
ወንጌላዊው ማቴዎስ እንደጻፈው ጌታችን አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ወደ ቤተመቅደስ ገብቶ በዚያ የሚሸጡትንና የሚለውጡትን ከመገሰጹ በፊት ከደቀመዛሙርቱ ሁለቱን ልኮ በእስራት ላይ ያሉ አህያና ውርንጭላዋን ፈትተው እንዲያመጡ አዞ ነበር። አትፍቱ የሚላችሁ ቢኖር ለጌታ ያስፈልጉታል በሉ የሚል መመሪያም ሰጥቷቸው ነበር። የሰው ልጆችን ሁሉ ከእስራት ሊፈታ እንደመጣ ሲያጠይቅ ይህን ተናገረ። ለምን ትፈታላችሁ የሚላችሁ ቢኖር ለጌታ ያስፈልጉታል በሉ አላቸው። እነሱም እንደታዘዙት ለጌታ ያስፈልጉታል ብለው ፈትተው አምጥተውለታል። ቃሉም እንዲህ ይነበባል " ወደ ኢየሩሳሌምም ቀርበው ወደ ደብረ ዘይት ወደ ቤተ ፋጌ ሲደርሱ፥ ያንጊዜ ኢየሱስ ከደቀ መዛሙርቱ ሁለት ላከ፥እንዲህም አላቸው፦ በፊታችሁ ወዳለችው መንደር ሂዱ፥ በዚያን ጊዜም የታሰረችን አህያ ውርንጫም ከእርስዋ ጋር ታገኛላችሁ፤ ፈትታችሁ አምጡልኝ።ማንም አንዳች ቢላችሁ፦ ለጌታ ያስፈልጉታል በሉ፤ ወዲያውም ይሰዳቸዋል።ለጽዮን ልጅ፦ እነሆ፥ ንጉሥሽ የዋህ ሆኖ በአህያ ላይና በአህያይቱ ግልገል በውርንጫይቱ ላይ ተቀምጦ ወደ አንቺ ይመጣል በሉአት ተብሎ በነቢይ የተነገረው ይፈጸም ዘንድ ይህ ሆነ።ደቀ መዛሙርቱም ሄደው ኢየሱስ እንዳዘዛቸው አደረጉ፥ ማቴ 21፥1"
ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ "በነጻነት ልንኖር ክርስቶስ ነጻነት አወጣን፤ እንግዲህ ጸንታችሁ ቁሙ እንደ ገናም በባርነት ቀንበር አትያዙ" ገላ 5፥1 ብሎ ለገላትያ ክርስቲያኖች እንደጻፈው የአምላክን ሰው መሆን ስናስብ አስቀድመን የምንረዳው በዲያብሎስ ታስሮ የነበረው የሰው ልጅ ከእስራት ነጻ መውጣቱን ሲሆን። ምንም እንኳን ክርስቶስ የሰውን ሥጋ ለብሶ ወደዚህ ዓለም እንዲመጣ ያደረገው የሰው ልጅ በነፍሱ የገጠመውን እስራት ሊያስወግድ ቢሆንም። ሰው አስቀድሞ ሲፈጠር የእግዚአብሄር አምሳል በመሆኑ በሥጋውም መታሰር ስለሌለበት ብዙዎችን ከሥጋ እስራት ነጻነትን ሲሰጣቸው አይተናል። ዮሐ 5፥1 ማር 10፥48 . . .. .
ሰውን ከክብሩ ዝቅ አድርጎ መግዛት የእግዚአብሔርን ህግ መሻር ነው። ሁላችንም በአርአያውና በአምሳሉ የተፈጠርን ለእግዚአብሔር እናስፈልገዋለን። ሰው ሲፈጠር የእግዚአብሔር ገንዘብ ሆኖ ነው የሚፈጠረው። ኃጢአትን በመስራት እራሱን ለሰይጣን አሳልፎ ከሚሰጥ ሰው በቀር ሁሉም የእግዚአብሔር ማደሪያ ነው። ለጌታ ያስፈልጉታል የተባሉት በላያቸው ተቀምጦ እየተመሰገነ ወደ ኢየሩሳሌም እንደገባው ሁሉ በእኛም ህይዎት ስፍራ ኖሮት እየተመሰገነ መኖር ይፈልጋል። 1ኛ ቆ 6፥19
በዓለም ውስጥ ያለውን እስራት ስንመለከት ፦ ወንጀል ሰርቶ የሚታሰር አለ ። ያለበደሉ ፍርድ ተዛብቶ የሚታሰር አለ። እራሱን በተለያየ ክፉ ስነ ምግባር የሚያስር አለ።
ወንጀል ሰርቶ የተመሰከረበት ይታሰር ዘንድ ይገባል። እንዲህ ዓይነቱን ሰው በእስር ማቆየት ሰውየውን ከመጉዳቱ ይልቅ ጥቅሙ ያመዝናል። ምክንያቱም ከስህተቱ እንዲታረም ትምህርት ያገኛል። እንዲሁም ሌሎችን ከተመሳሳይ አደጋ ለመጠበቅ ያለው አማራጭ እንቅስቃሴውን መግታት ነው። ይህም ሆኖ እንኳን በቀደመው ስህተቱ ተጸጽቶ ዳግም እንደማያጠፋ ከታመነበት ምህረት አይገባውም አይባልም። ሚክ 6፥8
ያልበደሉ ሰዎች ቅን ፈራጅ በማጣታቸው ምክንያት የሚታሰሩት ወገኖች በእግዚአብሔር ዘንድ ክብርና ትልቅ ዋጋ የሚቀበሉ ቢሆንም በእነሱ ምክንያት እግዚአብሔር ምህረቱን ቸርነቱን ከሰው ልጆች ያርቃል። ስለዚህ በአንድ ሀገር ውስጥ የሚበደሉ ሰዎች እንዳይኖሩ የሚመለከታቸው አካላት ጥንቃቄ ሊያደርጉ ይገባል። ዛሬ ላይ በሀገራችን እየሆነ ያለው በሙሉ የድሆች ሰቆቃ እንዲሁም ያለበደለቸው መከራና ስቃይ እየተቀበሉ ሌት ተቀን እንባቸውን የሚያፈሱ ወገኖቻችን ያመጣው ችግር መሆኑ ግልጽ ነው። ስለዚህ ለጌታ ያስፈልጉታልና ያለበደላቸው በማን አለብኝነት በእስር እንዲንገላቱ የፈረድንባቸውን ወገኖች ፈትተተን መከራችንን ማራቅ ይኖርብናል። ዘጸ 23፥3
አንዳንድ ሰው ከክፉ ስነምግባር ለመላቀቅ እርዳታ ይፈልጋል። መድኃኔዓለም ኢየሱስ ክርስቶስ የሰውን ልጆች አቅም ተረድቶ እንደ ክፋታቸው ሳይሆን ሁሉን ታግሶ ከክፉ ባህርያቸው እንዲላቀቁና በመልካም ስነምግባር ለሌሎች ምሳሌ እንዲሆኑ አዲስ ሰው ያደረጋቸው እንዳሉ እናውቃለን። ይሁን እንጅ ክፋት ተቆራኝቷቸው እስከእለተሞታቸው ድረስ የዲያቢሎስን ፈቃድ በመፈጸም ለንስሃ ጊዜ የማይኖራቸው እንዳሉም ይታወቃል። እንደዚህ ያሉትን ከክፉ የዲያቢሎስ መንፈስ ማላቀቅ እንደሚገባ ሐዋርያው ቅዱስ ታዴዎስ (ይሁዳ) እንዲህ ብሏል። "አንዳንዶች ተከራካሪዎችንም ውቀሱ፥ አንዳንዶችንም ከእሳት ነጥቃችሁ አድኑ፥አንዳንዶችንም በሥጋ የረከሰውን ልብስ እንኳ እየጠላችሁ በፍርሃት ማሩ ይሁዳ 1፥22"
No comments:
Post a Comment