Saturday, August 5, 2023

''ረኃብ ምንድነው?''

አባቶቻችን እንደነገሩን ረኃብ ምንድነው? ብሎ የጠየቀው የእስራኤል ንጉሥ የነበረው የቅዱስ ዳዊት ልጅ ንጉሥ ሰሎሞን ነው። ንጉሥ ሰሎሞን በእግዚአብሔርም በሰውም የተወደደና ከፈጣሪው ልዩ ጥበብና ሞገስ የተቸረው አስተዋይ ንጉሥ እንደነበር በቅዱስ መጽሐፍ ታሪኩ በሰፊው ተመዝግቧል በመሆኑም ከውልደቱ እስከንግሥናው ድረስ በቤተመንግስት በእንክብካቤና በተቀማጠለ ህይዎት የኖረ ሰው ነው  ከእለታት አንድ ቀን በቤተመንግስቱ በክብሩ ዙፋን ላይ ተቀምጦ ሳለ የተቸገረ፣ የተራበ፣ የተጠማ ሰው ወደ ደጁ መጣና እራበኝ እርዱኝ ብሎ ጮኸ ነገር ግን ወታደሮቹ እየደበደቡና እየገፉ ከአካባቢው ሲወስዱት በማየቱ ተደንቆ ምክንያቱን ጠየቀ የወታደሮቹም እራበኝ እርዱኝ እያለ ነው በአንተ ግዛት ሥር እንዴት የተራበ ሊኖር ይችላል? ብለው መለሱለት በዚህን ጊዜ ነበር ከላይ በርዕሳችን ላይ ያነሳነውን ጥያቄ ንጉሥ ሰሎሞን የጠየቀው ''ረኃብ ምንድነው?''(ታሪኩ ሰፊ ስለሆነ በሌላ ጊዜ እንመለስበታለን) በእውነት ረኃብ ምንድነው? ስንቶቻችን ነን ረኃብን ተርበን ያወቅነው? ስንቶቻችን ነን መጠማትን ተጠምተን ያወቅነው? ስንቶቻችን ነን መገፋትን ተገፍተን ያወቅነው? ስንቶቻችንስ ነን የትላንቱን መራብና መጠማት እንዲሁም መገፋት ያልዘነጋነው? ስንቶቻችን ነን የሌሎችን እንባ አይተን ያለቀስነው? የሰው ትንሹ ቸርነት በተፈጥሮ ያገኘው ሲያዝኑ አይቶ ማዘን ሲደሰቱ አይቶ መደሰት ነበር ቢያንስ ይህን ማድረግ ቢያቅተን እንዴት ሰዎች ተርበው እራበኝ፣ ተጠምተው ጠማኝ፣ መኖር ተነፍገው በህግ አምላክ ልኑር ሲሉ አፋችሁን ዝጉ እንላለለን?

ሰው ከእንስሳ የሚለየው የሚያገናዝብ ፍጥረት በመሆኑ ነው። መገንዘብ ማለት ደግሞ የክፉውንና የመልካሙን፣ የቀኝና የግራውን፣ የኋላና የፊቱን ወ ዘ ተ ለይቶ ማወቅና መረዳት ማለት ነው። ሰው ይህን ፀጋውን በተለያዩ ምክንያቶች ሊያጣ ይችላል። በጤና መታወክ፣ ከአቅም በላይ በሆነ ጫና ምክንያት፣ በራስ ወዳድነት፣ በንዝህላልነት፣ በእውቀት ማነስ፣ በምቾት ብዛት፣ በጥላቻ መታወር ወ ዘ ተ ብለን መዘርዘር እንችላለን።

ሰው ማገናዘብ ሲሳነው ምን ሊመስል ይችላል የሚለውን ቅዱስ መጽሐፍ ቁልጭ አድርጎ አስቀምጦልናል ''ሰው ግን ክቡር ሆኖ ሳለ አያውቅም፤ እንደሚጠፉ እንስሶች መሰለ'' መዝ 49፥12 ''አእምሮ የሌለው ክቡር ሰው እንደሚጠፋ እንስሶች መሰለ'' መዝ 49፥20 አባቶቻችን እንደነገሩን ሰው በመልካም ስራው ሲበረታ ወደ መላእክት ክብር ያድጋል ሲደክም ደግሞ ወደ እንስሳነት ዝቅ ይላል።

በዘመናችን የሚገጥሙን ችግሮች መፍትሄ አልባ የሆኑብን እናውቃለን በሚሉ የማያውቁትን በሚናገሩ ሰዎች ምክንያት ነው ብንል ብዙ ማስረጃዎች ስለሚኖሩን አልተሳሳትንም። ይህን ስንል ደርሶባቸው ስለማያውቁ ብቻ ሳይሆን ከላይ በገለጽናቸው ምክንያቶች ማወቃቸው ስለተወሰደባቸው መሆኑን ልብ ይሏል።

በሀገራችን በኢትዮጵያ በዘመናችን የሆነውን ሁሉ እንዘርዝር ብንል የምድራችን የብሱ ብራና ውሃው ቀለም ሆኖ ቢጻፍ ዘርዝሮ መጻፍ አይቻልም። እንዲሁ በጥቅሉ ''ሀሎኑ በዝ ሰማይ አምላክ አዶናይ'' የሚሉ እናቶችን ጩኸት እየሰማን ዘመናት አለፉ። ሰዎች ከሞላው ጎድሎባቸው ሲያለቅሱ አይተን አዝነን ነበር የባሰ አታምጣ የሚለውን ጸሎት ጥቅም ስላልተረዳነው የባሰ አታምጣ አላልንምና ወገኖቻችን ያላቸው ሁሉ ተወስዶ መኖር ቅንጦት ሲሆንባቸው ለማየት በቃን እድሜ ደጉ ማለት ባንችልም ብዙ ግን አሳየን። 

በሀገራችን ለዘመናት ሲደርስ የነበረው ግፍና መከራ ጽዋው ሞልቶ ሰዎች እየጮሁ የፍትህ ያለህ እያሉ እንደሆነ በዓለም ሚዲያ እያየን ነው። ይህ ጩኸት ተራ ጩኸት አይመስልም። ይህ የህዝብ ማእበል የተቃውሞ ድምጽ ሲያሰማ በንቀት ልንመለከተው የሚገባ አይመስልም ይልቁንም ሀገራችን ኢትዮጵያ ለህዝቦቿ በሙሉ የጋራ መሆኗን የምናይበት ጥሩ መስተዋት ይመስለኛል። ስለዚህ ሀገርንም ኦርቶዶክሳዊት ተዋህዶ ቤተክርስቲያንንም አፍርሶ ሌላ መልክ ለመስጠት እየተሄደበት ያለው መንገድ አዋጭ አለመሆኑን ተረድቶ ወደ ትክክለኛው መስመር በመመለስ ከሰላምና ከፍቅር የሚገኘውን በረከት መብላት ብልህነት ነው በእልክና በእብሪት ጥፋት እንጅ ልማት አይገኝም። 

ኢትዮጵያውያንን ከዓለም ልዩ የሚያደርጋቸው ባህርያቸው ሀገራቸውን እና ሃይማኖታቸውን አጥብቀው መውደዳቸው ነው። ሀገር ሲባል ሜዳ ገደሉ ብቻ ሳይሆን ለዘመናት የካበተው ባህልና ማንነት ማለት ነው። ሃይማኖት ማለት ደግሞ እግዚአብሔር ከሞት በኋላ ለሰው ልጆች ያዘጋጀውን የዘለዓለም ህይዎት ያሳየበት (የገለጠበት) መንገድ ማለት ነው። ኢትዮጵያውያን እነዚህን ለዘመናት ይዘዋቸው የኖሩትን ሀገርና ሃይማኖትን ሊጎዳ የሚችል ፈተና ስለገጠማቸው መራር ጭንቅና መከራ ላይ ይገኛሉ ታዲያ በዚህ ጊዜ ብንችል ሁሉን ለሚያውቀው ፈጣሪ ህዝቡን እንዲያስብ በጸሎት መጠየቅ ካልሆነ ዝም ማለት አስተዋይነት ነው። ፃድቁ ኢዮብ ከደረሰበት መከራ ይልቅ በዙሪያው የነበሩ ሰዎች በሚናገሩት ማስተዋል የጎደላቸው ቃላት እጅግ ይታመም እንደነበር በቅዱስ መጽሐፍ ተጽፏል። ኢዮ 6፥1

በተለይ አንዳንድ የቤተመንግስት እንጀራ መብላት እድል ያገኙ የረሃብን ስሜት ማጣጣል የጀመሩ ሰዎች የተዘረጋላቸው ማእድ እስኪታጠፍ ዝም ብለው ሆዳቸውን ቢሞሉ መልካም ሳይሆን አይቀርም ካልሆነ ግን መከራው በነሱ ጽኑዕ ሆኖ ይመጣልና እዳ በደል እንዳይሆንባቸው ሊመከሩ ይገባል። ''በሰው ቁስል እንጨት ስደድበት'' እንዲሉ በሰው ህመም ለማትረፍ መሞከር እንደ ግያዝ በሌሎች ላይ የተጫነው መከራ በተራገፈ ጊዜ በእነርሱ ላይ እጥፍ ሆኖ መውደቁ አይቀሬ ነውና ተዉ እንበላቸው። 2ኛ ነገ 5፥25

ይህ ሁሉ ለምን ሆነብን?

በእኛ ዘንድ እግዚአብሔርን መፍራት ከራቀ ሰነባበተ ቤቱን መድፈር የነፃነት፣ የስልጣኔ፣ የእድገት፣ የለውጥ መንገድ መሆኑን ማውረት ከጀመርን አመታት ተቆጠሩ እርሱ ግን አሁንም ትእግስቱን ከእኛ አላራቀም ። ትላንት መገፋትን መከራን ችግርን ያለፍን ሰዎች ጊዜ ሰጠን ብለን የድሆችን እንባ ቸል ብለናል። እራበኝ ለሚለው ጥይት ሰጥተናል ዳቦ ለሚለው ጅራፍ መዘናል ተጠማሁ ለሚለው መርዝ ሰጥተናል የሚለብሰው የሌለውን ቤቱን አፍርሰናል መሄጃ ያጣውን ከቅየው አሳደናል ብዙዎች ያፈሰሱት እንባ ተመልካች አጥቶ ወደ ፈጣሪ አንብተዋል ይህን ሁሉ ፈጣሪ የማያይ ይመስለናልን? በመጨረሻም የቅዱስ ዳዊትን ተናግረን እንፈጽም ''እግዚአብሔር የበቀል አምላክ ነው፤ የበቀል አምላክ ተገለጠ።የምድር ፈራጅ ሆይ፥ ከፍ ከፍ በል፤ ለትዕቢተኞች ፍዳቸውን ክፈላቸው።አቤቱ፥ ኃጢአተኞች እስከ መቼ? ኃጢአተኞች እስከ መቼ ይጓደዳሉ?ይከራከራሉ፥ ዓመፃንም ይናገራሉ፤ ዓመፃንም የሚያደርጉ ሁሉ ይናገራሉ።አቤቱ፥ ሕዝብን አዋረዱ፥ ርስትህንም አስቸገሩ።ባልቴቲቱንና ድሀ አደጉን ገደሉ፥ ስደተኛውንም ገደሉ።እግዚአብሔር አያይም፥ የያዕቆብ አምላክ አያስተውልም አሉ።የሕዝብ ደንቆሮች ሆይ፥ አስተውሉ፤ ሰነፎችማ መቼ ይጠበባሉ?ጆሮን የተከለው አይሰማምን? ዓይንን የሠራው አያይምን?'' መዝ 94፥1

                                            

ቀሲስ ዘለዓለም ጽጌ

ሐምሌ 28 ቀን 2015 ዓ/ም 

ሴንት ልውስ ሚዙሪ


  

No comments:

Post a Comment