Monday, July 22, 2019

መንግሥት ከወዳጅና ከተቃዋሚ የትኛውን ይጠንቀቅ?

እግዚአብሔር ቢፈቅድ የግል አቋሜ መንግሥትን በምችለው መንገድ በሃሳብ እንዲሁም በጸሎት ማገዝ እንጂ ለመንግሥት የቤት ሥራ መሆን አልፈልግም። ነገር ግን የሚታየውን ጉልህ ስህተት በግልጽ መንገር መንግሥትን ያነቃል እንጅ ጉዳት የለውም። ለሌሎችም የምመክረው ይኸንኑ ነው። ምክንያቱም ሀገር የሚመሩት ምንም መልካም ነን ቢሉ እንደ ሰው ደካማ ናቸውና ይሳሳታሉ። ስለዚህ መሪዎችን በጠላትነት ከመፈረጅ ይልቅ እንድንጸልይላቸው ታዘናል። እንኳን በከፍተኛ ኃላፊነት ውስጥ ሆነው ለሚሳሳቱት ይቅርና ለጠላቶቻችንም ልንጸልይ ይገባል። እንዲህ ተብሎ እንደተጻፈ '' እኔ ግን እላችኋለሁ፥ በሰማያት ላለ አባታችሁ ልጆች ትሆኑ ዘንድ ጠላቶቻችሁን ውደዱ፥ የሚረግሙአችሁንም መርቁ፥ ለሚጠሉአችሁም መልካም አድርጉ፥ ስለሚያሳድዱአችሁም ጸልዩ፤ እርሱ በክፎዎችና በበጎዎች ላይ ፀሐይን ያወጣልና፥ በጻድቃንና በኃጢአተኞችም ላይ ዝናቡን ያዘንባልና።
⁴⁶ የሚወዱአችሁን ብትወዱ ምን ዋጋ አላችሁ? ቀራጮችስ ያንኑ ያደርጉ የለምን? ማቴ ፭፥፵፭


ዛሬ ለደረስንበት አስከፊ ችግር የዳረጉን ስህተቶች የትኞቹ ናቸው ብለን ብናይ፦ሁሉን ወዳጅ አድርጎ ብዙ ውስብስብ ችግር ያለባትን ሀገር ያለ አንዳች ተቃውሞ አንድ አድርጎ ለመምራት የተሄደበት መንገድ ጥናት የጎደለውና ስሜት ያየለበት አካሄድ እንደነበር አፍን ሞልቶ መናገር ይቻላል።

ተቃዋሚ የሌለበት ዲሞክራሲያዊ ሀገር በምድር ላይ የለም ። ለሥም አጠራሩ ክብር ምስጋና ይግባውና ፈጣሬ ዓለማት የሆነው አምላካችን እግዚአብሔር  ሰይጣንን የመሰለ ክፉ አፍራሽ ጠላትን ለምን ማጥፋት አልፈለገም? ከሊቃውንት ጠይቆ መረዳት ይቻላል። ዶ/ር አቢይ ተቃዋሚ እንዳይኖራቸው የደከሙትን ያክል ኢትዮጵያን እንደ ሀገር እንድትቀጥል የሚያስፈልጋትን የህዝቦች ተቻችሎና ተሳስቦ የመኖር እሴቶች ተጠብቀው እንዲኖሩ ቢሰሩ  ኖሮ በህይወት እያለ ሀውልት የሚሰራለት የመጀመሪያው የዓለማችን መሪ ይሆኑ ነበር።

ታላቁ ሐዋርያ ቅዱስ ጳውሉስ ለቆሮንቶስ ክርስቲያኖች በጻፈው መልእክቱ ፲፩፥፱ ላይ '' በነገርም ሁሉ እንዳልከብድባችሁ ተጠነቀቅሁ እጠነቀቅማለሁ።
¹⁰ የክርስቶስ እውነት በእኔ እንዳለ፥ ይህ ትምክህት በእኔ ዘንድ በአካይያ አገር አይከለከልም።
¹¹ ስለ ምን? ስለማልወዳችሁ ነውን? እግዚአብሔር ያውቃል'' ብሏል ከቃሉ እንደምንረዳው ሰውን መጠንቀቅ ማለት መጥላት አይደለም ብዙ ጊዜ አላማን የሚያስተው በወዳጅነት ምክንያት የሚመጣ ቸልተኝነት በመሆኑ ነው። ሐዋርያው አስከትሎም ስለ አንዳንድ አስመሳይ ወዳጆች እንዲህ ይላል''   2ኛ ቆሮ 11
¹² ነገር ግን በዚያ በሚመኩበት እንደ እኛ ሆነው ሊገኙ፥ ምክንያትን ከሚፈልጉቱ ምክንያትን እቆርጥ ዘንድ አሁን የማደርገውን ከዚህ ወዲህ ደግሞ አደርጋለሁ።
¹³ እንደ እነዚህ ያሉ ሰዎች የክርስቶስን ሐዋርያት እንዲመስሉ ራሳቸውን እየለወጡ፥ ውሸተኞች ሐዋርያትና ተንኮለኞች ሠራተኞች ናቸውና።
¹⁴ ይህም ድንቅ አይደለም፤ ሰይጣን ራሱ የብርሃንን መልአክ እንዲመስል ራሱን ይለውጣልና።
¹⁵ እንግዲህ አገልጋዮቹ ደግሞ የጽድቅን አገልጋዮች እንዲመስሉ ራሳቸውን ቢለውጡ ታላቅ ነገር አይደለም፤ ፍጻሜአቸውም እንደ ሥራቸው ይሆናል። ።፪ኛ ቆሮ ፲፩፥፲፪ 

ልማት አስፈላጊ ነው ይኸን አላማ መደገፍ ያስፈልጋል። ነገር ግን ሰው እየነቀሉ ዛፍ መትከል፣ ሰውን ንቆ ዛፍን ማክበር፦ መንግሥት ቆም ብሎ ሊያስብበት የሚገባ አላማውን የሳተ አካሄድ ነው። 

በእኔ እምነት በአሁኑ ሰዓት ለመንግሥት ከደጋፊዎቹ ይልቅ ተቃዋሚዎቹ ይሻሉታል። ምክንያቱም ተቃዋሚዎች ሌት ተቀን የሚሰሩት የመንግሥትን ደካማ ጎን በማጥናትና የየእለት ስህተቶቹን በማቀናበር ለህዝብ ማጋለጥ ነው። ታዲያ መንግሥት ለምንድነው ስህተቶቹን ማረም የማይፈልገው? ምክንያቱም በወዳጆቹ የተከበበ ነዋ! ወዳጅ ደግሞ በጎው እንጅ ጥፋቱ አይታየውም፤ ስለዚህ ገደሉን ሜዳ፣ ጨለማውን ብርሃን፣ ትንሿን መልካም ነገር ተራራ አሳክሎ ማቅረብ ይወዳል። ታዲያ መንግሥት እንዴት እራሱን ለማስተካከል ይችላል? ብዙ ያደጉ ሀገራትን ታሪክ ስንመለከት የእድገታቸው መሰረት ተቃዋሚዎች በየእለቱ የሚተቹትን አሰራር ለማስተካከል በሚያደርጉት እሩጫ እና ከሌሎች ስህተት በመማር ሲሆን እኛ ከሁለቱም የለንበትም። 

በቅዱስ መጽሐፍ የተጻፈ አንድ ታሪክ አስተማሪ ነውና እንጥቀሰው፦ ንጉስ ሰሎሞን ከሞተ በኋላ በእርሱ ምትክ የነገሰው ልጁ ሮብዓም መልካም ምክርን ንቆ የደረሰበትን ውድቀት የሚያሳይ ታሪክ ነው እንዲህ ይነበባል''
³ ኢዮርብዓምና የእስራኤል ጉባኤ ሁሉ መጥተው ለሮብዓም፦
⁴ አባትህ ቀንበር አክብዶብን ነበር፤ አሁንም አንተ ጽኑውን የአባትህን አገዛዝ፥ በላያችንም የጫነውን የከበደውን ቀንበር አቃልልልን፤ እኛም እንገዛልሃለን ብለው ተናገሩት።
⁵ እርሱም፦ ሂዱ፥ በሦስተኛውም ቀን ወደ እኔ ተመለሱ አላቸው። ሕዝቡም ሄዱ።
⁶ ንጉሡም ሮብዓም፦ ለዚህ ሕዝብ እመልስለት ዘንድ የምትመክሩኝ ምንድር ነው? ብሎ አባቱ ሰሎሞን በሕይወቱ ሳለ በፊቱ ይቆሙ ከነበሩት ሽማግሌዎች ጋር ተማከረ።
⁷ እነርሱም፦ ለዚህ ሕዝብ አሁን ባሪያ ብትሆን ብትገዛላቸውም፥ መልሰህም በገርነት ብትናገራቸው፥ በዘመኑ ሁሉ ባሪያዎች ይሆኑልሃል ብለው ተናገሩት።
⁸ እርሱ ግን ሽማግሌዎች የመከሩትን ምክር ትቶ ከእርሱ ጋር ካደጉትና በፊቱ ይቆሙ ከነበሩት ብላቴኖች ጋር ተማከረ።
⁹ እርሱም፦ አባትህ የጫኑብንን ቀንበር አቃልልልን ለሚሉኝ ሕዝብ እመልስላቸው ዘንድ የምትመክሩኝ ምንድር ነው? አላቸው።
¹⁰ ከእርሱም ጋር ያደጉት ብላቴኖች፦ አባትህ ቀንበር አክብዶብናል፥ አንተ ግን አቃልልልን ለሚሉህ ሕዝብ፦ ታናሺቱ ጣቴ ከአባቴ ወገብ ትወፍራለች።
¹¹ አሁንም አባቴ ከባድ ቀንበር ጭኖባችኋል፥ እኔ ግን በቀንበራችሁ ላይ እጨምራለሁ፤ አባቴ በአለንጋ ገርፎአችኋል፥ እኔ ግን በጊንጥ እገርፋችኋለሁ በላቸው ብለው ተናገሩት።
¹² ንጉሡም፦ በሦስተኛው ቀን ወደ እኔ ተመለሱ ብሎ እንደ ተናገረ ኢዮርብዓምና ሕዝቡ ሁሉ በሦስተኛው ቀን ወደ ሮብዓም መጡ።
¹³ ንጉሡም ሽማግሌዎች የመከሩትን ምክር ትቶ ለሕዝቡ ጽኑ ምላሽ መለሰላቸው።
¹⁴ እንደ ብላቴኖችም ምክር፦ አባቴ ቀንበር አክብዶባችሁ ነበር፥ እኔ ግን በቀንበራችሁ ላይ እጨምራለሁ፤ አባቴ በአለንጋ ገርፎአችሁ ነበር፥ እኔ ግን በጊንጥ እገርፋችኋለሁ ብሎ ተናገራቸው።
¹⁵ እግዚአብሔርም በሴሎናዊው በአኪያ አድርጎ ለናባጥ ልጅ ለኢዮርብዓም የተናገረውን ነገር እንዲያጸና ከእግዚአብሔር ዘንድ ተመድቦ ነበርና ንጉሡ ሕዝቡን አልሰማም።
¹⁶ እስራኤልም ሁሉ ንጉሡ እንዳልሰማቸው ባዩ ጊዜ ሕዝቡ ለንጉሡ፦ በዳዊት ዘንድ ምን ክፍል አለን? በእሴይም ልጅ ዘንድ ርስት የለንም። እስራኤል ሆይ፥ ወደ ድንኳኖቻችሁ ተመለሱ፤ ዳዊት ሆይ፥ አሁን ቤትህን ተመልከት ብለው መለሱለት። እስራኤልም ወደ ድንኳኖቻቸው ሄዱ'' ፩ኛ ነገ፡፲፪፥፫  ከዚህ እምንማረው በአጠገባችን ካሉ ጥቂት አሳዎች ይልቅ ባህር የሆነውን ህዝብ ማዳመጥ ተገቢ መሆኑን ነው። የህዝብን የልብ ትርታ ማዳመጥ ከታሪክ ስህተት ያድናል።

በአብዛኛው ተቃራኒ ሃሳብ የያዙ ወገኖች ያሉት በህዝብ መካከል ነው። እነሱን ለማጥቃት የሚሰነዘረው በትር ህዝብንም ይጎዳል። በዚህ የተነሳ የመንግሥት የህልውና መሰረት የሆነው ህዝብ ሆዱ ይሻክራል። ስለዚህ መንግሥት ይህን ስህተት እንዳይሰራ መጠንቀቅ አለበት። አሁን በግልጽ እንደሚታየው የመንግሥት አካላት የሚሳተፋበት ወንጀልና ጉልህ ስህተቶች በህዝብ ላይ እየታዩ ነው መንግሥት ጆሮውን ከወዳጆቹ ይልቅ ወደ ተቃዋሚዎቹ ማዘንበል ከቻለ ለማስተካከል እድል አለው። ከአሁን በፊት የነበሩት መሪዎች ያለ ጊዜያቸውና ያለ ኢትዮጵያውያን ፍላጎት አለ ጊዜያቸው እየተቀጩ የወደቁት አንዱ ከሌላው መማር ባለመቻሉ ነው። ታላቁ ሊቅ መጋቤ ሀዲስ እሸቱ አለማየሁ እንደተናገሩት መንግሥት የማንቂያ ደወል(Alarm) የሆኑትን ተቃዋሚዎች በድንግዝግዝ ከማሳደድ ይልቅ በጊዜ ነቅቶ የገባውን ቃል ለመፈጸም ተግቶ ቢሰራ መልካም ነው ❝የንጉሥ ክብር በሕዝብ ብዛት ነው፤ በሰው ጥቂትነት ግን የገዥ ጥፋት አለ።❞ ምሳሌ 14: 28
ቸር እንሰንብት።

ቀሲስ ዘለዓለም ጽጌ
ሴንት ልውስ ሚዙሪ USA

No comments:

Post a Comment