Wednesday, September 12, 2018

ሰውና ማንነቱ

ሰው መሆን ከምንም በላይ ክብር የሚገባው ልዩ ማንነት ነው። ቅዱስ መጽሐፍ እንደሚነግረን ምድራዊ ህይዎታችን ጊዜያዊ ነው። ይህም በመሆኑ በምድር ያለው ሁሉ ኃላፊ ነው። ( ድንኳን የሚሆነው ምድራዊ መኖሪያችን ቢፈርስ፥ በሰማይ ያለ በእጅ ያልተሠራ የዘላለም ቤት የሚሆን ከእግዚአብሔር የተሠራ ሕንጻ እንዳለን እናውቃለንና። በዚህ ውስጥ በእውነት እንቃትታለንና፥ ከሰማይም የሚሆነውን መኖሪያችንን እንድንለብስ እንናፍቃለንና 2ኛ ቆሮ 5፥1)  በቋንቋው የሚመካ ካለ ሞኝ ነው። በዓለም ላይ እንግሊዝኛ የሚናገሩ በቢሊዮን የሚቆጠሩ ህዝቦች አሉ ማንነታቸው ግን አይደለም። እምነቱን መሰረት አድርጎ ሌላውን በመግፋት የግል ማንነት እንዲኖረው የሚፈልግ ካለ መንፈሱና ሥጋው የተጣሉበት ማስተዋል የተነሳው መሆን አለበት። አንተ የምታምነው አምላክ የሁሉ ፈጣሪ እንጅ የአንተ የግል ንብረት አይደለም። የትውልድ አካባቢውን መሰረት በማድረግ የነገሌ ዘር ነኝ ብሎ እራሱ ከሌላው ለመለየት አጥር የሚያጥር ካለ በዓለም ውስጥ የተሸነፈ ሰው ነው። ይህ ውሳኔ የሰው ሳይሆን የእግዚአብሔር ነው። ማንም በራሱ ላይ አንዳች ማድረግ የሚችል የለም። ጌታ በወንጌል እንዲህ ብሎ እንደተናገረው   ( ከእናንተ ተጨንቆ በቁመቱ ላይ አንድ ክንድ መጨመር የሚችል ማን ነው? ማቴ 6፥27) 
ማንነትን የሰጠ እግዚአብሔር ነው። እግዚአብሔር የሚወደውን በጎ ሥራ ለመስራት ሰው ሆኖ መገኘት አስፈላጊ መሆኑን ሲያስተምረን ንጉሱ ቅዱስ ዳዊት ልጁ ሰሎሞንን በወንበሩ ካስቀመጠው በኋላ  (ልጄ ሰው ሁን  (1ኛ ነገ 2፥3) ነበር ያለው። ሀገርን የሚረከብ ትውልድ ሰብአዊ ማንነቱን ጠብቆ ካልተገኘ ለሀገር የሚያበረክተው አስተዋጽኦ አይኖርም። ባለፉት ዘመናት ሃገራችን ማንነቱን የተገነዘበ ትውልድ እንዳይኖራት በመደረጉ ለሃገር አስተዋጽኦ በማድረግ ፈንታ ያልተሰጠውን ማንነት ፍለጋ ሲዋትት ይታያል።

 ሰብአዊ ማንነትን በቅጡ ላልተረዱ ማለት ያለብንን ከማለት አንቦዝንም። መጽሐፍ ቅዱስ እንደሚነግረን የሰው ማንነት ሌላ ነው። የእንስሳ ማንነት ሌላ ነው። የሌሎችም ፍጥረታት ማንነት እንደየወገናቸው ልዩ ልዩ ነው። ሰው መሆን ግን ከፍጥረታት ሁሉ የተከበረ ነው። በዚህ ዓለም አንዱ የሌላውን ማንነት አክብሮ እግዚአብሔርን እያመሰገነ እንዲኖር ለእያንዳንዱ የተሰጠው ፀጋ አለ። ያንን አክብሮ እንዲኖር እንጅ ያልተሰጠውን እንዲፈልግ አይደለም። ዲያቢሎስ የነበረውን ክብር ያጣው ያልተሰጠውን በመፈለጉ ነው። ባለንበት ዘመን ሰዎች ትልቁን ማንነታቸውን ዘንግተው ዘር ጎሳን በመቁጠር የማንነታቸው መገለጫ እንደሆነ ይናገራሉ። ነገር ግን ትልቁን ማንነት ጥሎ ሳይሆን ዋናውን ማንነት ይዞ መልካም የሆነውን ሁሉ የራስ ማድረግ ይቻላል። 

ዘር፤ ቋንቋ፤ ሃይማኖት ወዘተ ከሰውነት በኋላ የመጡ ናቸው። የእግዚአብሔር ትእዛዝ የሚለው፦ ሰው ከዘሩ፤ ከቋንቋው፤ ከእምነቱ በፊት በሰውነቱ መዋደድ፣ መከባበር ፣ መረዳዳት፣  አለበት። ዘር ቆጥሮ ቋንቋን መሰርት አድርጎ፣ እንዲሁም በእምነቱና በአመለካከቱ የሚመስለውን በመደገፍ የማንነቱ መገለጫ የሚያደርግ ሰው፤ የዘመናት ባለቤት እግዚአብሔር በየዘመኑ ለሰው ልጆች የገለጠውን እውነት ያልተረዳ ነው። 

ከአማራነት፣ ከኦሮሞነት፤ ከትግሬነት ፤ከጉራጌነት ወዘተ ኢትዮጵያዊነት ይበልጣል። ከኢትዮጵያዊነት ሰብአዊነት ይበልጣል። ይህን አልቀበልም የሚል ካለ ከገህዱ ዓለም ወጥቶ በራሱ ዓለም የሚኖር መሆን አለበት። ዓለም ኢትዮጵያን ከአማራም፤ ከኦሮሞም፤ ከትግሬም፤ ከጉራጌም ወዘተ በላይ በደንብ ያውቃታል። መልካችን  ሰብአዊነታችንንና ኢትዮጵያዊነታችንን እንጅ ጎጣችንን አያሳይም። ቅዱስ መጽሐፍ እንደዚህ ነው የሚለው፤  (በውኑ ኢትዮጵያዊ መልኩን ወይስ ነብር ዝንጕርጕርነትን ይለውጥ ዘንድ ይችላልን?  ኤር 13"26)   ምንም ተባለ ምን መልካችን አይቀየርም። ማወቅ ያለብን፤ ኢትዮጵያዊ ለመሆናችን የማናችንም አስተዋጽኦ የለበትም። እግዚአብሔር ፈቅዶ ከኢትዮጵያ ወገን እንድንፈጠር  አደረገ። ይህን አለመቀበል እግዚአብሔርን አለማወቅ ነው። በየዘመኑ የሚነሱ ክፉ ሰዎች በሚዘሩት ክፉ ዘር ዓለማችን መጠኑ ወደ ማይነገር ልዩነት ሄዳለች። ይህ የሆነው የክፉዎችን ምክር ተቀብሎ ተግባራዊ የሚያደርግ በመኖሩ ነው። 

የሰው ክፉ አስተሳሰብ ከእግዚአብሔር መንገድ ያስወጣል። ቅዱስ ጳውሎስ ለልጁ ለጢሞቴዎስ።  እምነትና በጎ ሕሊና ይኑርህ፥ አንዳንዶች ሕሊናን ጥለው፥ መርከብ አለ መሪ እንደሚጠፋ፥ በእምነት ነገር ጠፍተዋልና፤ 1ኛ ጢሞ 1፥19  ብሎ እንደመከረው። ሰው እንዴት የተከበረ ማንነት እያለው ማንነት ፍለጋ ይማትራል? ሰው ከማስተዋል እየጎደለ ሲመጣ ማንነቱን ዘንግቶ ሌላ ማንነት ውስጥ ይገኛል። ብዙዎች ከሰውነት ጎዳና ወጥተው እንስሳዊ ማንነትን ተላብሰው በመኖራቸው እንደ ስልጣኔ ይቆጥሩታል። ማንነትን ጥሎ መኖር  የመጨረሻው ውድቀት ነው። 

በተለያዩ ጊዜያት በሀገራችን የምንሰማው ማስተዋል የጎደለው ዓላማ ለብዙ ዘመናት ስንመኘው የነበረውን ሰላምና ፍቅር በማግኘታችን የተፈጠረውን ደስታ  የሚያደፈርስ ሆኖ ነው ያየሁት። ጥያቄ የሚያቀርቡ ወገኖች መብታቸው ተከብሮ ጥያቄያቸው ያለምንም አድልዎ ሊታይ እንደሚገባ አምናለሁ። ነገር ግን ወቅትና ጊዜ እንዲሁም ቦታን አስተካክሎ በህግ አግባብ መቅረብ ሲገባው ትልቁ ጉዳይ ይቅርና የእኔ ጥያቄ ይመለስ ማለት አለማስተዋል ነው። በዚህ ዘመን የጊዜ እጥረት ካልሆነ በቀር የሚታፈን ሃሳብ አለ ለማለት ያስቸግራል። እውር ነገ ዓይንህ ይበራል ቢሉት ዛሬ እንዴት አድሬ? አለ እንደተባለው  ዛሬውኑ የሌሎች ማንነት ጠፍቶ የሚታየውም የሚሰማውም የኛ ብቻ ይሁን ማለት እፍረት ያጣ እራስ ወዳድነት ነው። 

በእኔ አመለካከት ኢትዮጵያ ውስጥ የተፈጠረውን ልዩነት ያሰፉት ምሁራን ነን የሚሉ ነገር ግን በጎ ህሊና የሌላቸው ክፉ ሰዎች ናቸው። ወደ እውነቱ ስንመጣ አማራን ከኦሮሞ፣ ትግሬውን ከአማራ እንዲሁም አንዱን ዘር ከሌላው የምንለይበት በመረጃ የተደገፈ ማስረጃ አናገኝም። ከላይ ለመግለጽ እንደሞከርኩት ቋንቋ እንዲሁም እምነት፣ ባህል ወ ዘ ተ በቂ ማስረጃ ሊሆኑ አይችሉም። አንዱን ቋንቋ ብዙዎች ሊናገሩት ይችላሉ። አንዱን እምነት ብዙዎች ሊያምኑ ይችላሉ። አንዱን ባህል ብዙዎች ሊከተሉ ይችላሉ። ስለዚህ ኢትጵያውያን የምንለያይበት ምክንያት በሙሉ ሰው ሰራሽ እንጅ እንደ ሌሎች እንደ አረብና እስራኤል፣ እንደ ነጭና እንደ ጥቁር፣ እንደ ቻይና እና እንደነ ህንድ የመሳሰሉት ዓይነት በእኛ ዘንድ የሚታይ ልዩነት የለም። የልዩነታችን ዋናው ምክንያት አንዱ አንዱን እየተጫነ በማንነቱ እንዳይኮራ በመደረጉ ጥላቻ እንዲያድርበት ሆኗል። ለዚህ መፍትሄው እኩልነትን ለማምጣት በጋራ መስራት ነው።

እኔ ኢትዮጵያዊ በመሆኔ ደስ ይለኛል። ነገር ግን ሌላውን እጠላለሁ ማለት አይደለም። በኢትዮጵያ ምድር የበቀለው በሙሉ የእኔ አካሌ እንደሆነ አምናለሁ። ይህ ማለት ግን ሰው በመሆኔ ከማገኘው ደስታ ይበልጣል ማለት አይደለም። ሰው መሆን ልዩ ክብር ነውና።

                             ኢትዮጵያ ለዘላለም ትኑር ሰው ሆኘ ተፈጥሬባታለሁና።

No comments:

Post a Comment