Monday, April 2, 2018

'ነጻነት ከመንግስት ለህዝብ የሚበረከት ስጦታ አይደለም' (ዶ/ር አቢይ አህመድ)

ከእግዚአብሔር ለሰው ልጆች ከተሰጡት ጸጋዎች አንዱ የንግግር ስጦታ ሲሆን በተለይ ለመሪዎች አስፈላጊ መሆኑ አይካድም። ብዙ የእግዚአብሔር ሰዎች ለሰውም ለእግዚአብሔርም የሚመች ንግግር ከአንደበታቸው በመውጣቱ የተጣመመውን ማቅናት ችለዋል። በተሰጠን ጸጋ በአግባቡ ከተጠቀምንበት ዋጋ ይገኝበታል። ብዙዎች ግን ይህን ታላቅ ጸጋ ለክፉ ተግባር ሲጠቀሙበት አይተናል። 

ዶ/ር አቢይን በሚዲያ ስንተዋወቃቸው  ቃል ይገድላል ቃል ይተክላል ብለውን ነበር። በዚህም ምክንያት አብዛኛው የኢትዮጵያ ህዝብ እንዲህ ዓይነት መሪ በሰጠን እያለ ሲመኝ ሰንብቷል። ምኞቱም አልቀረ ቃሉን የተናገሩት መሪ ሆነዋል። በመጀመሪያ የፓርላማ ንግግራቸውም ያንኑ የንግግር ጸጋቸውን ተጠቅመው ተስፋ እርቆት የነበረውን የኢትዮጵያ ህዝብ ተስፋው እንዲለመልም አድርገዋል።


አዲሱን መሪ በደስታ ስንቀበል ያለፉትን በመውቀስና በመርገም መሆን እንደሌለበት ለኢትዮጵያውያን ማስረዳት ዘበት ነው የሚሆነው። ስለዚህ መሪው አዲስ ሃሳብ ይዞ ሲነሳ ጉዞውን ሊያሳካ የሚችለው ህዝብን ይዞ ነውና እና ያለፉትን በመውቀስ፣ እርስበርሳችን በመለያየት፣ አንዱ በአንዱ ላይ በመፍረድ ወደ ኋላ የምንመለስ ከሆነ ሀገር ሊለወጥ አይችልም። ከአንድ ሰው የሚጠበቀው ውሱን ነገር ነው። ህገር ደግሞ የብዙዎች ነች።  ስለዚህ ምናልባት መሪው የመልካም ተግባር አቅጣጫ ቀያሽ ሊሆን ይችላል እንጅ ሁሉን ተግባሪ መሆን አይችልም። እስከአሁንም ኢትዮጵያውያን መልካም መሪ እንጅ ያጡት ተፋቅሮ ለመኖር፣ ሰርቶ ሀገር ለማሳደግ፣ የህገርን ዳር ድንበር ለማስከበር  አስተማሪ አያሻቸውም። ኢትዮጵያውያንን ለመግዛት ኃይል ሳይሆን ፍቅር  ነው የሚያስፈልገው። ይህን ደግሞ ዶ/ር አቢይ በደንብ የተረዱ ይመስለኛል። 

በሳል ሰው ማለት ተፈጥሮን መመልከት የሚችልበት ዓይን ሲኖረው ነው። ባለፉት ጊዜያት የነበረው ችግር መነሻውም መድረሻውም ይህ እንደነበር ይታወቃል። ህዝቡ ሲል የነበረው አዲስ ነጻነት ስጡን ሳይሆን የቀማችሁንን ነጻነት መልሱልን ነበር ጥያቄው። የራሱን መብትና ነጻነት ያልተረዳ ሰው ለሌላው የሚሰጠው አይኖረውም። ካለፉት መሪዎቻችን የተረዳነው በውስጣቸው ባለው ጥላቻ ምክንያት ነጻነትን ለራሳቸውም ነፍገው እንደኖሩ ነው።

ነጻነት ከእግዚአብሔር ለሰው ልጆች የተሰጠ መሆኑን የሚያምን ሰው ለሰው ሁሉ ክብር ይኖረዋል ብየ አምናለሁ። በመሆኑም አዲሱ መሪያችን ለራስዎትና ለህዝቡ ጥንቃቄ በማድረግ መልካም ሰርተው ለልጆችዎ ኩራት ለዎገንዎ መመኪያ እንዲሆኑ በህዝብ ፊት ያከበሩት አምላክ ሥራዎን ያቃናልዎ ። 

No comments:

Post a Comment