ከፍጥረታት ሁሉ አወቂና ክቡር ሆኖ የተፈጠረ እንደ ሰው ያለ ፍጡር አልተገኘም። ይህን ክቡርና አዋቂ የሆነ ፍጡር ለመምራት በእውቀትም ሆነ በችሎታ ልቆ መገኘት ይጠይቃል። ከስነፍጥረት ጀምሮ ያለውን ታሪክ ስናነብ መሪዎች ነበሩ። ምንም እግዚአብሔር መርጦ መሪ ቢያደርጋቸውም በአስተሳሰባቸው ከሚመሩት ህዝብ በታች ሆነው በመገኘታቸው ፍጻሜያቸው ያላማረ ብዙዎች ናቸው። ብዙ ምሳሌ ማንሳት ይቻል ነበር ነገር ግን በሰው ሁሉ ዘንድ የታወቀ ስለሆነ ወደ ዋናው ሃሳቤ ልግባ።
የተነሳንበት ርእስ የተለያዩ ትርጉሞች ሊሰጥ የሚችል ቃል ስለሆነ በማጥበቅና በማላላት እንዲሁም በመተርጎም ፍሬ ሃሳቡን ማግኘት እንችላለን። ስናጠብቀው ሁሉ የሚሰማው, ሁሉ እሽ በጄ የሚለው እንዲሁም የሚደመጥ ወ ዘ ተ ማለት ሲሆን ስናላላው ደግሞ የሚሰማ,የሚያዳምጥ, ለሃሳቦች ቦታ የሚሰጥ ወ ዘ ተ ልንለው እንችላለን።
ቅዱስ ማርቆስ በቅዱስ ወንጌል እንደጻፈው ጌታችን አምላካችን መድኃኔዓለም ኢየሱስ ክርስቶስ በመዋእለ ስጋዌው በምድር በሚመላለስበት ወቅት ያስተምር የነበረው የህዝቡን ችግር እንዲሁም ጉድለት በማየት ነበር "፤ ኢየሱስም ወጥቶ ብዙ ሕዝብ አየና እረኛ እንደሌላቸው በጎች ስለ ነበሩ አዘነላቸው፥ ብዙም ነገር ያስተምራቸው ጀመር። " (ማር 6: 34) ይላል። ለህዝቡ ምሳሌ የሚሆን መሪ የጠፋበት ዘመን ስለነበር ህዝቡ ግራ ተጋብቶ ተስፋ መቁረጥ ተጭኖት የነበረበት ዘመን እንደነበር ተጽፏል። መሪ መንጋውን ማዳመጥ ከቻለ ችግሩን መረዳት አያቅተውም።
ሀገራችን የሰው ያለህ በምትልበት ወቅት ለብዙዎቻችን ድንገት ብቅ ያሉት አቶ ለማ መገርሳ መንገድ ጠራጊ ሆነው ሲመጡ የኢትዮጵያ ህዝብ ያልተለመደ ባይባልም ነገር ግን የተረሳ ሊባል በሚችል መልኩ የቀድሞ አባቶቻችንን የሚያስታውስ የህዝብ አቀባበል ሲደረግላቸው ባየንበት ወቅት ኢትዮጵያ የተዘረጋው እጇ መልስ ሊያገኝ ይሆንን?ብለን ተስፋ አድርገን ነበር። ቅዱስ ዮሐንስ የእግሩን ማዘቢያ ልፈታ የማይገባኝ ከኋላየ ይመጣል እንዳለው የተደገፍነው ለማ ፍቅሩ ሳይከስም ከእሱም ላቅ ብሎ የታየውን ዶክተር አቢይን ከፊት አድርጎ አሳየን። ዶ/ር አቢይም ኢትዮጵያዊነት፣ አንድነት፣ ድምር፣ ህብረት፣ እናት፣ እርቅ፣ ይቅርታ፣ ሰላም፣ ወዘተ የመሳሰሉትን የህሊና ምግብ የሆኑ ቃላቶችን እየዘራ መጣ ። አሁንም ጽኑ እምነትና ተስፋን ሰንቀን በፍቅር የተገነባች ኢትዮጵያን ለማየት በጉጉት ላይ ነን።
ከዶክተር አቢይ መልካም ባህርያት ያየሁት ማዳመጥ መቻላቸውን ሲሆን ወደውስጣቸው ያስገቡትን ሀሳብ ደግሞ አብስሎ ለህዝብ ማቅረብ መቻላቸው ይደነቃል። ከዚህም ሌላ የሚናገሩዋቸው ቃላት ወደ ሰው አእምሮ ለመግባት ጊዜ የሚፈጁ አይደሉም። በየስፍራው ደጋግሞ እንደታየው የህዝቡ ጭብጨባና ድጋፍ ይህን የሚያመለክት ነው። ባራክ ኦባማ መድረክ ላይ ሲወጡ እርሳቸው በንግግር ከሚወስዱት ደቂቃ ይልቅ ህዝቡ በጭብጨባና በድጋፍ የሚያጠፋው ጊዜ ይልቅ እንደነበር። የቅርብ ጊዜ ትዝታ ነው።
ከሁሉ ቅድሚያ ሊሰጠው የሚገባ ጉዳይ ቢኖር የሀገር ጉዳይ ነው። ለሀገርና ለህዝብ መልካም እስካደረገ ድረስ ከየትኛውም ወገን ቢመጣ መደገፍና መወደድ አለበት። ሰው በሰውነቱ አስቀድሞም ክብር አለው መልካም ምግባር ሲጨመርበት ደግሞ ክብር ይጨመርለታል። ስለዚህ በሃይማኖትም ሆነ በቋንቋ ልዩነት ቢኖረንም ሁላችንን አንድ አድርጋ የምታኖረን ሀገር መልካም ሰው ስታገኝ ደስ ሊለን ይገባል።
ካለፈው መልካሙን ካልሆነ በቀር ሌላውን እየተው መጓዝ ለመጭው ጉዞ የሚበጅ ነውና ባለፉት ዘመናት እንደየአቅማቸው ለሀገር አስተዋጽኦ ያበረከቱ ወገኖችን በሰለጠነ አካሄድ ክብር ልንሰጣቸው ይገባል። ያለፈው ከሌለ የዛሬው ሊኖር አይችልም። ተደጋግሞ እንደተነገረው የሀገሪቱ ውድቀት በጥቂት ሰዎች ብቻ ሳይሆን በሁላችንም አለማስተዋል መሆኑን መዘንጋት አይገባም። እያንዳንዱ ዜጋ ለሀገር የሚያበረክተው በጎ አስተዋጽኦ ብዙ እንደሆነ ሁሉ ለጉድለቱም የየራሱ ድርሻ ይኖረዋል። ለሀገራችን ሰላምና እድገት ከመሪው በላይ የእርስበርሳችን አንዱ የሌላውን ማንኛውንም ነገር አክብሮ መቀበል መቻል ነው ብየ አምናለሁ።
ዶ/ር አቢይ የህዝባችንን አመለካከት አቃንቶ እውነታውን በማሳየት የዛሬውን ሳይሆን ለነገ ተስፋ እንዲሰንቅ የሚያደርጉ ቃላቶችን በብዙ ስፍራ ሲናገሩ ለማየት ችለናል። ከመሪ የሚጠበቀው የመጀመሪያ ተግባር ይህ ነው። ቀጣዩ ተግባር ግን የሁሉንም ተሳትፎ የሚጠይቅና ጊዜም የሚፈልግ መሆኑ በግልጽ ተነግሯል። በሌሎችም ሀገሮች እንዳየነው የመንግስት ስራ ሜዳውን ማመቻቸት ነው። ሁሉም በተዘረጋለት መስመር እንዲጓዝ ፍትሃዊ አስተዳደር ከሰፈነ ሀገር ትለማለች።
ያፈረስነው ብዙ ነው ለመገንባት ቀላል አይደለም። ታሪክ አይጠገንም ነገር ግን ቀጣዩ ትውልድ ከተማረበት ጥቅም አለው። እንዲሁም የተበላሸውን ታሪክ በመልካም መቀየር ይቻላል። ስለዚህ ዳግም መጥፎ የታሪክ አሻራ ጥለን እንዳናልፍ ቆም ብለን ማሰቡ አይከፋም።
የኢትዮጵያ ህዝብ የብዙ ዘመን የሰው ርኃብ ያለበት በመሆኑ አሁን እያሳየ ያለው ተስፋና ምኞት በትንሹም ቢሆን መጠኑን ያለፈ እንዳይሆን ጥንቃቄ ማድረግ አስፈላጊ ይመስለኛል
No comments:
Post a Comment