ቅዱሱ መጽሐፋችን መጽሐፍ ቅዱስ ወንድም ወንድሙን መግደል የጀመረበትን ምክንያት በግልጽ ይነግረናል ዘፍ 4፥8 ነገር ግን ምክንያቱን ለመቀበል ከአእምሮ በላይ በመሆኑ እጅግ ያስደንቃል። እንኳን ሰው ይቅርና እንስሳ የራሱን ወገን በበጎ የሚያይበት ተፈጥሯዊ ስጦታ ታድሏል፦ ነገር ግን የሰው ልጅ ከእንስሳት አንሶ ሰው ሰውን እየበላ የክፋት እርሃቡን ለማስታገስ ሲሮጥ ማየት እጅግ ያሳዝናል። ሰላማውያን የምንባለውም እኛ ከመደጋገሙ የተነሳ እየለመድነው በመምጣታችን እንደቁም ነገር ለመቁጠር እየተቸገርን እንደሆነ በግልጽ እየታየ ነው። ሰሞኑን በኦሮሚያ ክልል ምሥራቅ አርሲ ዞን በተለያዩ ወረዳዎች ሥር የሚገኙ በርካታ ምዕመናን በጽንፈኞች እንደተገደሉ ሰምተናል። ይሁን እንጅ ከመንግሥትም ሆነ ከቤተክህነት ለሟቾችም ሆነ ለቤተሰቦች እንደዜጋ እና እንደ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ምዕመን ክብር እንዳልተሰጣቸው በተላለፉት መልእክቶች መረዳት ይቻላል። የኦርቶዶክስ ተዋህዶ ምዕመን መገደሉ በዚህ ደረጃ መቅለሉ በጣም ያሳዝናል።
የንፁሐን ደም የሚያመጣውን ወይም ያመጣውን መዘዝ ማወቅና መረዳት ለመንግሥትና ለሃይማኖት መሪዎች እንዴት ተሳናቸው? እንዲሁም ይህን በየጊዜው የሚፈስ ደምና እንባ የምንመለከት ወገኖች እንዴት በጋራ መጮህ አቃተን? ብለው የሚጠይቁ ብዙዎች ናቸው። ህጻናት፣ እናቶች፣ አባቶች፣ ዲያቆናት፣ ካህናት፣መነኮሳት (እስከ አሁን ጳጳሳትን አይጨምርም ለወደፊቱ ግን ስጋት አለን) ናቸው ደማቸው እየፈሰሰ ያለው። ማነው የንጹሐንን ደም ከመፍሰስ መታደግ ያለበት? የመንግስትም ሆነ የሃይማኖት መሪዎች ዘመኑን የዋጀ የአመራር ሥርዓት መዘርጋት ካልቻላችሁ ኃላፊነታችሁን እየተወጣችሁ አይደለም። ህዝብ መሪ አለኝ ብሎ ከልፋቱ ጥሪቱን ግብር እየከፈለ የሚኖረው ሰላምና ደህንቱን የሚያስጠብቅለት አካል አለኝ ብሎ አምኖ ነው።
ያለንበት ዘመን ለመረጃ እጅግ የቀረበ በመሆኑ ተጠንቅቆ ኃላፊነትን መወጣት ካልቻሉ መዋረድና ከክብር ማነስ አለና እግዚአብሔር ያከበራችሁ የበላዮቻችን እባካችሁ እራሳችሁን ጠብቁ። በዙሪያችሁ ያሉ አማካሪዎቻችሁንና የመረጃ ሰዎቻችሁን ፈትሹ ምክንያቱም አንዳንዶቹ ሆድ አደሮች በመሆናቸው ከእናንተ የሚያገኙትን ሥጋዊ ጥቅም በማሰብ መሬት ላይ ያለውን ሳይሆን ለእናንተ የሚመቸውን እየመረጡ ስለሆነ የሚያቀብሏችሁ እባካችሁ ሆዳቸው አምላካቸው ከሆኑ አማካሪዎች ይልቅ የሃይማኖት አባቶቻችን መዝሙረ ዳዊትና ውዳሴ ማርያምን አጥብቃችሁ ያዙልን። የአባቶቻችን ሥም ሲጎድፍ መስማት ለእኛ ለልጆቻችሁ የአእምሮ ህመም በመሆኑ ለመንጋውና ለራሳችሁ ስትሉ እባካችሁ ተጠንቀቁ። ዛሬ እንደሃይማኖት መሪ የተናቀና የተዋረደ እንዲሁም የተጠላ አለ ለማለት አያስደፍርም። በሄድንበት ቦታ ሁሉ የቀደመውን ክብር ማግኘት ቀርቶ መ መልካም ፊት ማየት እየናፈቀን ነው::
የሀገር መሪዎች የተቀመጣችሁበት ወንበር ያለፉትን የበላ ከነሱ አልፎ ለትውልዶቻቸው የተረፈ እዳ በደል ያለበት በመሆኑ አትመኩበት ይልቁንም ከራሳችሁ አልፎ ለትውልዶቻችሁ መከራና ችግር እንዳታወርሱ የህዝብን እሮሮና ለቅሶ ቸል አትበሉ።
መንጋውን የማይረሳው እግዚአብሔር የንጹሐንን ደም እንደሚበቀል እናምናለን፦ ነፍሳችሁ ያለችበትን ደማችሁን በእርግጥ እሻዋለሁ፤ ከአራዊት ሁሉ እጅ እሻዋለሁ፤ ከሰውም እጅ፥ ከሰው ወንድም እጅ፥ የሰውን ነፍስ እሻለሁ። የሰውን ደም የሚያፈስስ ሁሉ ደሙ ይፈስሳል፤ ሰውን በእግዚአብሔር መልክ ፈጥሮታልና ዘፍ 9፥5 ተብሎ እንደተጻፈ ገዳዮች በሰፈሩት ቁና መቀበላቸው አይቀሬ ነው።
ኢትዮጵያ ሀገራችን ልጆቿ በረሃብ፣ በጦርነት፣ በስደት፣ በአክራሪ ጽንፈኞች ወዘተ ደማቸው የሚፈስባት አኬልዳማ የደም መሬት የሐ ሥ 1፥19 ከሆነች ዘመናት ተቆጠሩ እውን ችግሩን ለመረዳት ያለፈው ዘመን በቂ አልነበረምን? የዘረኝነቱ የእምነት ጽንፈኝነቱ እውን ከመንግሥት አቅም በላይ ነውን? የመንግሥት ኃላፊነት የአንዲትን ሀገር ህዝቦች በእኩልነት ወጥተው ወርደው ሀገራቸውን በማልማት የልማቱ ተጠቃሚ እንዲሆኑ ማድረግ ሆኖ ሳለ አንዱ ሌላውን እየገፋ እንዲኖር የሚያደርግ ሥርዓት ዘርግቶ አንድ ህዝብ እርስ በእርሱ እንዲጫረስ ማድረግ በምንም መልኩ ተቀባይነት የለውም። ገዳዮች አቅም እንዲኖራቸው መብት በመስጠት፤ ንፁሐን እራሳቸውን እንዳይከላከሉ የተለያየ ሥም በመለጠፍ አቅም በማሳጣት በጭካኔ እየተጨፈጨፉ እንደሆነ በተደጋጋሚ አይተናል፦ ለምሳሌም በሻሸሸመኔ፣ በዝቋላ፣ በአርሲ ወዘተ በሚባሉት አካባቢዎች የመንግሥት ወታደሮች የንፁሐንን ቤት በመፈተሽ ምንም ዓይነት እራሳቸውን የሚከላከሉበት መሳሪያ እንዳይኖራቸው በማድረግ ለጥቃት መጋለጣቸውን በየጊዜው ሲገልጹ ሰምተናል።
ገዳይ ሁልጊዜም ገዳይ ነው ምክንያቱም ሰብአዊነቱ የተወሰደ በመሆኑ የሰው ደም አያስጨንቀውም፤ አያስደነግጠውም ከዚህም በላይ የሚገድልበት ዓላማ ስላለው ምንም እንኳን የሰው ደም አፍስሶ የሰላም እንቅልፍ መተኛት የማይችል ቢሆንም በመግደሉ ስይጣናዊ እርካታ ያገኛል፦ ነገር ግን የሰው ደም እንዲፈስ በተለያየ መንገድ የፈቀዱ፣ መከላከል ሲገባቸው የንጹሐንን ሞት እንደ ቀላል በመቁጠር አንዲት ገጽ የመግለጫ መልእክት ይዘው ወደ ሚዲያ በመውጣት የሃዘንተኞችን ልብ የሰበሩ ለገዳዮች እውቅና እንደሰጡ ያስቆጥርባቸዋል።
ዛሬ ቤተክርስቲያን የገንዘብ ባለፀጋ ነች። አገልጋዮች ከምዕመናን በተሻለ የኑሮ ደረጃ እንደሚገኙ ብዙ ማስረጃ ማቅረብ ይቻላል። የሚያበራየውን በሬ አፉን አትሰር ዘዳ 25፥4 ተብሎ እንደተጻፈ አገልጋዮች የሚገባቸውን ማግኘታቸው ወንጀል አይደለም ነገር ግን በሀብት መብዛት ዝንጋኤ የሚመጣ ከሆነ ከጥቅሙ ጉዳቱ በብዙ ያመዝናል። ምድራዊ ክብርና ዝና እንዳይጎድልብን ብለን የህዝብን ጩኸት የምናፍን ከሆነ ከገዳዮች ወገን ነው የምንመደበው። ህዝብ ተፋቅሮና ተሳስቦ እንዲኖር የሃይማኖት መሪዎች ትልቅ ሚና ሊኖራቸው ይገባል። የመንግሥትን ጉዳይ ለማስፈጸም የሚወጡ የሚወርዱ የሃይማኖት መሪዎች እግዚአብሔርን አያውቁትም።
በታላቁ ነቢይ በቅዱስ ሕዝቅኤል እንዲህ የሚል ተጽፏል፦ የሰው ልጅ ሆይ፥ ትንቢት ተናገር፥ በእስራኤል እረኞች ላይ ትንቢት ተናገር፥ እረኞችንም እንዲህ በላቸው፦ ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ ራሳቸውን ለሚያሰማሩ ለእስራኤል እረኞች ወዮላቸው! እረኞች በጎችን ያሰማሩ ዘንድ አይገባቸውምን? ጮማውን ትበላላችሁ ጠጕሩንም ትለብሳላችሁ፥ የወፈሩትን ታርዳላችሁ፤ በጎቹን ግን አታሰማሩም። የደከመውን አላጸናችሁትም የታመመውንም አላከማችሁትም የተሰበረውንም አልጠገናችሁትም የባዘነውንም አልመለሳችሁትም የጠፋውንም አልፈለጋችሁትም በኃይልና በጭቈናም ገዛችኋቸው። እረኛንም በማጣት ተበተኑ፥ ለምድርም አራዊት ሁሉ መብል ሆኑ፥ ተበተኑም። በጎቼ በተራሮች ሁሉና በረዘሙ ኮረብቶች ሁሉ ላይ ተቅበዝብዘዋል፥ በጎቼም በምድር ፊት ሁሉ ላይ ተበትነዋል፤ የሚሻም የሚፈልግም አልነበረም። ስለዚህ፥ እረኞች ሆይ፥ የእግዚአብሔርን ቃል ስሙ፤ ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ እኔ ሕያው ነኝና እረኛ ስለሌለ እረኞቼም በጎቼን ስላልፈለጉ እረኞችም ራሳቸውን እንጂ በጎቼን ስላላሰማሩ፥ በጎቼ ንጥቂያ ሆነዋልና፥ በጎቼም ለምድር አራዊት ሁሉ መብል ሆነዋልና ስለዚህ፥ እረኞች ሆይ፥ የእግዚአብሔርን ቃል ስሙ፤ ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ እነሆ፥ በእረኞች ላይ ነኝ፥ በጎቼንም ከእጃቸው እፈልጋለሁ፥ በጎቼንም ከማሰማራት አስተዋቸዋለሁ። ከዚያም ወዲያ እረኞች ራሳቸውን አያሰማሩም፤ በጎቼንም ከአፋቸው አድናለሁ፥ መብልም አይሆኑላቸውም። ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላልና፦ እነሆ፥ እኔ ራሴ በጎቼን እሻለሁ እፈልግማለሁ።እረኛ በተበተኑት በጎች መካከል ባለ ጊዜ መንጋውን እንደሚፈልግ፥ እንዲሁ በጎቼን እፈልጋለሁ፤ በደመናና በጨለማ ቀን ከተበተኑት ስፍራ ሁሉ አድናቸዋለሁ። ሕዝ 34፥2
ሰፊ ሀገር መልክአ ምድሩም ሆነ የአየር ጠባዩ የተወደደ ምድር ታድለን ሳለ መልካም መሪ በማጣት ልዩነታችንን ውበት አድርገን ተፋቅረን በሰላም መኖር እየቻልን ኢትዮጵያ ሀገራችንን አንዱ አንዱን እየገፋ ፍጥረት በሰላም የማይኖርባት ሀገር አደረግናት።
'' የሰላም አምላክ ሆይ ሰላምህን ስጠን''


No comments:
Post a Comment