Wednesday, March 7, 2012

ስምና ተግባር

ስም( noun) መጠሪያ  መለያ መገለጫ ወ , ዘ , ተ , ልንለው እንችላለን። በቀደመው ዘመን ስም ይሰጥ የነበረው ከተግባር ጋር ተያይዞ እንደነበር ቅዱስ መጽሐፍ ይነግረናል ። በተለያየ የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል ውስጥ ከመልካም ስራቸው የተነሳ እግዚአብሔር አዲስ ስም የሰጣቸው ሰዎች እንዳሉም እናያለን። አብርሃምና ሳራ << ከዛሬም ጀምሮ እንግዲህ ስምህ አብራም ተብሎ አይጠራ፥ ነገር ግን ስምህ አብርሃም ይሆናል ለብዙ አሕዛብ አባት አድርጌሃለሁና። ዘፍ 17፥5 እግዚአብሔርም አብርሃምን አለው፦ የሚስትህን የሦራን ስም ሦራ ብለህ አትጥራ፥ ስምዋ ሣራ ይሆናል እንጂ። ዘፍ 17፥15 ፣ ያዕቆብ << እግዚአብሔርም፦ ስምህ ያዕቆብ ነው ከእንግዲህም ወዲህ ስምህ ያዕቆብ ተብሎ አይጠራ፥ ስምህ እስራኤል ይባል እንጂ አለ ስሙንም እስራኤል ብሎ ጠራው። ዘፍ 35፥10 >> ቅ/ጳውሎስ የሐዋ ሥ 13፥9፣ ቅ/ጴጥሮስ ማቴ 16፥6  
ከእግዚአብሔር ቀጥሎ አዳም ለፍጥረታት ሁሉ መጠሪያ እንደሰጣቸው በመጽሐፍ ቅዱስ ተጽፏል። ይህም ገዥነቱን አስተዳዳሪነቱን ያመለክታል። << እግዚአብሔር አምላክም የምድር አራዊትንና የሰማይ ወፎችን ሁሉከመሬት አደረገ በምንስም እንደሚጠራቸውም ያይ ዘንድ ወደ አዳም አመጣቸው አዳምም ሕያው ነፍስ ላለው ሁሉ በስሙ እንደጠራው ስሙ ያው ሆነ። አዳምም ለእንስሳት ሁሉ፥ ለሰማይ ወፎችም ሁሉ፥ ለምድር አራዊትም ሁሉ ስም አወጣላቸው ዘፍ 2፥19 >>



( እስመ ስሙ ይመርሆ ኃበ ግብሩ) እንደተባለው ከዚህ ቀጥሎ ያሉትን ጥቂት የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅሶች ስንመለከት ስም በምክንያት ይወጣ እንደነበር እናያለን።  አዳምም ለሚስቱ ሔዋን ብሎ ስም አወጣ፥ የሕያዋን ሁሉ እናት ናትና ዘፍ 3፥20 አዳም ደግሞ ሚስቱን አወቀ ወንድ ልጅንም ወለደች ስሙንም ቃየን በገደለው በአቤል ፋንታ እግዚአብሄር ሌላ ዘር ተክቶልኛል ስትል ሴት አለችው ዘፍ 4፥25
ከእንግዲህ ወዲህ ስምህ እስራኤል ይባል እንጂ ያዕቆብ አይባል ከእግዚአብሔር ከሰውም ጋር ታግለህ አሸንፈሃልና። ዘፍ 32፥28
እርስዋም የእግዚአብሔር ታቦት ስለ ተማረከች ስለአማትዋና ስለ ባልዋም። ክብር ከእስራኤል ለቀቀ ስትል የሕፃኑን ስም። ኢካቦድ ብላ ጠራችው። 1 ሳሚ 4፥21
(ይስሃቅ) ሣራም፦ እግዚአብሔር ሳቅ አድርጎልኛል ይህንንም የሚሰማ ሁሉ በእኔ ምክንያት ይስቃል አለች። ዘፍ 21፥7
እኔ ከውኃ አውጥቼዋለሁና ስትልም ስሙን ሙሴ ብላ ጠራችው። ዘጸ 2፥10
ሐና ወንድ ልጅ ወለደች እርስዋም፦ ከእግዚአብሔር ለምኜዋለሁ ስትል ስሙን ሳሙኤል ብላ ጠራችው። 1ኛ ሳሙ 1፥20
ስለዚህም ስምዋ ባቢሎን ተባለ፥ እግዚአብሔር በዚያ የምድርን ቋንቋ ሁሉ ደባልቋልና ከዚያም እግዚአብሔር በምድር ሁሉ ላይ እነርሱን በትኖአቸዋል። ዘፍ 11፥9
እርስዋም ይናገራት የነበረውን የእግዚአብሔርን ስም ኤልሮኢ ብላ ጠራች የሚያየኝን በውኑ እዚህ ደግሞ አየሁትን? ብላለችና። ዘፍ 16፥13

 ፍጡር በሙሉ ሰውም ሆነ እንስሳ እጽዋትም ሆኑ አዝርዕት ህያውም ሆነ ግኡዝ የተገለጠም ሆነ ወደፊት ይገለጣል ተብሎ የሚታመን ነገር የሚቆጠርም ሆነ የማይቆጠር እንዲሁም በዓይን የማይታይ በሙሉ ስም አለው ከዚህም በላይ ፈጣሬ ዓለማት አምላካችን እግዚአብሔርም ስም አለው ስለዚህ ከሆነው ነገር ሁሉ ስም አስፈላጊ መሆኑን እናያለን። ።
አንድ ሰው በስጋ ከእናት ከአባቱ ሲወለድ በመጀመሪያ የሚሰጠው ስም ነው። ዘፍ 3፥20 ዘፍ 21፥3 ሉቃ 1፥59  እንዲሁም ወላጆች ለልጆቻቸው ፣ ባል ለሚስቱ፣ ሚስት ለባሏ ወ ዘ ተ የፍቅር መግለጫ የሆኑ የግል ስሞችን ይሰጣሉ። በሃገራችን በኢትዮጵያ ሴት ልጅ ስታገባ ቀድሞ ከነበራት ስም ሌላ የባሏ ቤተሰቦች የሚያወጡላት ስም አለ። ይህም የሚያመለክተው የልጅ ሚስት እንደልጅ እንደምትታይና ለልጆቻቸው ስም እንደሚያወጡት ሁሉ እሷም አዲስ ያገኟት ልጃቸው ስለሆነች አዲስ የሆነ መልካም ስም ቤተዘመድ በተሰበሰበበት ተመርጦ ይወጣላታል ።

በቤተክርስቲያናችን ስርዓት መሰረት በእውቀታቸው ፣ በምግባራቸው፣ በንጽህናቸው፣ በቅድስናቸው በሰውም ሆነ በእግዚአብሔር የተመሰከረላቸው ሰዎች የክብር የማእረግ ስም ይሰጣቸዋል።

ይህ ሁሉ መልካም እንደሆነ ሁሉም ይስማማበታል።  ባለንበት ዘመን ያለውን የስም አወጣጥ ስንመለከት ቀድሞ ከነበረው ጋር ለየቅል ሆኖ እናገኘዋለን። መልከ ጥፉን በስም ይደግፉ እንደሚባለው ዛሬ ላይ ያሉ ስም አውጭዎች የሰውን ባህርይና ተግባር ችሎታና እውቀት ያላገናዘበ ስም ሲሰጡ ይታያል። የስም ዋናው አላማ ምንነትን መግለጥ ነው። ለሰውም ሆነ ለእንስሳ ወይንም ለግኡዝ ነገር የምንሰጠው ስም ተግባሩን የሚያመለክት መሆን ይገባዋል። አንዳድንድ ጊዜ ከአንድ በላይ ስም የምንሰጠው ነገር ሊኖር ይችላል።  ተግባሩን የምንገልጥበት ነው።  ስም መውጣቱ መልካም ሆኖ ሳለ አለቦታው ስለሚሰጥ ስም ነው  ጥቂት ማለት የፈለኩት።

በአንድ ወቅት ነው አሉ ፥ አንድ የኔ ብጤ እውቀት ያነሰው ሰው አንድ የታወቁ የቤተክርስቲያንን ሊቅ መሃይምን ብሎ ሰደባቸው አሉ። ታዲያ ምናልባት ሊቁ በተሰነዘረባቸው ስድብ ቅር ተሰኝተው ይሆናል ብለው ያሰቡ ሽማግሌዎች ለማስታረቅ ተሰብስበዋል። አንድ ሰው በአካባቢው ሲያልፍ ምን እንደተፈጠረ ለማወቅ ከሽማግሌዎቹ ወደ አንዱ ቀረብ ብሎ ምን ሆናችሁ ነው የተሰበሰባችሁት? ቢላቸው ስም ተዛውሮብን ወደ ቦታው ለመመለስ ነው አሉት ይባላል። ዛሬ በኛም ህይዎት ብዙ የታዛወረ ስም አለ።  አለቦታው ገብቶ አልገጥም ብሎ የተንከረፈፈ ብዙ ስም አለ። ለአንድ ነገር ግጣም ሲሰራለት በልኩ ነው። ከልኩ ያለፈ እንደሆነ በትክክል ሊገጥም አይችልም። የድስት ክዳን ለጀበና ክዳን ሊሆን ፈጽሞ አይችልም። ምክንያቱም የጀበናና የድስት ተግባር ለየቅል ስለሆነ ማለት ነው።  
ዋናው የጽሁፌ አላማ ስለ ስም ትርጉም ሙያዊ ማብራሪያ ለመስጠት ስላልሆነ የተረፈውን ሰፊ በእውቀት ላይ የተመሰረተ ማብራሪያ ለቋንቋ ምሁራን ልተውና ወደ ሃሳቤ ልግባ። 

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ከምትታወቅባቸው መልካም ተግባራት አንዱ ሁሉን እንደስራው ስም ሰጥታ በታሪክ መዝግባ ለትውልድ ማስተላለፍ መቻሏ ነው።
በሙያቸው በእውቀታቸው እንዲሁም በመልካም ስራቸው የተመሰገኑ ሰዎችን የተለያያዩ የክብር ስም በመስጠት ህዝብ እንዲያከብራቸውና የነሱን አርአያ በመከተል ሌላውም ለክብር እንዲበቃ  በማለት የተለያየየ የክብር ስምን ትሰይማለች። መልካም ስም ከመልካም ሽቱ ይበልጣል እንደሚለው ቅዱስ መጽሐፍ መልካሙ ስራቸው መልካም ስም ያሰጣቸው ብዙ ቅዱሳን አሉ። ይልቁንም እራሱ እግዚአብሔር በህጉና በትእዛዙ ተጉዘው እሱን አክብረው ይህንን ዓለም አሸንፈው ወደሱ ለሄዱት(ለሚሄዱት) ቅዱሳን ለዘለዓለም የማይጠፋ ስምን እንደሚሰጣቸው እናያለን >  በቤቴና በቅጥሬ ውስጥ ከወንዶችና ከሴቶች ልጆች ይልቅ የሚበልጥ መታሰቢያና ስም እሰጣቸዋለሁ የማይጠፋም የዘለዓለም ስም እሰጣቸዋለሁ። ኢሳ 56፥5

ቀደም ሲል በነበረው ዘመን የነበሩት አባቶቻችንና እናቶቻችን እንደ እግዚአብሄር ሃሳብ የሚመላለሱ በመሆናቸው ክብር ለሚገባው ክብርን ይሰጡ ነበር። ዛሬ ላይ ያለነው ግን ከፈቃደ እግዚአብሔር የራቅን በመሆናችን ለማን ክብር መስጠት እንዳለብን ተስኖን ሁሉን በንቀት የምናይ ሆነናል። በእኛ ዘመን መልካም ስም የምንሰጠው ሰው ጠፍቶ ሳይሆን እኛ መልካም ስም የምንሰጥ ሳንሆን መልካሙን ስም ለማጉደፍ የምንፋጠን በመሆናችን ነው።
< ስም ይወጣ ከቤት ይከተል ጎረቤት >> እንደሚባለው ዛሬ ላይ እንደቀላል የምንለጥፋቸው ስሞች ለነገው ትውልድ ፈተና ነው የሚሆኑት። የምንወደውን ስንክብ፣ የምንጠላውን ደግሞ ያለ ስሙ ስም በመስጠት ከክብሩ እያዋረድን ብዙዎችን የምናሰናክል አለን። ለኛ ካልተመቸን የሱ መልካም ስራ የማይታየን ብዙዎች ነን። ዘመን በወለደው ነጻነት መሰል ህገወጥነት በመመካት ማንነታችንን የዘነጋን አለን። የሰው ልጅ አንድ ጊዜ ከእግዚአብሔር በተፈጥሮ የተሰጠው ነጻነት አለ። ክፉንና መልካሙን ለይቶ እንዲያውቅበት በተሰጠው አእምሮ በነጻነት እንዲወስን ፈቃድ አለው። ያም የሰላም ፣የፍቅር፣ የአንድነት፣ የማዘን፣ የመራራት መንፈስን ያዘለ ነው እንጅ ለክፋትና ለተንኮል እንዲጠቀምበት አይደለም። ዛሬ ላይ ይህ ሁሉ በጎ መንፈስ ከሰው ልጆች እየራቀ የመጣ ይመስላል፥

ዛሬ እንደቀላል ለምንጠላው መጥፎ ስም፣ ለምንወደው ደግሞ ከአቅሙ በላይ የስም ቱባ እያሸከምን ያለን ነገ ለትውልድ የተዛባ ታሪክ እያስቀመጥን እንደሆነ  መዘንጋት የለብንም። 

በተለይ በክርስቶስ ክርስቲያን ተብሎ ከአህዛብ የተለየ ክብርና ጸጋ የተሰጠው ክርስቲያን ሊያደርጋቸው የሚገቡና ሊጓዝባቸው የማይገቡ መንገዶች አሉ። አህዛብ ያሳድዷችኋል ተባለ እንጅ ወንድም ወንድሙን ለጠላት አሳልፎ ይስጠው አልተባለም ። በኛ ዘንድ ግን ይህ ሁሉ እየተፈጸመ ነው። የአንዲት ቤተክርስቲያን ልጆች እርስበርሳችን እየተጠፋፋን ነው። ነገር ግን እርስ በርሳችሁ ብትነካከሱና ብትበላሉ እርስ በርሳችሁ እንዳትጠፋፉ ተጠንቀቁ ገላ 5፥15  እንዳለው ። በዚህ ተግባራችን ሁላችንም እንጠፋለን እንጅ አንጠቀምም። ብርሃናችሁ በሰው ፊት ይብራ ተባለ እንጅ ለሰው ማሰናከያ ሁኑ አልተባለም። ክብር ለሚገባው ክብር ስጡ ተባለ እንጅ ሁሉን አዋርዱ አልተባለም። ከበጎ ነገር ጋር ተባበሩ ተባለ እንጅ አንዱ የሰራውን አንዱ ያፍርስ አልተባለም ።  ዛሬ በዓለም ፍርድ ቤት የኛ ጉዳይ ለምድራዊ ዳኞች የራስ ምታት እየሆነ ነው። ለዓለም የህግና የስርዓት ምንጭ የሆነች ቤተክርስቲያን ልጆቿን እንዴት መዳኘት አቃታት? የብዙዎች ጥያቄ ነው። ምናልባት በውስጧ ሆነው የሚያውኳት እውነተኛ ልጆች አይደሉ ይሆን? ልብንና ኩላሊትን መርምሮ ማወቅ የሚችለው አምላክ ይወቀው።
እውነት ለመናገር የቤተክርስቲያንችንን ሰላም እንደቀድሞው እንመልሰው ካልን እንችላለን ። ነገር ግን ይህን ማድረግ የምንችለው ስጋዊ ፍላጎታችንን መግታት ከቻልን ብቻ ነው። እኔ ከሞትጉ ሰርዶ አይብቀል ሆነና ሁሉም እራስ ወዳድ ስለሆነ እንጅ የሰላም መንገድ ጠፍቶ አይደለም። ሐዋርያው ቅ//ጳውሎስ ሁሉ የራሳቸውን ይፈልጋሉና፥ የክርስቶስ ኢየሱስን አይደለም።  ፊልጵ 2፥21 ሁሉም የራሳቸውን እንጅ ለጌታችን ለኢየሱስ ክርስቶስ አይደለም እንዳለው። የምንወዛገብበት ነገር ስለ ቤተክርስቲያን ተቆርቁረን ቢሆን መልካም ነበር ፥ ነገር ግን በእኛ ዘንድ ይህ አይደለም እየታየ ያለው፥ የራስን ክብርና ዝና ከፍ ማድረግ ሌላውን ማዋረድ ነው የተያዘው።  

ስለዚህ ባለፈው ስህተት ብዙ የተጎዱ የቤተክርስቲያን ልጆች እንዳሉ እናስብ። ምንም እንኳን በዚህ ሁሉ ማእበል ውስጥ ቤተክርስቲያን በመላው ዓለም እንደፋና እያበራች ቢሆንም በፍቅርና በሰላም አንድ ላይ ሆነን ብናገለግል ደግሞ ከዚህም የተሻለ ለብዙዎች መዳን ምክንያት እንሆናለን።  እኛ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ልጆች አላማችን አንድና አንድ ነው መሆን ያለበት። እሱም በፍቅር አንድ ሆኖ እግዚአብሔርን አክብሮ መኖርና መንግስቱን መውረስ። ከዚህ ውጭ ዓላማ ያለው ካለ ከኛ ወገን አይደለም ። ከመካከላችን ልናስወግደው ይገባል።
ከዚህ በፊትም ለመግለጽ እንደሞከርኩት የቤተክርስቲያናችን ጉዳይ ሁላችንንም ይመለከታል። የጳጳሱ፣ የቄሱ፣ የዲያቆኑ፣ ብቻ አይደለም። ለችግሩ ሁላችን አስተዋጽኦ አድርገናል። እውነተኛውንና የራሱን ዓላማ ለማስፈጸም የመጣውን ለይተን ማወቅ ተስኖን አብረን ድንጋይ ስንወረውር የነበርን ብዙዎች አለን። ስለዚህ አሁን ይብቃን አስተውለን ለመራመድ እንሞክር፥ በሃይማኖት ስትኖሩ እራሳችሁን መርምሩ 2ኛ ቆሮ 13፥5  ነው የተባለው። እኛ ካልደላን የቤተክርስቲያን መኖር ምንድነው ጥቅሙ? የምንል አቋማችንን መለወጥ አለብን። ይህ ከሆነ ሁሉም ወደ ቦታው ይመለሳል። የቤተክርስቲያናችንን ስም እንጠብቅ። ለማንም ቢሆን ስም ከመለጠፋችን በፊት አስቀድመን ማወቅ የሚገባንን እንወቅ ።ያ የሆነ እንደሆነ ለማንም ያለስሙ ስም ከመስጠት እንድናለን ማለት ነው።

የሰላም አምላክ ለሁላችንም ሰላምንና ፍቅርን ያድለን

መልካም የጾምና የጸሎት፣ የስግደትና የምጽዋት፣ የእርቅና የይቅርታ ጊዜ ይሁንልን      


 

No comments:

Post a Comment