Sunday, March 17, 2019

እጽፍላችሁ ዘንድ ግድ ሆነብኝ ይሁዳ 1፥3

ባለንበት ዘመን ከራስ አልፎ ስለሰው ማሰብ እጅግ ከባድ እንደሆነ እለት እለት ስለ ሌሎች የሚደክሙ ወገኖች ቢናገሩ መልካም ይሆናል። ነገር ግን ከራስ አልፎ ለሌላው የሚተርፍ ቅንጣትም እንኳ ብትሆን ዋጋ አላት ብየ አምናለሁ። ምናልባት የሁላችንም የእውቀት ደረጃ እና የአስተሳሰብ ችሎታ ስለሚለያይ ለሁሉ መልካም የማይመስል ሃሳብ ልንሰነዝር እንችል ይሆናል ቢሆንም ግን ለተጠቀመበት ሰው በጎ ያልሆነውም ነገር ቢሆን አስተማሪ ነው። 


አንዳንድ ሰዎች የሃይማኖት ሰው ስለ ሀገር ጉዳይ ምን አገባው የፖለቲከኞች ሥራ ነው ለምን ይናገራል ይላሉ ሌሎች ደግሞ የፖለቲካ አቀንቃኝ ስለ ሃይማኖት ጉዳይ አይመለከተውም ሲሉ ይሰማሉ። ነገር ግን ሰው መሆን ረቂቅ ምስጢር እንደሆነ ካለመረዳት ይመስለኛል። በየትኛውም አመለካከት ውስጥ ብንሆን በእውነትና በታማኝነት እስከሰራን ድረስ ሰዎችን የሚጠቅምና ወደ በጎ የሚመራ ዓላማ እስካለው ድረስ ሊነቀፍ አይገባውም። 

መቼም ከዓለም የተገለለና በአእምሮ ያልበሰለ ካልሆነ በቀር ሰው ሆኖ ክፉንና ደጉን ለይቶ የማያውቅ አለ ለማለት ያስቸግራል።  ዛሬ ዓለም በሰው ልጆች ተሞልታ መከፋፈልና መጠላላት ባልነበረበት ዘመን አንድ አድርገው ህዝብን የሚያገለግሉ ሰዎች እንደነበሩ ታሪክ ምስክር ነው። ስለዚህ የሃይማኖት ሰው እውነትን መመስከርና ማስተማር ግዴታው በመሆኑ እንደየአቅማችን በጎ ነው ያልነውን ለወገናችን መልእክት ማስተላለፉ ይጠቅማል እንጅ አይጎዳም ከሚሉት ወገኖች እራሴን እመድባለሁ።

ይህን ለማለት ያስገደደኝ አንዳንድ ሰዎች በሚሰጡት አስተያየት ሰዎችን እነሱ በሚፈልጉት አጥር ውስጥ ቆልፈው በማስቀመጥ ቀና እንዳይልና እውነትን እንዳይናገር በማሸማቀቅ እነሱ ግን እንደፈለጉ የመናገር ነጻነት እንዳላቸው አድርገው ስለሚያስቡ አላዋቂነታቸውን ወደማወቅ እንዲመልሱ ለማሳሰብ ነው። 

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ታሪክ ከኢትዮጵያ ታሪክ ጋር የተጣመረ ነው የሚባለው እኮ ዝም ብሎ የተፈበረከ ታሪክ አይደለም። ዛሬ ላይ የመናገር ነጻነት አግኝተናል በማለት  ሊያጠለሹ የተነሱ በመልካም ዘር መካከል የበቀሉ አረሞች እንደሚናገሩት ሳይሆን ቤተክርስቲያኗ ያፈራቻቸው ልጆቿ ለሀገር ያበረከቱት አስተዋጽኦ ለትውልድ የሚተርፍ በመሆኑ ነው። ብዙዎቹ የቤተክርስቲያኒቱ ልጆች ከቤተክርስቲያናቸው ይልቅ ለሀገር ያበረከቱት ስጦታ እጅግ ይልቃል። ዓለም የመዘገበውን ታሪክ በጥላቻ ተሞልተው ለማጠልሸት የሚሞክሩ ወገኖች ሌላ መጥፎ ታሪክ እያስመዘገቡ መሆኑን ማን በነገራቸው። 

ታሪክ አንድ ጊዜ የሚሰራ ነገር ግን ለዘለዓለም የሚኖር ነው። ታሪክ ኃያል ነው ። ታሪክን ለማጥፋት የሚጥሩ ከሁሉ ያነሱ ደካሞች ናቸው። ታሪክን በኃይል ማጠልሸት ወይንም ማጥፋት የሚቻል ቢሆን እነጀርመንና አሜሪካ ኃይላቸውን ሁሉ ተጠቅመው መጥፎውን ታሪካቸውን መደለዝ በቻሉ ነበር ነገር ግን ሌላ በጎ ታሪክ በመስራት ያለፈው ክፉ ስራ ለትውልድ እዳ እንዳይሆን ማድረግ ችለዋል። ዛሬ አንድ ጀርመናዊ በምድረ እስራኤል በነጻነት ገብቶ መውጣት ይችላል። እንዲሁም አንድ አሜሪካዊ በጃፓን ምድር በክብር መኖር ሲችል አይተናል። ታሪክ እንደሚነግረን ጀርመናዊው ሂትለር እስራኤላውያኑን እንደ አፈር ፈጭቶ ሳሙና ሰርቶባቸዋል። እንዲሁም በሁለተኛው የዓለም ጦርነት አሜሪካ በጃፓን ላይ በተኮሰችው የኒኩሌር ቦምብ ምክንያት አንድ ከተማ ያጠፋች ሲሆን እስከዛሬ ድረስ በዚያች ምድር የሚወለድ የሰው ዘር በሙሉ አካለ ስንኩል እየሆነ እንደሚወለድ በገሃድ የሚታወቅ ሃቅ ነው። ነገር ግን እድሜ ለስልጣኔ ዛሬ ላይ  በእነዚህ ህዝቦች መካከል ፍቅርን እንጅ ጸብን ከቶ ማየት አልቻልንም። ከዚህ የምንረዳው እኛ ምን ያክል ኋላ ቀር እንደሆንን እና መሪዎቻችን ለስልጣናቸው መራዘም እንጅ ለህዝብ ግድ የማይላቸው እራስ ወዳዶች እንደሆኑ ነው። የቀደሙት አባቶቻችን ዛሬ እኛ እምንባላበትን መሬት ያቆዩልን አጥንታቸውን ከስክሰው ደማቸውን አፍሰው ነው።

ስለዚህ ወገኔ ንቃ ለዘለዓለም በማትኖርባት ምድር እንደሰው ተፈጥረህ እንደ አውሬ እየተበላላህ እንዳታልቅ ቆም ብለህ አስብ። ዓለም ዛሬ በምድር ያለውን በቁጥጥር ስር አድርጎ በጨረቃ ላይ ቤት እየሰራ ነው። እንደ ሌላው መጨረስ ቢያቅተን ስልጣኔን ግን ለመጀመር እድሉ በእጃችን ነውና ክፉ ሰዎች በዘረጉልን የመለያየት መንገድ ተጉዘን ከምንጠፋ ተሳስበን ዓለም ከደረሰበት የምንደርስበትን መንገድ ለትውልድ ብንቀይስ ከታሪክ ተወቃሽነት መዳን እንችላለን። ዛሬ የምንቆፍራት ጉድጓድ የማንም አይደለችም እራሳችን እንገባባታለን። ስለዚህ መልካም ዘር ለመዝራት እንጅ ጸብንና መለያየትን ለመዝራት መድከም መጨረሻው ጥፋት ነውና ስሜታዊነትን ትተን ማስተዋልን ገንዘብ እናድርግ።  ቸር እንሰንብት።

ቀሲስ ዘለዓለም ጽጌ 
ሴንት ሉዊስ ሚዙሪ
USA




No comments:

Post a Comment