ህዝበ እስራኤል በምርኮ ሳሉ በባቢሎን የምትኖር ከእስራኤል ወገነ የሆነች ሶስና የምትባል አንዲት ሴት ነበረች። ይህች ሴት ከልጅነቷ ጀምሮ ህገ እግዚአብሔርን እየተማረች ነበር ያደገችው። እግዚአብሔር ይገድላል እንዲሁም ያድናል የሚለው ጽኑ እምነት የነበራት እና በምግባሯም እጅግ የተወደደችና የተከበረች ሴት ነበረች። ከዚህም ሌላ እጅግ መልከ መልካምና ማራኪ ውበት ነበራት። ባሏ ኢዮአቄም የሚባል ከሁሉ የተከበረና ባለ ፀጋ ነበር። በመሆኑም ከአይሁድ ወገን ብዙዎች ለጉዳያቸው ወደ እርሱ ይመጡ ነበር። ከባቢሎን ኃጢአት እንዲጠበቁ ህዝቡን እንመክራለን የሚሉ ሁለት የተሰወረ ተንኮል ያለባቸው ሁለት የአይሁድ መምህራን ነበሩ። እነዚህ ክፉ መምህራን ለኢዮአቄም ባለሟል ነበሩና ሶስናን እለት እለት እየተመለከቱ በዝሙት ፍቅር ወደቁ። አንዱ ለሌላው በልቡ ያለውን ሳይነግር አሳቻ ቦታ እየፈለጉ ሳለ ከቤቷ አቅራቢያ በሚገኘው የአትክልት ስፍራ እንደ ሥርዓቱ ለመታጠብ በሄደች ጊዜ ከሷ ቀድመው ወደ አትክልቱ ስፍራ በመግባት ተሰውረው ስለነበር አገልጋዮቿን አሰናብታ ለመታጠብ ስትዘጋጅ ከተደበቁበት ወጥተው በዝሙት እንድረስብሽ አሏት። ህገ እግዚአብሔርን ጠንቅቃ የምታውቅ በመሆኗ ይህን ኃጢአት እንደማትፈጽም ነገረቻቸው። እነሱ ግን በዝሙት አይናቸው ታውሮ ይህን ካልፈጸመች ያለበደሏ በሀሰት አስመስክረው እንደሚያስገድሏት ነገሯት። እሷም እኒያ አስመሳይ መምህራን ይህን ክፉ ኃጢአት እንድትፈጽም ባስጨነቋት ጊዜ እንዲህ አለች "ባደርገውም እሞታለሁ ባላደርገውም አልድንም" ይህን ብላ ድምጿን አሰምታ ጮኽች በዚያ የነበሩ ሰዎች ሲሰበሰቡ እነዚያ ተንኮለኞች መምህራን አስቀድመው እንደተናገሩት የሀሰት ቃል መናገር ጀመሩ ህዝቡም የመምህራኑን ቃል በመስማት በድንጋይ ተወግራ መገደል አለባት በማለት ተስማሙ። ሊገድሏት ሲሄዱ ያመነችው አምላክ ህፃን ልጅ ልኮ የነዚያን ተንኮለኞች መምህራን ስውር ሴራ ገልጦ በማውጣት የሷን ሞት እነሱ እንዲሞቱ አድርጓል። ያ ሶስናን ከሞት የታደገ ወጣት ነቢዩ ዳንኤል ነበር። መ. ሶስና ቁ 5
ሀገራችን ኢትዮጵያ ሁለት ሥጋቶች አሉባት። አንዱ መንግሥት የዘረጋው ዘረኝነትን ያነገሰ ሥርዓት ሲሆን ሌላው ደግሞ ይህን እንቃወማለን የሚሉ ነገር ግን ሌላ የማፍረስ አጀንዳ ያላቸውና ህዝቡ ያልወከላቸው በተቃዋሚ ስም የተደራጁ አካላት ናቸው። የሁለቱም አላማወች የኢትዮጵያዊነትን መልክ የሚያበላሹ ናቸው። በመሆኑም ኢትዮጵያውያን አይፈልጓቸውም። የራሳቸውን ዓላማ ለማስፈጸም ሲሉ በሌላው ላይ ያልተፈጠረ ታሪክ በማዘጋጀት ለህዝብ አሳቢ በመምሰል እራሳቸውን ለህዝብ ተቆርቋሪ ያደርጋሉ። ነገር ግን እውነት ምንጊዜም ህያው ነችና ልትሰወር አትችልም። ኢትዮጵያ ውስጥ እንደ ህዝብ የበደለ አለ ብሎ መናገር የበዛ ክፋት ነው። እንደ ህዝብ ከሌላው ተለይቶ የተበደለ ነበር ማለትም አለማስተዋል ነው። የምናምነው እንደ ግለሰብ የሚበድሉ ነበሩ ዛሬም አሉ። እንደ ግለሰብ የሚበደሉ ነበሩ ዛሬም አሉ። በኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ ኢትዮጵያዊ ሆኖ ተሳትፎ ያልነበረው የለም። ስለዙህ በጎውን ይዘን መጥፎን ደግሞ ተምረንበት ለሀገር የተሻለ መሥራት እያለ የነበረውን በሙሉ ካላፈረስኩ የኔ ሀውልት አይተከልም ብሎ ማሰብ ጤናማ አስተሳሰብ አይደለም። ከላይ ያነሳናቸውን የአይሁድ መምህራን ስንመለከት የተደበቀ ፍላጎት ይዘው ወደ ሶስና መጡ። የሚፈልጉትን ማግኘት ስላልቻሉ መሞት አለባት አሉ። ዛሬም ከኛ መካከል እነሱ የሚፈልጉትን እስካላደረጉ ድረስ ሀገሪቱ ብትሞት ግድ አይላቸውም። በመንፈሳዊውም ዓለም የታዘብናቸው አሉ ቤተክርስቲያን እነሱ እንደፈለጉ የሚፈነጩባት ካልሆነች ብትጠፋ አንዳች አይገዳቸውም። እንደ ነቢዩ ዳንኤል ያለ እውነትን ተናግሮ ህዝባችንን ወደ ቀደመ ማንነቱ የሚመልስ መሪ እግዚአብሔር እንደሚሰጠን እናምናለን። ብዙ ተስፋ የተጣለባቸው ዶ/ር አቢይ ኢትዮጵያን ከሞት አደጋ ይታደጓት ይሆን? ለእግዚአብሔር የሚሳነው ነገር የለምና ተስፋ እናድርግ።
መጋቤ ሃይማኖት ቀሲስ ዘለዓለም ጽጌ
St louis mo USA
No comments:
Post a Comment