በኛ ዘንድ የተዋረደውን ሳይሆን ያልተዋረደው ምንድነው ብሎ መጠየቅ ሳይሻል አይቀርም። ኢትዮጵያዊነት ከተኮነነ ሰነባበተ። ለኢትዮጵያ ትልቅ ውለታ ያበረከተችው ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ከተናቀች ውሎ አደረ። መቼም ይህን እውነት አለመናገር በሰውም በእግዚአብሔርም ዘንድ ያስጠይቃል። የትኛው በደል ይሆን ይህን ሁሉ ነገር በአንድ ወቅት ያመጣብን? ሰው ይበድላል። እግዚአብሔር ሊያስተምር እንደሚቀጣም እናምናለን እኛ ግን እየተማርን አይደለም። ሊያስተምረን ያመጣውን መከራ ለጥፋት እያደረግነው ይመስላል። ኢትዮጵያ የሚለውን ስም መጥራት የማይፈልግ ትውልድ ምድራችን አብቅላ አየን። ሁሉን እንደራሷ ልጆች አድርጋ ፊደል አስቆጥራ፣ መጠለያ ሰጥታ፣ በጎ ምግባር አስተምራ ሀገርን ከነሙሉ ታሪኩ ለዛሬው ትውልድ ያስረከበች ቤተክርስቲያን አንደበታቸው የስድብ አፍ በተመላ ክፉ ትውልዶች ተሰደበች ይህ ያመጣው መርገም ለብዙዎች ተርፎ ሰላም ከራቀን ሰነባበተ።
ሰው ሆኖ የማይበድል የለም በሚለው አባባል እስማማለሁ። ነገር ግን ሰው የተለየ ግፍና በደል ሲፈጸምበት እግዚአብሔር ዝም አይልምና ምናልባት እዚአብሔርን የሚያውቅ ቢገኝ በሚል ጥቂት ሃሳቦች ለመሰንዘር ወደድኩ ። ከሰማይ በታች አዲስ ነገር የለም እንዳለው ጠቢቡ የለመድነውን መከራ ለመተረክ ሳይሆን እራሱን እስረኛ ያደረገ ሰውን እንዲሁም ለዓለም እራሱን ሙት ያደረገ ሰውን ማንገላታት ምንድነው ትርፉ? ሰው የማያውቀው በደል የበደሉ እንኳን ምህረት ሲደረግላቸው አይተናል። እነ አባ ገብረ ሥላሴ ምን ይሆን በደላቸው? እነሱን ለማዋረድ ወይስ ቤተክርስቲያኗን?
ቤተክርስቲያናችን ከማንናውም የእምነት ተቋም ልዩ የሚያደርጋት እንኳን አለምን ንቀው ለሰማያዊው ዓለም እራሳቸውን ያስገዙትን ይቅርና በምድር ወጥተው ወርደው መልካም እየሰሩ፣ ዘር እየተኩ በትዳር ህይዎት የሚኖሩትንም ስንኳን በስነምግባር አንጻ ለሌላው መልካም ስራቸው ብርሃን እንዲሆን የምታደርግ እናት ነች። ይህን ኢትዮጵያዊ የሆነ ሁሉ ያውቀዋል።
የነ አባ ገብረ ሥላሴ ጉዳይ የግለሰብ ጉዳይ አይደለም። እንዳለመታደል ሆኖ የቤተክርስቲያኒቱ የበላይ አባቶች ለመንጋው የማይገዳቸው፣ ከቤተክርስቲያን ክብር ይልቅ ለራሳቸው ክብር የሚጨነቁ በመሆናቸው እንጅ የታሰረው የቤተክርስቲያን ክብር ነው። በመሬት ላይ እየተጎተቱ የማእረግ ልብሳቸውን እንዲያወልቁ ተገደዱ ሲባል ክብር ከኢትዮጵያ እንደለቀቀ ለብዙዎች መረጃ የሰጠ ጉዳይ ነበር ።
እስራኤላውያን በእግዚአብሔር ፊት የሚያጸይፍ ተግባር በመፈጸማቸው ምክንያት በጠላት እንዲሸነፉና ክብራቸው የነበረችው ታቦተ ጽዮን እንድትማረክ የእግዚአብሔር ፈቃድ ነበር። ከበደለኞቹ መካከል ፊንሃስ የተባለው የኤሊ ልጅ በጠላት በመገደሉ ሚስቱ ልትወልድ በምጥ ተይዛ ሳለች የታቦተ ጽዮንን መማረክና የባለቤቷን መሞት ሰማች። ወንድ ልጅ ወለደች። ነገር ግን የሰማችው ነገር ጆሮን ጭው የሚያደ,ርግ ነበርና በህይዎትና በሞት መካከል ሆና ክብር ከእስራኤል ለቀቀ ስትል ልጇን ኢካቦድ አለችው ተብሎ ተጽፎዋል 1ኛ ሳሙ, 4፥21
ዛሬ ኢትዮጵያያ በዓለም የማይፋቅ ታሪክ እንዲኖራት ሃይልን አጎናጽፎ ለድል ያበቃው የቃልኪዳኑ ታቦት በኮንቴነር ተጥሎ አባቶች ሲያለቅሱ ለማየት ችለናል። ነገ ደግሞ ምን እናይ ይሆን? የታደሉት ሀገራት እንኳን የራሳቸው ማንነት መገለጫ የሆነውን ይቅርና የሰውን የራሳቸው ለማድረግ የማይቆፍሩት ጉድጓድ የለም። እኛ ግን ለብዙ ዘመናት የቀደሙት ተንከባክበውና አክብረው ያቆዩልንን የሀገር ሀብት በማጥፋት የኢትዮጵያዊነትን መልክ እየቀየርነው እንገናለን።
ሊቀ ነቢያት ሙሴ ህዝበ እስራኤልን እየመራ ባህር አሻግሮ ከግብጽ ባርነት ነጻ ያወጣ መሪ ነው። ህዝቡ ግን እግዚአብሄር ያደረገላቸውን ነገር በመርሳት በስደት በመንገድ ላይ ሳሉ እግዚአብሄርን ያሳዝኑት ነበር። በጥፋታቸውም መከራ እያገናቸው ብዙዎቹ ያልቁ ነበር። መቅሰፍቱ ከእግዚአብሔር የሚታዘዝ ሲሆን ከህጉ በመውጣት ክፉ ያደርጉ ስለነበር በምድረበዳ ይቀሰፉ ነበር። ሙሴም ሲመክራቸው አምላካችሁን እግዚአብሔርን አትፈታተኑት ዘዳ 6፥16 ይላቸው ነበር ። ሰው እግዚአብሄርን መፈታተን ከጀመረ ብቻውን አደለም የሚጠፋው ብዙዎችን ለመከራ ይዳርጋል። ስለዚህ አያገባንም ብለን ዝም ያልን ሁላችን መናገር ይኖርብናል። ዝምታ እንደመስማማት ይቆጠራልና አደራ የተጣለባችሁ አባቶች ዝምታችሁ ሊሰበር ይገባል። መነኮሳት ከበዓታቸው ተወስደው ሲንገላቱ እያየን እየሰማን ዝም የምንል ከሆነ ሁላችንም እግዚአብሄርን እየተፈታተነው ነው።
ጌታ ሰባ ሁለቱን አርድእት ሾሞ ወደ ዓለም እንዲሄዱና ወንጌልን እንዲሰብኩ ካዘዛቸው በኋላ ቃላቸውን የሚሰማ የሰላም ልጅ ቢኖር ሰላማቸው እንዲያድርበት ቃል ኪዳን የሰጣቸው ሲሆን በእነሱ ላይ ማንኛውንም መከራ የሚያመጣ ፈጣሪውን እየተፈታተነ እንደሆነ ነግሯቸዋል። ( የሚሰማችሁ እኔን ይሰማል፥ እናንተንም የጣለ እኔን ይጥላል፤ እኔንም የጣለ የላከኝን ይጥላል። ሉቃ 10፥16)
ለጥፋት የታዘዘች ከተማ ነጋሪት ቢጎሰም አትሰማ እንዲሉ ይህ ሁሉ ጩኸት አንድ ቀን ዋጋ ያስከፍላል እና ከማንችለው ኃይል ጋር እየተዋጋን መኖሩ ቢበቃን መልካም ነው።
በብዙ ሀገሮች የህዝብ የሆነ ተቋምም ሆነ የማንነት መገለጫ የሆነው ሁሉ ክብር ተሰጥቶት ጥበቃ ይደረግለታል። እኛም ስደተኞቹ በማናውቀው ሀገር ጥቂቶችም ብንሆን ተሰባስበን በመገኘታችን የኛ የሆነው ሁሉ ስለኛ ሲባል ክብር ተሰጥቶት ጥበቃ ይደረግለታል። ይህን ስናይ በተደረገልን ከመጽናናት ይልቅ በገዛ ሀገሩ ክብር ያጣውን ወገን እያሰብን እጅግ እናዝናለን።
የሰላም አምላክ ሰላሙን ያድለን።
መጋቤ ሃይማኖት ቀሲስ ዘላለም ጽጌ
ሴንት ልውስ ሚዙሪ
የሰላም አምላክ ሰላሙን ያድለን።
መጋቤ ሃይማኖት ቀሲስ ዘላለም ጽጌ
ሴንት ልውስ ሚዙሪ
No comments:
Post a Comment