Monday, December 26, 2011

በጨለማ የሄደ ሕዝብ ብርሃን አየ ኢሳ 9፥2

የዛሬው ሰንበት እንደቤተክርስቲያናችን አስተምህሮ ብርሃን ይባላል። ስያሜው የተሰጠው በቅዱስ ያሬድ ሲሆን ወቅቱም የጌታን መወለድ በተስፋ ይጠባበቁ  የነበሩት የአዳምና የልጆቹን ደጅ ጥናትን የምናስታውስበት ነው። በመሆኑም ልበ አምላክ ቅዱስ ዳዊት ፈኑ ብርሃነከ ወጽድቀከ እማንቱ ይምርሃኒ (  ብርሃንህንና እውነትህን ላክ እነርሱ ይምሩኝ። መዝ 43፥3) ብሎ ተናግሯል። ስለሆነም ቤተክርስቲያናችን የጌታችንና የአምላካችን የመድኃኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስን ልደት አስቀድማ ለልጆቿ ጾም ጸሎት እያደረጉ ደጅ እንዲጠኑ ታዛለች።

 የሰው ልጅ የፈጣሪውን ትእዛዝ በማፍረሱ ምክንያት ለ5500 ዘመን በዲያቢሎስ ባርነት ተይዞ በጨለማ አገዛዝ ስር ወድቆ ይኖር ነበር። ይሁን እንጅ እግዚአብሔር አምላክ  የሰው ልጅ ደካማ በመሆኑ በዲያቢሎስ ክፉ ምክር ተታሎ እንደወደቀ ያውቅ ነበርና ከልጅ ልጅህ ተወልጄ አድንሃለሁ የሚለውን የተስፋ ቃል ነግሮት ነበር። በመሆኑም እስከ ዘመኑ ፍጻሜ ድረስ አዳምና ከእርሱ በኋላ የነበሩት ልጆቹ በሞተ ስጋ ላይ ሞተ ነፍስ ተጭኗቸው በሲኦል በዲያቢሎስ ተረግጠው  ይኖሩ ነበር።


በኋላም የዘመኑ ፍጻሜ በደረሰ ጊዜ መድኃኔዓለም ኢየሱስ ክርስቶስ ከንጽህት ቅድስት ድንግል ማርያም በስጋ ተወልዶ በጨለማ አገዛዝ ስር የነበሩትን አዳምንና ልጆቹን ነጻ አውጥቷቿዋል። ጌታችን በወንጌሉ እኔ የዓለም ብርሃን ነኝ፤ የሚከተለኝ የሕይወት ብርሃን ይሆንለታል እንጂ በጨለማ አይመላለስም ዮሐ 8፥12 ብሎ እንደተናገረው  በዓለም ስንኖር በብርሃኑ መመላለስ እንደሚገባን አስተምሮናል።

የሰው ልጅ የፈጣሪውን ትእዛዝ ካላከበረ የጨለማ ጉዞ እያደረገ መሆኑን ሊገነዘብ ይገባዋል። በጨለማ ተጉዞ ደግሞ ያሰቡት ቦታ መድረስ አይቻልም። በጨለማ የተመሰለ ክፉ ስራ ነው። የብርሃኑ ምሳሌ ደግሞ መልካም ስራ ነው።
መልካሙን ሥራችሁን አይተው በሰማያት ያለውን አባታችሁን እንዲያከብሩ ብርሃን ናችሁ እንዲሁ በሰው ፊት ይብራ። ማቴ 5፥16

ቅዱስ ጳውሎስ ለገላትያ ክርስቲያኖች  ገላ 5፥1  በነጻነት እንድንኖር ክርስቶስ ነጻ አወጣን ብሎ እንደተናገረው በክርስቶስ ያ ጥንተ ጠላታችን ዲያቢሎስ ድል ተነስቶልናል። ስለዚህ ብርሃን ሳለልን በብርሃን ልንመላለስ ይገባል። በተሰጠን እድሜ መልካም ስራ ሰርተን በንስሃ ታድሰን ስጋዉንና ደሙን ተቀብለን የመንግስተ ሰማያት ልጆች እንድንሆን አምላካችን በቸርነቱ ይርዳን።  

No comments:

Post a Comment