Monday, January 23, 2012

ይሉኝታ

በተነሳሁበት ርዕስ ዙሪያ ብዙ ጸሐፍያን እንደጻፉ፣ ወደፊትም እንደሚጽፉ እገምታለሁ። ነገር ግን ዛሬ ባለንበት ዘመን « ይሉኝታ » በብዙ ሰዎች ዘንድ የተዘነጋ በመሆኑ፣ አስፈላጊነቱንና አልፎ አልፎ ግን አላስፈላጊ የሚሆንበትም አጋጣሚ እንዳለ ለመጠቆም ያህል ነው። በተለይ ደግሞ በካህናት ዘንድ ከአስነዋሪ ተግባራት በስተቀር በይሉኝታ የምናልፋቸው ነገሮች ሊኖሩ እንደማይገባ በቅዱስ ወንጌሉ ተምረናል።ወንጌልንም ባልሰብክ ወዮልኝ 1ኛቆሮ 9፥16  ወንጌል ማለት ደግሞ እውነት ነው እንደጊዜው ሁኔታ እየተለዋወጡ የሚኖርበት አይደለም። ነገር ግን እግዚአብሔርን የማያስደስት ነገር ስንሰራ ሰውንም ሆነ እግዚአብሔርን ምን ይለኛል ማለት ይገባናል።


ከዛሬ 22 ዓመት በፊት የማውቃቸው አንድ የቤተክርስቲያናችን አባት ሁልጊዜ የማልዘነጋላቸው አባባል ነበራቸው። ማኅበረ ካህናትን ሰብስበው በሚያወያዩበት ጊዜ የሚያስተላልፉት መልእክት ነው። « ይሉኝ አለማለት ፣አቅምን አለማወቅ፣ አደራን መብላት» እነዚህ ሦስቱ አንድ ናቸው። የእግዚአብሔር አገልጋይ የሆነ እነዚህን መጠንቀቅ አለበት ይሉ ነበር።

ዛሬ ላይ በካህናትም ሆነ በምዕመናን ዘንድ እነዚህ ነገሮች እየተዘነጉ ያሉ ይመስላሉ። ነገር ግን መሰረታዊ ነገሮች ናቸው።

በመጀመሪያ ሰው ማንን ነው ምን ይለኛል ማለት ያለበት? አቅሙንስ ማወቅ ያለበት እንዴት ነው? የማንንስ አደራ ነው የሚበላው? ስንል ከሁሉ በፊት የሰው ልጅ ሁሉን ማወቅ የሚችለው እግዚአብሔር ምን ይለኛል ማለት አለበት። በእግዚአብሔር ፊት እራስን ከፍከፍ ማድረግም መጨረሻው ውርደት መሆኑንም መዘንጋት አያስፈልግም። እንዲሁም ደግሞ በኃላፊነት ቦታ ላይ ስንቀመጥ ሁሉም ነገር ያለ እግዚአብሔር ፈቃድ ስለማይሆን ኃላፊነትን በአግባቡ መወጣት ያስፈልጋል።

ሰው ከፈቃደ እግዚአብሔር ውጭ ሲሆን ሁልጊዜ እግዚአብሔርን እንዳሳዘነ ነው ማወቅ ያለበት። ምክንያቱም እግዚአብሔር አስቀድሞ ለሰው ልጅ በየዘመኑ በተለያየ መንገድ ህግጋቱን ይናግራልና።

ለአገልጋዮች ስልጣንን የሰጠ እርሱ ነው። ሲሰጥ ደግሞ እንዲሁ ዝም ብሎ ሳይሆን አስቀድሞ ነግሮ አደራ ብሎ ነው። ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ወደዚህ ዓለም መጥቶ የማዳኑን ስራ ከፈጸመ በኋላ በጥብርያዶስ ባህር አጠገብ ተገልጾ ለሐዋርያት አለቃ ለቅዱስ ጴጥሮስ እንዲህ ነው ያለው « የዮና ልጅ ስምዖን ሆይ፥ ከእነዚህ ይልቅ ትወደኛለህን? አለው። አዎን ጌታ ሆይ፥ እንድወድህ አንተ ታውቃለህ አለው። ግልገሎቼን አሰማራ አለው። ደግሞ ሁለተኛ። የዮና ልጅ ስምዖን ሆይ፥ ትወደኛለህን? አለው። አዎን ጌታ ሆይ፥ እንድወድህ አንተ ታውቃለህ አለው። ጠቦቶቼን ጠብቅ አለው። ሦስተኛ ጊዜ። የዮና ልጅ ስምዖን ሆይ፥ ትወደኛለህን? አለው። ሦስተኛ። ትወደኛለህን? ስላለው ጴጥሮስ አዘነና። ጌታ ሆይ፥ አንተ ሁሉን ታውቃለህ፤ እንድወድህ አንተ ታውቃለህ አለው። ኢየሱስም። በጎቼን አሰማራ። እውነት እውነት እልሃለሁ፥ አንተ ጐልማሳ ሳለህ ወገብህን በገዛ ራስህ ታጥቀህ ወደምትወደው ትሄድ ነበር፤ ነገር ግን በሸመገልህ ጊዜ እጆችህን ትዘረጋለህ፥ ሌላውም ያስታጥቅሃል ወደማትወደውም ይወስድሃል አለው። በምን ዓይነት ሞት እግዚአብሔርን ያከብር ዘንድ እንዳለው ሲያመለክት ይህን አለ። ይህንም ብሎ። ተከተለኝ አለው። ዮሐ 21፥15»

 ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ አስቀድሞ ይህን አደራ ከመስጠቱ በፊት በማቴ 16 እንደተጻፈው ለቅዱስ ጴጥሮስ  በሰማይና በምድር የጸና ስልጣንን ሰጥቶታል።  በምድር ያሰረው በሰማይ የታሰረ ፣ በምድር የፈታው በሰማይ የተፈታ እንደሆነ አረጋግጦለታል ስለዚህ  ስልጣኑ የተከበረ ነው። ምዕመናንም ይህን አክብረው አስከብረው ሊኖሩ ይገባቸዋል። ስልጣኑ የተሰጠው ስለካህኑ ብቃትና ጽድቅ ሳይሆን ለምዕመናኑ ኃጢአታቸውንና በደላቸውን እንዲያርቅላቸው ነው።

ሁሉም በየደረጃው የሚገኙ የቤተክርስቲያን አባቶችና ካህናት ይህ ትዕዛዝ ይመለከታቸዋል። ይህንን ሳያውቅ የገባ ካለ እራሱን ሊመረምር ይገባዋል። ይሉንታ ማጣት የሚመጣው ይህን የዘነጋን እንደሆነ ነው። ይህንን ትእዛዝ ስንዘነጋ ነው አደራ በላ የምንባለው። አደራ ብሎ የተናገረው ጌታ ደግሞ የሚገለጥበት ጊዜ አለ። ያንጊዜ ከያንዳንዱ የሚፈልገው ነገር አለ። በብዙ ለመሾም ጥቂት ይዞ መገኘት ያስፈልጋል። የዚያን ጊዜ ምን ይለኛል? ምን እመልሳለሁ? ማለት ይጠበቅብናል። እራሳችንን እንደ ሊባኖስ ዝግባ ከፍ ከፍ ብናደርግ  መዋረድ እንዳለ መዘንጋት የለበትም። 

ዛሬ በቤተክርስቲያናችን  የጠፋው አንዱ አቅምን አለማወቅ ነው። ዛሬ ላይ ለብዙዎቻችን የክህነት አገልግሎት እንደ ቀላል ነው የሚታየው፤ ነገር  ግን ለሰውልጅ ከተሰጠው ኃኃላፊነት ከባዱ የክህነት አገልግሎት ነው። የተቀበሉትን አደራ በአግባቡ ከተወጡ የሚከብሩበት፣ ካልሆነ ግን ዘለዓለማዊ ውርደት የሚከናነቡበት ነው።   ካባቶቻችን የወረስናት ቤተክርስቲያን እንደሌላው ባዶ ሳትሆን በስርዓት የታጠረች ሙሉ ነች። የሚጎድላት አንዳች ነገር የለም፣  ነገር ግን በህጓና በሥርዓቷ የማይጓዙ ሥርዓት አልበኞች በውስጧ ከገቡ ሰላም ታጣለች፣ በዚህም የተነሳ ይመስላል የሰላም መሰረት የሆነችው ቤተክርስቲያን ሰላም አጣች እየተባለ የሚነገረው።

በተለይ በውጭው ዓለም ላለችው ቤተክርስቲያን ትልቁ ፈተና በነጻነት ሰበብ የሚታየው ሥርዓተ አልበኝነት በጣም የሚያሳዝን ነው። እንኳን በክህነት በምዕመንነት እንኳን ቤተክርስቲያን በአግባቡ የማታውቃቸው ግለሰቦች  አንዳንድ ለሆዳቸው ያደሩ አገልጋዮችን በገንዘብ በመደለል የእግዚአብሔር ማደሪያ የሆነውን ታቦት ክብር በሚያቃልል መልኩ ቤተክርስቲያን ከፍተናል በማለት የዋሁን ህዝብ ሲያታልሉ ይታያሉ። የቤተክርስቲያኒቱ ሥርዓት አንድ ቤተክርስቲያን እንዴት እንደሚመሰረት፣ በማን እንደሚመሰረት፣ የህዝቡ ብዛት ምንያህል መሆን እንዳለበት፣ አገልጋዮችና ንዋየ ቅድሳት መሟላት እንዳለበት ይደነግጋል።

ሁላችንም እንደምናውቀው ቅድስት ቤተክርስቲያን በመርከብ ትመሰላለች መርከብ በውስጥም ሆነ በውጭ የሚያውከው ነገር ሲኖር ይናወጻል ማእበሉ ሲቆም በባህር ላይ ያለምንም ችግር ይጓዛል፣ ምክንያቱም  ነውጡን የፈጠረው መርከቡ ሳይሆን፣ በውጭ ያለው ማዕበልና በውስጥ ያሉት ተሳፋሪዎች በመሆናቸው ነው። ስለዚህ ዛሬ ቤተክርስቲያን ችግር አለባት የሚለውን ትተን በውስጥና በውጭ የሚያናውጿት ሰዎች ስለሆኑ ችግሩ እነሱጋ ነው ያለው።

አባቶቻችን ከፈጣሪያቸው የተሰጣቸውን አደራ ሞትን እንኳን ሳይፈሩ የዚህን ዓለም ተድላ ደስታ ንቀው ዛሬ ላለው ትውልድ ከነክብሯ አስረክበዋል፤ «ሰማይ ሩቅ አደራ ጥብቅ » እያሉ በእምነታቸው ጸንተው ኖረዋል።

ዛሬ የተከሰተው የቤተክርስቲያን ልጆች የሰላም እጦት ምክንያቱ ይሉኝ  ካለማለት ነው ። ጌታችን አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በመዋዕለ ስጋዌው ካስተማራቸው ትምህርቶች አንዱ « ሰዎች ማን ይሉኛል  ማቴ 16፥13» የሚል ነበር። ጌታችን ይህን የተናገረው ሰዎች  ስለሱ ምን እንደሚያስቡ ሳያውቅ ቀርቶ አይደለም  ነገር ግን ለእኛ አርአያና ምሳሌ ለመሆን  ነው የተናገረው።

እስቲ ዛሬ ላይ ሆነን አባቶቻችን ይህችን ቤተክርስቲያን እንዴት እንዳቆዩልን እናስብ፣ ብዙ ፈተና ደርሶባቸው ደማቸውን አፍሰው ፣ አጥንታቸውን ከስክሰው ነው ያወረሱን እኛ ዛሬ በተጋድሎ መጽናት ይቅርና አክብረን መያዝ እንኳን አቅቶን የአህዛብ መሳለቂያ ሆነናል።

ስንቶቻችንን ይሆን የቤተክርስቲያናችን ገበና  በአደባባይ መውጣት እንቅልፍ የነሳን ? ወይንም ደግሞ  በተለያየ ጎራ ተሰልፎ የራስን ክብር ከፍ ለማድረግ ሲባል የቤተክርስቲያንን ክብር ከሚያዋርደው ጋር በዝምድና  ወይንም በጥቅም ተደልለን የቤተክርስቲያን ጠላቶች የሆን ? ሆድ ይፈጀው ብሎ ማለፍ ሳይሻል አይቀርም

የሰው ዘር መጀመሪያ የነበረው አዳም አባታችንን እግዚአብሔር እንዲህ ብሎት ነበር  « እግዚአብሔር አምላክም ሰውን ወስዶ ያበጃትም ይጠብቃትም ዘንድ በዔድን ገነት አኖረው።  እግዚአብሔር አምላክም ሰውን እንዲህ ብሎ አዘዘው። ከገነት ዛፍ ሁሉ ትበላለህ፤ ነገር ግን መልካምንና ክፉን ከሚያስታውቀው ዛፍ አትብላ፤ ከእርሱ በበላህ ቀን ሞትን ትሞታለህና። ዘ2፥15 » እንግዲህ ከዚህ የምንማረው በገነት የተመሰለች ቤተክርስቲያንን እግዚአብሔር የሰጠን እንድንጠብቃት፣ እንድንከባከባት ነው እንጅ ስርዓቷን በፈለግነው መንገድ እንድንቀያይረው አይደለም። 

ዛሬ አንዲቱ ቤተክርስቲያን የኛ ፍላጎት በመብዛቱ የተነሳ የተለያየ መልክና ስም ሰጥተናት አንድነቷ አደጋ ላይ ሊወድቅ ችሏል። የማይሸራረፍና የማይገሰስ ህግና ስርዓት ያላት ቤተክርስቲያን ሰዎች እንደፍላጎታቸው ህግ እያረቀቁ የራሳቸውን ስጋዊ ኑሮ የሚያዳብሩባት ሆናለች። እነዚህን አካላት እውነተኛ የቤተክርስቲያን ልጆች የሆንን ሁላችን በአንድነት ሆነን ያለፈው ዘመን ይበቃችኋል ልንላቸው ይገባል። 

ቤተክርስቲያናችን እዚህ ደረጃ ላይ ለመድረሷ ተጠያቂዎች ሁላችንም ነን። አንዱ በአንዱ ሊያሳብብ አይችልም። ካህናቱም ኃላፊነታቸውን ባለመወጣታቸው፣ ምዕመናኑም ድርሻቸውን ባለመወጣታቸው በእግዚአብሔር ዘንድ ተጠያቂዎች ናቸው። ስለዚህ ሁላቸንም ስላለፈው በደል ንስሃ ገብተን ለወደፊቱም ህጉንና ስርዓቱን ጠብቀን ለመኖር ዛሬ መወሰን አለብን  

1 comment: