Monday, December 29, 2025

ጾመ ጋድ (ገሃድ)

በቅድሚያ እንኳን ለጌታችንና ለአምላካችን ለመድኃኒታችን ለኢየሱስ ክርስቶስ የልደት በዓል በሰላም አደረሳችሁ የዘንድሮው ዓመት 2018 ዘመነ ማርቆስ የገና እና የጥምቀት በዓላት እረቡዕ እና ሰኞ በመዋላቸው በምእመናን የሚጠየቁ ጥያቄዎች አሉ፡፡ እንዲህ ዓይነቶቹ ጥያቄዎች በሊቃውንት ጉባኤ የሚመለሱ ቢሆንም ቤተክርስቲያናችን ስንዱ እመቤት በመሆኗ አባቶቻችን አስቀድመው ሥርዓት ሠርተውልናል። በመሆኑም በመጠኑ ስለዘንድሮው ዓመት የገናና የጥምቀት በዓል ጋድ ወይም ገሃድ ጾም በመጠኑ ሃሳብ ለማካፈል ወደድኩ። ገና እና ጥምቀት ዓርብ እና ረቡዕ ቢውሉ ይበላባቸዋል ወይስ ይጾማሉ? በፍትሃ ነገሥት /ዐንቀጽ 15፣ቁ 603/ የዓርብን እና የረቡዕን ጾም ግን ከልደት፣ከጥምቀት እና ከበዓለ ሃምሳ በቀር ዘወትር ይጹሙ ተብሎ በተጻፈው መሰረትገናና ጥምቀት እረቡዕና ዓርብ ላይ ቢውሉ መብላት ይቻላል ማለት ነው ስለዚህ የ2018 ዓ/ም ገና ረቡዕ ቢውልም በዓለ ልደቱ የሚከበርበት እለት በመሆኑ ክርስቲያኖች በሥርአተ ቤተክርስቲያን በታዘዘው መሰረት ከቤተክርስቲያን አገልግሎት መልስ በቤታቸው በዓሉን በደስታ እንዲያከብሩ ተፈቅዷል። ጋድ ገሃድ ፍትሐ ነገሥት፡ የልደት እና የጥምቀት በዓላት ጋድ አላቸው /ዐንቀጽ 15፣ ቁ 566/ ትንታኔ፡ የገና ጾም 44 ቀናትን ይይዛል፡፡ 40 ጾመ ነቢያት 3 ጾመ አብርሃም ሶርያዊ 1 ጋድ ድምር 44
የገና ጋድ ከጾሙ ተያይዞ የተቀመጠ እንጂ ለብቻው የተቀመጠ አይደለም፡፡ ለምሳሌ ሰሙነ ሕማማት ለብቻው የሚቆጠር ጾም ነው፡፡ /ዐንቀጽ 15፣ቁ 565/ ነገር ግን አንድ ሰው ዐቢይ ጾምን ሳይጾም ከርሞ ሕማማትን ለብቻው መጾም አይችልም፡፡ የገናም ጋድ እንዲሁ ነው፡፡ ይህንን ጋድ የልደትን ጾም የማይጾሙ ሰዎች እንዲጾሙት የተሠራ ነውን? መልስ፡ በቤተ ክርስቲያን ላልተጠመቁ፣ ለማይቆርቡ፣ ንስሐ ለማይገቡ፣ ለማያስቀድሱ፣ ለማይጾሙ ሰዎች ተብሎ የተሠራ ልዩ ሥርዓት የለም፡፡ በፍትሐ ነገሥት ዐንቀጽ 15፣ ቁ 565 እንደተገለጠው ሰባቱ አጽዋማት «ለክርስቲያን ሁሉ» የታዘዙ ናቸው፡፡ ስለዚህም የገናን ጾም ክርስቲያን ሁሉ ጾመው በበዓለ ልደት ሊገድፉ ይገባቸዋል፡፡ ፍትሐ ነገሥት ስለ ገና ጾም ሲገልጥ «መጀመርያው የኅዳር እኩሌታ ፋሲካው የልደት በዓል ነው» ይላል /ዐንቀጽ 15፣ ቁ 568/፡፡ ይህም ከገና ጾም ተሸርፎ የሚጾም ነገር እንደሌለው ያሳያል፡፡ ቅድስት ቤተ ክርስቲያናችን ካሏት ሰባቱ የአዋጅ አጽዋማት መካከል አንዱ ጾመ ጋድ(ገሃድ) ነው፡፡ ገሃድ ማለት ለውጥ(ምትክ) ወይም ልዋጭ፤ እንዲሁም ግልጥ፣ ተገላጭ በማለት ይተረጎማል፡፡ ይህንንም ደስታ ተክለ ወልድ በመዝገበ ቃላት መጽሐፋቸው ጋድ(ገሃድ) እንዲህ ይተረጉሙታል፡- “ገና፣ የጥምቀት ከተራ (የልደትና የጥምቀት ዋዜማ) እንደ ዐርብ ረቡዕ እና ፍልሰታ፣ እንደ ሑዳዴ የሚጾም፡፡ ትርጓሜው የሚገለጥ፣ ተገላጭ፣ ግልጥ ማለት ነው፡፡ ጌታችን እንደ ሰውነቱ በአጭር ቁመት፣ በጠባብ ደረት ተወስኖ መታየቱን ያስረዳል” (ደስታ ተክለ ወልድ መዝገበ ቃላት፤ ገጽ ፪፻፴፪)፡፡ ጥር ፲ የሚነበበው ስንክሳር በጥምቀት ዋዜማ መጾም እንደሚገባ ሲገልጽ፡- “በዚች ዕለት ምንም መብልን ሳይቀምሱ ምእመናን ሁሉ እስከ ምሽት ይጾሙ ዘንድ ከእኛ አስቀድመው የነበሩ ታላላቅ ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን መምህራን ሥርዓትን ሠሩ፤ በምሽትም ቢሆን በታላቁ ጾም ከሚበላው በቀር ጥሉላትን አይቅመሱ፡፡ በዚህች ዕለት ምእመናን እስከ ምሽት እንዲጾሙት ያዘዙበት ምክንያት ይህ ነው፡- የልደትና የጥምቀት በዓል በረቡዕ ወይም በዐርብ ቀን ቢውል በበዓለ ሃምሳ የሚበላውን የጥሉላት መብል በጥዋት በመብላት ምእመናን ሁሉ በዓሉን እንዲያከብሩ አባቶቻችን ሐዋርያት አዝዘዋል፡፡ እሊህ ሁለቱ የእግዚአብሔር ታላላቅ በዓሎቹ ናቸውና፡፡” ይህም ማለት ልደት እና ጥምቀት ረቡዕና ዐርብ ከዋሉ በዋዜማው ማክሰኞና ሐሙስ ይጾማሉ። ረቡዕና ዐርብ ምንም እንኳን የጾም ቀናት ቢሆኑም የፍስክ ቀን ሆነው ይከበራሉ። የልደት እና የጥምቀት በዓል እሑድ ቢውሉ በዋዜማው ቅዳሜ የጥሉላት ምግብ አይበላም። እንዲሁም ልደት እና ጥምቀት ሰኞ ቢውሉ እሑድ ጥሉላት አይበላም። እንደ ሌሎች የአጽማዋት ቀናት እህልና ውኃ ግን አይጾሙም። ፍትሐ ነገሥት ስለ ጾም ሲገልጽ፡- “ጾምስ በሕግ ውስጥ በታወቀው ጊዜ የሰው ከምግብ መከልከል ነው፤ በደሉን ለማስተሥረይ ዋጋውንም ለማብዛት እርሱን ወዶ ሕግን ለሠራለት እየታዘዘ የፈቲውን ኃይል ያደክም ዘንድ ለነባቢት ነፍሱም ትታዘዝ ዘንድ” በማለት ይተረጉመዋል፡፡ በዚህ ጊዜ መጾም እንደሚገባም ቅድስት ቤተ ክርስቲያናችን ሥርዓት ሠርታለች፡፡ (ፍትሐ ነገሥት ንባቡና ትርጓሜው፣ አንቀጽ ፲፭፥፭፻፷፬)

Friday, December 19, 2025

የእግዚአብሔርን ዝማሬ በባዕድ ምድር እንዴት እንዘምራለን?'' መዝ 137፥1

ሕዝበ እሥራኤል የፈጣሪያቸውን ህግና ሥርዓት መጠበቅ እየተሳናቸው ብዙ ጊዜ በስደትና በጦርነት ተቀጥተዋል። ይሁን እንጅ እግዚአብሔር አምላክ አስቀድሞ ለአባቶቻቸው የገባው ቃል ኪዳን ስላለ የጠፉ ቢመስሉም እንደገና ያበረታቸዋል። 

ቅዱስ ዳዊት በመዝሙሩ የአባቶቹን ሃዘንና ሰቆቃ በምርኮ ሳሉ የደረሰባቸውንና ያደረጉትን አስታውሶ የተናገረውን ነው መነሻ ያደረኩት ''በባቢሎን ወንዞች አጠገብ በዚያ ተቀመጥን፤ ጽዮንንም ባሰብናት ጊዜ አለቀስን።በአኻያ ዛፎችዋ ላይ መሰንቆቻችንን ሰቀልን። የማረኩን በዚያ የዝማሬን ቃል ፈለጉብን፥ የወሰዱንም፦ የጽዮንን ዝማሬ ዘምሩልን አሉን። የእግዚአብሔርን ዝማሬ በባዕድ ምድር እንዴት እንዘምራለን?'' መዝ 137፥1

ሀገራችን ኢትዮጵያ በገጠማት ችግር ምክንያት ልጆቿ ስደትን እንደ ትልቅ እድል በመቁጠር በሰው ሀገር መኖርን ተለማምደዋል። ብዙዎች በገዛ ሀገራቸው የስደተኛነት ስሜት እየተሰማቸው የሰው ሀገር ይናፍቃሉ። ከዋና ከተማዋ አዲስ አበባ በመኪና ተጉዞ ቤተሰብ ማግኘት የማይታሰብ እየሆነ ነው። አዲስ አበባ ተውባለች ደምቃለች የሀገሪቱ ሰፊው ገጠራማ ክፍል ግን በሰላም እጦት ጭንቀት ላይ ይገኛል። ጦርነት፣ ርኃብ፣ ስደት ለእኛ ለኢትዮጵያውያን እንደ አዲስ ነገር የሚነገር ዜና አይደለም። በዚህም ምክንያት አንድ ሰው ተበደልኩ ብሎ ሲናገር ወይም አንዱ ስለሌላው መበደል ሃሳብ ቢሰጥ እንደቁም ነገር መቁጠር ካቆምን ሰነባብተናል። ይህ ሁሉ ችግር እያለ በዚህ ሰቆቃ ለበዛበት ማህበረሰብ የማይሆኑ አጀንዳዎችን የሚፈጥሩ አንዳንድ የቤተክርስቲያን አገልጋዮች በውዳሴ ከንቱ ተጠልፈው ''በቁስሉ ላይ እሾህ ስደድበት'' በሚመስል መልኩ ህዝቡን ግራ ያጋቡታል። ቢቻል ስለሃገር ሰላምና አንድነት መሥራት ይገባ ነበር ካልሆነም ህዝቡ ካለበት ችግር የሚወጣበትን ምክርና በጎ ሃሳብ ማቅረብ ሲገባ መለያየትን የሚያመጣ የግል ሃሳብ ማምጣት ለህዝብ ዴንታ ቢስ መሆን አይደለምን?

እውነት ለእኛ ለኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ልጆች በዚህ ሰዓት ጸሎት ነው መዝሙር ነው የሚያስፈልገው? ስሜትን ተወት አድርጎ በማስተዋል ነገሮችን ብናደርግ እግዚአብሔርም ይሰማናልና ቆም ብለን እናስብ። 

መዝሙር ማለት ለእግዚአብሔር የሚቀርብ የደስታ ጸሎት ወይም ምስጋና ማለት ነው ''ደስ የሚለውም ማንም ቢኖር እርሱ ይዘምር'' ያዕ 5፥13 እውነት እኛ ኢትዮጳያውያን በዚህ ወቅት ደስተኞች ነን? 


Friday, November 7, 2025

ክፉውን በመልካም አሸንፍ እንጂ በክፉ አትሸነፍ ሮሜ 12፥1

ከአባቶቻችን የወረስነው አባባል ''የወደቀ ዛፍ ምሳር ይበዛበታል'' ይላል። እውነትም ወድቆ የተገኘ ነገር ሁሉ የፈቀደውን ያደርግበታል ስለዚህ ለማንም የሚጠቅመው ወድቆ አለመገኘት ነው። 

ክፉ የሚባለው ጨካኝ፣ የማይራራ፣ እራስ ወዳድ ሃዘኔታ የሌለው ወዘተ ማለት ሲሆን መልካም ማለት ደግሞ ማዘን፣መራራት፣ ለሌላው ማሰብ፣ በኔ ሊደረግ የማይገባውን በሌላው አላደርግም ወዘተ ብሎ እራስን መግዛት ማለት ነው። አሸናፊነት ሁልጊዜ የበላይ መሆን ወይም ከሌላው በልጦ መገኘት ብቻ አይደለም። ክፉ ለሚያደርግ መልካም መመለስ አሸናፊነት ነው። የበደለን ይቅር ማለት አሸናፊነት ነው። የተቀሙትን መተው አሸናፊነት ነው ከዚህ አንጻር ብዙ ማለት ይቻላል። 

ሰው መሸነፍ የሚጀምረው ተስፋ መቁረጥ ውስጥ የገባ እለት ነው። በተለይ ክርስቲያን በፍሱም ተስፋ መቁረጥ የለበትም። ቅዱስ ጳውሎስ ለእብራውያን በጻፈው መልእክቱ'' እንግዲህ እነዚህን የሚያህሉ ምስክሮች እንደ ደመና በዙሪያችን ካሉልን፥ እኛ ደግሞ ሸክምን ሁሉ ቶሎም የሚከበንን ኃጢአት አስወግደን፥ የእምነታችንንም ራስና ፈጻሚውን ኢየሱስን ተመልክተን፥ በፊታችን ያለውን ሩጫ በትዕግሥት እንሩጥ፤ እርሱ ነውርን ንቆ በፊቱም ስላለው ደስታ በመስቀል ታግሦ በእግዚአብሔር ዙፋን ቀኝ ተቀምጦአልና። በነፍሳችሁ ዝላችሁ እንዳትደክሙ፥ ከኃጢአተኞች በደረሰበት እንዲህ ባለ መቃወም የጸናውን አስቡ'' እብ 12፥1 ብሎ እንደተናገረው ፈተና በማንኛውም መልኩ ቢገጥመን ልናሸንፈው እንደምንችል ከአባቶቻችን ተምረናል።

ክርስትና ከጌታችን ከአምላካችንና ከመድኃኒታችን ከኢየሱስ ክርስቶስ ጀምሮ የደም ዋጋ እየተከፈለበት ዛሬ ላይ የደረሰ ሃይማኖት ነው። ዛሬ በሰዎች ኃጢአት መብዛት የሃሳብ መለያየት በዝቶ ሁሉም የግል ሃሳቡን እያፈለቀ ብዙ ቤተ እምነት (Denomination) ቢፈጠርም መነሻው ግን አንድ ነው። ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ ለኤፌሶን ክርስቲያኖች በጻፈው መልእክቱ  ''በመጠራታችሁ በአንድ ተስፋ እንደ ተጠራችሁ አንድ አካልና አንድ መንፈስ አለ፤አንድ ጌታ አንድ ሃይማኖት አንዲት ጥምቀት፤ከሁሉ በላይ የሚሆን በሁሉም የሚሠራ በሁሉም የሚኖር አንድ አምላክ የሁሉም አባት አለ'' ኤፌ 4፥5  ብሎ እንደተናገረው የዓለማት ፈጣሪ እግዚአብሔር አንድ ነው። ወደ እርሱም የምንቀርብባት መንገድ አንዲት ናት እርስዋም አባቶቻችን የተጓዙባት ለነፍሳቸውም እረፍት ያገኙባት ናት። እርስዋ ቀዳማዊት ናት ደኃራዊት አይደለችም አዳም፣ አቤል፣ሴት፣ሄኖክ፣ኖህ፣አብርሃም፣ይስሃቅ፣ ያዕቆብ፣ ሙሴ፣ዳዊት፣ነቢያት፣ሐዋርያት የተጓዙባት ቀጥተኛ መንገድ ናት። ''ግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ በመንገድ ላይ ቁሙ ተመልከቱም፥ የቀደመችውንም መንገድ ጠይቁ፤ መልካሚቱ መንገድ ወዴት እንደ ሆነች እወቁ፥ በእርስዋም ላይ ሂዱ፥ ለነፍሳችሁም ዕረፍት ታገኛላችሁ፤ እነርሱ ግን፦ አንሄድባትም አሉ'' ኤር 6፥16


ዛሬም እኛ ልጆቻቸው ከአባቶቻችን የወረስናትን መንገድ ትተን በጊዜያዊ ጥቅም ተደልለን ከእውነት ፈቀቅ ልንል አይገባም። ከዚህች መንገድ መውጣት ትልቁ ሽንፈት ነው። ከሰዎች የሚመጣብን ፈተና ሁሉ በእግዚአብሔር ዘንድ ዋጋ የሚያስገንል በመሆኑ ደስ ሊለን ነው የሚገባው። ሲሰድቡን፣ ሲያሳድዱን፣ ሲገድሉን በሥሙ ስለሆነ አሸናፊዎች እኛ ነን። ጌታችን አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ እንዳስተማረን '' ሲነቅፉአችሁና ሲያሳድዱአችሁ በእኔም ምክንያት ክፉውን ሁሉ በውሸት ሲናገሩባችሁ ብፁዓን ናችሁ።ዋጋችሁ በሰማያት ታላቅ ነውና ደስ ይበላችሁ፥ ሐሴትም አድርጉ፤ ከእናንተ በፊት የነበሩትን ነቢያትን እንዲሁ አሳድደዋቸዋልና'' ማቴ 5፥11

Friday, October 31, 2025

እረኞች ሆይ፥ የእግዚአብሔርን ቃል ስሙ ሕዝ 34፥7

ቅዱሱ መጽሐፋችን መጽሐፍ ቅዱስ ወንድም ወንድሙን መግደል የጀመረበትን ምክንያት በግልጽ ይነግረናል ዘፍ 4፥8 ነገር ግን ምክንያቱን ለመቀበል ከአእምሮ በላይ በመሆኑ እጅግ ያስደንቃል። እንኳን ሰው ይቅርና እንስሳ የራሱን ወገን በበጎ የሚያይበት ተፈጥሯዊ ስጦታ ታድሏል፦ ነገር ግን የሰው ልጅ ከእንስሳት አንሶ ሰው ሰውን እየበላ የክፋት እርሃቡን ለማስታገስ ሲሮጥ ማየት እጅግ ያሳዝናል። ሰላማውያን የምንባለውም እኛ ከመደጋገሙ የተነሳ እየለመድነው በመምጣታችን እንደቁም ነገር ለመቁጠር እየተቸገርን እንደሆነ በግልጽ እየታየ ነው።  ሰሞኑን በኦሮሚያ ክልል ምሥራቅ አርሲ ዞን በተለያዩ ወረዳዎች ሥር የሚገኙ በርካታ ምዕመናን በጽንፈኞች እንደተገደሉ ሰምተናል። ይሁን እንጅ ከመንግሥትም ሆነ ከቤተክህነት ለሟቾችም ሆነ ለቤተሰቦች እንደዜጋ እና እንደ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ምዕመን ክብር እንዳልተሰጣቸው በተላለፉት መልእክቶች መረዳት ይቻላል። የኦርቶዶክስ ተዋህዶ ምዕመን መገደሉ በዚህ ደረጃ መቅለሉ በጣም ያሳዝናል።



የንፁሐን ደም የሚያመጣውን ወይም ያመጣውን መዘዝ ማወቅና መረዳት ለመንግሥትና ለሃይማኖት መሪዎች እንዴት ተሳናቸው?  እንዲሁም ይህን በየጊዜው የሚፈስ ደምና እንባ የምንመለከት ወገኖች እንዴት በጋራ መጮህ አቃተን? ብለው የሚጠይቁ ብዙዎች ናቸው። ህጻናት፣ እናቶች፣ አባቶች፣ ዲያቆናት፣ ካህናት፣መነኮሳት (እስከ አሁን ጳጳሳትን አይጨምርም ለወደፊቱ ግን ስጋት አለን) ናቸው ደማቸው እየፈሰሰ ያለው። ማነው የንጹሐንን ደም ከመፍሰስ መታደግ ያለበት? የመንግስትም ሆነ የሃይማኖት መሪዎች ዘመኑን የዋጀ የአመራር ሥርዓት መዘርጋት ካልቻላችሁ ኃላፊነታችሁን እየተወጣችሁ አይደለም። ህዝብ መሪ አለኝ ብሎ ከልፋቱ ጥሪቱን ግብር እየከፈለ የሚኖረው ሰላምና ደህንቱን የሚያስጠብቅለት አካል አለኝ ብሎ አምኖ ነው።

Saturday, October 18, 2025

የሃይማኖት ሰው ምግባር


1, ከእግዚአብሔር ሌላ አምላክ የለውም

2, የፈጣሪውን ስም በከንቱ አያነሳም

3, እለተ ሰንበትን ያከብራል


Saturday, October 11, 2025

ድንግል ማርያምን ማየት የተሳነው ኢየሱስ ክርስቶስን እንዴት ማየት ይችላል?

 ከመንበሩ ላይ ተቀምጦ የምናየው ስእል ምስለ ፍቁር ወልዳ ብለን የምንጠራም የእመቤታችን የቅድስት ድንግል ማርያም ልጇን ኢየሱስ ክርስቶስን ታቅፋ የሚያሳይ ስእለ አድህኖ ነው ብየ ልጽፍ አሰብኩና ይህን የማያውቅ ሰው ሊኖር አይችልም የሚል ሃሳብ ውስጤን ስለሞገተው በቀጥታ ማስተላለፍ ወደፈለኩት ሃሳብ ገባሁ። ሰሞኑን ስለ ቅዱሳን ስእላት የተነሳውን የተዛባ ሃሳብ ባሰብኩ ጊዜ ይህን ጻፍኩ።



Thursday, October 2, 2025


 በዚያች ሰዓት ደቀ መዛሙርቱ ወደ ኢየሱስ ቀርበው፦ በመንግሥተ ሰማያት ከሁሉ የሚበልጥ ማን ይሆን? አሉት። ሕፃንም ጠርቶ በመካከላቸው አቆመ እንዲህም አለ፦ እውነት እላችኋለሁ፥ ካልተመለሳችሁ እንደ ሕፃናትም ካልሆናችሁ፥ ወደ መንግሥተ ሰማያት ከቶ አትገቡም። እንግዲህ እንደዚህ ሕፃን ራሱን የሚያዋርድ ሁሉ፥ በመንግሥተ ሰማያት የሚበልጥ እርሱ ነው። እንደዚህም ያለውን አንድ ሕፃን በስሜ የሚቀበል ሁሉ እኔን ይቀበላል፤ በእኔም ከሚያምኑ ከነዚህ ከታናናሾቹ አንዱን የሚያሰናክል ሁሉ፥ የወፍጮ ድንጋይ በአንገቱ ታስሮ ወደ ጥልቅ ባሕር መስጠም ይሻለው ነበር። ማቴ 18፥1

፩ አሐዱ 1

  

አልቦ 0 ፩ አሐዱ 1 ፪ ክልኤቱ 2 ፫ ሠለስቱ 3 ፬ አርባዕቱ 4 ፭ ሐምስቱ 5 ፮ ስድስቱ 6 ፯ ስብዓቱ 7 ፰ ስመንቱ 8 ፱ ተሰዓቱ 9 ፲ አሠርቱ10 ፲፩ አሠርቱ ወአሐዱ 11 ፲፪ አሠርቱ ወክልኤቱ 12 ፲፫ አሠርቱ ወሠለስቱ 13 ፲፬ አሠርቱ ወአርባዕቱ 14 ፲፭ አሠርቱ ወሐምስቱ 15 ፲፮ አሠርቱ ወስድስቱ 16 ፲፯ አሠርቱ ወሰብዓቱ 17 ፲፰ አሠርቱ ወስመንቱ 18 ፲፱ አሠርቱ ወተሰዓቱ 19 ፳ እስራ 20 ፳፩ እስራ ወአሐዱ 21 ፳፪ እስራ ወክልኤቱ 22 ፳፫ እስራ ወሠለስቱ 23 ፳፬ እስራ ወአርባዕቱ 24 ፳፭ እስራ ወሐምስቱ 25 ፳፮ እስራ ወስድስቱ 26 ፳፯ እስራ ወሰብዓቱ 27 ፳፰ እስራ ወሰመንቱ 28 ፳፱ እስራ ወተሰዓቱ 29 ፴ ሠላሳ 30 ፴፩ ሠላሳ ወአሐዱ 31 ፴፪ ሠላሳ ወክልኤቱ 32 ፴፫ ሠላሳ ወሠለስቱ 33 ፴፬ ሠላሳ ወአርባዕቱ 34 ፴፭ ሠላሳ ወሐምስቱ 35 ፴፮ ሠላሳ ወስድስቱ 36 ፴፯ ሠላሳ ወሰብዓቱ 37 ፴፰ ሠላሳ ወሰመንቱ 38 ፴፱ ሠላሳ ወተሰዓቱ 39 ፵ አርብዓ 40 ፶ ሃምሳ 50 ፷ ስድሳ 60 ፸ ሰብዓ 70 ፹ ሰማንያ 80 ፺ ተሰዓ 90 ፻ ምዕት 100 ፻፩ ምዕት ወአሐዱ 101 ፻፪ ምዕት ወክልኤቱ 102 ፻፫ ምዕት ወሠለስቱ 103 ፻፬ ምዕት ወአርባዕቱ 104 ፻፭ መዕት ወሐምስቱ 105 ፻፮ ምዕት ወስድስቱ 106 ፻፯ ምዕት ወሰብዓቱ 107 ፻፰ ምዕት ወስመንቱ 108 ፻፱ ምዕት ወተሰዓቱ109 ፻፲ ምዕት ወአሠርቱ 110 ፻፲ወ፩ ምዕት አሠርቱ ወአሐዱ 111 ፻፲ወ፪ ምዕት አሠርቱ ወክልኤቱ 112 ፻፲ወ፫ ምዕት አሠርቱ ወሠለስቱ 113 ፻፲ወ፬ ምዕት አሠርቱ ወአርባዕቱ 114 ፻፲ወ፭ ምዕት አሠርቱ ወሐምስቱ 115 ፻፲ወ፮ ምዕት አሠርቱ ወስድስቱ 116 ፻፲ወ፯ ምዕት አሠርቱ ወሰብዓቱ 117 ፻፲ወ፰ ምዕት አሠርቱ ወስመንቱ 118 ፻፲ወ፱ ምዕት አሠርቱ ወተሰዓቱ 119 ፻፳ ምዕት ወእስራ 120 ፻፴ ምዕት ወሠላሳ 130 ፻፵ ምዕት ወአርብዓ 140 ፻፶ ምዕት ወሃምሳ 150 ፻፷ ምዕት ወስድሳ 160 ፻፸ ምዕት ወሰብዓ 170 ፻፹ ምዕት ወሰማንያ 180 ፻፺ ምዕት ወተሰዓ 190 ፪፻ ክልኤቱ ምዕት 200 ፪፻ወ፩ ክልኤቱ ምዕት ወአሐዱ 201 ፪፻ወ፪ ክልኤቱ ምዕት ወክልኤቱ 202 ፪፻ወ፫ ክልኤቱ ምዕት ወሠለስቱ 203 ፪፻ወ፬ ክልኤቱ ምዕት ወአርባዕቱ 204 ፪፻ወ፭ ክልኤቱ ምዕት ወሐምስቱ 205 ፪፻ወ፮ ክልኤቱ ምዕት ወስድስቱ 206 ፪፻ወ፯ ክልኤቱ ምዕት ወሰብዓቱ 207 ፪፻ወ፰ ክለኤቱ ምዕት ወስመንቱ 208 ፪፻ወ፱ ክልኤቱ ምዕት ወተሰዓቱ 209 ፪፻ወ፲ ክልኤቱ ምዕት ወአሠርቱ 210 ፪፻፲ወ፩ ክልኤቱ ምዕት አሠርቱ ወአሐዱ 211 ፪፻፲ወ፪ ክልኤቱ ምዕት አሠርቱ ወክልኤቱ 212 ፪፻፲ወ፫ ክልኤቱ ምዕት አሠርቱ ወሠልስቱ 213 ፪፻፲ወ፬ ክልኤቱ ምዕት አሠርቱ ወአርባቱ 214 ፪፻፲ወ፭ ክልኤቱ ምዕት አሠርቱ ወሐምስቱ 215 ፪፻፲ወ፮ ክልኤቱ ምዕት አሠርቱ ወስድስቱ 216 ፪፻፲ወ፯ ክልኤቱ ምዕት አሠርቱ ወሰብዓቱ 217 ፪፻፲ወ፰ ክልኤቱ ምዕት አሠርቱ ወሰመንቱ 218 ፪፻፲ወ፱ ክልኤቱ ምዕት አሠርቱ ወተሰዓቱ 219 ፪፻፳ ክልኤቱ ምዕት ወእስራ 220 ፪፻፴ ክልኤቱ ምሪዕት ወሠላሳ 230 ፪፻፵ ክልኤቱ ምዕት ወአርብዓ 240 ፪፻፶ ክልኤቱ ምዕት ወሃምሳ 250 ፪፻፷ ክልኤቱ ምዕት ወስድሳ 260 ፪፻፸ ክልኤቱ ምዕት ወሰብዓ 270 ፪፻፹ ክልኤቱ ምዕት ወሰማንያ 280 ፪፻፺ ክልኤቱ ምዕት ወተሰዓ 290 ፫፻ ሠለስቱ ምዕት 300 ፬፻ አርባዕቱ ምዕት 400 ፭፻ ሐምስቱ ምዕት 500 ፮፻ ስድስቱ ምዕት 600 ፯፻ ስብዓቱ ምዕት 700 ፰፻ ስመንቱ ምዕት 800 ፱፻ ተሰዓቱ ምዕት 900 ፲፻ አሠርቱ ምዕት 1000 ፳፻ እስራ ምዕት 2000 ፴፻ ሠላሳ ምዕት 3000 ፵፻ አርብዓ ምዕት 4000 ፶፻ ሃምሳ ምዕት 5000 ፷፻ ሳድስ ምዕት 6000 ፸፻ ሰብዓ ምዕት 7000 ፹፻ ሰማንያ ምዕት 8000 ፺፻ ተሰዓ ምዕት 9000 ፻፻ እልፍ 10,000 ፪፻፻ ክልኤቱ እልፍ 20,000 ፫፻፻ ሠለስቱ እልፍ 30,000 ፬፻፻ አርባዕቱ እልፍ 40,000 ፭፻፻ ሐምስቱ እልፍ 50,000 ፮፻፻ ስድስቱ እልፍ 60,000 ፯፻፻ ሰብዓቱ እልፍ 70,000 ፰፻፻ ስመንቱ እልፍ 80,000 ፱፻፻ ተሰዓቱ እልፍ 90,000 ፲፻፻ አሠርቱ እልፍ 100,000 ፳፻፻ እስራ እልፍ 200,000 ፴፻፻ ሠላሳ እልፍ 300,000 ፵፻፻ አርብዓ እልፍ 400,000 ፶፻፻ ሃምሳ እልፍ 500,000 ፷፻፻ ስድሳ እልፍ 600,000 ፸፻፻ ሰብዓ እልፍ 700,000 ፹፻፻ ሰማንያ እልፍ 800,000 ፺፻፻ ተሰዓ እልፍ 900,000 ፻፻፻ አእላፋት 1,000,000 ፲፻፻፻ ትእልፊት 10,000,000 ፻፻፻፻ ትልፊታት 100,000,000 ፲፻፻፻፻ ምእልፊት 1,000,000,000