Sunday, October 28, 2018

ሀገር አፍራሽ እንጅ ሀገር ገንቢ ስልጠና አያስፈልገውም

ይህን ጽሁፍ ከጻፍኩት ሰንበት ብሏል። ምናልባት የእኔ እይታ ሚዛናዊነት ይጎድለው ይሆን? የሚል ሃሳብ ብልቤ ይመላለስ ስለነበር ከብዙ ሰዎች ሃሳብ ለመውሰድ ሞክሬያለሁ ይሁን እንጅ ተመሳሳይ ስሜቶች ለማየት ስለቻልኩ ምናልባት ለሚመለከተውን አካል ጥቆማ መስጠቱ ከጉዳቱ ጥቅሙ ያመዝን ይሆናል በሚል ሃሳቤን ለመግለጽ ሞክሬያለሁ።

ከወር በፊት በተለያዩ ሚዲያዎች ይንጸባረቅ የነበረው ሃሳብ የብዙዎችን ቀልብ የሳበ ነበር። አህያውን ፈርቶ ዳውላውን እንዲሉ በቡድን በተደራጀ መልኩ የሰው ህይዎትና ንብረት  ሲያጠፉ የነበሩ ወገኖች ሊሰጣቸው ይገባ የነበረውን የስነ ባህርይ ትምህርት ስለ ሀገር ሰላምና አንድነት ዘብ የቆሙ የአዲስ አበባ ወጣቶችን መንግስት ሰብስቦ በማሰር ስልጠና እየሰጠሁ ነው የሚል መግለጫ ሲሰጥ ስንሰማ ይህ ነገር ከበስተጀርባው የምንፈውራ ችግር ይኖር ይሆንን? ለማለት ተገደናል? አንድ ጤነኛ የሆነ ሰውን ለህመምተኛ የሚታዘዝ መድኃኒት ቢሰጡት ከጥቅሙ ጉዳቱ የከፋ ነው። መድኃኒት የሚያስፈልገው ለበሽተኛ  ነው። ለጤነኛው ቢሰጡት በውስጡ በሽታውን ካላገኘ ሌላ የስሜት ህዋሱን ይጎዳና ለሌላ ችግር ይዳርገዋል።


በትክክለኛው መንገድ ዜጋ የማፍራት ፍላጎት ካለን ብዙ የሚታነጹ ዜጎች አሉን። እግዚአብሔርን የማይፈሩ፣ ሰውን የማያፍሩ፣ ይሉኝታ የሌለባቸው፣ የሀገር ፍቅር ስሜት የሌላቸው ብዙ ወጣቶች የመንግስትን ድጋፍ ይፈልጋሉ። መንግስት ዜጎቹን አእምሯዊና ተፈጥሯዊ ሀብታቸውን ጠብቀው እንዲኖሩ የማድረግ ኃላፊነት አለበት። በእኛ ሀገር እየሆነ ያለው ግን ሰው ከእንሳት ባነሰ መልኩ ክብሩን አጥቶ የማይገባውን ተግባር ሲፈጽም እየታየ ምንም ዓይነት ለለውጥ የሚያበቃ እገዛ እየተደረገለት አይደለም። ሰው ከስህተቱ ይማራረል። ከስህተቱ እንዲማር እየተሳሳተ መሆኑን የሚነግረው ይፈልጋል። ይህ ካልሆነ ማንኛውንም ወንጀል ሲሰራ ምንም ዓይነት የህሊና ጸጸት ላይሰማው ይችላል ምክንያቱም እውቀት በማጣት ከሰውነት ባህርይ  ወጥቷልና።

ሰውን ሰቅለው የገደሉ፣ እንደ እንስሳ አርደ ው በመግደል የንጹሐንን ደም ያፈሰሱ፣ ሀገር ለማፍረስ ሌት ተቀን የሚሰሩ ወገኖች ባሉበት ሀገር ሰው በመሆኑ ሁሉም እኩልነት ይገባዋል የሚል አቋም አንግበው ስለ ሀገር አንድነት የሚናገር መሪ በመነሳቱ ድጋፋቸውን እስከሞት ድረስ ያሳዩ የአዲስ አበባ ወጣቶችን ማሰር እህያው እያለ ዳውላውን እንደማለት ነው።

ሀገር ሊገነባና ሊበለጽግ የሚችለው ፍትሃዊ አስተዳደር ሲኖር ነው። ከምንም በላይ ሊሰራበት የሚገባው ጉዳይ ቢኖር ጨለምተኛ አስተሳሰብን ከመንግስት አካላት ማጥፋት ነው። መንግስት ሲባል ከጥቃቅን የመንግስት መስሪያ ቤት ሰራተኞች ጀምሮ መሆኑ ሊታወቅ ይገባዋል። ጠቅላይ ሚኒስትሩና ካቢኔያቸው በጎ ዓላማ ይዘዋል ማለት ብቻቸውን ሀገር ይገነባሉ ብሎ መታሰብ የለበትም። ሰፊውን ሚና ሊጫወቱ የሚችሉት በህዝቡ ውስጥ ያሉ የመንግሥት እና የሃይማኖት እንዲሁም የሲቪክ ተቋማት መሪዎች ናቸው። ዛሬ በየቦታው እየተፈጠረ ላለው ችግር ትልቁን ሚና እየተጫወቱ ያሉት እነዚህ አካላት ናቸው። የዶ/ር አቢይ የለውጥ ካቢኔ እነዚህን ተቋማት በመፈተሽ የለውጡ አካል እንዲሆኑ ማድረግ ካልቻለ በተሰበረ ማሰሮ ዉሃ እንደመሙላት ነው የሚሆነው።

የአዲስ አበባ ወጣቶች ኑሮን ለማሸነፍ ህግ አልባ በሆነችው ከተማ ጠዋት ወጥተው ማታ እስኪገቡ ያለ እረፍት ሲባዝኑ እንደሚውሉ ኖሬ አይቼዋለሁና ምስክር ነኝ። አዲስ አበባ  በልጅነት እድሜለተሻለ ኑሮ  ከተወለድንበት አካባቢ በመምጣት የህይዎት ለውጥ ያየንባት ከተማ በመሆኗ ሁላችንም የባለቤትነት ስሜት ይሰማናል። አዲስ አበባ ሲባል ምድሪቱ ብቻ ሳትሆን ህዝቧን ጭምር መሆኑን ልብ ይሏል።

በመጨረሻም በሀገራችን ለውጥ እንዳይመጣ የሚጥሩ አካላትን ቁጥጥር በማድረግ በህግ እንዲጠየቁ ማድረግ የመንግስት ኃላፊነት ነው ይህ ካልሆነ የለውጡን አካላት ተስፋ አልባ እያደረጉ የሚለወጥም ሆነ የሚቀየር ነገር አይኖርeመ ስለዚህ በጉልህ እንደታየው ክቡር ጠቅላይ ሚንስትር አቢይም እንደተነገሩት የአዲስ አበባ ወጣቶችም ሆኑ ሌሎች ዜጎች በስውር ደባ በደል ደርሶባቸዋልና ይቅርታ ሊባሉ ይገባል ይቅርታ የሰውን ሞራል ይደግፋልና።



ጥቅምት 2011 አዲስ አበባ ኢትዮጵያ።


No comments:

Post a Comment