Wednesday, February 15, 2023

ካህኑን ለምን???

ሰሞኑን በማህበራዊ ሚዲያ አንድ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያንን የክህነት አርማ የለበሰና በእጁ የክርስቶስን መስቀል የያዘ ካህን በአንድ የጥበቃ ሰራተኛ በጥፊ ሲመታ የሚያሳይ ቪዲዮ ተለቆ በዓለም ያሉ ኢትዮጵያውያን ሲመለከቱት ሰንብተዋል ብዙዎችም በማዘን ቁጣቸውን ሲገልጹ ሰንብተዋል። በሌላው ዓለም ላሉ ኢትዮጵያውያን ሀገራቸን ኢትዮጵያ ያለችበትን ደረጃ ለመረዳት ሳይጠቅም አይቀርም። እኔ በግሌ በጥፊ የተማታውን ወንድም ባገኘው ለዚህ ደረጃ ያደረሰውን ምክንያት ከመጠየቅ ያለፈ ካህን ወይም ኢትዮጵያዊ በመሆኔ በእርሱ ላይ የበቀል ምላሽ ለመስጠት አልሞክርም ነገር ግን እውነቱን ለማወቅ የምጠይቀው ብዙ ጥያቄ ነበረኝ።

ካህን ማለት የእግዚአብሔር አገልጋይ ፤ የምዕመናን አባት ፤ ጠባቂ ፤ መጋቢ ማለት ነው ። ስለሆነም ስለ እግዚአብሔርና ስለህዝቡ ሲባል እንኳን አካሉ የለበሰው ልብስ ክብር ይሰጠዋል በሀገራችን በኢትዮጵያ የእምነት አባቶች ሲከበሩ ኖረዋል ስለምን ቢባል ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ እንደነገረን ''እምነትም ተስፋ ስለምናደርገው ነገር የሚያስረግጥ፥ የማናየውንም ነገር የሚያስረዳ ነው። ለሽማግሌዎች የተመሰከረላቸው በዚህ ነውና።ዓለሞች በእግዚአብሔር ቃል እንደ ተዘጋጁ፥ ስለዚህም የሚታየው ነገር ከሚታዩት እንዳልሆነ በእምነት እናስተውላለን። እብ11፥1'' እንዳለው የእምነት ሰዎች ከምድራዊው ዓለም አልፈው ስለሰማያዊው ዓለም የሚያስተምሩ በመሆናቸው ክብር ይሰጣቸዋል። ይህን በማድረግ ደግሞ ሃገራችን ኢትዮጵያ ቀዳውን ስፍራ ትይዛለች ታዲያ ዛሬ ያ አባቶችን ማክበር እምነትን ማክበር የት ሄደ? ብዞዎች እያሉት እንዳለው የካህኑ መመታት የቤተክርስቲያንን ክብር ለማዋረድና ለማንቋሸሽ የተደረገ ነው። እንዲሁም ቤተክርስቲያንን ከመጥላት የተነሳ እንደሆ በግልጽ ማየት ይቻላል። ግብረገብነትንና ሰብአዊ ክብርን ስታተምር የኖረች ቤተክርስቲያን በዚህ ደረጃ እንዴት ልትጠላ ቻለች? 

ጌታችን ሲያስተምር ስለ ካህናት በብዙ ቦታ ተናግሯል ። ሂድና ራስህን ለካህን አሳይ ። ማቴ 8 ፥ 4 ። አንተ ብፁዕ ነህ ፡ የመንግስተ ሰማያትንም መክፈቻ እሰጥሃለሁ… ። ማቴ 16 ፥ 17 ። እውነት እላችኋለሁ በምድር ያሰራችሁት በሰማይ የታሰረ ፣ በምድር የፈታችሁት በሰማይ የተፈታ ይሆናል ። ማቴ 18 ፥ 18 ። ይህን የተናገረው በመዋዕለ ስብከቱ ሲሆን ከሙታን ከተነሳ በኋላም ለሐዋርያት አረጋግጦላቸዋል ። ሂዱና በአብ በወልድና በመንፈስ ቅዱስ ስም አጥምቋቸው ። ማቴ 28 ፥ 19 ።..እፍ አለባቸውና መንፈስ ቅዱስን ተቀበሉ ። ዮሐ 20 ፥ 22 ። በመጨረሻም ቅዱስ ዼጥሮስን “….ስምዖን ሆይ በጎቼን ጠብቅ ፤ (ለጊዜው አስራ ሁለቱን ሐዋርያት ፡ ለፍጻሜው ወላጆችን) ፣ ጠቦቶቼን ጠብቅ ፤ (ለጊዜው ሰብዓ አርድዕትን ፡ ለፍጻሜው ወጣቶችን) ፣ ግልገሎቼን ጠብቅ (ለጊዜው ሰላሳ ስድስቱ ቅዱሳት አንስትን ፡ ለፍጻሜው ህጻናትን)” በማለት ሐዋርያትን ዸዸሳት ፣ ቅዱስ ዼጥሮስን የመጀመሪያ ሊቀ ዻዻሳት አድርጎ ሾመው ። ዮሐ 21 ፥ 15 ። ኢትዮጵያ ሀገራችንም በመጽሐፍ ቅዱስ የተቃኘች ሀገር በመሆኗ ህዝቦቿ ለካህናት ክብር አላቸው አሁን እያየን ያለው ግን አዲሲቷ ኢትዮጵያ ትላንት የምናከብራቸውን የምታዋርድ ትሆንን? ብለን እንድንጠይቅ አድርጎናል።   


No comments:

Post a Comment