Sunday, October 28, 2018

በጎና ክፉ ቃላት የተናጋሪዎቹን ማንነት በጉልህ የሚያሳዩ በመሆናቸው ልንደነቅ አይገባም።

ሰዎች የሚናገሩትና የምንሰማው ሁሉ ወደ ተግባር የሚለወጥ ቢሆን በህይዎት መኖር የሚችል ፍጥረት ይኖራል ብሎ ማሰብ አይቻልም ነበር። በዓለም ላይ የተናገሩትን መፈጸም የቻሉ ሰዎች በመብራት ፈልጎ ማግኘት ከባድ ነው። በበጎም ሆነ በክፉ ሃሳብ ውስጥ ሆነው ብዙ ተናግረው ነገር ግን አንዱንም መፈጸም ያልቻሉ ብዙ ሰዎችን እናውቃለንና ምስክሮች ነን። ይህን ማድረግ የሚቻለው እግዚአብሔር ብቻ ነው። እስመ አልቦ ነገር ዘይሰአኖ ለእግዚአብሔር ሉቃ 1፥37  

የህይዎት ጉዞውን ለእግዚአብሔር መስጠት ያልቻለ ሰው ከስህተትና ከመሰናክል ሊያመልጥ አይችልም። አንዳንድ ጊዜ ከአቅም ጋር ያልተገናዘቡ ነገሮችን እሽ ብሎ መቀበል እራስን ለፈተና ማጋለጥ ነው። ብዙ ቅዱሳን አባቶቻችን ከእግዚአብሔር ያዘዘ ሹመት ስመጣላቸው ሀገር ጥለው የሸሹ እንደነበር ቅዱሳት መጻህፍት ምስክሮች ናቸው። ምክንያቱ ደግሞ እራሳቸውን ከፈተና ይጠብቁ ዘንድ ነው። እራሱን ከፍ የሚያደርግ  ሁሉ ይዋረዳል ራሱንም የሚያዋርድ ሁሉ ከፍ ይላል ማቴ 23፥ 12 - ሉቃ 14፥11


ምንም እንኳን ሹመት ያለ እግዚአብሔር ፈቃድ የማይሰጥ ቢሆንም አቅምን አገናዝቦ አደራን መቀበል የባለቤቱ ኃላፊነት ነው። በማቴ 25፥15 ላይ ተጽፎ እንደምናነበው ፈጣሪ አምላክ ለሁሉም የሚሰጠው ጸጋ እንዳለ እናያለን ነገር ግን የተቀበለው ሁሉ ያተርፋል ማለት እንዳልሆነም ጌታ በመዋእለ ትምህርቱ አስተምሮናል። ዛሬ ሥራቸው በጉልህ ተገልጦ የምናያቸው አባቶች ላሉበት ማእረግ ለመብቃት ብዙ ተጉዘው እንደነበርና ነገር ግን ሥልጣኑ ወደ እነርሱ ቀርቦ እንዳልነበር በወቅቱ ከነበሩት ነባራዊ ሁኔታዎች መረዳት ይቻላልለ።

 በአገልግሎት የማውቃቸው አንድ አባት የተናገሩትን ሁል ጊዜ አስበዋለሁ። በአንድ ደብር በመሪጌትነት ሲያገለግሉ ተግባራቸውን የሚመጥን ደመወዝ ቢሰጣቸው ’’ይህን የማስተዳድርበት አቅም ስለሌለኝ ያለኝ ይበቃኛል ለሌሎች ስጡት’’ ብለው ሲሄዱ አስታውሳለሁ። ገንዘብ ሲቀበሉት ያስደስታል ነገር ግን ብዙዎች በገንዘብ ህይዎታቸውን አጥተዋል ብዙዎች ደግሞ በገንዘብ ድህነታቸው ከብዙ መከራ አምልጠዋል። ስልጣንም እንዲሁ ነው ከአቅም ጋር ያልተገናዘበ ከሆነ ለውርደትና ለጥፋት ያጋልጣል። አባቶቻችን ከሰው መርጦ ለሹመት ከእንጨት መርጦ ለታቦት ይላሉ ይህ ያለምክንያት አልተነገረም ሹመት ሰውን አደባባይ ላይ ያቆማል በሌሎች አይን እይታ ውስጥ መግባት ማለት ነው። ጥንቃቄ ካልተደረገበት ስልጣኑንም ባለስልጣኑንም ማዋረድ ይሆናል። ስለዚህ መራጮችም ሆነ ተመራጮች ታላቅ ኃላፊነት አለባቸው በጥፋቱ ተጠያቂ በልማቱ ተመስጋኝ ይሆናሉና።

በተለይ ለትልቁ ማእረግ የሚታጩ አባቶች የቤተክርስቲያን ርእስ ስለሚሆኑ በየጊዜው ሰላማዊ ሰልፍ የሚወጣባቸው ሳይሆን እድሜ ይሰጥልን ተብሎ አቤቱታ የሚቀርብላቸው ቢሆኑ ቤተክርስቲያንንም ያስከብራሉ ለሌላውም ምሳሌ መሆን ይችላሉ። ዛሬ ግን እጅግ በሚያሳፍር መልኩ የተከበረው ሊቀጵጵስና በምግባረ ብልሹ ሰዎች ሲነቀፍ እያየን ማዘን የሁልጊዜ ቁጭታችን ሆኗል። ክህነት ከሁሉ የተከበረ ስጦታ ነውና በቸልተኝነትና በምንቸገረኝ ባይነት አለቦታው እንዳያርፍ ጥንቃቄ ቢደረግ መልካም ነው።

በ37ኛው አጠቃላይ የቤተክርስቲያን ጉባኤ መክፈቻ ላይ የተሰነዘሩት በጎና ክፉ ቃላት የተናጋሪዎቹን ማንነት በጉልህ የሚያሳዩ በመሆናቸው ልንደነቅ አይገባም። የብፁዕ አቡነ ቀውስጦስን ትምህርት የሰማ ሰው በሌላ ንግግር እራሱን ማቆሸሽ የለበትም። ሰው አንድን ነገር አንድ ጊዜ ነው ማወቅ ያለበት  ባወቀው ነገር እምነት ከሌለው በአግባቡ አላወቀም ማለት ነው። ስለዚህ በዚህ ጉባኤ ላይ የተነገሩት ቃላት በተናጋሪዎቹ ማናነት የሚለኩ ናቸው። ይህን ደግሞ ብዙ ጊዜ አይተን ሰምተን አውቀናል። ለእኔ ከኩርንችት በለስ መፈለግ ካልሆነ በቀር አዲስ ነገር አልታየኝም።

ዛሬ የምናያቸው ችግሮች በሙሉ ትላንት በማስተዋል እጥረት ትኩረት ያልሰጠናቸው ጉዳዮች ናቸው። አይመጣምን ትተሽ ይመጣልን ያዥ እንዲሉ ምንም አይመጣም ብሎ ኃላፊነትን ከመዘንጋት ይልቅ ለነገዋ ቤተክርስቲያን አስቦ ወርድና ቁመቷን የተረዳ መሪ እንዲኖራት ቢደረግ ኖሮ ዛሬ የሉአላዊቱ ቤተክርስቲያን ልጆች በየጊዜው አንገታቸውን የሚያስደፋ ቃል መስማት ባልቻሉ ነበር። 

በእኔ እይታ ያለን አማራጭ የሚሰጠንን መጋት ነው። እርፍ ተይዞ ወደኋላ አይታረስም ልናስተካክለው የማንችለውን ጉዳይ እየመላለስን ጊዜያችንን ከምናጠፋ  ካለፈው ተምረን ለነገው መዘጋጀቱ ነው የሚበጀን። ከዚህም በተጨማሪ የቤተክርስቲያን አካል የሆነውን ለሌሎች አሳልፎ በመስጠት ተጨማሪ ስህተት ከመፈጸም መቆጠብ ለቤተክርስቲያን ማሰብ ነው። ክፉውን ወደ በጎ በመቀየር እስኪያልፍ አብሮ መጓዝ የተሻለው አማራጭ ነው። ይህ አመለካከት ለብዙዎች ላይስማማ ይችላል ነገር ግን በህይዎታችን የሚጠቅመንን ብቻ ሳይሆን ብዙ የማይጠቅሙንን አካላት ተሸክመን እንደምንኖር መገንዘብ ያስፈልጋል። ያ ባይሆን ኖሮ አንዳንዶች የሰውነታቸው ግዝፈት አስጨንቀቸው እየቃተቱ ከሚኖሩ አራግፈውት መሄድ በቻሉ ነበር ነገር ግን አይቻልም አካል ነውና።

በቅዱሱ የቤተክርስቲያን ጉባኤ ላይ የምንሰማውን ኢ ክርሲቲያናዊ ንግግር ከመስማት ይልቅ ባንሰማው ለእኛ እጅግ መልካም ነበር ነገር ግን መልካሙን ነገር ለማቅረብ ተብሎ ህሊና የሚያቆሽሸውም አብሮ እንዲደርሰን ይደረጋል። ይህ የዓለም ጠባይ ነው። ዓለማችን ምን በጎ ዘመን ቢሆን መልካም ነገር ብቻ ልትሰጠን አትችልም ምድረ ፋይድ ነችና። ይቆየን,



                                               

No comments:

Post a Comment