Saturday, August 5, 2023

''ረኃብ ምንድነው?''

አባቶቻችን እንደነገሩን ረኃብ ምንድነው? ብሎ የጠየቀው የእስራኤል ንጉሥ የነበረው የቅዱስ ዳዊት ልጅ ንጉሥ ሰሎሞን ነው። ንጉሥ ሰሎሞን በእግዚአብሔርም በሰውም የተወደደና ከፈጣሪው ልዩ ጥበብና ሞገስ የተቸረው አስተዋይ ንጉሥ እንደነበር በቅዱስ መጽሐፍ ታሪኩ በሰፊው ተመዝግቧል በመሆኑም ከውልደቱ እስከንግሥናው ድረስ በቤተመንግስት በእንክብካቤና በተቀማጠለ ህይዎት የኖረ ሰው ነው  ከእለታት አንድ ቀን በቤተመንግስቱ በክብሩ ዙፋን ላይ ተቀምጦ ሳለ የተቸገረ፣ የተራበ፣ የተጠማ ሰው ወደ ደጁ መጣና እራበኝ እርዱኝ ብሎ ጮኸ ነገር ግን ወታደሮቹ እየደበደቡና እየገፉ ከአካባቢው ሲወስዱት በማየቱ ተደንቆ ምክንያቱን ጠየቀ የወታደሮቹም እራበኝ እርዱኝ እያለ ነው በአንተ ግዛት ሥር እንዴት የተራበ ሊኖር ይችላል? ብለው መለሱለት በዚህን ጊዜ ነበር ከላይ በርዕሳችን ላይ ያነሳነውን ጥያቄ ንጉሥ ሰሎሞን የጠየቀው ''ረኃብ ምንድነው?''(ታሪኩ ሰፊ ስለሆነ በሌላ ጊዜ እንመለስበታለን) በእውነት ረኃብ ምንድነው? ስንቶቻችን ነን ረኃብን ተርበን ያወቅነው? ስንቶቻችን ነን መጠማትን ተጠምተን ያወቅነው? ስንቶቻችን ነን መገፋትን ተገፍተን ያወቅነው? ስንቶቻችንስ ነን የትላንቱን መራብና መጠማት እንዲሁም መገፋት ያልዘነጋነው? ስንቶቻችን ነን የሌሎችን እንባ አይተን ያለቀስነው? የሰው ትንሹ ቸርነት በተፈጥሮ ያገኘው ሲያዝኑ አይቶ ማዘን ሲደሰቱ አይቶ መደሰት ነበር ቢያንስ ይህን ማድረግ ቢያቅተን እንዴት ሰዎች ተርበው እራበኝ፣ ተጠምተው ጠማኝ፣ መኖር ተነፍገው በህግ አምላክ ልኑር ሲሉ አፋችሁን ዝጉ እንላለለን?

ሰው ከእንስሳ የሚለየው የሚያገናዝብ ፍጥረት በመሆኑ ነው። መገንዘብ ማለት ደግሞ የክፉውንና የመልካሙን፣ የቀኝና የግራውን፣ የኋላና የፊቱን ወ ዘ ተ ለይቶ ማወቅና መረዳት ማለት ነው። ሰው ይህን ፀጋውን በተለያዩ ምክንያቶች ሊያጣ ይችላል። በጤና መታወክ፣ ከአቅም በላይ በሆነ ጫና ምክንያት፣ በራስ ወዳድነት፣ በንዝህላልነት፣ በእውቀት ማነስ፣ በምቾት ብዛት፣ በጥላቻ መታወር ወ ዘ ተ ብለን መዘርዘር እንችላለን።

Tuesday, April 4, 2023

ሆሳእና በአርያም

«ሆሳዕና፤ በጌታ ስም የሚመጣ የእስራኤል ንጉሥ የተባረከ ነው፡፡»
ዮሐ.12፥13
 
የአቢይ ጾም ስምንተኛው ሰንበት ሆሳዕና በመባል ይታወቃል፡፡ ሆሳእና የተባለበት ምክንያት በዚህ ሰንበትና በዋዜማዎቹ ዕለታት የሚዘመረው ጾመ ድጓ “ሆሳዕና በአርያም” የሆሳዕናን ቃል በእየቦታው እየጠቀሰና እያነሣ ጌታችን መድሃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ እየተመሰገነና እየተዘመረለት በአህያ ውርንጭላ ተቀምጦ ኢሩሳሌም የገባበትን ሁኔታ እየተረከ ስለሚዘምር ይህ ሰንበት ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በጌትነትና በክብር በውዳሴና ቅዳሴ ሆሳዕና በአርያም እየተባለ በሽግሌዎችና በሕፃናት አንደበት በድንጋዮች ልሣን ሳይቀር እየተመሰገነ ኢየሩሳሌም በአህያ ተቀምጦ ለመግባቱ መታሰቢያ ሆኖ ስለተሰጠ ነው፡፡  ማቴ 21፡1-17፣ ማር 11፡1-10፣ ሉቃ19፡29-38፣ ዮሐ12፡12-15፣ ዘካ 9፤9፣ 2ነገ 9፡13፣ መዝ 117፡25-26፣ ኢሳ 56፡7፣ ኤር 7፡12 እና መዝ 8፡2

Wednesday, February 15, 2023

ካህኑን ለምን???

ሰሞኑን በማህበራዊ ሚዲያ አንድ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያንን የክህነት አርማ የለበሰና በእጁ የክርስቶስን መስቀል የያዘ ካህን በአንድ የጥበቃ ሰራተኛ በጥፊ ሲመታ የሚያሳይ ቪዲዮ ተለቆ በዓለም ያሉ ኢትዮጵያውያን ሲመለከቱት ሰንብተዋል ብዙዎችም በማዘን ቁጣቸውን ሲገልጹ ሰንብተዋል። በሌላው ዓለም ላሉ ኢትዮጵያውያን ሀገራቸን ኢትዮጵያ ያለችበትን ደረጃ ለመረዳት ሳይጠቅም አይቀርም። እኔ በግሌ በጥፊ የተማታውን ወንድም ባገኘው ለዚህ ደረጃ ያደረሰውን ምክንያት ከመጠየቅ ያለፈ ካህን ወይም ኢትዮጵያዊ በመሆኔ በእርሱ ላይ የበቀል ምላሽ ለመስጠት አልሞክርም ነገር ግን እውነቱን ለማወቅ የምጠይቀው ብዙ ጥያቄ ነበረኝ።

ካህን ማለት የእግዚአብሔር አገልጋይ ፤ የምዕመናን አባት ፤ ጠባቂ ፤ መጋቢ ማለት ነው ። ስለሆነም ስለ እግዚአብሔርና ስለህዝቡ ሲባል እንኳን አካሉ የለበሰው ልብስ ክብር ይሰጠዋል በሀገራችን በኢትዮጵያ የእምነት አባቶች ሲከበሩ ኖረዋል ስለምን ቢባል ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ እንደነገረን ''እምነትም ተስፋ ስለምናደርገው ነገር የሚያስረግጥ፥ የማናየውንም ነገር የሚያስረዳ ነው። ለሽማግሌዎች የተመሰከረላቸው በዚህ ነውና።ዓለሞች በእግዚአብሔር ቃል እንደ ተዘጋጁ፥ ስለዚህም የሚታየው ነገር ከሚታዩት እንዳልሆነ በእምነት እናስተውላለን። እብ11፥1'' እንዳለው የእምነት ሰዎች ከምድራዊው ዓለም አልፈው ስለሰማያዊው ዓለም የሚያስተምሩ በመሆናቸው ክብር ይሰጣቸዋል። ይህን በማድረግ ደግሞ ሃገራችን ኢትዮጵያ ቀዳውን ስፍራ ትይዛለች ታዲያ ዛሬ ያ አባቶችን ማክበር እምነትን ማክበር የት ሄደ? ብዞዎች እያሉት እንዳለው የካህኑ መመታት የቤተክርስቲያንን ክብር ለማዋረድና ለማንቋሸሽ የተደረገ ነው። እንዲሁም ቤተክርስቲያንን ከመጥላት የተነሳ እንደሆ በግልጽ ማየት ይቻላል። ግብረገብነትንና ሰብአዊ ክብርን ስታተምር የኖረች ቤተክርስቲያን በዚህ ደረጃ እንዴት ልትጠላ ቻለች? 

Saturday, February 11, 2023

የትላንቱ እንቅፋት

ዛሬ ላይ እየመታን ያለው እንቅፋት ትላንት ከትላንት ወዲያ ሲያደናቅፈን ነበር በየወቅቱ አልፈናቸው የመጣናቸው እንቅፋቶች ቋጥኝ እየሆኑ ከእግራችን አልፈው ወደ ጉልበታችን ሊደርሱ ችለዋል::

እንቅፋት አንድ ጊዜ መትቶህ አልፈኸው ሄደህ ድጋሚ ከመታህ . . . . . ይባላል ታዲያ እውነትም እንደ አባባሉ አልፈነው የመጣነው እሾህ ከሆነ እየወጋን ያለው የማነው ስህተቱ? ቤተክርስቲያን ምንም በፈተና ውስጥ የምትኖር ነች ቢባልም ባለፉት አርባና ሃምሳ አመታት የገጠማት ፈተና ግን ከውስጧ ባሉ ልጆቿ የሚነሳ ሆኖ ለውጭ ጠላትም በር እየከፈተ ቤተክርስቲያንን ያለስሟ መጥፎ ስም የሚሰጡ ሰዎች እንዲበረክቱ ምክንያት የሆነ ነው።

ለቤተክርስቲያን ፈተና መብዛት ምክንያት የሆኑ ነገሮችን ነቅሶ ማውጣት መድኃኒቱን ለማግኘት መፍትሄ ይመስለኛል "ህመሙን ያልተናገረ መድኃኒት አይገኝለትም" እንደሚባለው ወደንም ሆነ ሳንፈልግ ችግሮቻችን ላይ እርምጃ ለመውሰድ መነሳት ካልጀመርን ሃዘንና ለቅሶ መከራን ይጨምራሉ እንጅ መፍትሄ አያመጡም።