኖረውም እንኳ፥ ነገር ግን እዚህ ሲመጣ ሁሉንም በአንድ ላይ ስለሚያገኛቸው ፍላጎቱን ተጠቅሞ የተመቸውን ይይዛል። ከጥቂቶች በስተቀር የቀደመ ማንነቱን ይዞ ለመኖር ይቸገራል።
 
በአሜሪካ ሌላው ትልቁ የኛ የኢትዮጵያውያን ችግር እርስበርስ ተፋቅሮ አለመኖር ነው። ምክንያቱ ተብሎ የሚታሰበው ሁሉም የደከመበትን ማግኘት ስለሚችል የሌላውን እርዳታ አይፈልግም። ቢቸገርም መንግስት ይረዳዋል። ስለዚህ ስለወገኑ አይጨነቅም። ይህን ለማለት የሚያስገድደው ብዙ ዘመን ተነፋፍቀው የተገናኙ ቤተሰቦች ለማመን በሚቸግር መልኩ ፍቅራቸው አልቆ ሲወጋገዙ ስለሚታይ ነው።  ብዙው አበሻ ከራሱ ወገን  ይልቅ ከሌላው ማህበረሰብ  ጋር ተስማምቶና ተፋቅሮ ይኖራል። ይሁን እንጅ አነሰም በዛም በሃዘንና በደስታ ጊዜ ለሌላው በሚገርም መልኩ ይተባበራል። ይህ የሚያሳየው በመካከል እንክርዳድ የሚዘሩ ሰዎች እንዳሉ ነው። እነዚህ አካላት ከክፋት ወደ በጎነት ቢመለሱ ሃበሻ ለዓለም የሚያስደንቅ ህብረትና አንድነት ሊኖረው ይችል እንደነበር ነው። ማን ያውቃል አንድ ቀን በመካከላችን ያለው የመለያየት መንፈስ ተወግዶ የአንድ እናት ልጆች መሆናችንን የምንረዳበት ዘመን ይመጣ ይሆናል።  እስቲ ሁላችንም ለዚህ ነገር አጥብቀን እንጸልይ? እግዚአብሔር ይርዳን።

 

No comments:

Post a Comment