ሕዝበ እሥራኤል የፈጣሪያቸውን ህግና ሥርዓት መጠበቅ እየተሳናቸው ብዙ ጊዜ በስደትና በጦርነት ተቀጥተዋል። ይሁን እንጅ እግዚአብሔር አምላክ አስቀድሞ ለአባቶቻቸው የገባው ቃል ኪዳን ስላለ የጠፉ ቢመስሉም እንደገና ያበረታቸዋል።
ቅዱስ ዳዊት በመዝሙሩ የአባቶቹን ሃዘንና ሰቆቃ በምርኮ ሳሉ የደረሰባቸውንና ያደረጉትን አስታውሶ የተናገረውን ነው መነሻ ያደረኩት ''በባቢሎን ወንዞች አጠገብ በዚያ ተቀመጥን፤ ጽዮንንም ባሰብናት ጊዜ አለቀስን።በአኻያ ዛፎችዋ ላይ መሰንቆቻችንን ሰቀልን። የማረኩን በዚያ የዝማሬን ቃል ፈለጉብን፥ የወሰዱንም፦ የጽዮንን ዝማሬ ዘምሩልን አሉን። የእግዚአብሔርን ዝማሬ በባዕድ ምድር እንዴት እንዘምራለን?'' መዝ 137፥1
ሀገራችን ኢትዮጵያ በገጠማት ችግር ምክንያት ልጆቿ ስደትን እንደ ትልቅ እድል በመቁጠር በሰው ሀገር መኖርን ተለማምደዋል። ብዙዎች በገዛ ሀገራቸው የስደተኛነት ስሜት እየተሰማቸው የሰው ሀገር ይናፍቃሉ። ከዋና ከተማዋ አዲስ አበባ በመኪና ተጉዞ ቤተሰብ ማግኘት የማይታሰብ እየሆነ ነው። አዲስ አበባ ተውባለች ደምቃለች የሀገሪቱ ሰፊው ገጠራማ ክፍል ግን በሰላም እጦት ጭንቀት ላይ ይገኛል። ጦርነት፣ ርኃብ፣ ስደት ለእኛ ለኢትዮጵያውያን እንደ አዲስ ነገር የሚነገር ዜና አይደለም። በዚህም ምክንያት አንድ ሰው ተበደልኩ ብሎ ሲናገር ወይም አንዱ ስለሌላው መበደል ሃሳብ ቢሰጥ እንደቁም ነገር መቁጠር ካቆምን ሰነባብተናል። ይህ ሁሉ ችግር እያለ በዚህ ሰቆቃ ለበዛበት ማህበረሰብ የማይሆኑ አጀንዳዎችን የሚፈጥሩ አንዳንድ የቤተክርስቲያን አገልጋዮች በውዳሴ ከንቱ ተጠልፈው ''በቁስሉ ላይ እሾህ ስደድበት'' በሚመስል መልኩ ህዝቡን ግራ ያጋቡታል። ቢቻል ስለሃገር ሰላምና አንድነት መሥራት ይገባ ነበር ካልሆነም ህዝቡ ካለበት ችግር የሚወጣበትን ምክርና በጎ ሃሳብ ማቅረብ ሲገባ መለያየትን የሚያመጣ የግል ሃሳብ ማምጣት ለህዝብ ዴንታ ቢስ መሆን አይደለምን?
እውነት ለእኛ ለኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ልጆች በዚህ ሰዓት ጸሎት ነው መዝሙር ነው የሚያስፈልገው? ስሜትን ተወት አድርጎ በማስተዋል ነገሮችን ብናደርግ እግዚአብሔርም ይሰማናልና ቆም ብለን እናስብ።
መዝሙር ማለት ለእግዚአብሔር የሚቀርብ የደስታ ጸሎት ወይም ምስጋና ማለት ነው ''ደስ የሚለውም ማንም ቢኖር እርሱ ይዘምር'' ያዕ 5፥13 እውነት እኛ ኢትዮጳያውያን በዚህ ወቅት ደስተኞች ነን?
በዚህ ሰዓት ደስተኛ መስሎ ለመታየት መሞከር በህዝቡ ላይ እየደረሰ ያለውን ሰቆቃና መከራ ለመሸፈን ነው የሚመስለው። የማስተዋል ማነስ ሆኖ ነው እንጅ በዚህ ዘመን በዚህ ደረጃ ለውዳሴ ከንቱ መሽቀዳደም የመጥፎ ታሪክ አካል ሆኖ በታሪክ መዝገብ መጻፍ መሆኑን መገንዘብ ያስፈልግ ነበር።
ቅዱስ ያእቆብ በመልእቱ ''ከእናንተ መከራን የሚቀበል ማንም ቢኖር እርሱ ይጸልይ'' ያዕ 5፥13 ይለናል እኛ ደግሞ ሰላም እንደተረፈው ደስታ እንደሞላው እንዘምር እንላለን ታዲያ እግዚአብሔር እንዴት ይታረቀን?
ከላይ እንደጠቆምኩት ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ባልተለመደ መልኩ ከቤተክርስቲያናችን የጌታ አበይት በዓላት መካከል በልደቱ በዓል እለት ክርስቲያኖች ከአጥቢያቸው እርቀው በዝማሬ በምስጋና እናሳልፋለን የሚለው ሃሳብ ከምን አንጻር እንደሆነ ብዙ ምዕመናንን ግራ እያጋባ ይገኛል። የሚያዘጋጁት አካላት ምናልባት በቅንነት አስበውት ነው እንበል ፈቃድ የሰጣቸው አካል እንዴት ፈቀደላቸው? የልደት በዓል ሥነስርዓት ያለው መንፈሳዊ አገልግሎቱም እንዴት መቅረብ እንዳለበት የተዘጋጀ መሆኑ እየታወቀ በጾም በጸሎት እንዲሁም በማህሌትና በቅዳሴ ልናሳልፈው የሚገባውን አቢይ በዓል ዘመኑ በፈጠረው የልጆች ጨዋታ በሚመስል እንዲከበር ለምን ተፈለገ?
ብዙዎች በቋሚነት ይህን መርሃ ግብር ለተለያዩ ዓላማዎች ለማዋል እየተጠቀሙበት ነው መረጃ አይናቅም የኛ ትልቁ ችግር ''ሳይቃጠል በቅጠል'' እንደሚባለው ቀድሞ በቀላሉ ህዝብን ማረጋጋት እየተቻለ ምንም አይመጣም በሚል በመዘናጋት ነገሮች አቅጣጫቸውን እንዲስት እናደርጋለን።
የልደትን በዓል ብዙ ምእመናን በቤተክርስቲያን ተገኝተው እንደ በዓለ ትንሣኤ አክፍለው የሚያስቀድሱበትና ቅዱስ ሥጋውንና ክቡር ደሙን የሚቀበሉበት እንደሆነ ይታወቃል እውነት ይህ ፕሮግራም አባቶቻችን ከሰሩልን ሥርዓት በልጦ ነው በድንገት አምጥተን የደረብነው?
ይህ ባህል ትላንት በኢትዮጵያ ተጀምሮ ዛሬ ላይ በመላው ዓለም በሚገኙት የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ አብያተክርስቲያናት ተስፋፍቶ እንደ ልምድ እየተወሰደ ይገኛል ወጣት ልጆቻችን ይህን እያዩ የሚያድጉ ከሆነ እውነተኛውን የቅዱስ ያሬድ ዜማና ሥርዓተ ማህሌት እየዘነጉ ነው የሚመጡት ስለዚህ የሚመለከተው የቤተክርስቲያኒቱ የበላይ አካል እርምት ሊሰጥበት ይገባል።
ወደ ጉዳዩ ስመለስ ከላይ እንደገለጽኩት ሃሳቡ በቅንነት ቀርቦ ከሆነ ሌላ ጊዜ መርጦ ማድረግ ይቻላል። ነገር ግን ለበዓለ ልደቱ የተዘጋጀውን ቃለ እግዚአብሔር መስማት ካለመፈለግ በሚመስል መልኩ አብያተክርስቲያናትን ባዶ አድርጎ እንዲሁም የቤተክርስቲያን አባቶች በሌሉበትና በማይመሩት መልኩ ጉባኤ ማዘጋጀት ለነገዋ ቤተክርስቲያን ፈተና ይዞ እንዳይመጣ ይታሰብበት።
በባለፈው ዓመት የመርሃግብሩ መጀመሪያ ላይ ቅዱስ ፓትርያርኩ ሳይቀር መገኘታቸውን አይተናል ይሁን እንጅ የብዙዎች አስተያየት የነበረው ለሚዲያ ፍጆታ እንጅ ተገቢነቱ ታምኖበት እንዳልነበረ ነው።
ቤተክርስቲያን ብዙ ፈተና የተጋረጠባቸው የአደባባይ በዓላት አሏት እነዚያን አጠናክሮ ለህዝቡ ማስገንዘብ እንጅ የነበረውን የሚሸረሽር ልምድ ማምጣት የለብንም። መስቀልና ጥምቀት ከቀድሞ ጀምሮ ከልጅ እስከ አዋቂ በደመቀ ሁኔታ ስናከብራቸው የኖሩ የአደባባይ በዓላቶቻችን ናቸው ይልቁንም እነዚህን በዓላት ህዝቡ ወደ መብልና መጠጥ ሳያዘነብል በተሰራው ሥርዓት መሰረት በምስጋናና በዝማሬ እንዲያከብር ልናስተምረው ይገባል።
በዚህ ወቅት የመንግሥት አካላት የሀገሪቱ ችግር በዝቶ ለመፍትሄ ውሉ ጠፍቶባቸው በሚዳክሩበት ሰዓት የሃይማኖት ተቋማት በህዝቡ መካከል ሰላምና አንድነት እንዲመጣ መንግሥትን ማገዝ ሲገባቸው ደጋፊና ተቃዋሚ ሆኖ ህዝብን ግራ ማጋባት ከእግዚአብሔር ህግ ጋር የተጻረረ አካሄድ ነው። የእምነት ተቋማት የሚቋቋሙት ለህዝብ ነው። ስለዚህ ህዝቡ የተረጋጋና ሰላም የሰፈነበት ሀገር እንዲኖረው ከፈለገ አንድ ሆኖ የመንግሥትንም ሆነ የሃይማኖት መሪዎች በአግባቡ ምሩን ብሎ ድምጹን ማሰማት መብቱ መሆኑን ሊያውቀው ይገባል። እርስበርስ እየተጠላለፈ የግለሰቦች መጠቀሚያ መሆኑን ማቆም አለበት።
ጦርነት ለአንድ ሀገር የሁሉም ችግሮች መነሻ ነው። ጦርነት ካለ መተማመን ይጎድላል፣ ጦርነት ካለ በሰላም ወጥቶ መሥራት አይቻልም፣ጦርነት ካለ የሀገር ሀብት በከንቱ ይባክናል፣ ጦርነት ካለ ህግና ሥርዓት ይጓደላል፣ ጦርነት ካለ በፍትህ እጦት ሕዝብ ይበደላል፣ጦርነት ካለ የሕዝብ ሰላምና አንድነት ይጠፋል ወዘተ ብዙ ማለት እንችላለን። ስለዚህ በአሁኑ ሰዓት ለኢትዮጵያ የሚያስፈልጋት ጦርነት እንዴት ይቁም? የአንድ ሀገር ልጆች እርስበርስ መገዳደላቸው እንዴት ይቁም ብሎ የሰላምና የእርቅ ጥሪ ማስተላለፍ እንጅ እኔን ምን አገባኝ ብሎ የደስታ መዝሙር ለመዘመር ነጭ ልብስ ለብሶ መሰለፍ በየቀኑ በሚሞቱት ወገኖች እሬሳ ላይ እንደመቆም ይቆጠራል።
No comments:
Post a Comment