Friday, November 7, 2025

ክፉውን በመልካም አሸንፍ እንጂ በክፉ አትሸነፍ ሮሜ 12፥1

ከአባቶቻችን የወረስነው አባባል ''የወደቀ ዛፍ ምሳር ይበዛበታል'' ይላል። እውነትም ወድቆ የተገኘ ነገር ሁሉ የፈቀደውን ያደርግበታል ስለዚህ ለማንም የሚጠቅመው ወድቆ አለመገኘት ነው። 

ክፉ የሚባለው ጨካኝ፣ የማይራራ፣ እራስ ወዳድ ሃዘኔታ የሌለው ወዘተ ማለት ሲሆን መልካም ማለት ደግሞ ማዘን፣መራራት፣ ለሌላው ማሰብ፣ በኔ ሊደረግ የማይገባውን በሌላው አላደርግም ወዘተ ብሎ እራስን መግዛት ማለት ነው። አሸናፊነት ሁልጊዜ የበላይ መሆን ወይም ከሌላው በልጦ መገኘት ብቻ አይደለም። ክፉ ለሚያደርግ መልካም መመለስ አሸናፊነት ነው። የበደለን ይቅር ማለት አሸናፊነት ነው። የተቀሙትን መተው አሸናፊነት ነው ከዚህ አንጻር ብዙ ማለት ይቻላል። 

ሰው መሸነፍ የሚጀምረው ተስፋ መቁረጥ ውስጥ የገባ እለት ነው። በተለይ ክርስቲያን በፍሱም ተስፋ መቁረጥ የለበትም። ቅዱስ ጳውሎስ ለእብራውያን በጻፈው መልእክቱ'' እንግዲህ እነዚህን የሚያህሉ ምስክሮች እንደ ደመና በዙሪያችን ካሉልን፥ እኛ ደግሞ ሸክምን ሁሉ ቶሎም የሚከበንን ኃጢአት አስወግደን፥ የእምነታችንንም ራስና ፈጻሚውን ኢየሱስን ተመልክተን፥ በፊታችን ያለውን ሩጫ በትዕግሥት እንሩጥ፤ እርሱ ነውርን ንቆ በፊቱም ስላለው ደስታ በመስቀል ታግሦ በእግዚአብሔር ዙፋን ቀኝ ተቀምጦአልና። በነፍሳችሁ ዝላችሁ እንዳትደክሙ፥ ከኃጢአተኞች በደረሰበት እንዲህ ባለ መቃወም የጸናውን አስቡ'' እብ 12፥1 ብሎ እንደተናገረው ፈተና በማንኛውም መልኩ ቢገጥመን ልናሸንፈው እንደምንችል ከአባቶቻችን ተምረናል።

ክርስትና ከጌታችን ከአምላካችንና ከመድኃኒታችን ከኢየሱስ ክርስቶስ ጀምሮ የደም ዋጋ እየተከፈለበት ዛሬ ላይ የደረሰ ሃይማኖት ነው። ዛሬ በሰዎች ኃጢአት መብዛት የሃሳብ መለያየት በዝቶ ሁሉም የግል ሃሳቡን እያፈለቀ ብዙ ቤተ እምነት (Denomination) ቢፈጠርም መነሻው ግን አንድ ነው። ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ ለኤፌሶን ክርስቲያኖች በጻፈው መልእክቱ  ''በመጠራታችሁ በአንድ ተስፋ እንደ ተጠራችሁ አንድ አካልና አንድ መንፈስ አለ፤አንድ ጌታ አንድ ሃይማኖት አንዲት ጥምቀት፤ከሁሉ በላይ የሚሆን በሁሉም የሚሠራ በሁሉም የሚኖር አንድ አምላክ የሁሉም አባት አለ'' ኤፌ 4፥5  ብሎ እንደተናገረው የዓለማት ፈጣሪ እግዚአብሔር አንድ ነው። ወደ እርሱም የምንቀርብባት መንገድ አንዲት ናት እርስዋም አባቶቻችን የተጓዙባት ለነፍሳቸውም እረፍት ያገኙባት ናት። እርስዋ ቀዳማዊት ናት ደኃራዊት አይደለችም አዳም፣ አቤል፣ሴት፣ሄኖክ፣ኖህ፣አብርሃም፣ይስሃቅ፣ ያዕቆብ፣ ሙሴ፣ዳዊት፣ነቢያት፣ሐዋርያት የተጓዙባት ቀጥተኛ መንገድ ናት። ''ግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ በመንገድ ላይ ቁሙ ተመልከቱም፥ የቀደመችውንም መንገድ ጠይቁ፤ መልካሚቱ መንገድ ወዴት እንደ ሆነች እወቁ፥ በእርስዋም ላይ ሂዱ፥ ለነፍሳችሁም ዕረፍት ታገኛላችሁ፤ እነርሱ ግን፦ አንሄድባትም አሉ'' ኤር 6፥16


ዛሬም እኛ ልጆቻቸው ከአባቶቻችን የወረስናትን መንገድ ትተን በጊዜያዊ ጥቅም ተደልለን ከእውነት ፈቀቅ ልንል አይገባም። ከዚህች መንገድ መውጣት ትልቁ ሽንፈት ነው። ከሰዎች የሚመጣብን ፈተና ሁሉ በእግዚአብሔር ዘንድ ዋጋ የሚያስገንል በመሆኑ ደስ ሊለን ነው የሚገባው። ሲሰድቡን፣ ሲያሳድዱን፣ ሲገድሉን በሥሙ ስለሆነ አሸናፊዎች እኛ ነን። ጌታችን አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ እንዳስተማረን '' ሲነቅፉአችሁና ሲያሳድዱአችሁ በእኔም ምክንያት ክፉውን ሁሉ በውሸት ሲናገሩባችሁ ብፁዓን ናችሁ።ዋጋችሁ በሰማያት ታላቅ ነውና ደስ ይበላችሁ፥ ሐሴትም አድርጉ፤ ከእናንተ በፊት የነበሩትን ነቢያትን እንዲሁ አሳድደዋቸዋልና'' ማቴ 5፥11

መከራችን የበዛው ከጠላቶቻችን መበርታት ሳይሆን ከእኛ ስንፍና መሆኑ ግልጽ ነው። ሰነፍ የሚለውን ቃል አባቶቻችን የተጠቀሙበት ቅዱስ መጽሐፍ ላይ ተጽፎ እንዳነበብነው ለከንቱ ነገር የሚተጋ የሚጠቅመውን የማያውቅ ባለው ነገር የማይጠቀም ወይም የማያመሰግን ማለት ሲሆን ወደ እኛ ስናመጣው ዘመኑ በሰጠን ስልጣኔ ተጠቅመን አንድነትን፣ መተባበርን፣ መረዳዳትን፣ መተሳሰብን፣ መንፈሳዊ እድገትን ልናመጣ ሲገባን ለጊዜያዊ ከንቱ ነገር ትኩረት በመስጠት በዘረኝነት፣ በአድመኝነት፣ በጎጠኝነት፣ በመለያየት ምክንያት በአንድነት መቆም ተስኖን ክቡር የሆነው የሰው ህይዎት እንደቀላል ሊቆጠር ችሏል። 

ቤተክርስቲያናችን በአሁኑ ዘመን ከመቸውም በላይ በሰው ኃይልና በኢኮኖሚ ጠንካራ የምትባል ቤተክርስቲያን ነች። አገልጋዮቿ እንደትላንቱ የሰው እጅ የሚያዩ ሳይሆን ከህዝቡ በተሻለ የኢኮኖሚ ደረጃ የደረሱበት ዘመን ላይ ነው ያለነው። ይሁን እንጅ የትላንቱ አገልግሎትና የእምነት ጽናት በአንዳንዶች ላይ የማይታይ በመሆኑ ብዙ ምዕመናን በመሰናከል ከቤተክርስቲያን ሲወጡ እናያለን። ሰው የሚሸነፈው ከእግዚአብሔር ይልቅ ተድላን በመፈለጉ ምክንያት ነው።

ምድራዊ ክብር የሚያኮራ ባይሆንም ሰው የሚፈልገውን ካገኘ ደስ ተሰኝቶ ለእግዚአብሔር ክብር መስጠት አለበት። እግዚአብሔርን ማክበር ማለት ደግሞ እራስን ከማክበር ይጀምራል። የእግዚአብሔር ባለሟል ተብሎ ለከንቱ ነገር መሮጥ ትልቅ ሽንፈት ነው። እውነተኛ የእግዚአብሔር አገልጋይ የሚባለው በስው ፊት ለእግዚአብሔር ታማኝነቱን ያሳየ እንደሆነ ነው። በሰው ፊት እውነትን ለመናገር የሚያፍር ለጥቅም ብሎ እውነትን ለመናገር የሚፈራ እርሱ የተሸነፈ ነው።  ''እላችሁማለሁ፥ በሰው ፊት የሚመሰክርልኝ ሁሉ፥ የሰው ልጅ ደግሞ በእግዚአብሔር መላእክት ፊት ይመሰክርለታል፤ በሰውም ፊት የሚክደኝ በእግዚአብሔር መላእክት ፊት ይካዳል። ሉቃ 12፥8''
ዛሬ እንዳለመታደል ሆኖ ትልልቆች የምንላቸው ሳይቀር እግዚአብሔርን ትተው የሰው ምስክር ሲሆኑ እያየን ነው። ከዚህ የበለጠ ሽንፈት አለ? ክርስቲያኖች ሲሳደዱ፣ ሲታረዱ፣ ሲገደሉ ዝም የሚል የሃይማኖት አገልጋይም ሆነ ክርስቲያን እግዚአብሔርን እየካደ እንደሆነ ማወቅ አለበት። ከቃሉም እንደምንረዳው የእግዚአብሔርን መንግስት አያይም። ስለዚህ ክርስቲያኖች እናስተውል ፤ ያለንበት ዘመን የተመረጡት የሚወድቁበት የተናቁት የበረቱበት ነውና ''ዘመኑን ዋጁ'' ተብሎ እንደተጻፈ ከመሰናክል እንድንድን በእምነታችን ጸንተን እንኑር።

No comments:

Post a Comment