Tuesday, January 13, 2026
የቤተክርስቲያንን ክብር እንጠብቅ
ሀገራችን ኢትዮጵያ ከምትታወቅባቸው በጎ ተግባራት አንዱ እንግዳ ተቀባይነታችን መሆኑ የታወቀ ነው። በባህላችን አንድ ሰው ከየትም ይምጣ ከየት እንግዳ እስከሆነ ድረስ ክብር ይሰጠዋል ይህ መልካም ስማችን ወደፊትም እንዲቀጥል የሁላችንም ኃላፊነት ነው። ይህ በእንዲህ እንዳለ የሀገር ሀብት የሆኑ በህዝቡ አእምሮ ውስጥ ትልቅ ሥፍራ ያላቸው ተቅዋማትና ቦታዎች በጥንቃቄና በክብር መያዝ አለባቸው። አንድ ሰው ታዋቂ ስለሆነ ወይም ባለጸጋ ስለሆነ ወይንም ደግሞ እንግዳ በመሆኑ ግዴለም ብለን ከፍተን ልናቃልላቸው አይገባም።
ሰሞኑን አንድ አሜሪካዊ የሚዲያ ሰው ወደ ኢትዮጵያ መጥቶ አንዳንድ ሥፍራዎችን ሲጎበኝ ባየው ነገርም ሲደነቅና ሲደሰት በሚዲያ እያየሁ ነበር። ከላይ ለመግለጽ እንደሞከርኩት ማንም ይሁን ማን ሀገራችንን ለማየት እስከመጣ ድረስ መከበርና መልካም የሆነ አቀባበል ልናደርግለት ይገባል። በተለይ የሚዲያ ሰው በመሆኑ ለመላው ዓለም የሀገራችንን መልካም ገጽታ ለማሳየት ይጠቅማል ነገር ግን ይህ ወጣት ዓለማዊ የሚዲያ ሰው እንጅ በመንፈሳዊ ተግባር በምንም አይታወቅም። ታዲያ በምን መስፈርት ነው ለብጹዓን ሊቃነ ጳጳሳት በሚደረግ አቀባበል ወንጌል ተይዞ መስቀል ቆሞ ቤተክርስቲያን ተከፍቶ እንዲገባ የተደረገው? ትንሽ አልበዛም?
ከዚህ በፊት አንዲት ታዋቂ ዘፋኝ ለጭፈራ ተጋብዛ ኢትዮጵያ በመምጣቷ ከመጠን ያለፈ ፈንጠዝያ ውስጥ ገብተን በቤተክርስቲያን መድረክ ላይ አስቀምጠን በቅዱስ ያሬድ ዜማ ስናወድሳት እንደነበር አስታውሳለሁ በዚህም ምክንያት ብዙ የቤተክርስቲያን ልጆች በማዘን ቅሬታቸውን ሲያሰሙ ነበር ነገር ግን ካለፈው ተምረን ከመጠንቀቅ ይልቅ ተመሳሳይ ድርጊቶችን በማድረግ ኦርቶዶክሳውያንን እያሳዘንን ነው። ''ነገር ግን ሁሉ በአገባብና በሥርዓት ይሁን'' 1ኛ ቆሮ 14፥40
የቤተክርስቲያን መሪዎች ትልቁ ኃላፊነት የቤተክርስቲያንን ሥርዓት ማስከበር ነው። ቤተክርስቲያን በዓለም ውስጥ ካሉት ተቅዋማት ሁሉ ልዩ ነች ሁሉን የምናደርግበት ጊዜና ቦታ ተወስኖልናል ስለዚህ የቤተክርስቲያን አገልጋዮች ከምንም በላይ ለቤተክርስቲያን ህግና ሥርዓት ጠበቃ ሆነን ልንቆም ያስፈልጋል እንጅ በጊዜያዊ ነገር ተደልለን የቤተክርስቲያንን ክብር ዝቅ የሚያደርግ በእምነት ያልጸኑትን የሚያሰናክል ድርጊት ልንፈጽም አይገባም።
Subscribe to:
Post Comments (Atom)

No comments:
Post a Comment