Friday, March 29, 2013

ዲያብሎስን ተቃወሙት ከናንተም ይሸሻል ያዕ 4፥7


ይህ ወቅት በቤተክርስቲያናችን በዓለም ውስጥ ላሉ ሁሉ ፍጥረታት ሰላምና ፍቅርን በረከትን እንዲያገኙ ወደ ፈጣሪያችን በጾም በጸሎት ተወስነን ልመና የምናቀርብበት ጊዜ ነው። ታዲያ በዚህ ጊዜ የሰው ልጅ ሁሉ ጠላት የሆነው ሰይጣን ዲያብሎስ በተለያየ መንገድ ከዓላማችን ወደ ኋላ እንድንል የማይቀይሰው መንገድ አይኖርም። ስለዚህ ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ በመልእክቱ መጋደላችን ከደምና ከሥጋ ጋር አይደለምና፥ ከአለቆችና ከሥልጣናት ጋር ከዚህም ከጨለማ ዓለም ገዦች ጋር በሰማያዊም ስፍራ ካለ ከክፋት መንፈሳውያን ሠራዊት ጋር ነው እንጂ ኤፌ 6፥12 ” እንዳለው በክርስትና ህይዎት ስንኖር ብዙ ልዩ ልዩ ዓይነት ፈተና ሊገጥመን ይችላል። ይህን ፈተና የምናልፍበት ጥበብና ማስተዋል ከሌለን ጠልፎ ሊያስቀረን ይችላል።

በቤተክርስቲያናችን ስርዓት መሰረት በዓመት ውስጥ በጾም በጸሎት ተወስነን የምንቆይባቸው ሰባት የአዋጅ አጽዋማት አሉ። በተለይ አሁን የያዝነው የጌታችንና የአምላካችን የመድኃኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ጾም /አቢይ ጾም/ ተብሎ ይታወቃል ። አቢይ የተባለበትም ምክንያት የሁሉ ጌታ የሁሉ ፈጣሪ እኛን ለማስተማር /አብነት ለመሆን/ የጾመው ጾም ስለሆነ ነው።
እንዲሁም ዲያብሎስ የሰውን ልጆች ለማጥመድ የሚጠቀምባቸውን አቢይ የኃጢአት መንገዶች ድል ስላደረገልን ነው።እነዚህም ትእቢትስስት እና ገንዘብን መውደድ ናቸው። የሰው ልጅ ሁልጊዜ በዲያቢሎስ ወጥመድ የሚያዘው በእነዚህ መንገዶች ነው።
ትእቢት አስቀድሞ ሰይጣን ዲያቢሎስ በፈጣሪው ላይ ታብዮ ወደ ምድረ ፋይድ የወረደበት የኃጢአት መንገድ ነው። ዛሬም ያንን ክፉ ስራውን በሰው ልጆች ላይ ለመዝራት ዲያብሎስ በየእለቱ ወጥመዱን ያጠምዳል። ስለዚህ በጾም በጸሎት ተወስነን ከፈጣሪያችን ጋር መገናኘት ከቻልን ይህንን የዲያብሎስ ክፉ ስራ የምንሰብርበትን የትህትና ኃይል እንጎናጸፋለን ማለት ነው።
ስስት ይህም ከዲያቢሎስ ስራዎች አንዱ ሲሆን በጾምና በጸሎት ድል ልንነሳው የምንችለው ክፉ መንፈስ ነው። የምንሰጠው ሳናጣ ነገር ግን የክፋትና የተንኮል ምንጭ የሆነው ዲያብሎስ እያለን እንደሌለን አስመስሎ ባለን ነገር መልካም ስራ እንዳንሰራበት ያደርገናል። ለዚህም ታዲያ የጾምና የጸሎት ጥቅም ከፍተኛ ነው። ወደ እግዚአብሔር ስንቀርብ ያለን ነገር ይበቃኛል ማለትን እንማራለን።
ገንዘብን መውደድ ይህ ትልቁ የሰውን ልጆች ከእግዚአብሔር መንግስት የሚያርቅ የዲያብሎስ ክፉ ስራ ነው። ዛሬ በዓለማችን ላይ ብዙ ኃጢአት የሚሰራው ለገንዘብ ተብሎ ነው። ብዙዎች ገንዘብ ካለ በሰማይ መንገድ አለ በማለት እግዚአብሔርን እረስተው የዲያቢሎስ ጉዳይ ፈጻሚዎች ሆነዋል።
በገንዘብ ፍርድ ይጣመማል። ገንዘብ የስልጣን ማግኛ ዘዴ ሆኗል። በገንዘብ ምክንያት ብዙ ንጹሃን ህይዎታቸውን ያጣሉ። በዓለማችን ላይ ከምንሰማቸው እጅግ ዘግናኝ ነገሮች ዋናው በገንዘብ የሚፈጸም ወንጀል ነው። የሰዎችን አካላት ለገንዘብ ብለው ነፍስ በማጥፋት ለገበያ የሚያቀርቡ የሰው ፍጥረቶችን እያየን ነው። ይህን ሁሉ ወንጀል እንድንሰራ የሚያደርገን ገንዘብን መውደድ ነው።
ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በቅዱስ ወንጌል ”ለሁለት ጌቶች መገዛት የሚቻለው ማንም የለም፤ ወይም አንዱን ይጠላል ሁለተኛውንም ይወዳል፤ ወይም ወደአንዱ ይጠጋል ሁለተኛውንም ይንቃል፤ ለእግዚአብሔርና ለገንዘብ መገዛት አትችሉም” ብሎ አስተምሯል ማቴ 6፥24
ይሁን እንጅ የገንዘብ ፍቅር ህሊናን እስከማሳወር ይደርሳልና ለሐዋርያነት ከተመረጡት እንኳን ሳይቀር እንደነ ይሁዳ አይነቶቹን ጠልፎ ወደኋላ እንዳስቀራቸው እንረዳለን።
ከዘመናት በፊት ለብዙ ቅዱሳን መሸሸጊያ የሆነችውና በአንድነቷ እና በሰላሟ ለዓለም ምሳሌ የነበረችው ቤተክርስቲያናችን ዛሬ ላይ ለአህዛብና ለመናፍቃን መሳለቂያ የሆነችው ገንዘብን የሚወዱ ልጆችን በማፍራቷ ነው። ገንዘብን የሚወድ ሰው የእናቱንም ገመና መሸፈን እንኳን አይችልምና።
ዲያብሎስን መቃወም ማለት ሁላችንም እንደምንረዳው በክፉ ስራው አለመተባበር ማለት ነው። በስራው ካልተባበርነው ከእኛ እንደሚሸሽ ተነግሯል። ስለዚህ ወደኛ እንዲቀርብና ከክፉ ስራው እንድንተባበር የሚያደርገን በእኛ ፈቃደኝነት ነው ማለት ነው። ለዚህ ደግሞ መድኃኒቱ ሐዋርያው ቅዱስ ያእቆብ እንደነገረን ወደ እግዚአብሔር መቅረብ ነው። ወደ እግዚአብሔር ከቀረብን እግዚአብሔርም ወደኛ ይቀርባል። እርሱ ከእኛ ጋር ከሆነ ደግሞ ሁልጊዜ አሸናፊዎች ነን።
አንዳንዶች እግዚአብሔርን እናመልካለን የሚሉ ነገር ግን የዲያቢሎስን ስራ ሲሰሩ ይታያሉ። ከላይ ለመግለጽ እንደሞከርኩት ከዲያብሎስ ጋር በስራ ሲተባበሩ ይታያሉ። ቅዱስ ጳውሎስ የአምልኮት መልክ አላቸው ኃይሉን ግን ክደዋል 2ኛ ጢሞ 3፥5 እንዳለው በስራ የማይተረጎም አምልኮት የእግዚአብሔርን መንግስት አያሰጥም።
ፍቅርን ገንዘብ ሳናደርግ በጥላቻና በክርክር እየኖርን ዲያቢሎስን ተቃውሚያለሁ ማለት አይቻልም። አንዱ የሌላውን ውድቀት እየተመኘ ከእግዚአብሔር ጋር እየኖርኩ ነው ቢል እራሱን ያታልላል። ለዚህ ሁሉ መፍትሔው የዲያብሎስን መምጫ መንገዶች ጠንቅቆ መረዳት ነው።
ቅዱስ መጽሐፍ እንደሚነግረን ዲያብሎስ የሰውን ልጆች ከእግዚአብሔር መንግስት የሚለይባቸው መንገዶች ብዙ ናቸው። በመጽሐፈ ምሳሌ 6፥16 ላይ “ እግዚአብሔር የሚጠላቸው ስድስት ነገሮች ናቸው፥ ሰባትንም ነፍሱ አጥብቃ ትጸየፈዋለች ትዕቢተኛ ዓይን፥ ሐሰተኛ ምላስ፥ ንጹሕን ደም የምታፈስስ እጅ፥ክፉ አሳብን የሚያበቅል ልብ፥ ወደ ክፉ የምትሮጥ እግር፥በሐሰት የሚናገር ሐሰተኛ ምስክር በወንድማማች መካከልም ጠብን የሚዘራ“ የሚል ቃል ተጽፏል። ይህም ማለት ዲያቢሎስን መቃወም ሳንችል ስንቀር በስሜት ህዋሳቶቻችን እኛ ሳንሆን የምናዘው እርሱ ይሆናል ማለት ነው። ለዚያ ነው ቅዱስ ጳውሎስ ”እንግዲህ ለምኞቱ እንድትታዘዙ በሚሞት ሥጋችሁ ኃጢአት አይንገሥ፤ ብልቶቻችሁንም የዓመፃ የጦር ዕቃ አድርጋችሁ ለኃጢአት አታቅርቡ፥ ነገር ግን ከሙታን ተለይታችሁ በሕይወትእንደምትኖሩ ራሳችሁን ለእግዚአብሔር አቅርቡ፥ ብልቶቻችሁንም የጽድቅ የጦር ዕቃ አድርጋችሁ ለእግዚአብሔር አቅርቡ” ሮሜ 6፥12 ብሎ የጻፈው።
የዲያቢሎስን ፈቃድ ለመፈጸም ከምንገፋፋባቸው መንገዶች አንዱ ከስጋዊ ምግብ እርቀን በጾምና በጸሎት ተወስነን የምንቆይባቸው ጊዜያት አለመኖራቸው ነው። የሰው ልጅ ደግሞ በስጋዊ ምግብ ብቻ መኖር እንደማይችል  ተጽፏል።  ”ሰው ከእግዚአብሔር አፍ በሚወጣ ቃል ሁሉ እንጂ በእንጀራ ብቻ አይኖርም” ማቴ 4፥4 ስለዚህ በህይዎት ለመኖር የነፍስና የስጋ ተዋህዶ መኖር አስፈላጊ እንደመሆኑ መጠን ለስጋ ምግብ እንደምንጨነቀው ሁሉ የነፍስ ምግብንም ለማግኘት ሁልጊዜ የተጋን መሆን ይጠበቅብናል።
ማንኛውም የኦርቶዶክሳዊ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ልጅ የሆነ ሁሉ የሥጋ ስራ ተብለው ከተገለጹት ከዲያቢሎስ ፈቃዳት እርቆ መኖር እንዳለበት የእግዚአብሔር ቃል ይነግረናል። የሁላችንም ዓላማ በዚህ ዓለም የእግዚአብሔርን ፈቃድ ፈጽመን በማታልፈው ዓለም በመንግስተ ሰማይ እንደቅዱሳን መላእክት እግዚአብሔርን እያመሰገኑ መኖር ነው። ስለዚህ በዚህ በጾሙ ወቅትም ሆነ ሌላ ጊዜ ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ እንደጻፈው የሥጋ ሥራ ከተባሉት ዝሙት፥ ርኵሰት፥መዳራት፥ ጣዖትን ማምለክ፥ ምዋርት፥ ጥል፥ ክርክር፥ ቅንዓት፥ ቁጣ፥ አድመኛነት፥መለያየት፥ መናፍቅነት፥ ምቀኝነት፥ መግደል፥ ስካር፥ ዘፋኝነት፥ ይህንም ከሚመሳስሉ ከዲያብሎስ መንገዶች እርቀን መኖር አለብን። ምክንያቱም  እንደዚህ ያሉትን የሚያደርጉ የእግዚአብሔርን መንግሥት አይወርሱም። ይለናልና  ቃሉ፣ የእግዚአብሔርን መንግስት መውረስ ካልቻልን ደግሞ ድካማችን ሁሉ ከንቱ ሆነ ማለት ነው። 
እንግዲህ ሐዋርያው ቅዱስ ጴጥሮስ  ባላጋራችሁ ዲያብሎስ የሚውጠውን ፈልጎ እንደሚያገሣ አንበሳ ይዞራልና፤ 1ኛ ጴጥ 5፥8 እንዳለው ከዓላማችን ወደ ኋላ እንዳያስቀረን በጾማችን ላይ ጸሎትን፣ ምጽዋትን፣ስግደትን፣ ይቅርታን ጨምረን ይዘን ልንጓዝ ይገባል። የሁሉ ማሰሪያ ደግሞ በንስሃ ታድሶ ቅዱስ ስጋውንና ክቡር ደሙን ተቀብሎ መክበር ነውና ይህን ገንዘብ ልናደርግ ይገባል። ይህ ከሆነ እውነትም ዲያብሎስን ተቃውመናል ማለት ነው። በመጨረሻም ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ ለኤፌሶን ክስርቲያኖች በጻፈው መልእክቱ በም 6 ቁ 10 ላይ ያለውን መንፈሳዊ መልእክት ልጠቁምና ላብቃ።  በቀረውስ በጌታና በኃይሉ ችሎት የበረታችሁ ሁኑ።የዲያብሎስን ሽንገላ ትቃወሙ ዘንድ እንዲቻላችሁ የእግዚአብሔርን ዕቃ ጦር ሁሉ ልበሱ።መጋደላችን ከደምና ከሥጋ ጋር አይደለምና፥ ከአለቆችና ከሥልጣናት ጋር ከዚህም ከጨለማ ዓለም ገዦች ጋር በሰማያዊም ስፍራ ካለ ከክፋት መንፈሳውያን ሠራዊት ጋር ነው እንጂ።ስለዚህ በክፉው ቀን ለመቃወም፥ ሁሉንም ፈጽማችሁ ለመቆም እንድትችሉ የእግዚአብሔርን ዕቃ ጦር ሁሉ አንሡ።እንግዲህ ወገባችሁን በእውነት ታጥቃችሁ፥ የጽድቅንም ጥሩር ለብሳችሁ፥ በሰላም ወንጌልም በመዘጋጀት እግሮቻችሁ ተጫምተው ቁሙ፤በሁሉም ላይ ጨምራችሁ የሚንበለበሉትን የክፉውን ፍላጻዎች ሁሉ ልታጠፉ የምትችሉበትን የእምነትን ጋሻ አንሡ፤የመዳንንም ራስ ቁር የመንፈስንም ሰይፍ ያዙ እርሱም የእግዚአብሔር ቃል ነው።በጸሎትና በልመናም ሁሉ ዘወትር በመንፈስ ጸልዩ፤ በዚህም አሳብ ስለ ቅዱሳን ሁሉ እየለመናችሁ በመጽናት ሁሉ ትጉ፤
የበረከት ጾም ይሁንልን
 
 
 

1 comment:

  1. ሚስተር ቤንጃሚን የኢሜል ዝርዝሮችን እነሆ ፣ Lfdsloans@outlook.com ፡፡ / ወይም ደግሞ ንግዴን ለመጀመር በ 90,000.00 ዩሮ ብድር የረዳኝ WhatsApp + 1-989-394-3740 እና እኔ በጣም አመስጋኝ ነኝ ፣ እዚህ አንድ ነጠላ እናት ነገሮች እንዳላደረጉ መንገድ ለመፍጠር እየሞከርኩ ነው ፡፡ ከእኔ ጋር ቀላል ይሁኑ ግን ንግዴ እየጠነከረ ሲመጣ እና እያሰፋ ሲሄድ እያየሁ በሚስተር ሚስተር እርዳታ ፊቴ ላይ ፈገግታ አሳየኝ ፡፡ የገንዘብ ድጋፍን መፈለግ ወይም በዚያ ንግድ ውስጥ መከራን ማለፍ ወይም የመነሻ የንግድ ሥራ ፕሮጀክት መጀመር መፈለግ ይህንን ማየት እና ከችግራቸው ለመውጣት ተስፋ ሊኖረው ይችላል ... እናመሰግናለን ፡፡

    ReplyDelete