Saturday, December 31, 2011

ዘመኑም ክፉ ነውና ቀጥ ብላችሁ አትሄዱም። ሚክ 2፥3

ዛሬ ስላለንበት ዘመን ስንናገር ምናልባትም ማንም የማይቀማንን ሙሉ መብት ተጠቅመን  በልበ ሙሉነት መናገር እንችላለን። ምክንያቱም  ክፉም ይሁን በጎ ዘመኑ እኛ የተፈጠርንበት በመሆኑ የኛ ዘመን ነው ብሎ ለመናገር ፈቃድ አያስፈልገውም። አንድን ነገር የኔ ነው ለማለት በህግ ፊት የሚቀርብ የባለቤትነት ማስረጃ ያስፈልጋል።እናም የኛ ማስረጃ በዚህ ዘመን መፈጠራችን ብቻ ነው።


በኖህ ዘመን ለነበሩ ህዝቦች በኃጢአት ተጨማልቆ መኖር የመልካም ዘመን ውጤት እነደሆነ ቆጥረውት ነበር። እግዚአብሔር ሰውን በመፍጠሩ እስኪጸጸት ድረስ ኃጢአታቸው የበዛ ነበር።  እግዚአብሔርን ለሚፈራው ኖህ ግን ክፉ ዘመን እንደነበር ዘፍ 6፥1  ስናነብ እናገኘዋለን።

የሎጥ ዘመን  ዘፍ 19፥1  የእስራኤል የግብጽ ባርነት  ዘጸ 1፥8   ተጽፎ እንደምገኘው  በአንድ ዘመን ሁለት ዓይነት የተለያዩ ህዝቦች በተለያየ ሁኔታ ይኖሩ እንደነበር ነው። እግዚአብሔርን የሚያውቁት የተጨነቁበት እግዚአብሔር ማነው ብለው ይገዳደሩ የነበሩት በተድላና በደስታ ይኖሩ የነበረበት ዘመን ነበር። ነገር ግን የዚህ ዓለም ደስታ እንደ አይን ቅጽበት ብልጭ ብሎ የሚጠፋ በመሆኑ በቅጽበት ደስታቸው ወደ ሃዘን እንደተለወጠ እናያለን።

ወደተነሳሁበት ርእስ ስመለስ ምናልባትም ቃሉ የኛንም ዘመን የሚጠቁም በመሆኑ ለመነሻነት መረጥኩት። << ዘመኑም ክፉ ነውና ቀጥ ብላችሁ አትሄዱም። ሚክ 2፥3  >>  እገምታለሁ በብዙም ባይሆን በጥቂቱ አሁን የኛን ዘመን ማን ክፉ አደረገው ? የሚል ሃሳብ ያላቸው ወገኖች ሊኖሩ ይችላሉ። ምክንያቱም የሰው ልጅ የስጋዊ ፊላጎቱ  ከተሟላለት ዘመኑን በጎ አድርጎ የማየት ልምድ ስላለው ነው።

ነቢየ እግዚአብሔር ሚክያስ ከክርስቶስ ልደት በፊት በ722 ዓ/ዓ  አካባቢ ትንቢት ይናገር የነበረ ነቢይ ነው። ትንቢቱም ስለሰማርያና ስለ ኢየሩሳሌም መፍረስ፣ እንዲሁም እግዚአብሔር እስራኤልን እንደመንጋ እንደሚሰበስብ፣ ኢየሩሳሌም እንደገና እንደምትሰራና አህዛብም እግዚአብሔርን እሚያውቁበት ዘመን እንደሚመጣ ፣ስለጌታ በቤተልሄም መወለድም ትንቢት ተናግሯል ።  ሚክ 1፥3 - 5፥1

የትንቢቱን እውነተኛነት ስንመለከት የዓለም መድኃኒት ኢየሱስ ክርስቶስ በቤተልሄም ተወልዷል፣ ማቴ 2፥1፣ ለአህዛብ ምስክር ይሆን ዘንድ የእግዚአብሔር መንግስት ወንጌል በዓለም ተሰብኳል ማቴ 24፥14 ፣ ጠፍተው የነበሩት የእስራኤል ልጆች ከመላው ዓለም ተሰብስበው በማእከለ ምድር በዓለም የምትፈራ ሃገር መስርተው እየኖሩ ነው።

ወደ እኛ ስንመለስ ሃገራችን ኢትዮጵያ ከዓለም ሃገራት የተለየች ሃገር መሆኗ በብዙዎች ዘንድ የሚታወቅ ነው። በመጽሐፍ ቅዱስ ተጽፎ እንደምናገኘው አንድም ጊዜ ቢሆን ኢትዮጵያ እግዚአብሔርን ከማምለክ ያቋረጠችበት ዘመን እንደሌለ እንረዳለን።

ስለ ኢትዮጵያ ማንነት ከማንም በላይ ምስክሩ መጽሐፍ ቅዱስ ነው። በዚህ ታላቅና ቅዱስ መጽሐፍ ውስጥ ከ40 ጊዜ በላይ ስሟ ተጠቅሶ ይገኛል። በተለይም ከዚህ በታች ያሉትን የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍሎች ስንመለከት ኢትዮጵያ ከእግዚአብሔር ጋር ያላትን ወዳጅነት በግልጽ እናይበታለን
ሙሴም ኢትዮጵያይቱን አግብቶአልና ባገባት በኢትዮጵያይቱ ምክንያት ማርያምና አሮን በእርሱ ላይ ተናገሩ። ዘኁል 12፥1
መኳንንት ከግብጽ ይመጣሉ ኢትዮጵያ እጆችዋን ወደ እግዚአብሔር ትዘረጋለች። መዝ 68፥31
በፊቱም ኢትዮጵያ ይሰግዳሉ፥ ጠላቶቹም አፈር ይልሳሉ መዝ 72፣9



አንተም የዘንዶውን ራሶች ቀጠቀጥህ ለኢትዮጵያ ሰዎችም ምግባቸውን ሰጠሃቸው። መዝ 74፥14
የኢትዮጵያ ንግድ ቁመተ ረጅሞችም የሳባ ሰዎች ወደ አንተ ያልፋሉ ለአንተም ይሆናሉ እጆቻቸውም ታስረው ይከተሉሃል በፊትህም ያልፋሉ፥ ለአንተም እየሰገዱ። በእውነት እግዚአብሔር በአንተ አለ፥ ከእርሱም ሌላ አምላክ የለም ብለው ይለምኑሃል። ኢሳ 45፥14
በውኑ ኢትዮጵያዊ መልኩን ወይስ ነብር ዝንጕርጕርነትን ይለውጥ ዘንድ ይችላልን? በዚያን ጊዜ ክፋትን የለመዳችሁ እናንተ ደግሞ በጎ ለማድረግ ትችላላችሁ። ኤር 13፣23


የእስራኤል ልጆች ሆይ፥ እናንተ ለእኔ እንደ ኢትዮጵያ ልጆች አይደላችሁምን? ይላል እግዚአብሔር፦ አሞ 9፥7

ከኢትዮጵያ ወንዞች ማዶ የሚማልዱኝ፥ የተበተኑት ሴቶች ልጆቼ፥ ቍርባኔን ያመጡልኛል። ሶፎ 3፥10

የጌታም መልአክ ፊልጶስን። ተነሥተህ በደቡብ በኩል ከኢየሩሳሌም ወደ ጋዛ ወደሚያወርደው ምድረ በዳ ወደ ሆነ መንገድ ሂድ አለው።
ተነሥቶም ሄደ። እነሆም፥ ህንደኬ የተባለች የኢትዮጵያ ንግሥት አዛዥና ጃንደረባ የነበረ በገንዘብዋም ሁሉ የሠለጠነ አንድ የኢትዮጵያ ሰው ሊሰግድ ወደ ኢየሩሳሌም መጥቶ ነበር      የሐዋ ሥ 8፥26

ዛሬ ዛሬ ኢትዮጵያ የእግዚአብሔር ሃገር፣ የክርስቲያን ደሴት ብሎ መናገር እንደወንጀል እየተቆጠረ ይመስላል። ሃገሪቱንም ያለስሟ ስም ለመስጠት የሚሞክሩ አካላት እንዳሉ እያየን ነው። የዛሬን አያርገውና ዛሬ ላይ ስሟን ሊቀይሩ የሚሞክሩት አካላትም ቢሆኑ ለመጀመሪያ ጊዜ የሚያውቋት የክርስቲያን ደሴት በሚለው ስሟ ነበር ዛሬ ከምን ተነስተው ስሟን ለመቀየር ደፈሩ?
 << አያያዙን አይተህ ጭብጦውን ቀማው >>  እንደተባለው በስሟ የተጠሩ ልጆቿ ይህን የክብር ስም ጠብቀው ለትውልድ ማስተላለፍ ስላልቻሉ ይሆን? በጥያቄ አልፈዋለሁ።

ሰሞኑን እንደተለመደው አህዛብ በቤተክርስቲያናችን ላይ አስነዋሪ ድርጊት ፈጽመዋል። የወንጀሉን ፈጻሚዎች ለህግ አቅርቦ እርምጃ የመውሰዱን ኃላፊነት ለመንግስትና ለቤተክርስቲያኒቱ ኃላፊዎች እንተወውና ከኛ ስለሚጠበቀው ነገር እናንሳ። እውነት ይህች ቤተክርስቲያን እንደጠላት መታየት ነበረባት? የሚለውን ጥያቄ ስናነሳ ህሊናውን ያጣ ወገን ካልሆነ በቀር ይህንን ሃሳብ አያስበውም። ህሊና የሌለው ሰው በሚያደርገው ነገር የመጸጸትም ሆነ የርህራሄ ልብ ስለሌለው ወዳጅና ጠላት ለይቶ ለማወቅ አይችልም በዚህም የተነሳ የበላበትን ወጭት ሊሰብር ይችላል። ስለዚህ ዘመኑ ህሊናቢሶች የበዙበት በመሆኑ እንደትላንቱ ተንጋሎ መተኛት ይቅርና ማንነትንና ክብርን ለመጠበቅ ዘብ መቆም ያስፈልጋል። ይህም ሲባል እንደአህዛብ ሰይፍ እንምዘዝ ማለት ሳይሆን ሁሉን ማድረግ ወደሚችለው አምላክ በአንድነት ሆነን በጾም በጸሎት እንመለስ።

የቤተክርስቲያኒቱ አርማዎች የሆኑት ሰላምና ፍቅር እንደ ጥንቱ መመለስ አለባቸው። ግርግር ለሌባ ይመቻል እንደተባለው ዛሬ ታፍራና ተከብራ በኖረችው ሃገራችን ላይ የሚፈነጩት አህዛብና መናፍቃን የሃገሪቱ ሰንደቅ አላማ የሆነችው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ማእበል እየናጣት መሆኑን በመረዳት ይመስላል። ስለዚህ ጆሮ ያለው መስማትን ይስማ ብሎ ጌታ በወንጌሉ እንደተናገረው የቤተክርስቲያን ልጆች በማይጠቅም ነገር እርስ በራሳችን ስንበላላና ስንንነካከስ እርስበርሳችን እየተጠፋፋን ነውና ወደ ማስተዋል እንመለስ ከምንጊዜውም በላይ ዛሬ ቤተክርስቲያን እውነተኛ ልጅ ያስፈልጋታል ዛሬ የቤተክርስቲያንን ሮሮ መስማት ካልቻልን ልጆቿ ነን ብንል መዘበት ይሆናል። ያለንበት ዘመን ክፉ ስም ይዞ የሚያልፈው በላዘመኖቹ እኛ በምንፈጽመው ክፉ ድርጊት በመሆኑ የትንቢቱ መፈጸሚያዎች እንዳንሆን በጊዜ ወደ ንስሃ
እንመለስ። በትምክህትና በትእቢት ኃጢአት አጉብጦን ቀና ማለት የተሳነን በይቅርታ መንፈስ እንመላለስ። ያን ጊዜ ቀና ብለን መሄድ እንችላለን።

  ዘመኑ ክፉ ነውና ቀጥ ብላችሁ አትሄዱም  ወስብሃት ለእግዚአብሔር ።















 












1 comment: