የተስተካከለ መንገድ ካለ በአግባቡ መጓዝ ይቻላል። ወጣ ገባና ኮረኮንች የበዛበት መንገድ እንደ ልብ ሊያራምድ አይችልም። ሥርዓት ሰዎችን ካልጠቀመ ችግር አለበት ማለት ነው። ሥርዓት ያስፈለገው የሰው ልጆችን እኩልነት ለማስፈን መሆኑ የታወቀ ነው። ይህም ሆኖ ሥርዓት አስከባሪ እስካልተገኘ ድረስ ፋይዳ የለውም። ሥርዓት ካለ የሚበደል ሰው መኖር የለበትም። በየስፍራው ሰዎች የመኖር ህልውናቸው የሚገፈፍ ከሆነ ሥርዓቱ ጤነኛ አይደለም ማለት ይቻላል።ሌላው ሥርዓት መኖሩ የሚታወቀው ገዥና ተገዥ ውዴታና ግዴታቸውን ማወቅ ሲችሉ ነው። በሥርዓት ለመምራት ህዝቡን ሥርዓት ማስተማር ተቀዳሚ ተግባር ሊሆን ይገባዋል። ህዝቡ የማያውቀውን፣ ያልተቀበለውን፣ እምቢ እያለ በኃይል የተጫነበትን ተከፋፍሎ የመኖር ሥርዓት ለማስተካከል ጊዜ ባይወሰድ ከሁሉ የተሻለ መልካም ነው። መንግሥት ይህን ማድረክ ከቻለ ግዴታውን ተወጣ ሊባል ይችላል።
ለምሳሌ ሰሞኑን ከቤንሻንጉል ክልል ተፈናቀሉ የተባሉ ወገኖቻችን በገዛ ሀገራቸው ለስደተኞች እንኳን የሚሰጠው መብት ተነፍጓቸው በቤተክርስቲያን ደጅ ከነልጆቻቸው ተጠልለው አይተናል። የሰዎችን መብት ለማስጠበቅ ተብሎ የተዘረጋው ሥርዓት መብት በማስከበር ፈንታ ሰብአዊነትን የሚገፍ ከሆነ ችግር አለ። አንድ ሰው አይደለም በተወለደበት ምድር በሰው አገርም ቢሆን የሚከበርለት ሰብአዊ መብት አለው። እነዚህ ወገኖች ግን ሲናገሩ እንደተሰማው ጥረው ግረው ያፈሩትን ሀብት እንኳን መሰብሰብ አልቻሉም። የሚሰበስቡበት ጊዜ ስላልተሰጣቸው ትተው አካባቢውን ለቀው ለመውጣት እንደተገደዱ ነው የተናገሩት። ይህ ችግር በተለያዩ አካባቢዎች የተፈጸመ ቢሆንም መንግሥት ሊያስቆመው አልቻለም። ምክንያቱም በሥርዓቱ በተደነገገው መሰረት ሁሉም ክልል መንግሥት አለው። መንግሥትን ደግሞ መንግስት ሊያዘው አይችልም። በአንድ ሀገር ብዙ መንግስታት እንዲኖሩ ያደረገው ሥርዓቱ ነው። ትላንት የነበረው አብሮነት የፈረሰው በሥርዓቱ ምክንያት መሆኑ ግልጽ ነው። ስለዚህ ሥርዓቱ ለሀገር ጉዳት በዚህ መጠን አስተዋጽኦው የጎላ መሆኑ ከታመነበት ሥርዓቱን ማስተካከል ብቸኛው አማራጭ ሊሆን ይገባል።
ባልተስተካከለ ሥርዓት ውስጥ መልካም ሰዎች ቢኖሩም በጎ ሥራ ለመስራት ቀላል አይሆንላቸውም። በየዘመኑም እንዳየነው መልካም ሰዎች በመጥፎ ሥርዓቶች ተጠልፈው እየወደቁ እድሜያቸው በአጭሩ የተገታ ብዙዎች ናቸው።
አዲሱ መሪያችን በአጠገባቸው ካሉ ባለስልጣናት አልፎ እታች በችግር ላይ እስካለው ህብረተሰብ የሚደርስ አርአያነት ያላቸውን ዘርፈ ብዙ ተግባራት እየፈጸሙ እንደሆነ የማይታበል ሀቅ ነው። ሥርዓቱ የፈጠረው በሽታ አሁንም እያመረቀዘ ያለ ቢሆንም ጠቅላይ ሚንስትር ዓቢይ በሥርዓቱ ምክንያት በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን የተፈጠረውን መከፋፈል ወደ አንድነት ለማምጣት በሚደረገው ጥረት መንግሥትም የበኩሉን አስተዋጽኦ እንደሚያደርግ መግለጻቸው ተሰምቷል። ከዚህም ሌላ ለሀገሪቱ ባለቸው ፀጋና እውቀት በጎ ነገር ያበረከቱ ኢትዮጵያውያንን ክብር በመስጠት አስታውሰው ድጋፋቸውን ሲገልጹ ታይተዋል። ታዋቂው ደራሲ ይስማእከ በህመም ላይ በመሆኑ እግዚአብሔር ይማርህ ለማለት ስልክ ደውለው እንደነበር ሲሰማ እሱ ብቻ ሳይሆን ብዙ አስታዋሽ የለንም ብለው ተስፋ የቆረጡ ኢትዮጵያውያን መጽናናትን አግኝተዋል።ጠቅላይ ሚንስትሩ እንደኛው ሰው በመሆናቸው ይህን ማድረጋቸው ለምን ተደነቀ ብንል ካለባቸው የሥራ ብዛት አንጻርና በሌሎች ያልተለመደ በመሆኑ ነው። የእሳቸው በዚህ ዘመን መገኘት ቢያንስ ዳግመኛ ብሶት የወለደው ትውልድ ምድሪቱ እንዳታበቅል ይረዳል። ይህ ለእሳቸውም ሆነ ፍቅር ለተራበው የኢትዮጵያ ህዝብ እንደ መታደል ይቆጠራል።
የዶ/ር አቢይ ተስጥኦ በመጠኑ እንደተረዳሁት፦ ሀሳባቸውን በግልጽ ይናገራሉ፣ በንግግራቸው አሽሙር ፈልጎ ማግኘት ከባድ ነው፣ ማዳመጥ ይችላሉ፣ የመረጃ ሰው መሆናቸውን ለመረዳት የህዝቡን የልብ ትርታ ማወቃቸው በቂ ነው፣ ከየአቅጣጫው የሚነሱ ሃሳቦችን (negatively) ሳይሆን በበጎ ተርጉመው አስተካክለው ሲመልሱ አይተናል፣ ክብር ለሚገባው ክብር ሲሰጡም አይተናል፣ ሻክሮ የነበረውን የመንግሥትና የህዝብ ግንኙነት በአጭር ጊዜ ውስጥ እንዲሻሻል ብልሃት በተመላው መንገድ ሰርተዋል፣ መጽሐፍ ቅዱስ ማንበባቸው እንደ እባብ ብልህ እንደ ርግብ የዋህ መሆን በህይዎት ዘመን ለትልቅ ስኬት እንደሚያበቃ እንዲረዱ ያገዛቸው ይመስላል፣አንዳንዶች ከኢህአዴግ መንደር እንዲህ ዓይነት መልካም ሰው እንዴት ወጣ ብለው ግራ የተጋቡ ቢሆንም ኢትዮጵያ ከናዝሬት ክርስቶስ እንደተገኘ የሚያምን ህዝብ የሚበዛባት ሀገር በመሆኗ ብዙኃኑ እግዚአብሔር ከየትም ስፍራ ሰው ሊያስነሳ እንደሚችል ያምናሉ። ይሁን እንጅ አይሁድ የኦሪትን ሥርዓት ሰላም ይዞ የመጣውን ክርስቶስን ለማሰናከል እንደተጠቀሙበት አንዳንዶች የሳቸውን በጎ ዓላማ ለማደናቀፍ ሥርዓቱን እንዳይጠቀሙበትና ብልጭ ያለችውን የሰላምና የፍቅር ተስፋ እንዳያጨልም ቢስተካከል መልካም ነው።
ተዘርግቶ የነበረው ሥርዓት ለባለቤቶቹም (ለመንግሥት አካላት) ቀላል ቀንበር እንዳልነበር የሚያሳዩ ሁኔታዎችን ለማየት ችለናል። ከግርማዊ ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ በኋላ የተነሱ መሪዎቻችን ለራሳቸውና ለቤተሰቦቻቸው ያተረፉት ነገር ለብዙዎች እንቆቅልሽ ነው። እምነታቸውን ለመግለይ ሲጨነቁ፣ ለቤተሰቦቻቸው የሚገባውን ለማድረግ ሲጨነቁ፣ ልጆቻቸው በገዛ ሀገራቸው ባይተዋር ሲሆኑ ነው ያየነው። ያለፉትን ትተን በቅርቡ የተሰናበቱት ጠቅላይ ሚኒስቴር ኃይለ ማርያም ደሳለኝ ሲናገሩ" ልጆቼ በታክሲ እየተመላለሱ ትምህርታቸውን ይከታተሉ ነበር በዚህም አኩርተውኛል" ሲሉ ሰምተናል። ሊሆን ይችላል ብሎ ለማመን ይከብዳል እንጅ ሆኖ ከሆነ በየቦታው የምናየውን የታክሲ ሰልፍ የወለደው የቤተመንግስት ልጆች ታክሲ መጠቀም ስለጀመሩ ይሆን?እንድንል የሚጋብዝ ነው።
ወደ እውነታው ስንመጣ በነጻነት የመኖር ችግር ያለባቸው ወገኖች እንዳሉ ሁሉ ቤተ መንግስት የሚኖሩትንም በነጻነት ለመናገር እንዳይችሉ ስርዓቱ እንደተጫናቸው ማሳያ ነው። ሌላው ከዚሁ ጋር ተያይዞ በብዙዎች የተተቸው የቀድሞው ጠቅላይ ሚንስትር ግልጽ ያልሆነ ማንነት- የእምነት ሰው መሆናቸው ቢነገርም አንድም ቀን የእግዚአብሔር ስም በምንም መልኩ ሲጠሩ አልተሰማም። "ስለዚህ በሰው ፊት ለሚመሰክርልኝ ሁሉ እኔ ደግሞ በሰማያት ባለው በአባቴ ፊት እመሰክርለታለሁ፤ በሰው ፊትም የሚክደኝን ሁሉ እኔ ደግሞ በሰማያት ባለው በአባቴ ፊት እክደዋለሁ። ማቴ 10፥32" ተብሎ እንደተጻፈ እግዚአብሔር ያደረገላቸውን መመስከር ይገባቸው ነበር። በመጨረሻው የቤተ መንግሥት ንግግራቸው "ከአሁን በኋላ ሽማግሌ ነኝ" የሚል ቃል ሲናገሩ ተሰምተዋል ከሽማግሌ የሚጠበቀውን ለመናገርና ለማድረግ ግን ሲቸገሩ ታይተዋል። ከዚህ የምንረዳው ዶ/ር አቢይ እስከገቡበት እለት ድረስ የነፃነት እጦት ቤተ መንግስትም እንደነበረ ነው። ስለዚህ ለሆነው ሁሉ ምክንያቱ በአንድ ሀገር ውስጥ ጨቋኝና ተጨቋኝ እንዲኖሩ ጉልህ አስተዋጽኦ ያደረገው አሁን ኢትዮጵያ እየተመራች ያለችበት ሥርዓት በመሆኑ ሰዎችን ብቻ ሳይሆን መመሪያውን መፈተሽ ከዳግም ስህተት ያድናልና ቢታሰብበት መልካም ነው።
No comments:
Post a Comment