ያለንበት ዘመን በጎ ነገር የማይፈልቅበት እንዲሁም ቀድሞ የነበረው መልካም
ነገር እንደ ኋላቀርነት የሚቆጠርበት ጊዜ ከመሆኑ አንጻር በጥቂቱም ቢሆን በበጎ ሃሳብ ተነሳስቶ ለበጎ ዓላማ በህብረት ለመቆም መጣር
በራሱ መስዋዕትነት ነው።
መቸም በሁሉም የሰው ልጆች ዘንድ መልካም ስራ ሰርቶ እና መልካም ስም አትርፎ
ማለፍ ይፈለጋል። ነገር ግን የዓለምን ፈተና አሸንፎ መልካም ቦታ ላይ ቆሞ መገኘት እንዴት ይቻላል? ጌታ በወንጌል “ ያለ
እኔ ምንም
ልታደርጉ አትችሉም ” ዮሐ 15፥5 እንዳለው ያለ እግዚአብሔር ፈቃድ አንዳች ነገር ልናደርግ አንችልምና መንገዳችንን ለእግዚአብሔር
አደራ መስጠት ይገባናል መዝ 37፥5
ለጽሑፌ መነሻ የሆነኝ ባለፈው ወር የ2005 ዓ/ም ማብቂያ ነሐሴ መገባደጃው
ላይ የተካሄደው የጻድቁ የአባታችን የአቡነ ተክለሃይማኖት የመንፈስ
ቅዱስ ልጆች በዋሽንግተ ዲሲ ያደረጉት መንፈሳዊ ጉባኤ ነው። በህብረት ሆነን በጎ ነገር እንስራ በሚል ከተለያዩ እስቴቶች ተሰባስበው
መልካም ስራ ለመስራት ሲተባበሩ ላያቸው መንፈሳዊ ቅናት ያሳድር ነበር። በዚህ ዘመንም እንዲህ አይነት አለ እንዴ ?ያሉም አልጠፉ
ነበር ።
በተለይም ደግሞ በዋሽንግተን ዲሲና አካባቢዋ የሚኖሩ ጥቂት የሚሆኑ የጻድቁ
ልጆች ከተለያየ ቦታ የመጡ እንግዶችን ለማስተናገድ ያደርጉት የበረው ሽርጉድ እውነትም የተክልየ ልጆች ያስብላቸው ነበር።
በዋሽንግተን ዲሲ የርእሰ አድባራት ቅ/ማርያም ቤተክርስቲያን ቄሰ ገበዝ የሆኑት
መጋቤ ሃብታት ኃይሉ ዘለቀ ጌታ በወንጌል እንደተናገረው “ ጻድቅንም በጻድቅ ስም
የሚቀበል የጻድቁን ዋጋ
ይወስዳል ማቴ 10፥41 “ እንዳለው ባለቤታቸውንና የመንፈስ ቅዱስ ልጆቻቸውን በማስተባበር
ለሶስት ቀናት እንግዶችንና የበአሉን ታዳሚዎች ያለመሰልቸት በማስተናገድ ሁላችንም በጻድቁ ስም የቀረበውን በረከት ቀምሰን የጻድቁ
ዋጋ ተካፋዮች እንድንሆን በማድረጋቸው እኔም ሆነ የበዓሉ ታዳሚዎች ልባዊ ምስጋናችንን እናቀርባለን።
ማህበራችን
ጅምር እንደመሆኑ ለወደፊት ብዙ መስዋዕትነት የሚጠይቁ ጉዳዮች እንደሚገጥሙን ከብዙዎች ትምህርት ወስደናል ብየ አስባለሁ። ሐዋርያው
ቅዱስ ጳውሎስ ” በእሽቅድምድም ስፍራ
የሚሮጡት፥ ሁሉ እንዲሮጡ
ነገር ግን
አንዱ ብቻ
ዋጋውን እንዲቀበል አታውቁምን?
እንዲሁም ታገኙ ዘንድ
ሩጡ። የሚታገልም ሁሉ በነገር
ሁሉ ሰውነቱን
ይገዛል፤ እነዚያም የሚጠፋውን
አክሊል ሊያገኙ ነው፥
እኛ ግን
የማይጠፋውን 1ኛ ቆሮ 9፥24” ብሎ እንደተናገረው እርፍ ተይዞ ወደኋላ ማረስ የለምና ይህ መንፈሳዊ አገልግሎት
ትልቅ ዋጋ ያለው ነውና ምናልባት በጉዟችን የሚከብድብን ነገር ቢኖር እንኳን ዘወትር በጸሎትና በምልጃ እየታገዘ የማይጠፋውን የክብር
አክሊል የሚያስገኝ መሆን አለበት።
በእንዲህ አይነቱ መንፈሳዊ ህብረት ውስጥ ያለን ሁላችን ከሁሉ አስቀድመን
አላማውንና ተግባሩን እንመርምር። በጎ መሆኑን ከተረዳን ለአላማዉና ለተግባሩ እራሳችንን እናስገዛ።
መሰባሰብ ሲባል፥ እርግጥ ነው በዘመናችን በተለያየ ምክንያት ሰዎች ለአንድ
አላማ ይሰባሰባሉ። ነገር ግን ጥቂትም ሳይጓዙ ሁሉም የራሱን አላማና ፍላጎት ይዞ ስለሚመጣ የተጀመረው ነገር ዘለቄታ ሳይኖረው በጎነቱ
ቀርቶ ሽኩቻ የነገሰበት ይሆናል።
ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ ለቆሮቶስ ክርስቲያኖች በጻፈው መልእክቱ ለበጎ አላማ
ያልሆነ መሳባሰብ የማይገባ መሆኑን እንዲህ ብሎ ጽፏል “ ነገር ግን በምትሰበሰቡበት
ጊዜ ለሚከፋ
እንጂ ለሚሻል
ስላልሆነ ይህን ትእዛዝ
ስሰጥ የማመሰግናችሁ
አይደለም በመጀመሪያ ወደ ማኅበር
ስትሰበሰቡ በመካከላችሁ መለያየት
እንዳለ እሰማለሁና ”
መቸም የሰው ልጅ ሁልጊዜ የሚወድቀው ከራሱ በሚመጣ ፈተና ነው ። ይህም ማለት
ከኋላ ሆኖ የሚገፋውን ሰይጣን ወደ መጥፎ ጎዳና ሲመራው ፈቃዱን ባለመፈጸም
ድል ማድረግ ስለሚያቅተው ነው። መሰባሰብ ለበጎ አላማ ከሆነ እጅግ መልካም ነው። በቅዱሳት መጻህፍትም ተጽፎ የምናገኘው ይህንኑ
የሚያረጋግጥ ነው። “ ሁለት
ወይም ሦስት
በስሜ በሚሰበሰቡበት
በዚያ በመካከላቸው
እሆናለሁና ” ማቴ 18፥20
ወንድሞች
በኅብረት ቢቀመጡ፥ እነሆ፥
መልካም ነው፥ እነሆም፥
ያማረ ነው። መዝ
133፥1 በሐዋርያትም ትምህርትና
በኅብረት እንጀራውንም በመቍረስ
በየጸሎቱም ይተጉ ነበር። የሐ ሥ 2፥42
የብዙዎችን ማህበራት ችግር ስንመለከት ተመሳሳይነት አለው። አንዱና ዋናው
ችግር በህገ ቤተክርስቲያን የተደገፈ አለመሆኑ ነው። ሁለተኛው ችግር በመሪነት የሚቀመጡት በዓለም ጥበብ የሰለጠኑ ሰዎችን እንጅ
በእድሜ የበሰሉ ወይም በመንፈሳዊ ህይዎት የታነጹ ሰዎችን ስለማያስቀድሙ ነው። ከቀድሞ ጀምሮ የምናውቀው አባቶቻችን ያቆዩልን ትውፊት
ግን አባቶች ከፊት ልጆቸ ከኋላ ሆነው መጓዝን ነበር። ዛሬ ላይ ይህ እንደ ጎጅ ባህል ተቆጥሮ ካህናት አባቶች ተቀምጠው ልጆች መሪ
ይሆናሉ። በዚህም የተነሳ የብዙዎች ድካም ከንቱ ሆኖ ይቀራል።
ለጽሁፌ መነሻ
በሆነኝ ስብስብ ላይ ያየሁት ግን የቀድሞዉን ሥርዓት በመጠበቅ አባቶች ካህናትን ከፊት በማስቀደም የቤተክርስቲያንን ቁሳዊ ችግሮች
ለመፍታት የሚንቀሳቀስ ህብረት ነው። ይህ በሌሎችም መንፈሳዊ ማህበራት ዘንድ ሊለመድ የሚገባው አካሄድ ነው እያልኩ፥ በዋሽንግተን
ዲሲና አካባቢው ለምትገኙ የጻድቁ ልጆች በነበረን ቆይታ ላሳያችሁን መንፈሳዊነትና ቅንነት የተላበሰ መስተንግዶ እኔና ከተለያየ ቦታ
በስፍራው የታደምን እንግዶች ሁላችን በእግዚአብሔር ስም እናመሰግናለን።
የተክልዬ ልጆች እግዚአብሔር በየአህጉራቱ ያብዛችሁ
ReplyDelete