Friday, July 1, 2011

የዘላለም ሕይዎት

የዘላለም ህይዎትን እንድዎርስ ምን ላድርግ ?

ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ለአዳም የገባውን ቃል ሊፈጽም ሰው በሆነበት ዘመን  በሰፊው ያስተምር የነበረው የዘለዓለም ህይወትን ሊሰጥ እንደመጣ ነበር። ነገር ግን ብዙዎች የቃሉን ትምህርት የእጁን ተአምራት እያዩ ቢያምኑበትም እስከ መጨረሻው የተከተሉት ጥቂቶች ነበሩ። ስለ ዘላለም ህይወት አራቱም ወንጌላውያን በሰፊው ጽፈዋል። ወንጌላዊው ሉቃስ የጻፈውን እናስቀድም ,, ከአለቆችም አንዱ። ቸር መምህር፥ የዘላለምን ሕይወት እንድወርስ ምን ላድርግ? ብሎ ጠየቀው። ኢየሱስም፦ ስለ ምን ቸር ትለኛለህ? ከአንዱ ከእግዚአብሔር በቀር ቸር ማንም የለም። ትእዛዛቱን ታውቃለህ፥ አታመንዝር፥ አትግደል፥ አትስረቅ፥ በሐሰት አትመስክር፥ አባትህንና እናትህን አክብር አለው። እርሱም፦ ይህን ሁሉ ከሕፃንናቴ ጀምሬ ጠብቄአለሁ አለ። ኢየሱስም ይህን ሰምቶ። አንዲት ገና ቀርታሃለች፤ ያለህን ሁሉ ሽጠህ ለድሆች ስጥ፥ በሰማይም መዝገብ ታገኛለህ፥ መጥተህም ተከተለኝ አለው። እርሱ ግን ይህን ሰምቶ እጅግ ባለ ጠጋ ነበርና ብዙ አዘነ። ኢየሱስም ብዙ እንዳዘነ አይቶ። ገንዘብ ላላቸው ወደ እግዚአብሔር መንግሥት መግባት እንዴት ጭንቅ ይሆናል። ባለ ጠጋ ወደ እግዚአብሔር መንግሥት ከሚገባ ይልቅ ግመል በመርፌ ቀዳዳ ሊገባ ይቀላል አለ። ሉቃ 18፥18


ከቃሉ እንደምንረዳው ይህ ሰው እድሜ ዘመኑን በሙሉ ህገ እግዚአብሔርን ጠብቆ ይኖር ነበር። ነገር ግን በሃብቱ መብዛት ምክንያት ሁሉንም ከንቱ አደረገው። ማሰናከያ ይመጣ ዘንድ ግድ ነው እንደተባለው የዘለዓለም ህይወትን ለመውረስ ብዙ መሰናክል ማለፍን ይጠይቃል። በዓለም ላይ ለፍተን የምናፈራው ምድራዊ ሃብትም ሆነ እውቀት ለአዳም የአምስት ሽ አምስት መቶ ዘመን መከራ ምክንያት ከሆነችው ከእጸ በለስ ጋር ይመሳሰላል። ምንም እንኳን ለፍቶ ደክሞ ያገኙትን ነገር መጠቀም የተፈቀደ ቢሆንም የሚገኘው ኃላፊ ከሆነችው ዓለም ስለሆነ ልንመካበት አንችልም። ብዙዎች የዘለዓለም ህይዎትን ማግኘት እየፈለጉ በዚህ ወጥመድ ወድቀው ቀርተዋል። ሐዋርያው ቅዱስ ዮሐንስ በመልዕክቱ ,, ዓለምን ወይም በዓለም ያሉትን አትውደዱ፤ በዓለም ያለው ሁሉ እርሱም የሥጋ ምኞትና የዓይን አምሮት ስለ ገንዘብም መመካት ከዓለም ስለ ሆነ እንጂ ከአባት ስላልሆነ፥ ማንም ዓለምን ቢወድ የአባት ፍቅር በእርሱ ውስጥ የለም።ዓለሙም ምኞቱም ያልፋሉ፤ የእግዚአብሔርን ፈቃድ የሚያደርግ ግን ለዘላለም ይኖራል። 1ኛ ዮሐ 2፥15 እንዳለው ማንም በዓለም ባለጸጋ የሆነ ቢመስለው ሊመካ አይገባውም። ይህ ሲባል ግን እጅን አጣጥፎ መቀመጥ ማለት እንዳልሆነ ሊታወቅ ይገባዋል። በጥረቱ የሚያፈራውን ምድራዊ ሃብት በጎ ሥራ ሊሰራበት ይገባዋል ለማለት ነው።
 
የሰው ልጅ አስቀድሞ ሲፈጠር ዘለዓለማዊነትን ያለድካምና ያለፈተና ከእግዚአብሔር ተሰጥቶት ነበር። ሰው ደካማ ሆኖ በመገኘቱ የፈጣሪውን ትዕዛዝ ባለመጠበቁ ዘለዓለማዊ መሆኑ ቀርቶ ጊዜያዊ ፣ ህያው መሆኑ ቀርቶ ሟች፣ ቋሚ መሆኑ ቀርቶ ኃላፊ ሊሆን ችሏል። ምንም እንኳን የሰው ልጅ የበደለው ወዶና ፈቅዶ ቢሆንም እግዚአብሔር ከፍጥረታት ሁሉ አክብሮና አልቆ የፈጠረው የእጁ ስራ ስለሆነ የዲያቢሎስ ባሪያ ሆኖ እንዲቀር ፈቃዱ አልነበረም። ከልጅ ልጅህ ተወልጄ አድንሃለሁ ብሎ ተስፋ ሰጥቶት ነበር። ያለውም አልቀረ የሰው ወገን ከሆነችው ከእመቤታችን ከቅድስት ድንግል ማርያም ተወልዶ፣ የሰውን ባህርይ ተላብሶ፣  በምድር ላይ ተመላልሶ፣ አስተምሮ፣ አምላክነቱን ገልጾ፣ እስከ መስቀል ሞት ድረስ የታዘዘ ሆኖ ወደ ቀደመ ክብሩ መልሶታል።
 
አባቶቻችን እግዚአብሔር ዓለምን ከፈጠረበት ይልቅ ያዳነበት ጥበቡ እጅግ ይደንቃል ይላሉ። እውነትም እግዚአብሔር  ለሰው ያለው ፍቅር የፍጡር ህሊና ሊደርስበት የማይቻል ነው። ጌታ እራሱ በወንጌል እንዲህ ብሏል ,,ሙሴም በምድረ በዳ እባብን እንደ ሰቀለ እንዲሁ በእርሱ የሚያምን ሁሉ የዘላለም ሕይወት እንዲኖረው እንጂ እንዳይጠፋ የሰው ልጅ ይሰቀል ይገባዋል። በእርሱ የሚያምን ሁሉ የዘላለም ሕይወት እንዲኖረው እንጂ እንዳይጠፋ እግዚአብሔር አንድያ ልጁን እስኪሰጥ ድረስ ዓለሙን እንዲሁ ወዶአልና።  ዮሐ 3፥14
 
የዘለዓለም ህይወትን ለመውረስ የሚያበቁ መሰረታዊ ነገሮች አሉ።  የመጀመሪያው መንገድ ፈጣሬ አለማት እግዚአብሔር አንድነቱን ሦስትነቱን ገልጾ ከሶስቱ አካላት አንዱ ወልድ ወደዚህ ዓለም መጥቶ ለአዳም የገባውን ቃል ለመፈጸም ሰው እንደሆነ እና ሰው በመሆኑም በኃጢአት ወድቆ የነበረው የሰው ልጅ  የአምላክነትን ክብር እንዳገኘ ማመን ነው። ይህንም ጌታ እንዲህ ብሎ ተናግሯል ,, እውነት እውነት እላችኋለሁ በእኔ የሚያምን የዘላለም ሕይወት አለው። ዮሐ 6፥47
 
ሁለተኛው መንገድ ጥምቀት ነው። ይህንም ጌታ እራሱ ነው የተናገረው። ,, ኢየሱስም መልሶ፦ እውነት እውነት እልሃለሁ፥ ሰው ዳግመኛ ካልተወለደ በቀር የእግዚአብሔርን መንግሥት ሊያይ አይችልም አለው። ኒቆዲሞስም። ሰው ከሸመገለ በኋላ እንዴት ሊወለድ ይችላል? ሁለተኛ ወደ እናቱ ማኅፀን ገብቶ ይወለድ ዘንድ ይችላልን? አለው። ኢየሱስም መለሰ፥ እንዲህ ሲል፦ እውነት እውነት እልሃለሁ፥ ሰው ከውኃና ከመንፈስ ካልተወለደ በቀር ወደ እግዚአብሔር መንግሥት ሊገባ አይችልም። ከሥጋ የተወለደ ሥጋ ነው፥ ከመንፈስም የተወለደ መንፈስ ነው። ዮሐ 3፥3
 
ሶስተኛው የሁሉ ነገር ማሰሪያ የሆነው እና ህይወታችንን ወደ ቅድስና የሚለውጠው ቅዱስ ስጋውና ክቡር ደሙን መቀበል ነው። ይህንም ጌታ እራሱ ነው ያዘዘው። ,, ስለዚህ ኢየሱስ እንዲህ አላቸው፦ እውነት እውነት እላችኋለሁ፥ የሰውን ልጅ ሥጋ ካልበላችሁ ደሙንም ካልጠጣችሁ በራሳችሁ ሕይወት የላችሁም። ሥጋዬን የሚበላ ደሜንም የሚጠጣ የዘላለም ሕይወት አለው፥ እኔም በመጨረሻው ቀን አስነሣዋለሁ። ሥጋዬ እውነተኛ መብል ደሜም እውነተኛ መጠጥ ነውና። ሥጋዬን የሚበላ ደሜንም የሚጠጣ በእኔ ይኖራል እኔም በእርሱ እኖራለሁ። ዮሐ 6፥54

በየዋህነትና በቅንነት ካልሆነ በቀር በሰው ጥበብ የእግዚአብሔር መንግስት አትወረስም። መንግስተሰማያትን  እንደ ህጻናት ራሳችንን ዝቅ ካላደረግን እንደማንወርስ ከጌታ ትምህርት እንረዳለን ። ,, እንዲህም አለ፦ እውነት እላችኋለሁ፥ ካልተመለሳችሁ እንደ ሕፃናትም ካልሆናችሁ፥ ወደ መንግሥተ ሰማያት ከቶ አትገቡም።እንግዲህ እንደዚህ ሕፃን ራሱን የሚያዋርድ ሁሉ፥ በመንግሥተ ሰማያት የሚበልጥ እርሱ ነው። ማቴ 18፥3
 
ሌላው የህይወት መንገድ መልካም ስራ ነው። ሰው በእምነት ሲኖር መልካም ስራ መስራት አለበት። የሰራው በጎ ስራው ይከተለዋል እንደተባለው እምነታችን በስራ ካልተገለጠ ህይወት የለውም።,,እንደዚሁም ሥራ የሌለው እምነት ቢኖር በራሱ የሞተ ነው,, ያዕ 2፥17  ስለሆነም ሁልጊዜ ሥራችን መልካም መሆን አለበት። ቅዱስ ጳውሎስ በሮሜ መልእክቱ እንዲህ ብሏል ,,በበጎ ሥራ በመጽናት ምስጋናንና ክብርን የማይጠፋንም ሕይወት ለሚፈልጉ የዘላለምን ሕይወት ይሰጣቸዋል፤ ለዓመፃ በሚታዘዙ እንጂ ለእውነት በማይታዘዙትና በአድመኞች ላይ ግን ቍጣና መቅሠፍት ይሆንባቸዋል። ክፉውን በሚያደርግ ሰው ነፍስ ሁሉ መከራና ጭንቀት ይሆንበታል፥ አስቀድሞ በአይሁዳዊ ደግሞም በግሪክ ሰው ሮሜ 2፥7
 
በአዳም በደል ምክንያት ከሱ በኋላ የነበሩ ልጆቹ እስከ ጌታ ልደት ድረስ በጨለማ ይኖሩ ነበር። በጨለማ ለሚኖሩ ብርሃን ወጣላቸው ተብሎ እንደተጻፈው እውነተኛው ብርሃን ኢየሱስ ክርስቶስ ከቅድስት ድንግል ማርያም በቤተልሄም በተወለደ ጊዜ በመላእክት አንደበት ለሰው ልጆች የምስራች ተሰበከ። ወንጌላዊው ሉቃስ እንደጻፈው> ,, መልአኩም እንዲህ አላቸው፦ እነሆ፥ ለሕዝቡ ሁሉ የሚሆን ታላቅ ደስታ የምሥራች እነግራችኋለሁና አትፍሩ፤ ዛሬ በዳዊት ከተማ መድኃኒት እርሱም ክርስቶስ ጌታ የሆነ ተወልዶላችኋልና,, ሉቃ 2፥10 ከዚህ የምስራች በኋላ አዳምና ልጆቹ የህይዎትን መንገድ ጭላጭል ማየት ችለዋል። በቤተልሄም የተወለደው ጌታ ለአይሁድ እራሱን አሳልፎ ሰጥቶ፣ በቀራንዮ ተሰቅሎ፣ ሞቶ፣ ወደ መቃብር ወርዶ፣ መግነዝ ፍቱልን መቃብር ክፈቱልኝ ሳይል በስልጣኑ ሞትን ድል አድርጎ ተነስቷል። በመሆኑም ሁላችን ትንሳኤውን በሚመስል ትንሳኤ በክብር እንነሳለን።

ቅዱስ ጳውሎስ በሮሜ መልዕክቱ ,, አሁን ግን ከኃጢአት አርነት ወጥታችሁ ለእግዚአብሔርም ተገዝታችሁ፥ ልትቀደሱ ፍሬ አላችሁ፤ መጨረሻውም የዘላለም ሕይወት ነው።የኃጢአት ደመወዝ ሞት ነውና፤ የእግዚአብሔር የጸጋ ስጦታ ግን በክርስቶስ ኢየሱስ በጌታችን የዘላለም ሕይወት ነው ,, ሮሜ 6፥22 እንዳለው በጎ ስራ ሰርተን የዘለዓለምን ህይወት እንድንወርስ የእግዚአብሔር ቅዱስ ፈቃዱ ነው።
 
በሌላም ቦታ ሐዋርያው እንዲህ ብሏል ,, አትሳቱ፤ እግዚአብሔር አይዘበትበትም። ሰው የሚዘራውን ሁሉ ያንኑ ደግሞ ያጭዳልና፤ በገዛ ሥጋው የሚዘራ ከሥጋ መበስበስን ያጭዳልና፥ በመንፈስ ግን የሚዘራው ከመንፈስ የዘላለምን ሕይወት ያጭዳል,, ገላ 6፥7 ሰው በህይወት ዘመኑ የሰራው ክፉም ሆነ ደግ በመጨረሻው ሰዓት ይጠብቀዋል። ስለዚህ የሰው ልጆች በእያንዳንዷ እርምጃ ምግባራችን መልካም ሊሆን ይገባዋል።

ወንጌላዊው ዮሐንስ በመልዕክቱ,, ስለ ሕይወት ቃል ከመጀመሪያው የነበረውንና የሰማነውን በዓይኖቻችንም ያየነውን የተመለከትነውንም እጆቻችንም የዳሰሱትን እናወራለን፤ ሕይወትም ተገለጠ አይተንማል እንመሰክርማለን፥ ከአብ ዘንድ የነበረውንም ለእኛም የተገለጠውን የዘላለምን ሕይወት እናወራላችኋለን,, 1ኛ ዮሐ 1፥1 እንዳለው እግዚአብሔር ለሰው ልጆች የገለጸውን ምህረትና ይቅርታ በየዘመኑ የሚያስነሳቸው ሐዋርያት መስክረዋል። ፍቁረ እግዚዕ ቅዱስ ዮሐንስ ከጌታ እግር ስር ሆኖ ቃሉን የተማረ፤ እስከ መስቀሉ ድረስ የጌታን መከራና ስቃይ የተካፈለ ሐዋርያ ነው። የዘለዓለም ህይወት ስለሚገኝበት መንገድ በሰፊው ጽፏል። በተለይ ስለፍቅር የጻፋቸው መልእክቶቹ እውነተኛ ምስክርነቱን ያስረዳሉ። ,, እኛ ወንድሞችን የምንወድ ስለ ሆንን ከሞት ወደ ሕይወት እንደ ተሻገርን እናውቃለን፤ ወንድሙን የማይወድ በሞት ይኖራል። ወንድሙን የሚጠላ ሁሉ ነፍሰ ገዳይ ነው፥ ነፍሰ ገዳይም የሆነ ሁሉ የዘላለም ሕይወት በእርሱ እንዳይኖር ታውቃላችሁ። እርሱ ስለ እኛ ነፍሱን አሳልፎ ሰጥቶአልና በዚህ ፍቅርን አውቀናል፤ እኛም ስለ ወንድሞቻችን ነፍሳችንን አሳልፈን እንድንሰጥ ይገባናል። ነገር ግን የዚህ ዓለም ገንዘብ ያለው፥ ወንድሙም የሚያስፈልገው ሲያጣ አይቶ ያልራራለት ማንም ቢሆን፥ የእግዚአብሔር ፍቅር በእርሱ እንዴት ይኖራል? ልጆቼ ሆይ፥ በሥራና በእውነት እንጂ በቃልና በአንደበት አንዋደድ። 1ና ዮሐ 3፥14

እንግዲህ ከላይ ለመጠቆም እንደሞከርኩት ቅዱሳት መጻህፍት በሙሉ የሚነግሩን በዚህ ዓለም ላይ ስንኖር መዘናጋት እንደሌብን፣ የምንኖረው በድንኳን በምትመሰል አለም ውስጥ እንደሆነ እና የማያልፍና ዘለዓለማዊ የሆነ ሰማያዊ ቤት እንዳለን ነው። ስለዚህ ጌታ በወንጌል እንደነገረን,, እውነት እውነት እላችኋለሁ፥ ቃሌን የሚሰማ የላከኝንም የሚያምን የዘላለምሕይወት አለው፥ ከሞትም ወደ ሕይወት ተሻገረ እንጂ ወደ ፍርድ አይመጣም,, ዮሐ 5፥24 እንዳለው በርሱ አምነን የሚከብድብንን ነገር ሁሉ በርሱ ላይ ጥለን,, ሥጋዬን የሚበላ ደሜንም የሚጠጣ የዘላለምሕይወት አለው፥ እኔም በመጨረሻው ቀን አስነሣዋለሁ,, ማቴ 6፥54 ያለውን አምላካዊ ቃል ፈጽመን የዘለዓለም ህይዎት ወራሾች እንድንሆን የአምላካችን ቸርነት የድንግል ማርያም አማላጅነት የቅዱሳን አባቶቻችን ጸሎት የቅዱሳን መላእክት ጥበቃና ተራዳኢነት ከሁላችን ጋር ይሁን።

No comments:

Post a Comment