Thursday, December 29, 2011

እኔ በእግዚአብሔር ፊት የምቆመው ገብርኤል ነኝ ሉቃ 1፥19


ዛሬ በሃገራችን በኢትዮጵያ እና በመላው ዓለም በሚገኙ ኢትዮጵያውያን ክርስቲያኖች ዘንድ የመላእክት አለቃ ቅዱስ ገብርኤል የሚታሰብበት እለት ነው። የመላእክት አለቃ ቅዱስ ገብርኤል በዛሬው እለት ሠለስቱ ደቂቅን ( ሶስቱን ወጣቶች ) ከእሳት ያወጣበት እለት ነው። የቤተክርስቲያን አባቶች ሊቃውንት ዓመቱን በሙሉ እግዚአብሔርን እናከብር ዘንድ በተለያየ ጊዜ በቅዱሳኑ ላይ አድሮ ያደረገውን ታላላቅ ተዓምራት እናስብ ዘንድ እለታቱን በሙሉ እግዚአብሔርን እንድናመሰግንባቸው ስርዓትን ሰርተውልናል። 

በሃገራችን በኢትዮጵያ በዛሬው እለት በየአብያተክርስቲያናቱ  እግዚአብሔር ይመሰገናል። በተለይም የመላእክት አለቃ ቅዱስ ገብርኤል ለመታሰቢያው በተሰራለት ቤተክርስቲያን አካባቢ የሚገኙ ክርስቲያኖች ምዕመናን ከበዓሉ አስቀድመው እንግዶችን ለመቀበል ቤታቸውን ያዘጋጃሉ፣ ለእንግዶች የሚያስፈልገውን ጸበል ጸዲቅ ያዘጋጃሉ፣ እንግዶች በሚመጡበት ጊዜም እግራቸውን ያጥባሉ፣ እንግዶች ወደየመጡበት እስኪመለሱ በደስታ ተቀብለው ያስተናግዳሉ።

ይህም የሚሆንበት ምክንያት በቅዱስ  መጽሐፋችን በመጽሐፍ ቅዱስ  እንደተገለጸው በቃል የተነገረውን በተግባር በመፈጸም ነው። 

 እንግዳ ሆኜ ተቀብላችሁኛልና ማቴ 25፥35


 እንግዶችን ለመቀበል ትጉ። ሮሜ 12፥13  



እንግዶችን መቀበል አትርሱ፤ በዚህ አንዳንዶች ሳያውቁ መላእክትን እንግድነት ተቀብለዋልና። ዕብ 13፥1     እኛ ኢትዮጵያውያን ከመላው የዓለም ህዝብ የምንለይበት በዙ ሃይማኖታዊና ትውፊታዊ ስርዓት አለን። በዚህም የተነሳ በአሁኑ ወቅት በዓለም ብቸኛ የሆነችውን የሃይማኖት የባህልና የስርዓት ባለጸጋ የሆነችውን ሃገራችንን በተለያየ መንገድ ስሟን ለማጉደፍ ከውጭም ከውስጥም በሚነሱ ጠላቶች ተከባ ትገኛለች። በተለይ ለሃገሪቱ መታወቂያና መገለጫ የሆነችውን ቅድስት ተዋሂዶ ቤተክርስቲያንን ለማጥፋት ያልተሞከረ ነገር የለም። ነገር ግን  ፈቃዱ የእግዚአብሔር ስለሆነ እስከ አሁን ደርሰናል። ለወደፊትም ይህችን የቃል ኪዳን ምድር በቅዱሳኑ ጸሎት እንደሚጠብቃት እናምናለን።  

ወደ ዛሬው በዓል ስንመለስ ሁላችንም እንደምናውቀው የቅዱስ ገብርኤል በዓል ሲነሳ የቁልቢው ገብርኤል በሁላችንም አእምሮ የማይዘነጋ ነው። የመላእክት አለቃ ቅዱስ ገብርኤል በዚህ ቦታ ላይ ያደራጋቸውን ተዓምራት ዘርዝሮ ለመጻፍ አቅምና ጊዜ ስለማይበቃ ለመዘርዘር አይሞከርም እንዲሁ እፁብ ድንቅ ብሎ ማለፉ የተሻለ ነው። 

ቅድስት ሃገር ኢትዮጵያ  በነበርኩበት ጊዜ ከማገለግልባት ከደብረ አሚን ተክለሃይማኖት ቤተክርስቲያን በየዓመቱ ታህሣስና ሐምሌ ምዕመናንን በጋራ ይዘን ከመሰል ወንድሞቼ ጋራ ወደ ቁልቢ ገብርኤል እንጓዝ ነበር። በጉዟችን ወቅት በመንገድ ላይ መንፈሳዊ  ትምህርትና ዝማሬ በሰፊው ይቀርባል። እንዲሁም ከጉዞው ተሳታፊዎች በኩል መልአኩ ቅዱስ ገብርኤል ያደረገላቸውን ተዓምራት የሚናገሩበት ክፍለ ጊዜም ነበረን። ከሁሉ የሚደንቀው ነገር በጉዟችን ላይ የተወሰኑት የእስልምና እምነት ተከታዮች ነበሩ ። ግማሾቹ ታመው በህክምና ገንዘባቸውን ጨርሰው ተስፋ ሲቆርጡ የቅዱስ ገብርኤልን የተአምራት ዜና በመስማት ስዕለት ተስለው ከህመማቸው የተፈወሱ፣ ከፊሎቹ ልጅ መውለድ ፈልገው ወደውጭ ሃገር ድረስ ሄደው በህክምና ሞክረው አልሆን ሲላቸው በመጨረሻ ቢሆንም ባይሆንም እንሞክረው ብለው እንደቀልድ በአንደበታቸው ለቅዱስ ገብርኤል ተስለው ልጅ ያገኙ እና ሌሎችም ብዙ ለአእምሮ የሚከብዱ ጉዳዮች የተፈጸሙላቸው ይገኙበት ነበር ።

አስታውሳለሁ አቶ ጀማል የሚባሉ ሰው ልጃቸው በኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ውስጥ ታዋቂ እግር ኳስ ተጫዋች የሆነ (ሳዳት ጀማል)የሚባል በየዓመቱ ከጉዟችን ተሳታፊዎች አንዱ ነበሩ።

እግዚአብሔር አምላክ ለቅዱሳን መላእክት የሰጣቸውን ስልጣንና ክብር እንመልከት ።


የዚያን ጊዜም ንጉሡ ናቡከደነፆር ተደነቀ ፈጥኖም ተነሣ አማካሪዎቹንም። ሦስት ሰዎች አስረን በእሳት ውስጥ ጥለን አልነበረምን? ብሎ ተናገራቸው። እርሱም፦ ንጉሥ ሆይ፥ እውነት ነው ብለው ለንጉሡ መለሱለት።
እርሱም፦ እነሆ፥ እኔ የተፈቱ በእሳቱም መካከል የሚመላለሱ አራት ሰዎች አያለሁ ምንም አላቈሰላቸውም የአራተኛውም መልክ የአማልክትን ልጅ ይመስላል ብሎ መለሰ።
የዚያን ጊዜም ናቡከደነፆር ወደሚነድደው ወደ እሳቱ እቶን በር ቀርቦ። እናንተ የልዑል አምላክ ባሪያዎች፥ ሲድራቅና ሚሳቅ አብደናጎም፥ ኑ ውጡ ብሎ ተናገራቸው። ሲድራቅና ሚሳቅም አብደናጎም ከእሳቱ መካከል ወጡ። ዳን 3፥24
 
በመንገድ ይጠብቅህ ዘንድ ወዳዘጋጀሁትም ስፍራ ያገባህ ዘንድ፥ እነሆ፥ እኔ መልአክን በፊትህ እሰድዳለሁ።
በፊቱ ተጠንቀቁ፥ ቃሉንም አድምጡ ስሜም በእርሱ ስለ ሆነ ኃጢአት ብትሠሩ ይቅር አይልምና አታስመርሩት።
አንተ ግን ቃሉን ብትሰማ፥ ያልሁህንም ሁሉ ብታደርግ፥ ጠላቶችህን እጣላቸዋለሁ፥ የሚያስጨንቁህንም አስጨንቃቸዋለሁ።
መልአኬ በፊትህ ይሄዳልና፥ ወደ አሞራውያንም ወደ ኬጢያውያንም ወደ ፌርዛውያንም ወደ ከነዓናውያንም ወደ ኤዊያውያንም ወደ ኢያቡሳውያንም ያገባሃል እኔም አጠፋቸዋለሁ። ዘጸ 23፥20

ወደ እግዚአብሔርም በጮኽን ጊዜ ድምፃችንን ሰማ፥ መልአክን ሰድዶ ከግብፅ አወጣን እነሆም፥ በምድርህ ዳርቻ ባለችው ከተማ በቃዴስ ተቀምጠናል። ዘኁል 20፥16
 
እግዚአብሔርም የበለዓምን ዓይኖች ከፈተ የእግዚአብሔርን መልአክ በመንገድ ላይ ቆሞ የተመዘዘም ሰይፍ በእጁ ይዞ አየ ሰገደም፥ በግምባሩም ወደቀ። ዘኁል 22፥31
 

ጌዴዎንም የእግዚአብሔር መልአክ እንደ ሆነ አየ ጌዴዎንም። አቤቱ አምላኬ ሆይ፥ ወዮልኝ የእግዚአብሔርን መልአክ ፊት ለፊት አይቻለሁና አለ። መሳፍ 6፥22

ዳዊትም ዓይኖቹን አነሣ የእግዚአብሔር መልአክ በምድርና በሰማይ መካከል ቆሞ፥ የተመዘዘም ሰይፍ በእጁ ሆኖ ወደ ኢየሩሳሌም ተዘርግቶ አየ። ዳዊትም ሽማግሌዎችም ማቅ ለብሰው በግምባራቸው ተደፉ። መ ዜና መዋ 21፥16

የእግዚአብሔር መልአክ በሚፈሩት ሰዎች ዙሪያ ይሰፍራል፥ ያድናቸውማል። መዝ 34፥7
 

የእግዚአብሔርም መልአክ መልሶ፦ አቤቱ፥ የሠራዊት ጌታ ሆይ፥ እነዚህ ሰባ ዓመት የተቈጣሃቸውን ኢየሩሳሌምንና የይሁዳን ከተሞች የማትምራቸው እስከ መቼ ነው? አለ።

እግዚአብሔርም መልሶ ከእኔ ጋር ይነጋገር ለነበረው መልአክ በመልካምና በሚያጽናና ቃል ተናገረው። ትን ዘካ 1፥12
 

መልአኩም መልሶ፦ እኔ በእግዚአብሔር ፊት የምቆመው ገብርኤል ነኝ፥ እንድናገርህም ይህችንም የምሥራች እንድሰብክልህ ተልኬ ነበር፤

እነሆም፥ በጊዜው የሚፈጸመውን ቃሌን ስላላመንህ፥ ይህ ነገር እስከሚሆን ቀን ድረስ ዲዳ ትሆናለህ መናገርም አትችልም አለው።

ሕዝቡም ዘካርያስን ይጠብቁት ነበር፤ በቤተ መቅደስም ውስጥ ስለ ዘገየ ይደነቁ ነበር።

በወጣም ጊዜ ሊነግራቸው አልቻለም፥ በቤተ መቅደስም ራእይ እንዳየ አስተዋሉ፤ እርሱም ይጠቅሳቸው ነበር፤ ድዳም ሆኖ ኖረ።

ሉቃ 1፥19

በስድስተኛውም ወር መልአኩ ገብርኤል ናዝሬት ወደምትባል ወደ ገሊላ ከተማ፥

ከዳዊት ወገን ለሆነው ዮሴፍ ለሚባል ሰው ወደ ታጨች ወደ አንዲት ድንግል ከእግዚአብሔር ዘንድ ተላከ፥ የድንግሊቱም ስም ማርያም ነበረ።

መልአኩም ወደ እርስዋ ገብቶ። ደስ ይበልሽ፥ ጸጋ የሞላብሽ ሆይ፥ ጌታ ከአንቺ ጋር ነው፤ አንቺ ከሴቶች መካከል የተባረክሽ ነሽ አላት።

እርስዋም ባየችው ጊዜ ከንግግሩ በጣም ደነገጠችና። ይህ እንዴት ያለ ሰላምታ ነው? ብላ አሰበች።

መልአኩም እንዲህ አላት፦ ማርያም ሆይ፥ በእግዚአብሔር ፊት ጸጋ አግኝተሻልና አትፍሪ።

እነሆም፥ ትፀንሻለሽ ወንድ ልጅም ትወልጃለሽ፥ ስሙንም ኢየሱስ ትዪዋለሽ።

እርሱ ታላቅ ይሆናል የልዑል ልጅም ይባላል፥ ጌታ አምላክም የአባቱን የዳዊትን ዙፋን ይሰጠዋል፤

በያዕቆብ ቤትም ላይ ለዘለላም ይነግሣል፥ ለመንግሥቱም መጨረሻ የለውም።

ማርያምም መልአኩን። ወንድ ስለማላውቅ ይህ እንዴት ይሆናል? አለችው።

መልአኩም መልሶ እንዲህ አላት፦ መንፈስ ቅዱስ በአንቺ ላይ ይመጣል፥ የልዑልም ኃይል ይጸልልሻል ስለዚህ ደግሞ ከአንቺ የሚወለደው ቅዱስ የእግዚአብሔር ልጅ ይባላል።

እነሆም ዘመድሽ ኤልሳቤጥ፥ እርስዋ ደግሞ በእርጅናዋ ወንድ ልጅ ፀንሳለች፥ ለእርስዋም መካን ትባል ለነበረችው ይህ ስድስተኛ ወር ነው፤

ለእግዚአብሔር የሚሳነው ነገር የለምና።

ማርያምም። እነሆኝ የጌታ ባሪያ እንደ ቃልህ ይሁንልኝ አለች። መልአኩም ከእርስዋ ሄደ። ሉቃ 1፥26

ጥበበኛው ሶሎሞን በመጽሐፈ ምሳሌ 4፥23 ላይ
አጥብቀህ ልብህን ጠብቅ፥ የሕይወት መውጫ ከእርሱ ነውና።

ብሎ እንደተናገረው ልባቸውን የጠበቁ ህሊናቸውን ለዓለም ከንቱ ነገር ያላስገዙ ሰዎች ይህን ድንቅ ምስጢር ለወዳጆቹ የገለጸውን እግዚአብሔርን እያመሰገኑ ህይዎታቸውን በደስታ ይመራሉ። ነገር ግን የስንፍና መንፈስ ተጭኗቸው እግዚአብሔር በቅዱሳኑ ላይ አድሮ የሚሰራውን ተዓምራት ማየት ተስኗቸው በጨለማ ዓለም ውስጥ የሚኖሩ ብዙዎች ናቸው።

አስተዋይ ልቦና ለሁላችንም ያድለን የበዓሉ በረከት በሁላችንም ላይ ይደር


2 comments:

  1. ቀሲስ እንኳን ለመልአኩ ለቅዱስ ገብርኤል በሰላም አደረሰን ቃለህይዎት ያሰማልን

    ReplyDelete
  2. KHY! E/BER yagelgelot zemenehen yabzale,yibarkele

    ReplyDelete