ዛሬ ላይ እየመታን ያለው እንቅፋት ትላንት ከትላንት ወዲያ ሲያደናቅፈን ነበር በየወቅቱ አልፈናቸው የመጣናቸው እንቅፋቶች ቋጥኝ እየሆኑ ከእግራችን አልፈው ወደ ጉልበታችን ሊደርሱ ችለዋል::
እንቅፋት አንድ ጊዜ መትቶህ አልፈኸው ሄደህ ድጋሚ ከመታህ . . . . . ይባላል ታዲያ እውነትም እንደ አባባሉ አልፈነው የመጣነው እሾህ ከሆነ እየወጋን ያለው የማነው ስህተቱ? ቤተክርስቲያን ምንም በፈተና ውስጥ የምትኖር ነች ቢባልም ባለፉት አርባና ሃምሳ አመታት የገጠማት ፈተና ግን ከውስጧ ባሉ ልጆቿ የሚነሳ ሆኖ ለውጭ ጠላትም በር እየከፈተ ቤተክርስቲያንን ያለስሟ መጥፎ ስም የሚሰጡ ሰዎች እንዲበረክቱ ምክንያት የሆነ ነው።
ለቤተክርስቲያን ፈተና መብዛት ምክንያት የሆኑ ነገሮችን ነቅሶ ማውጣት መድኃኒቱን ለማግኘት መፍትሄ ይመስለኛል "ህመሙን ያልተናገረ መድኃኒት አይገኝለትም" እንደሚባለው ወደንም ሆነ ሳንፈልግ ችግሮቻችን ላይ እርምጃ ለመውሰድ መነሳት ካልጀመርን ሃዘንና ለቅሶ መከራን ይጨምራሉ እንጅ መፍትሄ አያመጡም።
ፖለቲካን ከቤታችን እናርቅ,
ፖለቲካ በባህርይው ከሃይማኖት ጋር ተቃራኒ ነው የእምነት ሰው ከእኔ ይልቅ ለወንድሜ ቅድሚያ፣ ከሃሰት ይልቅ እውነት፣ ከምድራዊ ነገር ይልቅ ሰማያዊ ነገር ይበልጣል፣ የሚል ሲሆን ፖለቲከኛ ግን ተቀባይነት ለማግኘት ሲል ከሰይጣን ማህበርም ጋር ሊተባበር ይችላል። ስለዚህ ፖለቲከኞች ቤተክርስቲያን ውስጥ ቦታ ሊኖራቸው አይገባም። ይህም ማለት የቤተክርስቲያኒቱ መሪዎችም ሆነ አገልጋዮች ቤተክርስቲያኒቱን በተመለከተ ከሚደረግ ግንኙነት ውጭ ከፖለቲከኞች ጋር ያላቸውን ያልተቀደሰ ጋብቻ ስለቤተክርስቲያን ክብር ሲባል ፍች ሊያደርጉ ይገባል። ፖለቲከኞች ያለቤተክርስቲያን ህልውናቸው አደጋ እንደሚገጥመው ስለሚያውቁ የሚጠቅሙ መስለው በመቅረብ ዓላማቸውን ያስፈጽማሉ ቤተክርስቲያን ግን ያለፖለቲከኞች እርዳታ መኖር ትችላለች። በእኔ እድሜ ኦርቶዶክሳዊት ተዋህዶ ቤተክርስቲያንን በጠላትነት የሚመለከት እንጅ በጎ ሥራዋን ተመልክቶ እውቅና የሰጠ መንግስት አላየሁም። ስለዚህ ለቤተክርስቲያናችን ፖለቲካ ትልቅ እንቅፋት እየሆነባት ስለሆነ ፖለቲካን በሩቁ ማድረግ አለባት
ዘረኝነት
ቤተክርስቲያን ምንም መንፈሳዊ ተቋም ብትሆንም የሰው ልጆች እንዲሰባሰቡባት በእግዚአብሔር ፈቃድ የተመሰረተች የቅዱሳን ማህበር ነች ይሁን እንጅ በየዘመኑ የሰው ልጆች የሥጋ ፈቃዳቸውን ሳያሸንፉ ወደ ቤተክርስቲያን ስለሚጠጉ ማንነቷን የሚያጎድፍ ሥራ ሊሰሩ ይችላሉ ይህ የሚሆነው ከሰው ልጆች የስጋ ፈቃድ የተነሳ እንጅ የቤተክርስቲያን ባህርይ ሆኖ አይደለም የቤተክርቲያን ባለቤት አምላካችን ፈጣሪያችን መድኃኔ ዓለም ኢየሱስ ክርስቶስ ወደዚህ ዓለም የመጣው አዳምን ሊያድን ነው የምንለው ሰው ሁሉ ከአንድ አዳም የተገኘ በመሆኑ ነው ቅዱስ ቃሉ እንደሚነግረን ''ሁሉ በአዳም እንደሚሞቱ እንዲሁ ሁሉ በክርስቶስ ደግሞ ሕያዋን ይሆናሉና'' 1ኛ ቆሮ 15፥22 እንዳለ ቅዱስ ጳውሎስ ሁላችን በክርስቶስ አንድ የአዳም ዘሮች ነን ስለዚህ እንኳን መንፈሳዉያን የተባልን ይቅርና ለሰው ዘር በሙሉ ዘረኝነትን ማራመድ በእግዚአብሔር ዘንድ የተጠላ ነው ስለዚህ ቤተክርስቲያን እግዚአብሔር የሚጸየፈውን ነገር ከውስጧ ልታጠፋ ይገባታል። ዘረኝነትን የሚያራምዱ ሰዎችንም በፍጹም ልትታገሳቸው አይገባም። በመሰረቱ በዘረንነት የተጠመዱ ሰዎች ወገናቸውን የሚወዱ ሆነው ሳይሆን እራስ ወዳዶች ስለሆኑ ነው የራሴ የምለው ሰው ይጠቅመኛል በሚል ሥጋዊ ፍትወት እንጅ ወገንን ከመውደድ የሚመጣ በጎነት አይደለም እንዲህ ዓይነት ሰዎች የራሴ ዘር ከሚሉት ወገን ብቻ ሳይሆን ይጠቅመኛል ብለው ካሰቡ ከማንኛውም ጋር ሊስማሙ ይችላሉ ስለዚህ ይህ ከመንፈሳዊ ህይዎት ፍጹም ተቃራኒ በመሆኑ ለቤተክርስቲያን እንቅፋት ይሆናል ሁላችንም ልንጸየፈው ያስፈልጋል።
ቤተክርስቲያን ከገንዘብ ይልቅ ጸጋ እግዚአብሔር የሚገኝባት መሆኗን ማሳየት,
ገንዘብ ለመንፈሳዊ ህይዎት ትልቅ እንቅፋት ነው በአሁኑ ወቅት ጥቂት የማይባሉ የሃይማኖት መሪዎችና አገልጋዮች ቤተክርስቲያንን የሚወዷት ጥሩ ደመወዝ ስለምትከፍል እንዲሁም የተለያዩ ጥቅማ ጥቅሞች ስለሚገኝባት እንጅ በረከት የሚገኝባት የሰማይ ደጅ ናት ብለው አይደለም። እነርሱ የሚፈልጉት ገንዘብ ነው ስለዚህ በቤተክርስቲያን የሚመጣው ፈተና አያስጨንቃቸውም። ስለመንጋው መበተን ግድ የላቸውም ጠባያቸው እንደ ወንበዴ ነው ለመንጋው አይራሩም ስለዚህ ገንዘብ የሚገኝበት ከሆነ ቤተክርስቲያንንም ቢሆን ከመሸጥ ወደኋላ አይሉም። ቅዱስ ጳውሎስ “ነገር ግን፥ ወንድሞች ሆይ፥ እናንተ የተማራችሁትን ትምህርት የሚቃወሙትን መለያየትንና ማሰናከያን የሚያደርጉትን ሰዎች እንድትመለከቱ እለምናችኋለሁ፥ ከእነርሱ ዘንድ ፈቀቅ በሉ፤”“እንዲህ ያሉት ለገዛ ሆዳቸው እንጂ ለጌታችን ለኢየሱስ ክርስቶስ አይገዙምና፥ በመልካምና በሚያቆላምጥ ንግግርም ተንኮል የሌለባቸውን ሰዎች ልብ ያታልላሉ። ሮሜ 16፥17 “መጨረሻቸው ጥፋት ነው፥ ሆዳቸው አምላካቸው ነው፥ ክብራቸው በነውራቸው ነው፥ አሳባቸው ምድራዊ ነው።” ፊልጵስዩስ 3፥19
የሃይማኖት እና የምግባር ችግር ያለባቸው ሰዎች ሌሎቹ እንቅፋቶች
በቤተክርስቲያናችን ውስጥ ትልቁን ችግር እየፈጠሩ ያሉት የእምነትና የምግባር ችግር ያለባቸው ሰዎች ናቸው እየተወሰደ ያለው እርምጃ ደግሞ አስተማሪ ሳይሆን ማናለብኝነት ሥር እንዲሰድ የሚያደርግ ነው ዛሬ ቤተክርስቲያንን አደጋ ላይ ለመጣል እየሮጡ ያሉ ወገኖች በተለያየ ጊዜ ከሃይማኖት ያፈነገጠ ተግባር ሲፈጽሙ ታይተው በዝምታ የታለፉ ናቸው በሌላ የእምነት ተቋም ውስጥ ሆነው ቤተክርስቲያንን በመሳደብ ላይ ያሉ መናፍቃንም ትላንት የማይገባቸውን ክብርና ማእረግ በመስጠት በቤተክርስቲያን ውስጥ ትልቅ ስፍራ ተሰጥቷቸው ምእመናንን ሲያሰናክሉ የነበሩ ናቸው ይህ ሁሉ ሲሆን የነበረው ደግሞ የቤተክርስቲያን መሪዎች ከቤተክርስቲያን ክብር ይልቅ የራሳቸውን ክብር በማስቀደም ለጊዜያዊ ከንቱ ውዳሴ ሲባል የተቀደሰውን ለውሾች አትስጡ የተባለውን ዘንግተው ክቡሩን ስልጣነ ክህነት ሳይቀር በመስጠት ምስጢረ ቤተክርስቲያን እንዲጎድፍ በማድረጋቸው ነው። ለአገልግሎት እውቀትን ብቻ ሳይሆን ሃይማኖትንም መስፈርት ማድረግ ያስፈልጋል ለጥንታዊቷ ቤተክርስቲያን ታላቅ ፈተና ይዘው የመጡት እነ አርዮስ እነ ንስጥሮስ በእውቀት የማይታሙ ነበሩ ነገር ግን እውቀታቸው ከጥፋት አላዳናቸውም ከእውቀት በፊት እምነት ያስፈልጋል ለእውቀት መሰረቱ እምነት መሆን አለበት አለበለዚያ ሰው በእውቀት ብቻ አንዳች ነገር ሊያደርግ አይችልም እንደውም እውቀቱ መጥፊያ ሊሆነው ይችላል ስለዚህ ቤተክርስቲያን አገልጋዮችንንና መሪዎችን ስትሰይም ለመንጋው የሚራሩ በእምነታቸው በምግባራቸው የተመሰከረላቸውን መሆን አለበት ለዓለም ረብና ጥቅም የማይደለለሉመሆናቸውን ማረጋገጥ አለባት በቀድሞው ዘመን የነበረውን መስፈርት መልሶ ማምጣት ያስፈልጋል። ብርሃነ ዓለም ቅዱስ ጳውሎስ ስለ አገልግሎት መመረጥ ለሐዋርያው ለቅዱስ ጢሞቴዎስ ''ማንም ኤጲስ ቆጶስነትን ቢፈልግ መልካምን ሥራ ይመኛል የሚለው ቃል የታመነ ነው።እንግዲህ ኤጲስ ቆጶስ እንዲህ ሊሆን ይገባዋል፤ የማይነቀፍ፥ የአንዲት ሚስት ባል፥ ልከኛ፥ ራሱን የሚገዛ፥ እንደሚገባው የሚሰራ፥ እንግዳ ተቀባይ፥ ለማስተማር የሚበቃ፥የማይሰክር፥ የማይጨቃጨቅ ነገር ግን ገር የሆነ፥ የማይከራከር፥ ገንዘብን የማይወድ፥ልጆቹን በጭምትነት ሁሉ እየገዛ የራሱን ቤት በመልካም የሚያስተዳድር፤ሰው ግን የራሱን ቤት እንዲያስተዳድር ባያውቅ፥ የእግዚአብሔርን ቤተ ክርስቲያን እንዴት ይጠብቃታል?በትዕቢት ተነፍቶ በዲያብሎስ ፍርድ እንዳይወድቅ፥ አዲስ ክርስቲያን አይሁን።በዲያብሎስ ነቀፋና ወጥመድም እንዳይወድቅ፥ በውጭ ካሉት ሰዎች ደግሞ መልካም ምስክር ሊኖረው ይገባዋል።እንዲሁም ዲያቆናት ጭምቶች፥ በሁለት ቃል የማይናገሩ፥ ለብዙ ወይን ጠጅ የማይጎመጁ፥ነውረኛ ረብ የማይወዱ፥ በንጹሕ ሕሊና የሃይማኖትን ምሥጢር የሚይዙ ሊሆኑ ይገባቸዋል።እነዚህም ደግሞ አስቀድሞ ይፈተኑ፥ ከዚያም በኋላ ያለ ነቀፋ ቢሆኑ በዲቁና ሥራ ያገልግሉ።እንዲሁም ሴቶች ጭምቶች፥ የማያሙ፥ ልከኞች፥ በነገር ሁሉ የታመኑ ሊሆኑ ይገባቸዋል።ዲያቆናት ልጆቻቸውንና የራሳቸውን ቤቶች በመልካም እየገዙ እያንዳንዳቸው የአንዲት ሴት ባሎች ይሁኑ።በዲቁና ሥራ በመልካም ያገለገሉ ለራሳቸው ትልቅ ማዕርግና በክርስቶስ ኢየሱስ ባለው እምነት ብዙ ድፍረት ያገኛሉ'' 1ኛ ጢሞ 3፥1 ብሎ ጽፎለታል። በሌላም ስፍራ ለቅዱስ ቲቶ በጻፈው መልእክቱ '' በሃይማኖት ኅብረት እውነተኛ ልጄ ለሚሆን ለቲቶ፤ ከእግዚአብሔር አብ ከመድኃኒታችንም ከጌታ ከኢየሱስ ክርስቶስ ጸጋና ምሕረት ሰላምም ይሁን።ስለዚህ ምክንያት የቀረውን እንድታደራጅ በየከተማውም፥ እኔ አንተን እንዳዘዝሁ፥ ሽማግሌዎችን እንድትሾም በቀርጤስ ተውሁህ፤የማይነቀፍና የአንዲት ሚስት ባል የሚሆን፥ የሚያምኑም ልጆች ያሉት፥ ስለ መዳራትም ወይም ስለ አለመታዘዝ የማይከሰስ ማንም ቢኖር፥ ሹመው።ኤጲስ ቆጶስ፥ እንደ እግዚአብሔር መጋቢ፥ የማይነቀፍ ሊሆን ይገባዋልና፤ የማይኮራ፥ የማይቆጣ፥ የማይሰክር፥ የማይጨቃጨቅ፥ ነውረኛ ረብ የማይወድ፥ነገር ግን እንግዳ ተቀባይ፥ በጎ የሆነውን ነገር የሚወድ፥ ጠንቃቃ፥ ጻድቅ፥ ቅዱስ፥ ራሱን የሚገዛ ይሁን፤ሕይወት በሚገኝበት ትምህርት ደግሞ ሊመክር ተቃዋሚዎቹንም ሊወቅስ ይችል ዘንድ፥ እንደተማረው በታመነ ቃል ይጽና " ቲቶ 1፥4 የቤተክርስቲያንን የውስጥ ፈተናዎችን ለመቀነስ ብቁና ታማኝ የሆኑ አገልጋዮችን ማሰለፍ ቀዳሚው መፍትሄ ይመስለኛል።
ቤተክርስቲያን አገልግሎቷ ዘመኑን የዋጀ እንዲሆን መስራት
ያለንበት ዘመን መረጃ ለማግኘትም ሆነ ለማድረስ ምቹ መሆኑ ግልጽ ነው የዘመኑ የሃይማኖት ፖለቲካም ሆነ የእምነት ተቋም ትልቁን ሥራ የሚሰሩ ዘመኑ በፈጠረው ማህበራዊ መገናኛ መረብ ነው እኛ ቤት ግን የቤተክርስቲያን አባቶች ከህዝቡ ሲጠብቁ ህዝቡም ኃላፊነቱን ለአባቶች በመስጠት መስራት የሚገባንን መስራት ባለመስራታችን ቤተክርስቲያንን አደጋ ላይ እየጣልናት ነው። ስለዚህ የቤተክርስቲያን አባቶች የሚሰሩትን እና በየደረጃው ያሉ የቤተክርስቲያን ልጆች ሊያደርጉ የሚገባውን አስተዋጽኦ በግልጽ መመሪያ በማውጣት ኃላፊነቱን ሊወጣ ለሚችል አካል ልንሰጥ ይገባል እንደ እውነቱ ከሆነ ቤተክርስቲያንን ክርስቶስ ስለሚጠብቃት እንጅ እንደቤተክርስቲያን መሪዎች ቢሆን ኖሮ በበረቱ አንድም መንጋ ባልተገኘ ነበር። በመጨረሻም በአሁኑ ወቅት የቤተክርስቲያንን ቀኖና በመጣስ የምእመናንን ሰላም በማደፍረስ ላይ ላላችሁ ወገኖች ይህን ማለት እወዳለሁ አባቶቻችን እንዳስተማሩን ''ቤተክርስቲያን አንዲት ናት፡፡ ቤተክርስቲያን አንዲት (አሐቲ) ናት፡፡ ሁለት ወይም ሦስት ወይም ከዚያ በላይ አትሆንም፡፡ ከአንድም አታንስም፡፡ አይጨመርባትም፡ አይቀንስባትምም፡፡ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ …”በዚህ አለት ላይ ቤተክርስቲያኔን እመሠርታለሁ” አለ እንጂ “ቤተክርስቲያኖቼን” አላለም፡፡ ማቴ 16፡18 በአንድ መሠረት ላይ አንዱ መሥራች የመሠረታት ስለሆነች ቤተክርስቲያን አንዲት ናት'' ስለዚህ እንኳን በምድራዊ ስልጣንና ገንዘብ ይቅርና መንፈሳዊ ጥያቄ እንኳን ቢኖረን ዶግማዋንና ቀኖናዋን እንዲሁም ሥርዓቷን ጠብቀን እውነትን መሰረት በማድረግ በፊት ለፊት በእምነት በጾም በጸሎት እንታገላለን እንጅ እኔ ከሞትኩ ሰርዶ አይብቀል በሚል ምድራዊ ፍትዎት ተይዘን ቤተክርስቲያንን ለመጉዳት መነሳት መጨረሻው ጥፋት ነውና ከያዝነው የጥፋት መንገድ በጊዜ ብንመለስ ብልህትና አስተዋይነት ነው እላለሁ። ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ ለቆሮንቶስ ክርስቲያኖች በጻፈው መልእክቱ ''ነገር ግን፥ ወንድሞች ሆይ፥ ሁላችሁ አንድ ንግግር እንድትናገሩ በአንድ ልብና በአንድ አሳብም የተባበራችሁ እንድትሆኑ እንጂ መለያየት በመካከላችሁ እንዳይሆን በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ስም እለምናችኋለሁ።ወንድሞቼ ሆይ፥ በመካከላችሁ ክርክር እንዳለ ስለ እናንተ የቀሎዔ ቤተ ሰዎች አስታውቀውኛልና።ይህንም እላለሁ፦ እያንዳንዳችሁ፦ እኔ የጳውሎስ ነኝ፥ እኔስ የአጵሎስ ነኝ፥ እኔ ግን የኬፋ ነኝ፥ እኔስ የክርስቶስ ነኝ ትላላችሁ።ክርስቶስ ተከፍሎአልን? ጳውሎስስ ስለ እናንተ ተሰቀለን? ወይስ በጳውሎስ ስም ተጠመቃችሁን? 1ኛ ቆሮ 1፥10 ብሎ እንደጻፈልን ቤተክርስቲያን የክርስቶስ ቤት ነች እኛ ልጆቹ በፍቅርና በአንድነት እንድንኖርባት እንጅ በመለያየት የወንበዴዎች ዋሻ እንድናደርጋት አልሰጠንም።
Saturday, February 11, 2023
የትላንቱ እንቅፋት
Subscribe to:
Post Comments (Atom)
No comments:
Post a Comment