Thursday, January 23, 2014

ወደ ጌታህ ደስታ ግባ

ባለንበት ዘመን የብዙዎቻችን ጥረትና ድካም ሰውን ለማስደሰት መሆኑ እሙን ነው። ሰው ከተደሰተ እግዚአብሔር ይደሰታል ብለንም እናምናለን። እውነት ነው ለሌላው በጎ ማሰብ ከዚህ የሚበልጥ በረከት የለም። ነገር ግን የሰው ፍላጎት የማይገታ ስለሆነ ዛሬ ብናስደስተው ነገ ይከፋብናል። ሰው ሲባል ሁሉንም ያጠቃልላል ለምሳሌ ባል ሚስት ልጅ እናት አባት እህት ወንድም ባልንጀራ ወ ዘተ ነገር  ግን እውን ሰውን ደስ ማሰኘት ይቻላል? ሰው ስሜታዊ ነው ስሜት ደግሞ አንድ ጊዜ ይሞቃል አንድ ጊዜ ይቀዘቅዛል።  ብዙ ሰዎች ሰውን ለማስደሰት መልካም ሆኖ መገኘት በቂ መስሏቸው ለሰው ሲሉ የህይዎት መስዋዕትነት እስከ መክፈል ይደርሳሉ ነገር ግን ለሰው ልጅ ዘላቂ ደስታ መስጠት አይችሉም። አንዳንዶች እግዚአብሔርን ፈልገው ሄደው የሰው አገልጋይ የሚሆኑበት ጊዜ አለ። የነዚህ ሰዎች ችግር እግዚአብሄርን መፈለጋቸው ሳይሆን እግዚአብሔርን ፈልጎ ለማግኘት የሚያስፈልገው እምነት እና መንፈሳዊ እውቀት ስለሚጎላቸው ነው። ይህ በመሆኑ ምክንያት ሰዎች ከእግዚአብሔር ጋር እንዳይገናኙ የሚፈልገው ሰይጣን የሰው አገልጋይ ያደርጋቸዋል። ከዚያም ከሰው የሚገጥማቸው ፈተና ደስታቸውን ያርቅባቸዋል። ተስፋ ይቆርጡና እግዚአብሔርን መፈለግ   አቁመው አሰናካይ እስከመሆን ይደርሳሉ። ዛሬ  ከማን ወገን እንደሆኑ በማይታወቁ የበግ ለምድ ለብሰው በመጡ ባህታውያን ነን፣ መነኮሳት ነን ካህናት ነን በሚሉ አስመሳዮች ደስታቸውን ተነጥቀው  በተመሳቀለ መንገድ ላይ የቆሙ ብዙዎች ናቸው። ለሰው ሲሉ ሃይማኖታቸውን የሚቀይሩ፣ ለሰው ሲሉ ከቤተእግዚአብሔር የሚቀሩ፣ ለሰው ሲሉ ከአላማቸው ወደኋላ የሚሉ ወ ዘ ተ ብዙ ናቸው። እነዚህ ሰዎች በራሳቸው መልካም እንዳደረጉ ያስባሉ ። ነገር ግን ለሰው የምናደርገው መልካም ነገር ከእግዚአብሔር ጋር ላለን ግኝኙነት መሰናክል እስካልሆነን ጊዜ ድረስ ብቻ ነው።   

ደስታ ምንድነው
 
ሰፊ ትንተና የሚጠይቅ ርዕስ ቢሆንም ጥቂት ነገር ጠቁሜ  አልፋለሁ። በመጀመሪያ ሁለት አይነት ደስታ አለ መንፈሳዊ ደስታና ስጋዊ ደስታ። ከሁሉ አስቀድሞ የሁለቱን ልዩነት ማወቅ ያስፈልጋል። መንፈሳዊው ዘለዓለማዊ ሲሆን ስጋዊው ደግሞ ጊዜያዊና የሚያስከትለውም መራራ ፀፀት አለበት።
 
መንፈሳዊ ደስታ,, ከሰው ይልቅ እግዚአብሔርን ደስ ማሰኘት ነው። ይህን ለማድረግ ደግሞ  በዓለም ከንቱ ነገር መመካትን፣ ትዕቢትን ማራቅ እንዲሁም በአንደበት ሰውን ከማሳዘን፣በሃሜትን የሰውን ስጋ ከመብላት፣በጭካኔ በሰው ላይ ከመፍረድ፣ ያመነንን ከመክዳት እና ከመሳሰሉትን የዲያቢሎስ ግብሮች መቆጠብ ያስፈልጋል። እግዚአብሔርን ለማስደሰት የመጀመሪያው መስፈርት እነዚህን ክፉ ተግባራት ማራቅ ነው።  ቅዱስ መጽሐፍ እንደሚነግረን ደስታ ከመንፈስ ፍሬዎች አንዱ ነው ገላ 5፥26 ። የመንፈስ ፍሬ ማፍራት ደግሞ እግዚአብሔርን ደስ ማሰኘት ማለት ነው። በምድርም ሆነ በሰማይ የሰው ልጅ በሙሉ የሚመኘውና የሚያስበው  ደስታን ለማግኘት ነው። ነገር ግን የሁለቱን ልዩነት ባለማወቅ ሰዎች እግዚአብሔርን ያስደሰቱ መስሏቸው ለዲያቢሎስ ፊት አውራሪዎች ሆነው የሚታዩበት ጊዜ አለ። 
 
መንፈሳዊ ደስታ በጎ ነገር ከማድረግ ብቻ ይገኛል። ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከሶስቱ አገልጋዮች ታማኝ ለተባለው አገልጋይ እንዲህ ነበር ያለው  << ጌታውም። መልካም፥ አንተ በጎ ታማኝም ባሪያ፤ በጥቂቱ ታምነሃል፥ በብዙ እሾምሃለሁ፤ ወደ ጌታህ ደስታ ግባ አለው ማቴ 25፥21 >>  ከዚህ እምንረዳው የሰው ልጅ ፈቃደ እግዚአብሔርን በመፈጸሙ የሚያገኘው የጌታውን ደስታ እንደሆነ ነው። በእግዚአብሔር ዘን ለልጆቹ የተዘጋጀው ሁሉ በደስታ የተመላ ስለሆነ የጌታ ደስታ ተባለ። እግዚአብሔር ለቅዱሳኑ የሚሰጠው ጸጋና በረከት በደስታ ስለሆነ ደስታን የተመላ ነው። ትልቁ አባት ሐዋርያው ቅዱስ ያዕቆብም እንዲህ ይለናል << ወንድሞቼ ሆይ፥ የእምነታችሁ መፈተን ትዕግሥትን እንዲያደርግላችሁ አውቃችሁ፥ ልዩ ልዩ ፈተና ሲደርስባችሁ እንደ ሙሉ ደስታ ቍጠሩት ያዕ 1፥2  ከዚህ የምንረዳው መንፈሳዊ ደስታ በድካምና በፈተና ውስጥም እንዳለ ነው። ቅዱሳን መንፈሳዊ ደስታን እንዲህ ይገልጹታል።  ወደ እግዚአብሔር ቤት እንሄድ ባሉኝ ጊዜ ደስ አለኝ መዝ 122፥2 እግዚአብሔር የጽዮንን ምርኮ በመለሰ ጊዜ፥ እጅግ ደስተኞች ሆንን።በዚያን ጊዜ አፋችን ደስታን፥ አንደበታችንም ሐሴትን ሞላ በዚያን ጊዜ በአሕዛብ ዘንድ። እግዚአብሔር ታላቅ ነገርን አደረገላቸው ተባለ።እግዚአብሔር ታላቅ ነገርን አደረገልን፥ ደስም አለን። መዝ 126፥1 ምንም እንኳ በለስም ባታፈራ፥ በወይንም ሐረግ ፍሬ ባይገኝ፥ የወይራ ሥራ ቢጐድል፥ እርሾችም መብልን ባይሰጡ፥ በጎች ከበረቱ ቢጠፉ፥ ላሞችም በጋጡ ውስጥ ባይገኙ፥ እኔ ግን በእግዚአብሔር ደስ ይለኛል በመድኃኒቴ አምላክ ሐሤት አደርጋለሁ። ዕንባ 3፥17

ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ስለእውነተኛው ደስታ። ለመረጣቸው ለሰባ አርድዕት እንዲህ ነበር ያላቸው << ሰብዓውም በደስታ ተመልሰው። ጌታ ሆይ፥ አጋንንት ስንኳ በስምህ ተገዝተውልናል አሉት ,,, ,, ,, ,, ,, ,, , , , , , , , , ,  ነገር ግን መናፍስት ስለ ተገዙላችሁ በዚህ ደስ አይበላችሁ፥ ስማችሁ ግን በሰማያት ስለ ተጻፈ ደስ ይበላችሁ። ሉቃ 10፥17 >>  
 
ስጋዊ ደስታ  በዓለም ላይ የምናጘኘው ነገር ሁሉ ያስደስተናል ነገር ግን ጊዜያዊ በመሆኑ ደስታችን ዘላቂ አይሆንም። በጎም ብንሰራ ለውዳሴ ከንቱ ከሆነ ስጋዊ ደስታን እንጅ መንፈሳዊ ደስታን አያስገኝልንም ማቴ 6፥2 ስለዚህ በምድር ዋጋና ክብር አጘኝበታለሁ ብለን ደክመን የምናገኘው ደስታ ሁሉ  ስጋዊ ደስታ ይባላል። በመዝፈን፣ በመጨፈር፣ በመስከር፣ በዝሙት፣ በስርቆት እና በመሳሰለው እንዲሁም በራሳችን ላይ ሊደረግ የማንፈልገውን ነገር በሌላው ላይ አድርገን የምናጘኘው ደስታ ሁሉ ጊዜያዊና ከንቱ ነው።
 
ከላይ እንዳየነው በነገሮች እውነተኛ ደስታ ማግኘት የማንችለው አስቀድመን እውነተኛው ደስታ እንዴት ነው የሚገኘው? ብለን ስለማንመራመር ነው።
 
አንዳንድ ሰዎች ገንዘብ በማግኘት ብቻ ሙሉ ደስታ የሚያገኙ ስለሚመስላቸው ሌላውን የህይወት አማራጭ ሁሉ ትተው ገንዘብ ለማግኘት ይጥራሉ። ሰው ከሰራ ከለፋ የድካሙን ማግኘቱ ስለማይቀር ገንዘብ ያጘኛሉ ነገር ግን የተመኙትን ደስታ በገንዘባቸው መግዛት አይችሉም። ነገር ግን በተቃራኒው ፀፀትና ጭንቀት ውስጥ ይገባሉ። ሹመት በማግኘት ፣ጉዋደኛ በማግኘት፣ ትዳር በመመስረት፣ ልጅ በመውለድ ፣ብዙ ዘመን በመኖር  ሃገር በመቀየር ወ ዘ ተ ደስታ የሚገኝ የሚመስለንም ብዙዎች ነን፤ እነዚህ ሁሉ ግን እኛ እራሳችንን ሆነን ሁሉንም በጊዜውና በወቅቱ ማድረግ ካልቻልን ደስታን በራሳቸው ሊፈጥሩልን አይችሉም። የሰው ልጅ በየዘመኑ ሊያደርጋቸው የሚገቡ የተፈጥሮ ስርዓቶችን መጠበቅ ይኖርበታል። ልጅነት ፣ ወጣትነት፣ ጉልምስና፣ ሽምግልና፣ እነዚህ ሁሉ በጊዜያቸው ከተጠቀምንባቸው ይዘውት የሚመጡት ደስታ አለ። ቅዱሳን ሐዋርያት እንዳስተማሩን  <<  ከሰው ይልቅ ለእግዚአብሔር ልንታዘዝ ይገባል። የሐዋ ሥ  5፥29  >>  እንዳሉት ሁሉንም ነገር የእግዚአብሔርን ፈቃድ ጠይቀን ካደረግን ደስታችን ሙሉ ይሆናል። ስለዚህ የሰውን ፈቃድ ብቻ ለመፈጸም ከመትጋት የእግዚአብሔርን ፈቃድ መከተል ያስፈልጋል።  ይህ የሆነ እንደሆን ዘለዓለማዊውን ደስታ እንጎናጸፋለን።    

 

No comments:

Post a Comment