Monday, July 22, 2019

መንግሥት ከወዳጅና ከተቃዋሚ የትኛውን ይጠንቀቅ?

እግዚአብሔር ቢፈቅድ የግል አቋሜ መንግሥትን በምችለው መንገድ በሃሳብ እንዲሁም በጸሎት ማገዝ እንጂ ለመንግሥት የቤት ሥራ መሆን አልፈልግም። ነገር ግን የሚታየውን ጉልህ ስህተት በግልጽ መንገር መንግሥትን ያነቃል እንጅ ጉዳት የለውም። ለሌሎችም የምመክረው ይኸንኑ ነው። ምክንያቱም ሀገር የሚመሩት ምንም መልካም ነን ቢሉ እንደ ሰው ደካማ ናቸውና ይሳሳታሉ። ስለዚህ መሪዎችን በጠላትነት ከመፈረጅ ይልቅ እንድንጸልይላቸው ታዘናል። እንኳን በከፍተኛ ኃላፊነት ውስጥ ሆነው ለሚሳሳቱት ይቅርና ለጠላቶቻችንም ልንጸልይ ይገባል። እንዲህ ተብሎ እንደተጻፈ '' እኔ ግን እላችኋለሁ፥ በሰማያት ላለ አባታችሁ ልጆች ትሆኑ ዘንድ ጠላቶቻችሁን ውደዱ፥ የሚረግሙአችሁንም መርቁ፥ ለሚጠሉአችሁም መልካም አድርጉ፥ ስለሚያሳድዱአችሁም ጸልዩ፤ እርሱ በክፎዎችና በበጎዎች ላይ ፀሐይን ያወጣልና፥ በጻድቃንና በኃጢአተኞችም ላይ ዝናቡን ያዘንባልና።
⁴⁶ የሚወዱአችሁን ብትወዱ ምን ዋጋ አላችሁ? ቀራጮችስ ያንኑ ያደርጉ የለምን? ማቴ ፭፥፵፭

Sunday, March 17, 2019

እጽፍላችሁ ዘንድ ግድ ሆነብኝ ይሁዳ 1፥3

ባለንበት ዘመን ከራስ አልፎ ስለሰው ማሰብ እጅግ ከባድ እንደሆነ እለት እለት ስለ ሌሎች የሚደክሙ ወገኖች ቢናገሩ መልካም ይሆናል። ነገር ግን ከራስ አልፎ ለሌላው የሚተርፍ ቅንጣትም እንኳ ብትሆን ዋጋ አላት ብየ አምናለሁ። ምናልባት የሁላችንም የእውቀት ደረጃ እና የአስተሳሰብ ችሎታ ስለሚለያይ ለሁሉ መልካም የማይመስል ሃሳብ ልንሰነዝር እንችል ይሆናል ቢሆንም ግን ለተጠቀመበት ሰው በጎ ያልሆነውም ነገር ቢሆን አስተማሪ ነው። 

Wednesday, March 6, 2019

የድሃዋ እንባ መዘዝ

ህዝበ እስራኤል በግብጽ ስደት በነበሩበት ዘመን የደረሰባቸው መከራ እጅግ የከፋ እንደነበር በኦሪት ዘጸአት ምእራፍ 1፥8 ጀምሮ ያለውን ታሪክ ስናነብ በሰፊው እንረዳለን። ምንም እንኳን በስደት በሰው ሀገር የሚኖሩ ቢሆንም እንደሰው ሊሰጣቸው የሚገባውን ክብር በማጣታቸው የመከራ ኑሮ ይኖሩ ነበር። ሰው በሰውነቱ የትም ቢሆን ክብር ሊሰጠዉ ይገባል። ወደ ታሪኩ ስንመለስ እንደ ሰው ሰርቶ መብላት፣ ቀን ሰርቶ ሌሊት ማረፍ፣ ወልዶ መሳም፣ ሰርቶ የድካምን ዋጋ ማግኘትወ ዘ ተ አይፈቀድላቸውም ነበር። ዛሬ በእኛም ሀገር ይህ ሲፈጸም በተደጋጋሚ አይተናል። በእስራኤላውያን ላይ ይህ ግፍ ሊደርስ የቻለው አስቀድሞ ለምድረ ግብጽ መልካም ያደረገ እስራኤላዊ ዮሴፍን የማያውቅ ንጉስ በመነሳቱ ነበር። ክፉና ጠማማ ሰው ደግነትን ቢያውቃትም የበጎ ነገር ጠላት መሆኑ የተለመደ ነው። ዛሬ በየክፍለ ሀገሩ ሰዎች እየተፈናቀሉ ያለው በጎው ነገር ጠፍቶ ሳይሆን የበጎውን ዘመን ሰዎች ታሪክ መዘከር ስለማይፈለግ ነው። እስራኤላውያን ችግራቸውን የሚመለከት ዳኛ በማጣታቸው አምርረው አለቀሱ። የለቅሷቸው መጠን ምን ያክል እንደሆነ ለመረዳት በፈርኦን ላይ የመጣውን መአት አይቶ መረዳት ይቻላል። ዛሬም በሞኝነት አይናችሁ ታውሮ የድሆችን እንባ ቸል የምትሉ ነገ ጎርፍ ሆኖ እናንተንና የኔ የምትሉትን ያሰጥማችኋልና አስቡበት።




Monday, February 18, 2019

ነነዌን እናስብ

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ከሌሎች ልዩ የሚያደርጋት በጎ ሥራዎችንና መልካም ያደረጉ ሰዎችን አክብራ ለትውልድ እንዲተላለፍ ማድረጓ ነው። መቼም በጎ ነገር ሲታወስ ክፋቱም አይረሳምና ለትምህርት እንዲሆን ይዘከራል። ስለ ቃየን ባንሰማ ኖሮ የአቤልን ደግነት ልንረዳው አንችልም ነበርና።

የነነዌ ሰዎችን ስናስብ የእግዚአብሔርን ቸርነትና ከሃሊነት፣ የዮናስን አለመታዘዝ፣ የኃጢአታቸውን መጠን፣ እንዲሁም ለንስሃ ታዛዥነታቸውን እናገኛለን።

እግዚአብሔር ቸርና መኃሪ አምላክ መሆኑን ከቅዱሳት መጻህፍት ተረድተን በህይዎታችን አውቀነዋል። እንዲህ ተብሎ እንደተጻፈ ‘’እርሱ ግን መሓሪ ነው፥ ኃጢአታቸውንም ይቅር አላቸው፥ አላጠፋቸውምም፤ ቍጣውንም መመለስ አበዛ፥ መዓቱንም ሁሉ አላቃጠለም’’ መዝ 78፥38 እዚህ ላይ ልንገነዘበው የሚገባው የእግዚአብሔር ቸርነት ወደ ንስሃ የሚያቀርብ እንጅ የሰውን ልጅ ነጻነት የሚከለክል እንዳልሆነ ማስተዋል ያስፈልጋል።

Sunday, February 10, 2019


ዘርፌ የተዋህዶ ዘማሪ አልነበረችም።

ዘመኑ የፈጠረው ክፉ ነገር ቢኖር አንድ ሰው እራሱን የፈለገው ቦታ አስቀምጦ በሚዲያ ሲያሰራጭ የጉዳዩን እውነተኛ ነት ሳያረጋግጡ የሚያራግቡ ሰዎች መብዛታቸው ነው። ብዙ ሰዎች ቤተክርስቲያንን ወክለው መግለጫ ይሰጣሉ ብዙ ተቀባይ አላቸው። አንዳንዶች እራሳቸውን ከመንግስት በላይ አድርገው ስለሀገር ጉዳይ መግለጫ ይሰጣሉ እነሱም ብዙ ደጋፊ አላቸው። ይህ ችግር በብዙዎች እይታ ስልጣኔ ተነፍጎ ለኖረ ህዝብ ከአቅሙ በላይ የሚሰጥ ነጻነት የሚያመጣው በሽታ እንደሆነ ታምኖበታል።