Sunday, January 4, 2026

'' የተቀላቀለ እንዳይሆን እንለይ ''

ሰሞኑን የአእላፋት ዝማሬን በተመለከተ ብዙ አገልጋዮችና ምእመናን የራሳቸውን ምልከታ እያጋሩ መሆኑ ይታወቃል ይሁን እንጅ አንዳንድ ሰዎች ያላቸው መረጃ የተዛባ በመሆኑ የተነሳ ከአውዱ የወጣ ሃሳብና አስተያየት ሲሰጡ ይታያል። ሁሉም ማወቅና መረዳት ያለበት ያለንበት ዘመን ለመረጃ ልውውጥ አመች በመሆኑ የፈለግነውን ሃሳብ በቀላሉ ወደ ሰዎች ማድረስ እንችላለን። ነገር ግን ማወቅ ያለብን እኛ የሃሳብ ነጻነት እንዳለን ሁሉ የሌሎችንም ያልተገደበ ሃሳብን በነጻት የመግለጽ መብት እንዳንጋፋ ጥንቃቄ ልናደርግ ያስፈልጋል። ይህንኑ ጉዳይ በተመለከተ ከምንቀርባቸው ሰዎች ሳይቀር የሚሰጡት ሃሳቦች ፈጽሞ የማይጠበቁ ከመስመሩ የወጡ ሆነው አግኝቻቸዋለሁ። በተለይ በዚህ ጉዳይ ላይ አስተያየት የሚሰነዝሩ ወንድሞችን ዘረኞች፣ ፖለቲከኞች፣ ምቀኞች ወዘተ እያሉ መዝለፍ ፍጹም ተቀባይነት ሊኖረው አይችልም በተለይ ከኦርቶዶክሳውያን አይጠበቅም።
እኔ እንደተረዳሁት የተቃውሞው ፍሬ ሃሳብ 1ኛ.በዓለ ልደት በቤተክርስቲያን በማህሌትና በቅዳሴ የሚከበር በመሆኑ ምዕመናን በቤተክርስቲያን ዙሪያ ሆነው እየዘመሩ እያመሰገኑ በማህሌቱም ሆነ በቅዳሴው ይሳተፋሉ ሥጋውን ደሙን ተቀብለው ወደቤታቸው ይሄዳሉ እንጅ እንደ አደባባይ በዓላት ከቤተክርስቲያን እርቀው የልደቱን በዓል ማክበር አዲስ ሥርዓት ነው ምክንያቱም የሚያስቀድስ የሚቆርብ ሰው ለቅዳሴ ቅድመ ዝግጅት ያደርጋል እንጅ ከአጥቢያው እርቆ መሄድ አይገባውም። 2ኛ.የመዝሙር ጉባኤ የሚል ከዚህ በፊት በቤተክርስቲያናችን የተለመደ አይደለም ምዕመናንን ወደ አልተፈለገ ልምምድ ይወስዳል ዛሬ ከአበይት በዓላት ትልቁን የልደት በዓል በመዝሙር እንድናሳልፍ ከተደረገ ነገ ደግሞ ለትንሳኤ ምን ሊፈጠር እንደሚችል አናውቅም። ስለዚህ አንድ ሰው ብዙ ደጋፊ ስላለው ብቻ የራሱ ሥርዓት በቤተክርስቲያን ሥርዓት ላይ በፈለገው ጊዜ የሚደርብ ከሆነ ቤተክርስቲያን ''በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ'' እንዲሉ ያለባት የውጭና የውስጥ ፈተና ሳያንስ ሌላ ችግር እንዳይመጣ ቀድሞ ማሰብ ያስፈልጋል። 3ኛ.ያለንበት ወቅት በቤተክርስቲያናችን በውጭም በውስጥም ብዙ ፈተና የሚታይበት ወቅት በመሆኑ ለዚህ ደግሞ ጌታችን አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ እንዳስተማረን ''ከክፉም አድነን እንጂ ወደ ፈተና አታግባን ማቴ 6፥13'' ''ወደ ፈተና እንዳትገቡ ትጉና ጸልዩ፤ ማቴ 26፣41'' ባለው መሰረት ቤተክርስቲያን በሰራችልን ሥርዓት መሰረት በጸሎት ልንበረታ ይገባል እንጅ ጸሎታችንን ትተን እልልታና ሽብሸባ መምረጥ የደላው ያስመስለናልና ትክክል አይደለም ነው እየተባለ ያለው። ምናልባት ይህን ጉዳይ ለፖለቲካም ሆነ ለሌላ ዓላማ ሊያውሉት የሚፈልጉ አካላት ሊኖሩ ይችላሉ ነገር ግን እውነታውን መመርመር እንጅ ከዚያ ባለፈ ቤተክርስቲያን በገጠማት ችግር ምክንያት ልባቸው የተሰበረ ኦርቶዶክሳውያንን በአንድ ላይ ጨፍልቆ የማይገባ ሥም መስጠት ተገቢ አይመስለኝም። ይህን ማህበር የበላይ ሆኖ በማስተባበር ሲንቀሳቀስ ያየነው ወንድማችን ዲያቆን ሄኖክ ሃይሌ መሆኑ ይታወቃል። በመሆኑም ጉዳዩ በቀጥታ እሱን ይመለከታል በሚል እሳቤ ብዙ ጊዜ ሥሙ ይነሳል ነገር ግን ለሥሙ መነሳት ምክንያቱ ይዞት የመጣው አጀንዳ እንጅ ከማንነቱ ጋር ምንም የሚያገናኘው ጉዳይ አለ ብየ አላስብም። ምናልባት የፖለቲካም ሆነ የግል ፍላጎት ግጭት ያለባቸው ሰዎች ካሉ በግሌ አይመለከተኝም ምክንያቱም ፖለቲከኛም አይደለሁም ከዲያቆን ሄኖክ ጋር የሚያገናኘንም የምድራዊ ጥቅም ጉዳይ የለም። እንደ አንድ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ልጅ በሩቁ ሲያገለግል ከማየት በቀር በአካል አንድ ቀንም አግኝቸው አላውቅም። ስለዚህ እኔና መሰሎቼ የምናነሳቸው ሃሳቦች በስሜት ዛሬ ላይ የሚመሰርተው መሰረት ትልቋን ቤተክርስቲያን ከነገ በኋላ ብዙ ዋጋ እንዳያስከፍላት በመስጋት እንጅ ከምንም ምድራዊ ጥቅም ጋር እንደማይያያዝ ለማሳወቅ እወዳለሁ።

No comments:

Post a Comment