«ሆሳዕና፤ በጌታ ስም የሚመጣ የእስራኤል ንጉሥ የተባረከ ነው፡፡»
ዮሐ.12፥13
የአቢይ ጾም ስምንተኛው ሰንበት ሆሳዕና በመባል ይታወቃል፡፡ ሆሳእና የተባለበት ምክንያት በዚህ ሰንበትና በዋዜማዎቹ ዕለታት የሚዘመረው ጾመ ድጓ “ሆሳዕና በአርያም” የሆሳዕናን ቃል በእየቦታው እየጠቀሰና እያነሣ ጌታችን መድሃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ እየተመሰገነና እየተዘመረለት በአህያ ውርንጭላ ተቀምጦ ኢሩሳሌም የገባበትን ሁኔታ እየተረከ ስለሚዘምር ይህ ሰንበት ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በጌትነትና በክብር በውዳሴና ቅዳሴ ሆሳዕና በአርያም እየተባለ በሽግሌዎችና በሕፃናት አንደበት በድንጋዮች ልሣን ሳይቀር እየተመሰገነ ኢየሩሳሌም በአህያ ተቀምጦ ለመግባቱ መታሰቢያ ሆኖ ስለተሰጠ ነው፡፡ ማቴ 21፡1-17፣ ማር 11፡1-10፣ ሉቃ19፡29-38፣ ዮሐ12፡12-15፣ ዘካ 9፤9፣ 2ነገ 9፡13፣ መዝ 117፡25-26፣ ኢሳ 56፡7፣ ኤር 7፡12 እና መዝ 8፡2
ከዚህ በላይ የተሰጠሱትን ምዕራፎችና ቁጥሮች በፅሞና ብንመለከት ስለሆሣዕና በትንቢት የተገሩትንና በድርጊት የተፈፀሙትን መረዳት ይቻላል፡፡ ከዚህ በላይ እንደተጠቀሰው የሰንበታቱ ስያሜ በቂ የሆነ የቅዱሳት መፃሕፍት ታሪክ ድጋፍ ያለውና የፆም ድጓውን ባህል የተከተለ መሆኑን መገንዘብ ይገባል፡፡
በዕለተ ሆሣዕና የቤተ መቅደሱ በር ተዘግቶ የነገሥታት ንጉሥ የጌቶች ጌታ የሆነው አምላክ በበር ቆሞ “አርኅው ኆኀተ መኳንን'' መኳንንት ደጆቻችሁን ክፈቱ” በማለት ጥሪውን ያስተላልፋል፡፡ ካህናተ አይሁድ የልቡናቸውን በር ቆልፈው አምላክነቱን ክደው እሩቅ ብእሲ እንደሆነ በማሰብ “ደጆቻችንን እንከፍትልህ ዘንድ አንተ ማነህ?” ማለታቸውን ለማስታወስ የዕለቱ ቀዳስያን በቤተ መቅደሱ ውስጥ ይሆናሉ፡፡
ምስባክ መዝ 80፡3 ንፍሑ ቀርነ በዕለተ ሠርቅ፡፡ በዕምርት ዕለት በዓልነ፡፡ እስመ ሥርዓቱ ለእስራኤል
ውእቱ፡፡
ትርጓሜው፡- በመባቻ ቀን በከፍተኛው በዓላችን ቀን፡፡ መለከት ንፉ፡፡ ለእስራኤል
ሥርዓቱ ነውና፡፡
የሌሊተ ሆሣዕና ምስባክ መዝ 16፡3
ቡሩክ ዘይመፅእ በስመ እግዚአብሔር፡፡ ባረክናክ እምቤተ እግዚአብሔር፡፡
እግዚአብሔር እግዚእ አስተርአየ ለነ፡፡
ትርጓሜው፡- በእግዚአብሔር ስም የሚመጣ ቡሩክ ነው፡፡ ለእግዚአብሔር ቤት
መረቅናችሁ፡፡ እግዚአብሔር አምላክ ነው ለእኛም በራልን፡፡
ዘነግህ/በጊዜ ዑደት ውስተ ቤተ መቅደስ ምስባክ መዝ.121፥1
ተፈሣሕኩ እስመ ይቤሉኒ ቤተ እግዚእብሔር ነሐውር፡፡ ወቆማ እገሪነ ውስተ
አዕፃድኪ ኢየሩሳሌም፡፡ ኢየሩሳሌምሰ ሕንፅት ከመ ሀገር።
ትርጉም፦ ወደ እግዚአብሔር ቤት እንሂድ ስላሉኝ ደስ አለኝ፡፡ ኢየሩሳሌም ሆይ
እግሮቻችን በአደባባዮችሽ ቆሙ፡፡ ኢየሩሳሌምስ እንደ ከተማ የታነጸች ናት፡፡
ወንጌል ምስባክ
መዝ.147÷1
ትሴብሖ ኢየሩሳሌም ለእግዚአብሔር፡፡ ወሰብሒዮ ለአምላክኪ ጽዮን፡፡ እስመ
አጽንዐ መናስግተ ኆኃትኪ፡፡
ትርጉም:- ኢየሩሳሌም ሆይ እግዚአብሔርን አመስግኚ፡፡ ጽዮንም ሆይ አምላክሽን
አመስግኚ፡፡ የደጆችሽን መወርወሪያ አጸንቶአልና ልጆችሽንም በውስጥሽ
ባርኮአልና፡፡
መዝ.117፥27
ግበሩ በዓለ በትፍሥሕት በኃበ እለ ያስተሐምምዎ
ትርጉም፦ ጌታ እግዚአብሔር ተገለጠልን፤ እስከ መሠዊያው ቀንዶች ድረስ
በሚያስተነትኑበት በደስታ በዓልን አድርጉ፡፡
መዝ. 67፥34
መዝሙር ዘምዕዋድ አርእዩነ ፍኖቶ
አርእዩኖ ፍኖቶ ወንሑር ቤቶ እስመ እምጽዮን ይወጽእ ሕገ ወቃለ እግዚአብሔር እምኢየሩሳሌም ንሣለማ ለመድኃኒትነ በትፍሥሕት ተቀበልዋ ለታቦት እስመ ዋካ ይእቲ ወብርሃን
መዝሙር ሰመያ አብርሃም
ሰመያ አብርሃም ወይቤላ ዛቲ ዕለት በዓለ እግዚአብሔር ንፍሑ ቀርነ በዕለት ሠርቅ በዕምርት ዕለት በዓልነ ሶበ ተዘከርናሃ ለጽዮን
መዝሙር ወትቤ ጽዮን
ወትቤ ጽዮን አርኅው ሊተ አናቅጸ ይባኡ ሕዝብ ብዝዙኃን ወያዕትቱ ዕብነ እምፍኖት ለንጉሥ ለወልደ ዳዊት ንጉሦሙ ለእስራኤል ውእቱ ይብሉ ሆሣዕና በአርያም
መዝሙር ባርኮ ያዕቆብ
ባረኮ ያ ዕቆብ ለይሁዳ ወልዱ ወይቤሎ ሀሎ ንጉሥ ዘይወጽ እ እምኔከ ዘየሐጽብ በወይን ልብሶ ወበደመ አስካል ሰንዱኖ ንጉሦሙ ውእቱ ይብሉ ሆሣዕና በአርያም
«ሆሳዕና፤ በጌታ ስም የሚመጣ የእስራኤል ንጉሥ የተባረከ ነው፡፡» ዮሐ.12፥13
ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በአልዓዛር ቤት በቢታኒያ የመጨረሻውን ራት ከበላ በኋላ ሐዋርያቱን ልኮ የአህያ ውርንጫ አስመጥቶ በርሷ ላይ ተቀምጦ ወደ ኢየሩሳሌም ገባ፡፡ በዚህም የሚከተሉት ነገሮች ተገልጠዋል፡ ፣
1. መንግሥቱ የትህትና እና የፈቃድ መሆኗን
አህያ ከእንሰሳት ሁሉ የማታስፈራ ናት፡፡ ጌታም እንደ ነገሥታቱ ስርዓት በከበረ ሰረገላና በፈረስ ሳይሆን በአህያ ውርንጫ ላይ ተቀምጦ ወደ ኢየሩሳሌም መግባቱ መንግሥቱ የትህትና መሆኗንና ሁሉም ሰው ተገዶ እና ፈርቶ ሳይሆን በፈቃዱ የሚገባባት መሆኗን ለማሳየት ነው፤ በአህያ ሰውን አባሮ መያዝ እንኳ አይቻልምና፡፡ ይህም በአጋጣሚ እንደ አንግዳ ደራሽ እንደ ውኃ ፈሳሽ የሆነ ሳይሆን ነቢያት በትንቢት የተናገሩትና በእግዚአብሔር የድህነት ጉዞ የታሰበ ነው፡፡ ነቢዩ ዘካርያርስ ስለዚህ ሲናገር «አንቺ የጽዮን ልጅ ሆይ እጅግ ደስ ይበልሽ፤ አንች የኢየሩሳሌም ልጅ ሆይ እልል በዬ፤ እነሆ ንጉሥሽ ጻድቅና አዳኝ ነው፤ ትሑትም ሆኖ በአህያም በአህያይቱ ግልገል በውርንጫይቱ ላይ ተቀምጦ ወደ አንች ይመጣል» በማለት ገልጦታል፡፡ ዘካ.9፥9፡፡
2. የመገለጡ አላማ ለድህነት እንጅ ለክብር አለመሆኑ
እስራኤላውያን የፋሲካን በዓል ከማክበራቸው ከአምስት ቀን በፊት በዚህ ዕለት ለፋሲካ የሚሆኑት ጠቦቶችን ወደ ኢየሩሳሌም ይዘው ይገቡ ነበር፡፡ /ዘጸ.12፥1- 36/ ጌታችንም በዚህ ዕለት ወደ ኢየሩሳሌም መውጣቱ የመንግስቱን ምሥጢር በመስቀልና በመስዋዕትነት ፍቅር የሚገልጽ የእግዚአብሔር በግ መሆኑን ለማጠየቅ ነው፡፡ ስለዚህ ነው ከላይ በተጠቀሰው የዘካርያስ ትንቢት ላይ « እነሆ ንጉሥሽ ጻድቅና አዳኝ ነው» የሚለው፡፡ ጌታችን ንጉሥ ሆኖ ወደ ኢየሩሳሌም የገባው ለመመስገን አስቦ ሳይሆን ይቀበሉት ዘንድ አለምን ለማዳን የመጣው ንጉሥ እርሱ መሆኑን በአደባባይ ለማወጅ ነው፡፡ ስለዚህ ነው ምሥጋናን ከህፃናት የተቀበለው፤ ሕፃናት ሁሉን ይቀበላሉና፡፡ ለዚህም ነው እንደ ሕፃናት ካልሆናችሁ ወደ እግዚአብሔር መንግሥት አትገቡም በማለት የተናገረው፡፡ /ሉቃ. 18፥17/ የመዳን ተስፋ የተነገረላቸው እስራኤላውያን ባልተቀበሉት ጊዜ ግን የመጣበት ዓላማ ይህ ስለነበር ስለነርሱ አለቀሰ፡፡ ሲቀርብም ከተማይቱን አይቶ አለቀሰላት፤ እንዲህም አለ «ለሰላምሸ የሚሆነውን በዚህ ቀን አንቺስ እንኳ ብታወቂ አሁን ግን ከአይንሽ ተሰውሯል» ሉቃ 19.41፡፡ የመምጣቱ ዓላማ ለዓለም ሰላምን የሚሰጥ /እግዚአብሔርንና ሰውን የሚያስታርቅ/ አዳኝ ንጉሥ፣ የፋሲካ በግ መሆኑን ለማወጅ ነበርና ባልተቀበሉት ጊዜ አለቀሰላቸው፡፡ «ሆሳዕና» ማለት ግን «አሁን አድን» ማለት ስለሆነ አዳኝነቱ መቀበል ነበር፡፡ ንጉሥነቱን በአዳኝነቱ መግለጡም መንግሥቱ የፍቅር መሆኑንና ዙፋኑም መስቀል መሆኑን ለመግለጥ ነው፤ በጉ «የነገሥታት ንጉሥና የጌቶች ጌታ» ነውና፡፡ ራዕይ.19፥13-16
የሆሳዕና አከባበር በቅድስት ቤተክርስቲያናችን
ቅድስት ቤተክርስቲያናችን ሆሳዕና በታላቅ ክብር ታከብራለች፡፡ አከባበሯም እንደ አይሁድ እሁድ ሆሳዕና በእግዚአብሔር ስም የመጣች የአባታችን የዳዊት መንግሥት የተባረከች ናት፣ ሆሳዕና በአርያም ካሉ በኋላ አርብ « ይሰቀል ይሰቀል» በማለት ሳይሆን እስከ መጨረሻው ድረስ ከእርሱ ጋር መሆንን በሚያሳይ አስደሳችና መንፈሳውያን ስርዓቶቿ ነው፡፡ እነዚህም የሚከተሉት ናቸው፡፡
ዑደት
በቤተከርስቲያትን ሥርዓት መሰረት የሆሳዕና ጠዋት ቅዳሴ ከመገባቱ በፊት ዑደት ይደረጋል፡፡ ዑደቱም ከቤተመቅደስ ተጀምሮ በየአራት በሮች እየቆመ ምስባክ እየተሰበከ ወንጌል እየተነበበ ከተዞረ በኋላ በመጨረሻ ካህናቱና ዲያቆናቱ ወደ ቤተመቅደሱ ሲመለሱ ያልቃል፡፡ ዑደቱንም ዲያቆናት መስቀልና ስዕል /የእመቤታችን/ ይዘው፣ ካህኑ ማዕጠንት እያጠኑ ይመሩታል፡፡
ይህ ዑደት የቤተክርስቲያን ዘላለማዊው ጉዞዋ ነው፡፡ የቤተክርስቲያን ጉዞ ከእግዚአብሔር ይጀምራል፡፡ ክርስትና የእግዚአብሔር ጅማሬ እንጅ የሰው አይደለምና፡፡ በዚህም ምክንያት ይህ ዑደት ከመሰዊያው ይጀምራል፤ መስዊያው ሰማያዊ ነውና፡፡ የዚህ የቤተክርስቲያን ጉዞ መሪ ሕዝቡን ወደ እግዚአብሔር መርቶ ያደረሰ ሊቀ ካህናት ኢየሱስ ክርስቶስ ነው፡፡ ስለዚህ ካህኑ ዕጣን እያጠነ ይመራል፡፡ ይህ ጉዞ መከራ ያለበት መንገዱ ጠባብ ይሁን እንጅ በደስታ የተሞላ ነው፡፡ ስለዚህ ዲያቆኑ መስቀል ሲይዝ ሕዝቡ ደግሞ ይዘምራሉ፡፡ ደስታና መስቀልን በአንድ ላይ ለመግለጥ ነው፡፡ የዚህ ጉዞ ፍጹም አርአያ ደግሞ እመቤታችን ናት ሁለቱንም ታሳያለችና፡፡ በአንድ በኩለ «ኅዘን በልቧ ያለፈ» ሲሆን በሌላ በኩል «ተአብዮ ነፍስዬ ለእግዚአብሔር ወትተሐሰይ መንፈስየ» ብላ ዘምራለችና፡፡ ዑደቱ በምዕራብ በር በኩል /በዋናው በር/ መጀመሩ እና በእያንዳንዱ በር መቆማችን የዘላለም ደጆች መከፈታቸውንና ሰማያውያንም የጉዞአችን /የማኅብራችን/ ተካፋዮች መሆናቸውን ያጠይቃል፡፡ በመጨረሻም ዑደቱ በካህናቱ ወደቤተ መቅደሱ መግባት መጠናቀቁ የክርስትና ጉዟችን ከእግዚአብሔር ጋር ለዘላለም በመኖር መፈጸሙን ያሳያል፡፡ በዚህ ጉዞዋ ቤተክርስቲያናችን እስከ መጨረሻው ከክርስቶስ የሚጸና ዘላለማው ጉዞዋን ትናገራለች፡፡
ቅዳሴ
ከዑደት በኋላ ቅዳሴ ይቀጥላል፡፡ በቅዳሴም የክርስቶስን ሥጋና ደም እንቀበላለን በዚህም እስከሞት ድረስ የሚዘልቅ አንድነታችን እንገልጣለን፡፡ ጌታ ወደ ኢየሩሳሌም ሲገባ «ወደ ኢየሩሳሌም እንወጣለን ስለ ሰው ልጅም በነቢያት የተጻፈው ሁሌ ይፈጸማል፡፡ ለአህዛብ አሳልፈው ይሰጡታልና ይዘብቱበትማል፣ ያንገላቱትማል፣ ይተፉበታል፤ ከገረፉትም በኋላ ይገድሉታል በሦስተኛውም ቀን ይነሳል፡፡» እንዳለ የኢየሩሳሌም ጉዞው ወደሞት የተደረገ ጉዞ ነበር፡፡ ስለዚህ በሥጋወደሙ ከእርሱ ጋር የሆንን ምእመናንንም ከእርሱ ጋር ወደ ሙት እንሄዳለን፡፡
ፍትሐት
ከቅዳሴ በኋላ ፍትሃት ይደረጋል፤ ይህም ለህዝቡ ሁሉ ነው፡፡ አንዳንዶች ይህ ፍትሃት ምናልባት በዚህ ሰሞን የሚሞቱ ካሉ በሚል የሚደረግ እንደሆነ ይናገራሉ፡፡ ነገር ግን ይህ ፍትሃት ለሁሉም ክርስቲያን ጭምር ነው፡፡ በዚህ ሳምንት የጌታን ሞትና ትንሳኤ ማሰብ ሳይሆን አብረነው ሞቱን ትንሳኤውን እንካፈላለንና፡፡ ሰውነታችን በጸሎትና በስግደት ለዓለማዊ ፈቃዳችን ሁሉ ገድለን በእርሱ ትንሳኤ ትንሳኤ ልቦናን እንነሳለንና፡፡ ይህም ለመነኮሳት እንደሚደረግ ፍትሃት ያለ ነው፡፡ መነኮሳት ሲመነኩሱ ለዚህ ዓለም የሞቱ መሆናቸውንና የክርስቶስን መስቀል መሸከማቸውን ለማጠየቅ የሙታን ጸሎት እንደሚደረግላቸው ምእመናንንም የጌታን መስቀል በመሸከምና መከራውን በመካፈል ለዓለም ለመሞት በመወሰን ቤተክርስቲያን የሙታን ጸሎት ታደርግላቸዋለች፡፡ በዚህም ጌታችንን አብረን ወደ ሞቱ እንከተለዋለን፡፡
ወስብሐት ለእግዚአብሔር
No comments:
Post a Comment