የጥያቄዎ መልስ

                         ከመናፍቃን የማታለያ መንገዶች እንዴት ማምለጥ እንችላለን?


በቅዱስ ወንጌል እንደተገለጸው ሰይጣን የሰውን ልጆች ለማሳት በተለያየ መንገድ እራሱን እየቀየረ ይመጣል እንጅ ማንነቱን እየነገረ ሰዎችን አያስትም። የብዙ ሰዎች ችግር የሰይጣንን መምጫ  መንገዶች አለማወቃቸው ነው። ከዚህ በታች ያሉትን የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅሶች እንመልከት።

ፈታኝም ቀርቦ። የእግዚአብሔር ልጅ ከሆንህ፥ እነዚህ ድንጋዮች እንጀራ እንዲሆኑ በል አለው።እርሱም መልሶ፦ ሰው ከእግዚአብሔር አፍ በሚወጣ ቃል ሁሉ እንጂ በእንጀራ ብቻ አይኖርም ተብሎ ተጽፎአል አለው። ከዚህ በኋላ ዲያቢሎስ ወደ ቅድስት ከተማ ወሰደውና እርሱን በመቅደስ ጫፍ ላይ አቁሞ። መላእክቱን ስለ አንተ ያዝልሃል እግርህንም በድንጋይ ከቶ እንዳትሰናከል በእጃቸው ያነሡሃል ተብሎ ተጽፎአልና የእግዚአብሔር ልጅስ ከሆንህ፥ ወደ ታች ራስህን ወርውር አለው። ኢየሱስም፦ ጌታን አምላክህን አትፈታተነው ተብሎ ደግሞ ተጽፎአል አለው። ደግሞ ዲያቢሎስ እጅግ ረጅም ወደ ሆነ ተራራ ወሰደው፥ የዓለምንም መንግሥታት ሁሉ ክብራቸውንም አሳይቶ።ወድቀህ ብትሰግድልኝ ይህን ሁሉ እሰጥሃለሁ አለው።ያን ጊዜ ኢየሱስ፦ ሂድ፥ አንተ ሰይጣን ለጌታህ ለአምላክህ ስገድ እርሱንም ብቻ አምልክ ተብሎ ተጽፎአልና አለው። ያን ጊዜ ዲያቢሎስ ተወው ማቴ 4፥3 ከዚህ የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል የምንረዳው ዲያቢሎስ የሰውን ልጆች ከሚያጠምድባቸው ዋና ዋና መንገዶች የኃጢአት ቁንጮዎች የተባሉትን ሶስቱን ነው። እነሱም ትዕቢት፣ ስስት፣ ገንዘብን መውደድ ናቸው። የሰው ልጅ ከነዚህ ከሶስቱ እራሱን መጠበቅ ከቻለ ዲያቢሎስን ማሸነፍ ይችላል። ይህም ማለት በትዕቢት የሚመጣብንን በትህትና በስስት የሚመጣብንን በልግስና በገንዘብ ፍቅር ሲመጣብን ዓለምን በመናቅ ድል ማድረግ ማለት ነው።

መናፍቃን በትዕቢት የተሞሉ ናቸው። እግዚአብሔር ያከበራቸውን ቅዱሳንን መሳደብ የመጀመሪያ ተግባራቸው ነው። እነሱ ራሳቸውን ለእግዚአብሔር የቅርብ ባለሟል እንደሆኑ አድርገው ይቆጥራሉ። ሌላውን ደግሞ በእግዚአብሔር የተጠላ እና የረከሰ መሆኑን በእርግጠኝነት ይናገራሉ። እነሱ ብቻ እንደ ዳኑ ሌላው ዓለም የተኮነነ እንደሆነ መናገር ባህላቸው ነው። ,, በድፍረትና በትዕቢት በመናቅም በጻድቅ ላይ የሚናገሩ የሽንገላ ከንፈሮች ድዳ ይሁኑ,, መዝ 31፥18 የሚለውን የመጽሐፍ ቅዱስ ቃል ዘንግተው ጻድቃንን መሳደብ የእውቀታቸው መለኪያ ነው። ይህ ባህርይ የትዕቢት አባት የዲያቢሎስ ነው።   እናንተ ከአባታችሁ ከዲያብሎስ ናችሁ የአባታችሁንም ምኞት ልታደርጉ ትወዳላችሁ። እርሱ ከመጀመሪያ ነፍሰ ገዳይ ነበረ፤ እውነትም በእርሱ ስለ ሌለ በእውነት አልቆመም። ሐሰትን ሲናገር ከራሱ ይናገራል፥ ሐሰተኛ የሐሰትም አባት ነውና። ,,ዮሐ 8፥44  ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስም  ,, እግዚአብሔር ለእያንዳንዱ የእምነትን መጠን እንዳካፈለው፥ እንደ ባለ አእምሮ እንዲያስብ እንጂ ማሰብ ከሚገባው አልፎ በትዕቢት እንዳያስብ በመካከላችሁ ላለው ለእያንዳንዱ በተሰጠኝ ጸጋ እናገራለሁ,,  ሮሜ 12፥3 ብሎ እንደጻፈው ለሁሉም የተሰጠው የእምነት መጠን አለ። በትዕቢት አንዱ አንዱን ሊንቀው አይገባም። ሐዋርያው በዚሁ ምዕራፍ ላይ ,, እርስ በርሳችሁ በአንድ አሳብ ተስማሙ፤ የትዕቢትን ነገር አታስቡ፥ ነገር ግን የትሕትናን ነገር ለመሥራት ትጉ። ልባሞች የሆናችሁ አይምሰላችሁ።ለማንም ስለ ክፉ ፈንታ ክፉን አትመልሱ፤ በሰው ሁሉ ፊት መልካም የሆነውን አስቡ። ቢቻላችሁስ በእናንተ በኩል ከሰው ሁሉ ጋር በሰላም ኑሩ ሮሜ 12፥16 ይላል ።

 መናፍቃን ሌላው ችግራቸው መጽሐፍ ቅዱስ ከሚነግረን የተለየ ትምህርት ማስተማራቸው ነው። ለዚህም ቅዱስ ጳውሎስ ለጢሞቴዎስ እንዲህ ብሎ ጽፎለታል። ,,እነዚህን አስተምርና ምከር። ማንም ልዩ ትምህርት የሚያስተምር ከጌታችንም ከኢየሱስ ክርስቶስ በሆነው ጤናማ ቃልና እግዚአብሔርን ለመምሰል በሚስማማ ትምህርት የማይጠጋ ቢሆን፥በትዕቢት ተነፍቶአል አንዳችም አያውቅም፥ ነገር ግን ምርመራን በቃልም መዋጋትን እንደ በሽተኛ ይናፍቃል፤ ከእነዚህም ቅንዓትና ክርክር ስድብም ክፉ አሳብም እርስ በርስ መናደድም ይወጣሉ፥ አእምሮአቸውም በጠፋባቸው እውነትንም በተቀሙ፥ እግዚአብሔርን መምሰል ማትረፊያ የሚሆን በመሰላቸው ሰዎች ይገኛሉ። እንደነዚህ ካሉት ራቅ 1ኛ ጢሞ 6፥3 ጌታ በወንጌል እንደነገረን በመጨረሻው ዘመን የበግ ለምድ ለብሰው ይመጣሉ። በውስጣቸው ግን ነጣቂዎችና ተኩላዎች ናቸው ከነዚህ ተጠንቀቁ እንዳለው ዛሬ ላይ ይህ ትንቢት ምንም ሳይቀየር በትክክል እየደረሰ ነው። በመጽሐፍ ቅዱስ ለሰው ልጅ የተሰጡትን የመዳኛ መንገዶች በማጥላላት ከእግዚአብሔር መንግስት በማስወጣት ላይ ይገኛሉ። መጾም ፣ መስገድ፣ መጠመቅ፣ ስጋውንና ደሙን መቀበልና የመሳሰሉት በእነሱ ዘንድ የተናቁ ናቸው። ይህን የሚያደርገውም ይሰደባል። ይህ ዲያቢሎስ የሰውን ልጆች ከእግዚአብሔር መንግስት የሚያርቅበት መንገድ ነው።

የመናፍቃን ሌላው የማታለያ ዘዴ ያልነበሩትን ነበርን፣ ያልሆኑትን ሆንን ማለት ነው። ለማሳመኛ የሚጠቀሙባቸው መንገዶች  ዲያቆን ነበርኩ ዘማሪ ነበርኩ በቆሎ ትምህርት ቤት ተምሬያለሁ ልዩ ልዩ ገዳማትን በመጥቀስ ሄደው እንዳገለገሉ ነገር ግን ባለማወቅ እንዳረጉት እና አሁን እውነተኛውን መንገድ እንደያዙ አድርገው መናገር የተለመደ የማታለያ ስልታቸው ነው። የሚገርመው መናፍቅ የተባለ በሙሉ ቋንቋው ተመሳሳይ ነው። ነገር ግን ጠበቅ አድርጎ የሚጠይቅ ከገጠማቸው ርዕሳቸውን ቀይረው ይከራከራሉ፤ ወይም ከአካባቢው ይጠፋሉ። በወንጌሉ ላይ የበግ ለምድ ለብሰው ይመጣሉ ያለው ይህንን ነው። ስለ ሃይማኖቱ ጠለቅ ያለ ግንዛቤ የሌለው ሰው ያምናቸውና ይሰናከላል። ዋናው አላማቸው ሰውን በጥርጥር ከሃይማኖት ማስወጣት ነው። ሰው በጥርጥር ልቦናው ከተከፈለ ለሰይጣን እጅግ ቅርብ ይሆናል፤ እስቲ ልሞክረው ይባልና ወደ አዳራሻቸው መሄድ ይጀመራል እዚያም የሚዘራው የዲያቢሎስ መንፈስ በውስጡ ይሰርጽና ምናለበት ማለት ይጀምራል፤ ከዚያ በኋላ በዙሪያው በሚመደቡ አባላት ከፍተኛ እንክብካቤ ይደረግለታል። እነዚህ አባላት ጥርጥሩ ወደ ማመን እስኪደርስ ድረስ ሰማያዊ መልአክ መስለው እንዲቀርቡት ይደረጋል። በዚህ የተነሳ የሚያመልከውን እግዚአብሔርን ሳይሆን የነሱን በጎነት ማውራት ይጀምራል። ከዚያ በኋላ እራሱ ሰባኪ ይሆናል።   

ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ እንደተናገረው ያለንበት ዘመን እጅግ የሚያስጨንቅ ነው። ,,ነገር ግን በመጨረሻው ቀን የሚያስጨንቅ ዘመን እንዲመጣ ይህን እወቅ።ሰዎች ራሳቸውን የሚወዱ ይሆናሉና፥ ገንዘብን የሚወዱ፥ ትምክህተኞች፥ ትዕቢተኞች፥ ተሳዳቢዎች፥ ለወላጆቻቸው የማይታዘዙ፥ የማያመሰግኑ፥ቅድስና የሌላቸው፥ ፍቅር የሌላቸው፥ ዕርቅን የማይሰሙ፥ ሐሜተኞች፥ ራሳቸውን የማይገዙ፥ ጨካኞች፥ መልካም የሆነውን የማይወዱ፥ከዳተኞች፥ ችኩሎች፥ በትዕቢት የተነፉ፥ ከእግዚአብሔር ይልቅ ተድላን የሚወዱ ይሆናሉ፤የአምልኮት መልክ አላቸው ኃይሉን ግን ክደዋል፤ ከእነዚህ ደግሞ ራቅ።ወደ ቤቶች ሾልከው እየገቡ፥ ኃጢአታቸው የተከመረባቸውን በልዩ ልዩ ምኞትንም የሚወሰዱትን ሁልጊዜም እየተማሩ እውነትን ወደ ማወቅ ሊደርሱ ከቶ የማይችሉትን ሞኞችን ሴቶች የሚማርኩ፥ ከእነዚህ ዘንድ ናቸውና።ኢያኔስና ኢያንበሬስም ሙሴን እንደ ተቃወሙት፥ እንዲሁ እነዚህ ደግሞ አእምሮአቸው የጠፋባቸው ስለ እምነትም የተጣሉ ሰዎች ሆነው፥ እውነትን ይቃወማሉ። 2ኛ ጢሞ 3፥1      ይቀጥላል