ስለ ዘመናችን የስልጣኔ ደረጃ ስናነሳ ሁላችንም የምንገነዘበው ነገር አለ። ኃያላን መንግሥታት ቀድሞ ከነበራቸው አመለካከት ይልቅ የአሁኑ የተሻለ በመሆኑ የስልጣኔ መሪዎች ይባላሉ። ቀድሞ በኃይል ሁሉን ማሸነፍ የሚችሉ ይመስላቸው ስለነበር የሌሎችን መብት በመግፈፍ በጭቆና ይገዙ ነበር። ዛሬ ላይ ያንን አመለካከት ከመጥላታቸውም በላይ በየጊዜው ሲያወግዙ እንሰማቸዋለን። ምድራዊ ገዥዎች ምንጊዜም ከስህተት የማይርቁ ቢሆኑም የሰውን ልጅ መብት ለማስከበር በየሀገራቸው የሚጥሩ መሪዎች በመኖራቸው በደልና ስቃይ ጎልቶ እንዳይወጣ ለማድረግ ችለዋል።
ታሪክን ጠብቆ ማኖር የሚችል ትውልድ ከክፉውም ሆነ ከበጎውም ተምሮ እራሱን እና ሀገርን ይለውጣል። ያለፈን ታሪክና ወገን በመጥላት በብሶት የተሞላ ትውልድ ለራሱም ሆነ ለሀገር በጎ የሚሰራበት አቅም አይኖረውም። ጥላቻ የራስን ብቻ ሳይሆን የወገንንም ታሪክ ያበላሻል። ቃኤል በወንድሙ ላይ በቅንዓት መጥፎ ጥላቻ ስላደረበት የሚወደውን ወንድሙን ገደለ፣ ከእግዚአብሔር ጋር ተጣላ፣ ከወገኖቹ ኮበለለ፣ እሱና የሱ ዘሮች በምድር ላይ ተቅበዝባዥ ተባሉ።
በምድር ላይ እግዚአብሔር ያስነሳቸው መልካም የተባሉ እንደነ ቅዱስ ዳዊት ያሉ የህዝብ መሪወችን ብንመለከት ምንም መልካም ቢሰሩም ነገር ግን በሰውነታቸው ይበድሉ ነበር። በበደላቸው ተቀጥተዋል በበጎው ሥራቸው ተመስግነዋል። በሰሩት ክፉ ሥራ ሳይሆን በበጎ ሥራቸው እግዚአብሔር ቃልኪዳን ገብቶላቸዋል። ከእነሱ በኋላም የትተነሱት መሪወች በቃል ኪዳናቸው ተጠቅመውበታ። በጎ ባልሆነው ምግባራቸውም ተምረውበታል።
ዛሬ ላይ ያሉ መሪዎቻችን ካለፉት መሪወች በጎ የሆነውን እየወሰዱ በጎ ካልሆነው እየተማሩ ቢገዙ በየእለቱ የምንሰማው ጩኽት ይውረዱልን ሳይሆን እግዚአብሔር ሆይ እድሜ ስጥልን የሚል ይሆን ነበር። ክርሲቲያን ተስፋ አይቆርጥም አንድ ቀን ጩኽታችን ይቀየር ይሆናል። ዛሬ ላይ ሆነን የምናየውን ክፉ ሥራ ካልተቃወምን በጎውን ካላበረታታን የህሊና ወቀሳ ይኖራልና ምክር አዘል ሃሳብ ለማስተላለፍ ወደድኩ። ሀገር የሚመራው በመንግስት ብቻ አይደለም እስከ ትንሹ ቤተሰብ ድረስ ኃላፊነት ተጥሏል ብየ አምናለሁ። ሰውን የሚገዛው ፍቅር ነው። እግዚአብሔር ለኛ የሰጠንን ፍቅር ስንመለከት ስላፈቀረን እንገዛለታለን። ማንንም እግዚአብሔር በኃል አይገዛም። ስለሆነም በዓለም ላይ ያለውም ሆነ በሰማያት የሚኖሩት መላእክት በፍቅር ይገዙለታል። ሁሉን እግዚአብሔር በፍቅር አሸንፏልና። ገዥውን፣መንጋውን፣ጠባቂውን ወዘተ። እግዚአብሔር አሸናፊ ነው። ሁሉን ማድረግ ይችላል ነገር ግን ሊያስተምረን ፍቅርን አብዝቶ ሰጠን። ስለዚህ እኛም ጧት ማታ አብዝተን እናመሰግነዋለን።
እያፈቀሩ፣ እየማሩ፣ እየቸሩ፣ እየታገሱ፣ ይቅር እያሉ፣ ወ ዘ ተ መምራት ይቻላል። ለመሪዎች አስቀድሞ የተሰጠውም አደራ ይህ ነበር። እያሰሩ ብቻ ሳይሆን እየማሩም እየራሩም መምራት ይቻላል። ብዙ ዘመን እያሰርን እየቀጣን ሞከርን መፍትሄ አላመጣም። በማሰርና በመግደል ሰላም ማምጣት የሚቻል ቢሆን ደርግን የሚደርስበት አይኖርም ነበር። ነገር ግን ከሱ ውድቀት መማር አለመቻል እንዳለመታደል ይቆጠራል።
ትላንት በሰማሁት ዜና ውስጤ በሃሴት ተሞልቶ ነው የዋለው ብየ ልጽፍ ፈለኩና መቼም የዚህ ዘመን ደስታ አፍራሽ የበዛበት አይደል? ለካ ሰዎቹ የተፈቱት በወሬ ነው። ከወሬው ተግባሩ ቢቀድም መልካም ነበር። ሰይጣን የአፍን እንጅ የልብን አያውቅም ይባላል። ሁሉ ነገር አልሳካ ያለን ከተግባሩ ወሬው እየቀደመ ነው። የታሰሩ ሊፈቱ ነው ሲባል ብዙዎች ደስታቸውን ሲገልጹ ሰማን። ምነው የሆነብን ነገር ሁሉ ሳይሆን ይህ ነገር በሆነ ብየ አሰብኩኝ። ለሚያልፍ ጊዜ የማያልፍ ጠባሳ እንዳናኖር ማሰቡ መልካም ነው። ይሁን እንጅ ሄደት መለስ የሚል መንፈሳዊ ሃሴት በውስጤ አለ። ለካ በሀገርና በወገን ጉዳይ አይመለከተኝም ማለት አይቻልም?
ያለኝ መረጃ በመስማት ላይ የተመሰረተ በመሆኑ ስለሚያስሩትም ሰለሚታሰሩትም ግላዊ ህይዎት ምንም ማለት አልችልም። ነገር ግን ከማሰር መፍታት ይሻላል; ከመሞት መኖር ይሻላል። ይህን ከህሊና የተነሳ እናገራለሁ። መንግሥት በማሰር ብቻ መፍትሄ ለማምጣት መሞከሩ ለሀገርም ለራሱ ለመንግሥትም አይበጅም። በተለይ የህዝቡን አንድነት ሊሸረሽሩ የሚችሉ ጉዳዮችን በጥንቃቄ ማየት ይገባል።የታሪክ ተወቃሽ መሆን አለና። በእኔ እምነት ኢትዮጵያውያን ሁላችን አንድ ህዝቦች ነን ይህን ያደረገው ደግሞ እግዚአብሔር ነው። "እግዚአብሔር ያጣመረውን ሰው አይለየው ማቴ 19፥6 " እኛ ዓለም የሚያውቀን አንድ ህዝቦች በመሆናችን ነው። ለራሳችን የተለያየ ስም ሰጥተን ስንራኮት የሀገራችንን መልክ በትልቁ የሚለውጥ ታሪክ እያስመዘገብን ነው። የቤተክርስቲያናችን መመሪያ የሆነው መጽሐፍ ቅዱስ ስለ ሰው ልጅ መነሻና መድረሻ አምልቶ ይናገራል። ሰው በሥጋ የሚኖርበት ዘመኑ እንደ ጥላ ያልፋል። ስለዚህ በዚህ ከንቱ በሚመስል ህይዎቱ የፈጣሪውን ህግ አክብሮ ቢኖር መልካም ነው። የሰው ዘር በሙሉ ከአንድ። አካል የተገኘ ነው። አስገኝውም እግዚአብሔር ነው። " በአንድ አካል ብዙ ብልቶች እንዳሉን፥ የብልቶቹም ሁሉ ሥራ አንድ እንዳይደለ፥ እንዲሁ ብዙዎች ስንሆን በክርስቶስ አንድ አካል ነን፥ እርስ በርሳችንም እያንዳንዳችን የሌላው ብልቶች ነን" ሰው ሃይማኖት የለሽ ሲሆን ይህን የፈጣሪ ትእዛዝ አያውቅም። እንኳን በአንድ ቤተስብ ያለው ይቅርና (ቤተሰብ ማለት የአንድ ሀገር ሰዎችን በሙሉ ማለት ነው) ዘርና ቀለሙ የተለየ ተብሎ የሚጠራው ስንኳን የሰው ዘር በመሆኑ ወገን ነው።
በተለይ በሀገር ጉዳይ ሰው ሲታሰር አንድ ሰው ብቻ አይደለም የሚታሰረው; ይህን ከግምት ውስጥ በማስገባት መፍትሄ መስጠት ያስፈልጋል። ወንጀል የሰራ ሰው ይታሰር ዘንድ ይገባል። ለመጉዳት ሳይሆን ለማስተማር ። ነገር ግን የህዝብን ሃሳብ የሚያንፀባርቁ ሰዎችን ማሰር ከህዝብ ጋር መጣላት ነው። ሰው የሚታሰረው ህሊናው ነው። ስለዚህ ያሰረም የታሰረም ህሊናው ሰላም አያገኝም። ናቡከደነጾር ዳንኤልን ወደ አንበሳ ጉድጓድ ቢያስጥለውም ከዳንኤል ይልቅ የእሱ ጭንቀት የበረታ ነበር። ጭንቀቱን ያመጣው ማንአለብኝነቱ ነው። ዳንኤልን አስሮት የነበረው አጥፍቶ በድሎ አልነበረም። ህሊናህን መሸጥ አለብህ ብሎ ነበር። መጥምቁ ዮሐንስ በሄሮድስ እስር ቤት ተጣለ ከዚያም አንገቱ ተቆርጦ እንዲሞት ሆነ ሄሮድስ ግን ያለ በደሉ እንዳሰረው ያውቅ ነበርና በህሊናው ይፀፀት ነበር። ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስን ለሞት ተላልፎ እንዲሰጥ ያደረገው ጲላጦስ ከእርሱ አልፎ ቤተሰቡ በፀፀት ውስጥ ወድቆ ነበር።
የሰው አስተሳሰብ ምንጊዜም ቢሆን ይለያያል። የአንድ እናት ልጆች ኤሳውና ያእቆብ በአንድ ወቅት፣ በአንድ ማህፀን መፀነሳቸው እንዲሁም ዘጠኝ ወር በአንድ ማህፀን ውስጥ መኖራቸው በሃሳብ እንዳይለያዩ አልረዳቸውም። ስለዚህ በተለያየ መንገድ ህዝብን እንድናገለግል እግዚአብሔር የመረጠን ሁላችን ይህን የተፈጥሮ መርህ አክብረን መኖር ይገባናል። እኔ እንደማስበው ካላሰብክ ማለት የተፈጥሮን ህግ መቃወም ነው። የሚመርቅ እንዳለ ሁሉ የሚራገም እንዳለ ማመን አለብን። የሚመርቀውም የሚረግመውም ወደ እኛ ሊደርስ የሚችለው እንደየምግባራችን ነው። ሆኖ አለመገኘት እንጅ የተረገመ ሁሉ አይወድቅም። ሆኖ መገኘት እንጅ የተመረቀ ሁሉ አይባረክም።
በመጨረሻም እንደ አንድ የሃይማኖት መምህር ማስተላለፍ የምፈልገው። እያሰሩ መፍታት ብቻ ሳይሆን ያለ በቂ ምክንያት ማሰር በየትኛውም መስፈርት ተቀባይነት የለውም። ስለዚህ ታሞ ከመማቀቅ አስቀድሞ መጠንቀቅ እንደሚባለው ሀገርም መንግሥትም ከሚታመሙ አስቀድሞ መጠንቀቅ መልካም ነው። ለሀገር ልማት ለህዝብ ሰላምና ደህንነት ፍትሃዊ አስተዳደር ወሳኝ ነው። ሀገርን ለማልማት ደፋ ቀና የሚል መንግስት ይህን መዘንጋት የለበትም።
ሀገር ለሰውና የሰው ነው።ሰው ደግሞ በምድር ላይ ለዘላለም አይኖርም ዘመኑ እንደ ጥላ ያልፋል። በዚህ ዓለም ሲኖር መልካም ሥራ እንዲሰራ ፍርድ ሊጓደልበት አይገባም። ሰው ሊበደል አይገባም። በብሶት ውስጥ ያለ ህብረተሰብ መልካም ሰው ሊበቅልበት አይችልም። ስለዚህ መልካም ትውልድ እያጣን እንደሆነ መገንዘብ አለብን። ለመንጋው ምሳሌ ሁኑ እንደተባለው ህዝቡ እንዲፋቀር ተፋቅረን እናስተምረው። አንድ እንዲሆን መፍክራችን ስለ አንድነት መሆን አለበት። በዘርና በቋንቋ ወደ መለያየት እየተጓዘ ያለውን ህዝብ እንደቀድሞው በአንድ ሃሳብ ጸንቶ እንዲኖር ለማድረግ ከመሪዎች ፍቅርና ትእግስት አስተዋይነት በበብዙ ይጠበቃል።
No comments:
Post a Comment