ሰሞኑን በሶሻል ሚዲያ እየተናፈሰ ያለውን የአንድ ግለሰብ አመለካከትን
የሚያንጸባርቅ ንግግር ብዙዎች ትኩረት በመስጠት ሲቀባበሉት ተመልክተናል። አቶ ጃዋር መሐመድ የሚባል የፖለቲከኝነትና የዘረንነት
እንዲሁም የሃይማኖት አክራሪነትን በማንጸባረቅ የሚታወቅ ግለሰብ እንዳለ ግልጽ ነው። ይህንንም ዓላማውን በተለያዩ መድረኮች ባገኘው
አጋጣሚ ሲያንጸባርቅ እንደነበር የሚያውቁት ሁሉ ምስክሮች ናቸው።
ታዲያ አሁን ምን አዲስ ነገር ተሰማና ነው ሽብር እየተነዛ ያለው? በጆሮየ ባልሰማውም ቤተክርስቲያን ይፍረስ ብሎ ተናግሯል
በሚል ነው መወያያ የሆነው። ጌታ በወንጌል ‘’ከእሾህ ወይን ከኩርንችትስ በለስ ይለቀማልን ማቴ 7፥16’’ ብሎ እንደተናገረው በእኔ
መረዳት ከእሱ ንግግር ይልቅ የእሱን እኩይ ዓላማ ለደጋፊዎቹ በማሰራጨት ላይ ያለነው እኛ ነን ቤተ ክርስቲያንን እየጎዳን ያለነው።
በረከታቸው ይደርብንና ታላቁ የቤተክርስቲያናችን አባት ብፁዕ አቡነ ጎርጎርዮስ በሁሉ ዘንድ የሚታወቅ ንግግር/ አባባል አላቸው
’’ሥራህን ሥራ” ይህ አባታዊ ምክር ብዙዎችን አንጿል። ዛሬ በየሚዲያው የቤተክርስቲያን ጠላቶች የሆኑ አካላት የሚሰነዝሩትን ቃላት
ከምንሰነጥቅ ሥራችንን ብንሰራ መልካም ነው። ቤተክርስቲያን እንኳን ጃዋር የመሃመድ ልጅ መሃመድ እራሱም ቢነሳ አትሸበርም። ጃዋር
ስለተናገረ ቤተክርስቲያን ይፈርሳል ብሎ የሚደነግጥ ካለ ጠባቂዋ እግዚአብሔር መሆኑን መዘንጋት ነው።
ጃዋር በጠባብ መንግድ ውስጥ ባገኘው አጋጣሚ ተልእኮውን እየፈጸመ ነው።
እኛ ደግሞ እለት እለት የ
ሀገርና የቤተክርስቲያን አንድነት የሚያስጨንቀው መሪ እግዚአብሔር ሰጥቶን ስለምናምንቴው ጃዋር ማስታወቂያ እንሰራለን። እንደ አለመታደል ሆኖ
እንጅ ዛሬ ላይ እግዚአብሔር በሰራው ድንቅ ስራ ተመርኩዘን ብዙ በጎ ነገር ማድረግ ነበረብን። ትላንት በመንግስት ምክንያት የተዘጋው
የሰላምና የእድገት በር በእግዚአብሔር ኃይል ተከፍቷል። አሁን መሆን ያለበት ስለ ሰዎች የምናወራበት ሳይሆን በሰላሙ መንገድ ተጉዘን
መልካም ፍሬ ለማፍራት የምንሽቀዳደምበት ነው። ከጃዋር በፊት የምናውቃቸው ዓላማቸውን በተግባር ያሳዩ እነግራኝ መሃመድ በቂ የጥፋት
ታሪክ አስቀምጠውልን ሄደዋል። ያንን ዓላማ ይዞ የሚመጣ ሁሉ እድል ቢያገኝ ቤተክርስቲያንን ለማጥፋት ዓላማው ግድ ይለዋል። ስለዚህ
የሱን ንግግር እንደ ማንቂያ ደወል መመልከትና እራስን ከጥፋት ለማዳን መዘጋጀት እንጅ እንካ ሰላምታ መግባት ብልሃት ማጣት ነው። የቤትክርስቲያናችን ችግሮች እንደጃዋር አይነቶቹ ሳይሆኑ፣ ከቤተክርስቲያን
አናት ላይ ተቀምጠው መንጋውን መሰብሰብ ሳይሆን መበተን ተባራቸው ያደረጉ የእኛው አባቶች ናቸው። ሌሎቹ ደግሞ ሳይላኩ ተልከናል፣
ሳያውቁ አውቀናል፣ በስሜት እንጅ በእምነትና በእውቀት ያልታነጹ ወገኖች ናቸው። እነዚህ ወገኖች የራሳቸውን እይታ ብቻ በማንጸባረቅ
ለቤተክርስቲያን ጠላቶች ኃይል እየሆኑ ነው። ከአጥፊዎች ወገን የሚሰነዘረውን ክፉ ሃሳብ በማስተዋል ህዝቡን በእግዚአብሔር ቃል አንጾ
ከማረጋጋት ይልቅ ሽብር በመንዛት በፍርሃት እንዲኖር እያደረጉት ነው። እኔ ግን ደግሜ እላለሁ ቤተክርስቲያን በእግዚአብሔር ፈቃድ
እንጅ በፕሮፓጋንዳ አትፈርስም አትሰራም።
አባቶቻችን ቤተክርስቲያናችንን በክብር ከሁሉ በላይ ከፍ እንድትል ያደረጉት
በዝምታ እና በበጎ ምግባር እንጅ በመለፍለፍ አይደለም። ዛሬ ላይ ቤተክርስቲያንን የማያውቁ በማይመለከታቸው ቤተክርስቲያንን በማይመጥን
መልኩ እየጻፉና እየተናገሩ ቤተክርስቲያን የሌላትን ባህርይ ክርክር ጥላቻ ዘረኝነት መለያየት በዙሪያዋ እንዲከባት እያደረጉ ነው።
በዚህም የተነሳ መልካም ስሟን በድፍረት የሚያጎድፉ ሰዎች ሊነሱ ችለዋል። ስለዚህ ካለፈው ስህተት ተምረን ቤተክርስቲያናችንን መጥቀም
ቢያቅተን የጉዳቷ ተባባሪ ከመሆን መቆጠብ አለብን።
እንደምናየው ዛሬ ላይ እግዚአብሔር ይመስገን ቤተክርስቲያን ከላይ እስከታች
ድረስ የአገልጋይ ችግር የለባትም። ለአንድ ህገረ ስብከት ሁለት ሶስት ሊቃነ ጳጳሳት መመደብ የሚቻልበት ደረጃ ላይ ደርሰናል የአብነት
ትምህርት ቤቶችና የግቢ ጉባኤያት በየጊዜው አገልጋይ እያፈሩ ነው።
ትላንት በመለያት ምክንያት የተበተነው መንጋ የሚሰበሰብበት እድል ሰፊ ነው። ስለዚህ እግዚአብሔር የጀመረውን የቸርነትሥራ እስኪፈጽም
ዲያቢሎስ በነዛው የሃሰት ወሬ በመሸበር አንታወክ። ቤተክርስቲያን በፕሮፓጋንዳ አትፈርስም አትሰራም።
መጋቤ ሃይማኖት ዘለዓለም ጽጌ
ጥቅምት 2011 ዓ/ም አዲስ አበባ ኢትዮጵያ።
No comments:
Post a Comment