ሃይመነ አሳመነ ፤ ካለው የግዕዝ ግሥ የተገኘ ሲሆን “ማመን፣ መታመን፣ እምነት፣ ጽኑ ተስፋ፣ በልብ በረቂቅ ሐሳብ የሚሣል ማለት ነው፡፡ ትርጉሙም በአንድ አምላክ ማመን እና ለአንድ አምላክ መታመን ማለትን ያመለክታል ፤ በዓይናችን ለምናየው ለግዙፉ ዓለምና ለማይታየው ለረቂቁ ዓለም ፈጣሪ አስገኝ ፣ መጋቢ አለው ፤ እሱም እግዚአብሔር ነው ብሎ ማመን ማለት ነው ።(አለቃ ኪዳነ ወልድ ክፍሌ መዝገበ ቃላት፣ ገጽ ፫፻፷፱) ይህ የሁሉ ፈጣሪ ደግሞ እግዚአብሔር ነው! ታዲያ ሁሉን ያስገኘ (የፈጠረ) እግዚአብሔር መሆኑን ያወቅነው በሃይማኖት ነው፤ በእምነት ነው፤ በኋላም “መንግሥተ ሰማያትን ያወርሰናል” ብለን ጽኑ ተስፋ እናደርጋለን፡። ሃይማኖት የሚፈጸም፣ የሚሆን፣ በዓይን የማይታይ፣ በሥራ የሚገለጥ ረቂቅ የሆነ ነው፡፡
ሃይማኖት ከእግዚአብሔር ጋር የምንገናኝበት ረቂቅ የሆነ (በዓይን የማይታይ) መንገድ ነው፤ መንገድ ሩቅ እና ሩቅ ያሉትን ሰዎች እንደሚያገኛኝ ሃይማኖትም የፍጥረታት ፈጣሪ እግዚአብሔርን እና እኛን ሰዎችን ስለምታገናኘን በመንገድ ተመሰለች፡፡
ስለ ሃይማኖት በጥቂቱ ገለጽን እንጂ ሃይማኖት ብዙ ምሥጢር እና ትርጉም ያላት ናት! እምነትን (ሃይማኖትን) ከምግባር ጋር ማጣጣም ያስፈልጋል፤ እምነትና ሥነ ምግባር አብረው ሲሆኑ ነው እምነታችን ጽኑ ሆኖ ኃይልና ብርታት የሚሆነን፤ ስለዚህ ሃይማኖታችንን በሥራ ሊገለጥ ያስፈልጋል፡፡
ቅዱስ ጳውሎስ ለኤፌሶን ክርስቲያኖች በላከው መልእክቱ ‹‹..ፍሬ ከሌለው ከጨለማ ሥራ ጋር አትተባበሩ…›› በማለት እንደ መከራቸው እምነታችን በሥራ የተገለጠ ፍሬን የሚያፈራ፣ ጨለማ ከተባለ ክፉ ምግባር መለየት እንዳለበት አስተምሮናል፡፡ (ኤፌ.፭፥፲፩)
እንዲሁም ባሕል ማለት የአንድ ኅብረተሰብ አኗኗር ነው። እንደ የሰው ልጅ ጥናት «ባህል» የኅብረተሠቡ ቋንቋ ፣ ሥነ ጥበብ ፣ ሥነ ጽሑፍ ፣ ሙዚቃ ፣ ጭፈራ ፣ ቴክኖሎጂ ፣ አበሳሰል ፣ አለባበስ፣ ስነ ሕንጻ ፣ ሕግ ፣ አስተያየት፣ ፍልስፍና ፣ አፈ ታሪክ እና ብዙ ሌሎች ረገዶች ያጠቅልላል።
ከላይ እንደተጠቀሰው ባህልና ሃይማኖት ለአንድ ህዝብ አስፈላጊና ከትውልድ ወደ ትውልድ የሚሸጋገር መልካም ቅብብል መሆኑ የታመነ ነው ይህን ሲባል ግን ባእድ አምልኮንና ጎጅ ባህልን አይጨምርም።
ይህን መልእክት ለማስተላለፍ የወደድኩት ከጊዜ ወደ ጊዜ እየታየ ያለው የሃይማኖትና የባህል መቀላቀል እንዲሁም ጥንት የነበረው የሁለቱ እሴቶች መከባበር እየጠፋ በመምጣቱ አሳሳቢ ሆኖ ስላየሁት ነው። ሁሉም ነገር ያለቦታው መልካም እንደማይሆን የታመነ ነው ስለዚህ መንፈሳዊውን ከባህላዊው ስንቀላቅለው የሁለቱንም ውበትና መልካም ነገር ያጠፋዋል።
በተለይ የሃይማኖታዊ በዓላቶቻችን ላይ እየተደረቡ ያሉ ባህላዊ እሴቶች ቁጥጥር ካልተደረገባቸው አንዱ አንዱን እንዳያጠፋው ያሰጋል። ለምሳሌ በዓመት አንድ ጊዜ የምናከብረው የጥምቀት በዓል ሃይማኖታዊ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን በዓል መሆኑ ይታወቃል ነገር ግን በበዓሉ እለት የሚታየው ሁኔታ የጌታ ጥምቀትን ሳይሆን ሀገራዊ የድል መታሰቢያ በዓል ነው እየመሰለ የመጣው። ታቦት ቆሞ መድረክ ላይ ቃለ እግዚአብሔር መተላለፍ እንዲሁም ህዝቡ ቃለ እግዚአብሔር መስማትና እየዘመረ በዓሉን ማክበር ሲኖርበት ጥምቀተ ባህሩ ባዶ ሆኖ በዙሪያው ባሉ መጠጥ ቤቶችና ምግብ ቤቶች ጊዜውን ማሳላፉ ከሃይማኖቱ ሥርዓት ጋር የሚጋጭ ነው በተለይ ደግሞ ታቦተ ህጉ በቆመበት ሥፍራ የተለያዩ የመንግሥት ባለሥልጣናት የሚያስተላልፉት መልእክት ምንም የእንኳን አደረሳችሁ መልእክት ቢሆንም ሌላ መድረክና ቦታ ቢዘጋጅለት መልካም ይሆናል። ወይንም ደግሞ ታቦታቱ ከመንበረ ክብራቸው ሳይነሱ እንዲህ ዓይነቶቹ መሰል ፕሮግራሞች ቀድመው ቢጠናቀቁ ሰውን ከመሰናከል መጠበቅ ያቻላል።
ቤተክርስቲያን ከመንግሥት ጋር ተባብራ መሥራቷ የሚወገዝ ባይሆንም ነገር ግን ሃይማኖታዊ ሥነ ሥርዓት ከፍተኛ ጥንቃቄ የሚጠይቅ በመሆኑ ቀድሞ ከሃይማኖቱ ሥርዓት ጋር የማይጋጭ ፕሮግራም ማውጣት የቤተክርስቲያን መሪዎች ተቀዳሚ ኃላፊነት ነው።
ከዚህም በተጨማሪ በየዓመቱ በሚካሄዱት የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን በዓላት ወቅት የሚዘጋጁ ዓለማዊ ዝግጅቶች ትምህርት ሊሰጥባቸውና ቤተክርስቲያኗ የአቋም መግለጫ ልታወጣበት ያስፈልጋል። ከላይ ለመግለጽ እንደሞከርኩት ህዝቡ ባህሉን ጠብቆ የተለያዩ ፕሮግራሞቹን ማድረጉ ሊወገዝ አይገባውም ነገር ግን ጊዜና ወቅቱን ያልጠበቀ ከሆነ ምልኩ ይጠፋልና በሃይማኖታዊ በዓላት ጊዜ ከሃይማኖታዊ ሥነ ሥርዓት ውጭ ሌላ ነገር እንዳይካሄድ ቤተክርስቲያን አቋም ልትይዝ ያስፈልጋል።


No comments:
Post a Comment