ከመንበሩ ላይ ተቀምጦ የምናየው ስእል ምስለ ፍቁር ወልዳ ብለን የምንጠራም የእመቤታችን የቅድስት ድንግል ማርያም ልጇን ኢየሱስ ክርስቶስን ታቅፋ የሚያሳይ ስእለ አድህኖ ነው ብየ ልጽፍ አሰብኩና ይህን የማያውቅ ሰው ሊኖር አይችልም የሚል ሃሳብ ውስጤን ስለሞገተው በቀጥታ ማስተላለፍ ወደፈለኩት ሃሳብ ገባሁ። ሰሞኑን ስለ ቅዱሳን ስእላት የተነሳውን የተዛባ ሃሳብ ባሰብኩ ጊዜ ይህን ጻፍኩ።
ይህን ስእል የሳለው ቅዱስ ሉቃስ እንደሆነ አባቶቻችን ነግረውን አምነን ተቀብለናል። አንድን ነገር ለማመን ማስረጃ እንደሚያስፈልገው ሁሉ በስሜት ሳይሆን ከቅዱስ መጽሐፍ ያገኘነውን እውነተኛ ታሪክ መሰረት በማድረግ ነው። ይኸው ወንጌላዊ በጽሑፍ ያስቀመጠልንን ቀጥሎ እናንብብ።
''በስድስተኛውም ወር መልአኩ ገብርኤል ናዝሬት ወደምትባል ወደ ገሊላ ከተማ፥ከዳዊት ወገን ለሆነው ዮሴፍ ለሚባል ሰው ወደ ታጨች ወደ አንዲት ድንግል ከእግዚአብሔር ዘንድ ተላከ፥ የድንግሊቱም ስም ማርያም ነበረ። መልአኩም ወደ እርስዋ ገብቶ፦ ደስ ይበልሽ፥ ጸጋ የሞላብሽ ሆይ፥ ጌታ ከአንቺ ጋር ነው፤ አንቺ ከሴቶች መካከል የተባረክሽ ነሽ አላት። እርስዋም ባየችው ጊዜ ከንግግሩ በጣም ደነገጠችና፦ ይህ እንዴት ያለ ሰላምታ ነው? ብላ አሰበች። መልአኩም እንዲህ አላት፦ ማርያም ሆይ፥ በእግዚአብሔር ፊት ጸጋ አግኝተሻልና አትፍሪ። እነሆም፥ ትፀንሻለሽ ወንድ ልጅም ትወልጃለሽ፥ ስሙንም ኢየሱስ ትዪዋለሽ። እርሱ ታላቅ ይሆናል የልዑል ልጅም ይባላል፥ ጌታ አምላክም የአባቱን የዳዊትን ዙፋን ይሰጠዋል፤ በያዕቆብ ቤትም ላይ ለዘለላም ይነግሣል፥ ለመንግሥቱም መጨረሻ የለውም። ሉቃ 1፥26'' ሙሉ መረጃ እንዲኖረን ከቁጥር አንድ ጀምሮ እስከመጨረሻው ብናነበው ሰአሊውን በደንብ እንረዳዋለን ብየ አስባለሁ።
እኔ ዘወትር ለጸሎት ለአገልግሎት ወደ ቤተመቅደስ ስገባ ይህን ስእል ስመለከት የማስታውሰው የሉቃስ ወንጌልን ነው ። እንዲሁም አስቀድሞ በትንቢት የተናገረውን ነቢዩ ኢሳኢያስን ነው ''ስለዚህ ጌታ ራሱ ምልክት ይሰጣችኋል፤ እነሆ፥ ድንግል ትፀንሳለች፥ ወንድ ልጅም ትወልዳለች፥ ስሙንም አማኑኤል ብላ ትጠራዋለች'' ኢሳ 7፥14
ከላይ ነቢዩም ሆነ ወንጌላዊው እየተናገሩ ያሉት በቀጥታ ስለ እመቤታችን መሆኑ ግልጽ ነው። ወንድ ልጅ ትወልዳለች የተባለችው እርሷ ናት ኢሳ 7፥14 የወለደችውም እርሷ ናት ሉቃ 2፥7 ቤተልሄም ሰብአ ሰገል ሲሄዱ ያገኙት ከእርሷ ጋር ነው። ማቴ 2፥11 ወደ ቤተመቅደስ ይዛው የሄደችው እርሷ ናት። ሉቃ 2፥22 በእርሱ ላይ የሚደርሰው መከራ ሰይፍ ሆኖ እንደሚቆርጣት የተነጋራት እርሷ ናት። ሉቃ 2፥34 ወደ ምድረ ግብጽ ይዛ የተሰደደደች እርሷ ናት። ማቴ 2፥13 በቤተመቅደስ ቢጠፋባት ስትጨነቅ የታየች እርሷ ናት። ሉቃ 2፥48 የመጀመሪያውን ተአምር እንዲያደርግ የጎደለውን እንዲሞላ የጠየቀች በሃዘን የተሞላውን ቤት ወደ ደስታ እንዲለወጥ ያደረገች እርሷ ናት። ዮሐ 2፥3 በመጨረሻው ሰዓት ከመስቀሉ ሥር የተገኘች ልጇም ኢየሱስ ክርስቶስ በዚያ በስቃይ ሰዓት ያልረሳት ለተመረጠው ለታማኙ ለቅዱስ ዮሐንስ እንዲንከባከባት የሰጣት እርሷ ናት። ዮሐ 19፥26
እንግዲህ እኛ የኦርቶዶክስ ተዋህዶ ልጆች የምናምነው ከላይ በቅዱስ መጽሐፍ የተጻፈውን እንድንረዳው እግዚአብሔር የመረጣቸው የጥበብ ሰዎች በስእል እንማርበት ዘንድ ያዘጋጁልን በመሆኑ ስለ ቅዱስ ቃሉ አክብረን እንጠቀምበታለን።
ለሁላችንም ማስተዋሉን ያድለን።
No comments:
Post a Comment