በምድራችንም ላይ አንዳንድ ሰዎች አሉ እንደሻማ የሚያበሩ ለሌላው ብርሃን የሆኑ ማንም ውስጣቸውን የማይረዳላቸው ምክንያቱም ይስቃሉ ደስተኛ ይመስላሉ ለሌሎች ደስታን ይፈጥራሉ ነገር ግን እንደሻማው እየቀለጡ እድሜያቸው እያጠረ ይሄዳል።
ዓለማችን በየዘመኑ ደስታን ሰላምን የሚፈጥሩ ሰዎችን ማፍራት ባትችል ማንም መኖርን አይመኝም ነበር። አንዳንድ ሰዎች በዘመናት ብቅ ይሉና ታሪክ ሆነው ያልፋሉ ታሪካቸው ለትውልድ መጽናኛ ሆኖ የመኖርን ተስፋ እያጎናጸፈ ለትውልድ መተካካት አስተዋጽኦ ያደርጋል።
ከዘመናት በፊት በስነ ጽሁፍ በፍልስፍና ይታወቁ የነበሩ ሰዎች ብዙ ሽ ዓመታት ካለፉ በኋላ እንኳ ሥራዎቻቸው በታሪክ ተሰንዶ ለትውልድ የአእምሮ ግንባታ ለደስታና ለአእምሮ መነቃቃት በእጅጉ እንደሚጠቅሙ የተረጋገጠ ነው።
በዚህ ዘመን በሀገራችን ከሚተላለፉት ሚዲያዎች ሁላችንም አይተን ትኩረት ሳንሰጥ የማናልፈው የቴሌቭዥን ፕሮግራም ቢኖር አርቲስት ነጻነት ወርቅነህ የሚያቀርበው የጥያቄና መልስ ውድድር መሆኑ ግልጽ ነው። በተለይ በውጭው ዓለም ለምንኖር ኢትዮጵያውያን ሀገራችንን እንድንናፍቅ ከሚያደርጉን ፕሮግራሞች አንዱ ይኸው ፕሮግራም ነበር። በልዩ ተሰጥኦና በኢትዮጵያዊ የአነጋገር ለዛ መድረኩን ስለሚመራው በሁሉ ዘንድ በጉጉት የሚጠበቅ ፕሮግራም ነበር።
የጥበብ ሰው ወንድማችን ነጻነት ወርቅነህ ለኢትዮጵያውያን ዘመናችን ካፈራቻቸው ደስታንና ሰላምን እንዲሁም ፍቅርንና አንድነትን እያዋዙ በህዝብ መካከል ከሚዘሩ ልዩ ተሰጥኦ ካላቸው የመድረክና የሚዲያ ባለሙያዎች አንዱ ነበር። ይህን ባለብዙ ጸጋ ወገን ማጣት ለቤተሰቡ ብቻ ሳይሆን እንደሀገር ትልቅ ጉዳት ነው። በተለይ ዝናና የሰው ፍቅር እያለው አንደበቱን ለክፉ ሳይከፍት በጥንቃቄ ከወገንተኝነት የጸዳ ጊዜያዊ ጥቅምና ትእቢት የሌለበት አገልግሎት የሚሰጥ ሰው በዚህ ዘመን ማግኘት እጅጉን ከባድ በመሆኑ ይህን የመሰለ ባለሙያ በማጣታችን ሃዘናችን ቀላል አይደለም።
ወይ ግሩም ነበር ማለት ለካ እንዲህ ቀላል ነው?
እግዚአብሔር አምላክ የንስሃ እድሜን ለሁላችንም ያድለን።
ለቤተሰቡና ለወዳጆቹ በሙሉ መጽናናትን ያድልልን ነፍሱን በአጸደ ገነት ያሳርፍልን።
No comments:
Post a Comment