Tuesday, May 1, 2018

"ክፉውን ስለ ክፉ ፈንታ አትመልሱ"


ስለ ክፋት ታሪካዊ አመጣጥ በመጠኑ ለመጠቆም አሰብኩና ምናልባት የክፋት ሰዎችን ቅር ያሰኝ ይሆን የሚል ሀሳብ ጎበኘኝ ነገር ግን ክፋት ምንጊዜም በጎ አያስብምና ወደ ኋላ ትቶ እውነቱን ማሳየቱ የክፋትን ጎጅነት ብዙ ሳይረዱ የክፋት ሰላባ የሆኑ ወገኖቻችን ማንቃት ይገባልና የግል ሃሳቤን ላካፍል ወደድኩ። 

ሰዎች በባህሪያቸው ክፉ ናቸው ከማለት ይልቅ የአንዳንድ ሰው ባህርይ የክፋት አባት ለሆነው ለዲያብሎስ ምቹ ሆኖ ስለሚገኝ የሰይጣን ፈረስ ሊሆን ይችላል ማለቱ ይቀላል። በቅዱስ መጽሐፍ ከሰውም ከእንስሳም ተንኮለኛ የተባሉ አሉ። ነገር ግን ባህርያቸው ሆኖ ሳይሆን የክፋት አባት ለሆነው ለዲያብሎስ ምቹ ሆነው በመገኘታቸው ነው። ለምሳሌ ይሁዳን ብንወስድ; በፊቱ ካለው በረከት ይልቅ ለማይጠቅም ለሚጠፋ ገንዘብ ልቡን ስለከፈተ፦  "፤ ሰይጣንም ከአሥራ ሁለቱ ቍጥር አንዱ በነበረው የአስቆሮቱ በሚባለው በይሁዳ ገባ፤  (ሉቃ22: 3)" ይላል።  እንዲሁም አስቀድሞ በሰው ልጅ ላይ ዲያብሎስ ሞትን ሲያመጣ በእባብ ተመስሎ እንደሆነ አይዘነጋም። "፤ እባብም እግዚአብሔር አምላክ ከፈጠረው ከምድር አውሬ ሁሉ ይልቅ ተንኰለኛ ነበረ። ዘፍ 3: 1)"

ክፋትን አጉልቶ በማሳየት ከዲያብሎስ ቀጥሎ ቃየንን የሚቀድመው የለም። ዲያቢሎስ አዳምን ክፉ ለማሰራት የደከመውን ያክል ምድረ ፋይድ ነውና ያገኘው  ለቃየን አልደከመም። ወንድሙን እንዴት መግደል እንዳለበት አሳየው ቃየንም በጎ ህሊናውን የጣለ ሰው በመሆኑ ወንድሙን ለመግደል ጊዜ አልፈጀበትም። ምክንያቱ ደግሞ እግዚአብሔር መስዋእቱን ለምን ተቀበለለት ብሎ ነበር። በመሆኑም በውንድሙ ሞት ተጠያቂ የሆነው እራሱ ነው። የአዳምን በደል እና ቅጣት ስንመለከት ከበስተጀርባው የነበሩ ፍጥረታት ተገልጸዋል። ሰይጣን፣ እባብ፣ ሄዋን ለአዳም ውድቀት ምክንያቶች ነበሩ።

በገነት ኃጢአት መሥራት እና በምድረ ፋይድ አንድ አይደለም። ይህም በአዳምና በቃየን ታይቷል አዳም በገነት ሳለ እፀ በለስን ለመብላት ብዙ ተከራክሯል በሄዋን በኩል ተሸነፈ እንጅ ዲያቢሎስን አሳፍሮ መልሶት ነበር። ቃየን ግን በምድረ ፋይድ ነውና ያለው በማሰብም፣ በመናገርም፣ በማድረግም ኃጢአት ሲሰራ ቆም ብሎ ማሰብ አልቻለም። ካለው ነገር ላይ ለእግዚአብሔር መስዋዕት ማቅረብ ሰሰተ፣ በወንድሙ ላይ በቅንአት ተነሳሳ፣ ወላጆቹን አሳዘነ፣ ወንድሙን ገደለ፣ በፈጣሪው ላይ ክፉ ቃል ተናገረ ይህን ሁሉ በማድረጉ ተቅበዝባዥ ሆነ። "ኃጥኣንን ኃጢአቱ ታጠምደዋለች፥ በኃጢአቱም ገመድ ይታሰራል። " ( ምሳ 5: 22) እንዲል ቅዱስ መጽሐፍ ኃጢአት ያሳድደው ጀመር።

በዘመናችን ያሉ የቃየል አምሳያዎች ብዙ ናቸው። ይኖሩም ዘንድ ግድ ነው። አንዳንዶች የክፉ ሰዎችን በዓለም ላይ መብዛት በማሰብ ዓለም ልትጠፋ ነው ብለው ያስባሉ ነገር ግን ክፉ ሰዎች ያልነበሩበት ጊዜ የለም ወደፊትም ይኖራሉ። በመሰረቱ ክፉ ባይኖር መልካም እሚባል ነገር አይኖርም፣ ጨለማ ባይኖር የብርሃን ክብር አይገለጥም፣ ሞት ባይኖር ህይዎት መኖሩን እንዴት እናውቅ ነበር? ቅዱስ ዳዊት " "፤ እግዚአብሔርን እንዲህ በሉት። ሥራህ ግሩም ነው። " (መዝ 66: 3) እንዳለው እግዚአብሔር በፍጥረቱ እጅግ ድንቅ ነው። 

ክፉ ሰው ሁልጊዜም ክፍትን ማድረግ ያስደስተዋል ለባህርይው የሚስማማው በመሆኑ ክፋትን ለማድረግ ብዙ ዋጋ ይከፍላል። ዛሬ ላለንበት ክፉ የዘረኝነትና የመለያየት በሽታ ብዙ ክፉ ሰዎች ዋጋ ከፍለዋል። እነሱ የዘሩትን ነው እኛ ዛሬ እያጨድን ያለነው። ከሁሉ በላይ ሊሰመርበት የሚገባው አሁን ላለው ትውልድ ከአቅሙ በላይ ክፉ ዘር ተዘርቶበታል። የሆነው ሁሉ የክፋት ዓላማ ነበረው። ክፉ ሰዎች ሰይጣን መልኩን እንዲለውጥ በጎ መስለው ብዙ የተንኮል ዘር ሲዘሩ ቆይተዋል። ጌታ በወንጌል  "ከፍሬያቸው ታውቋቸዋላችሁ። ከእሾህ ወይን ከኩርንችትስ በለስ ይለቀማልን? እንዲሁ መልካም ዛፍ ሁሉ መልካም ፍሬ ያደርጋል፥ ክፉም ዛፍ ክፉ ፍሬ ያደርጋል። መልካም ዛፍ ክፉ ፍሬ ማፍራት፥ ወይም ክፉ ዛፍ መልካም ፍሬ ማፍራት አይቻለውም ማቴ 7፥16 " ብሎ እንደተናገረው። በጥላቻ በተሞላ ህብረተሰብ ውስጥ መልካም ትውልድ ማፍራት ከባድ ነው። አሁንም ለትውልድ የሚተርፍ መልካም ዘር መዝራት ካልቻልን ካለፈውም የከፋ በደል ይሆናል። ክፉውን ነገር ተጸየፉት እንደተባለው  የክፉ ሃሳብ ውጤቱ ምን እንደሆነ ዛሬ ላይ ያለን ሁላችን ምስክሮች ነን።

ክፉ ሰው መጀመሪያ የሚጎዳው እራሱን ነው። ክፉ ሰዎችን ወደ በጎ መመለስ ከእሳት እንደ ማውጣት ይቆጠራል "፤ አንዳንዶችንም ከእሳት ነጥቃችሁ አድኑ፥ " (የይሁዳ መልእክት 1: 22) እንዳለው ሐዋርያው በፍቅር ከክፋት መንገዳቸው ልንመልሳቸው ይገባል። የብዙ ሰዎችን ህይዎት ስንመለከት በክፋትና በተንኮል ተጠምደው ሰዎችን የሚጎዳ ነገር ያደርጋሉ። የሚያሳዝነው ክፉ እያደረጉ መሆናቸውን አለማወቃቸው ነው። ጌጌታ በመስቀል ላይ ሳለ ከተናገራቸው ቃላት አንዱ ""፤ ኢየሱስም። አባት ሆይ፥ የሚያደርጉትን አያውቁምና ይቅር በላቸው አለ። " (ሉቃ 23: 34) ይህን ቃል እያሰብን ለክፉዎች ልንጸልይ ይገባል።

በሀገራችን በኢትዮጵያ አሁን እየታየ ያለው መረጋጋት ለብዙዎች እፎይታን አስገኝቷል። ይሁን እንጅ አሁንም ጥንቃቄ ካልተደረገለት በየስፍራው የተዳፈነ እሳት እንዳለ ከሚሰጡት አስተያየቶች ለመረዳት ይቻላል። መንግሥት እንደ መሪነቱ የችግሩም ባለቤት በመሆኑ ከላይ እስከታች ያሉት የስራ አስፈጻሚዎች የተበላሸውን ለመጠገን በጠቅላይ ሚንስትሩ እየተገለጸ ያለውን በህዝቡ ዘንድ ተቀባይነት ያገኘ መልካም አርዓያ የመሆን ጅምር ለማስፈጸም ቁርጠኝነት ማሳየት አለባቸው። በክፋትና በተንኮል ውስጥ ለሚኖሩ ሰዎች ልጓም ሊበጅላቸው ይገባል። 

ኢትዮጵያዊያን ከሌሎች ህዝቦች ልዩ የሚያደርገን ዛሬ ያለው ትውልድ ስላላስረከብነው ቢዘነጋውም ከጥንት የመጣ የመልካም ወግና ባህል ባለቤቶች ነን። ቀድሞ የነበሩት የሀገራችን መሪዎች በሰብአዊ ክብር ላይ ለሚፈጸም በደል ትእግስት ያልነበራቸውና ስለ ሰው ልጆች ምንቸገረኝ የማይሉ ነበሩ። የእነ አፄ ዳዊትን ታሪክ ስናነብ ከሀገራቸው አልፈው ለሌሎች ህዝቦች ጥብቅና ይቆሙ እንደነበር በታሪክ አንብበናል። ዛሬ ላይ በገዛ ሀገራችን በደል ደረሰብን የሚሉ ሁሉ የእነዚህ አባቶች ልጆች በመሆናቸው በደልን መቋቋም ከባድ ቢሆንባቸውም አይደል?

ክፋት ለምን በዛ ብንል መልካም ሰዎች በክፉዎች በመሸነፋቸው መሆኑ ግልጽ ነው። ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ "፤ ክፉውን በመልካም አሸንፍ እንጂ በክፉ አትሸነፍ (ሮሜ  12: 21)" እንዳለው በጎ ህሊና ያላችሁ ወገኖች መልካምነትን፣ ፍቅርን፣ መዋደድን፣ መከባበርን፣ መተዛዘንን፣ ከምንም በላይ እግዚአብሔርን መፍራትን በተግባር ማሳየት አለባችሁ። በዚህ ዘመን ብዙ የሚናገሩ እንዳሉ ሁሉ ብዙ መልካም አንደበቶች ተለጉመው ኃላፊነታቸውን የዘነጉ እንዳሉ የማይታበል ሐቅ ነው። በክፉ ወሬ ህዝብ እየታመሰ ዝም ብሎ ማዳመጥ ግዴታን አለማወቅ ነው።

ኦርቶዶክሳዊት ተዋህዶ ቤተክርስቲያናችንን በተመለከተ; የሌሎች የእምነት ተቋማት መስፋፋት አያስፈራትም። የኔ የግሌ ሃሳብ የነሱ መብዛት የእኛ ድክመት እንጅ የነሱ መብት በዝቶ የኛ በመጓደሉ ብቻ አይመስለኝም። አሁንም የግሌ አስተያየት ነው; ቤተክርስቲያናችን ውስጥ ያለው ብልሹ አስተዳደር ቢስተካከል ስፍራ አይበቃንም ነበር። በየ አዳራሹ የአጋንንት መጫወቻ የሆነው መንጋ ወደ እውነተኛ በረቱ የሚያስገባው በማጣቱ እንጅ ከኦርቶዶክሳዊት ተዋህዶ ቤተክርስቲያን የተሻለ ስፍራ አግኝቶ አይደለም።  በሌላም መልኩ አባቶቻችን ያስተማሩን ሁሉንም እየወደድን በፍቅር ልንማርክ እንጅ በግድ አይደለም ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን መቼም ቢሆን አልጋ በአልጋ ሆኖላት አያውቅም ወደፊትም አይጠበቅም። ከአባቶቻችን የተማርነው ሰማያዊ ክብርን እንጅ ምድራዊ ተድላ ደስታን አይደለም። በኑሯችን ልንተገብረው የሚገባንን ጌታ በመዋእለ ሥጋዌው። ያስተማረው እንዲህ ይነበባል፦ " ስለ ጽድቅ የሚሰደዱ ብፁዓን ናቸው፥ መንግሥተ ሰማያት የእነርሱ ናትና። ሲነቅፉአችሁና ሲያሳድዱአችሁ በእኔም ምክንያት ክፉውን ሁሉ በውሸት ሲናገሩባችሁ ብፁዓን ናችሁ። ዋጋችሁ በሰማያት ታላቅ ነውና ደስ ይበላችሁ፥ ሐሴትም አድርጉ፤ ከእናንተ በፊት የነበሩትን ነቢያትን እንዲሁ አሳድደዋቸዋልና። እናንተ የምድር ጨው ናችሁ፤ ጨው አልጫ ቢሆን ግን በምን ይጣፍጣል? ወደ ውጭ ተጥሎ በሰው ከመረገጥ በቀር ወደ ፊት ለምንም አይጠቅምም። እናንተ የዓለም ብርሃን ናችሁ። በተራራ ላይ ያለች ከተማ ልትሰወር አይቻላትም። መብራትንም አብርተው ከዕንቅብ በታች አይደለም እንጂ በመቅረዙ ላይ ያኖሩታል በቤት ላሉት ሁሉም ያበራል። መልካሙን ሥራችሁን አይተው በሰማያት ያለውን አባታችሁን እንዲያከብሩ ብርሃናችሁ እንዲሁ በሰው ፊት ይብራ ማቴ 5፥10   ስለ ሌሎች ስናወራ የቤት ሥራችንን እንዳንዘነጋው ያስፈልጋልና የቤተክርስቲያናችንን አስተምህሮ ከሁሉ በፊት ማወቁ መልካም ነው። 
ቸር እንሰንብት።.

No comments:

Post a Comment