ዘመኑ የፈጠረው ክፉ ነገር ቢኖር አንድ ሰው እራሱን የፈለገው ቦታ አስቀምጦ በሚዲያ ሲያሰራጭ የጉዳዩን እውነተኛ ነት ሳያረጋግጡ የሚያራግቡ ሰዎች መብዛታቸው ነው። ብዙ ሰዎች ቤተክርስቲያንን ወክለው መግለጫ ይሰጣሉ ብዙ ተቀባይ አላቸው። አንዳንዶች እራሳቸውን ከመንግስት በላይ አድርገው ስለሀገር ጉዳይ መግለጫ ይሰጣሉ እነሱም ብዙ ደጋፊ አላቸው። ይህ ችግር በብዙዎች እይታ ስልጣኔ ተነፍጎ ለኖረ ህዝብ ከአቅሙ በላይ የሚሰጥ ነጻነት የሚያመጣው በሽታ እንደሆነ ታምኖበታል።
ሰሞኑን በየሚዲያው ከሚናፈሱት ጉዳዮች አንዱ ዘርፌ የተባለች ዘፋኝ ኦርቶዶክስ ተዋህዶን ትታ ወደሌላ የእምነት ድርጅት ተቀላቀለች የሚለው የጎላ ሆኖ ሰንብቷል። እንደ እውነቱ ከሆነ ወሬው ከበሬው ወለደ ያላነሰ ነው። ዘርፌ መቼም የኦርቶዶክስ ተዋህዶ ጉያ ገብታ አታውቅም። እግዚአብሔር ፈቅዶ ንስሃ ገብታ ከጥፋት ብትድን መልካም ነበር; ነገር ግን ያዳቆነ ሰይጣን ሳያቀስ አይቀርም እንዲሉ አበው; አስቀድሞ በዘፈን፣ በዝሙት፣ በስካር፣ ወዘተ ሲያረክሳት የኖረው ሰይጣን ሄዋንን እንዳሳታት የተሻለ መንገድ ላሳይሽ ብሎ በማታለል በምንፍቅናቸው ከሚታወቁት ከነትዝታውና በጋሻው እጅ ጣላት እነርሱም እንደ እባብ መልካቸውን ለውጠው በመቀበል የክፉ ዓላማቸው ተባባሪ አደረጓት። ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ ለቆሮንቶስ ክርስቲያኖች በጻፈው መልእክቱ እንዲህ ብሎ ነበር። እንደ እነዚህ ያሉ ሰዎች የክርስቶስን ሐዋርያት እንዲመስሉ ራሳቸውን እየለወጡ፥ ውሸተኞች ሐዋርያትና ተንኮለኞች ሠራተኞች ናቸውና።ይህም ድንቅ አይደለም፤ ሰይጣን ራሱ የብርሃንን መልአክ እንዲመስል ራሱን ይለውጣልና።እንግዲህ አገልጋዮቹ ደግሞ የጽድቅን አገልጋዮች እንዲመስሉ ራሳቸውን ቢለውጡ ታላቅ ነገር አይደለም፤ ፍጻሜአቸውም እንደ ሥራቸው ይሆናል። 2ኛ ቆሮ 11፥13
ታዲያ ዛሬ ብዙ ሰው ለምን በዚች ዘፋኝ ተሰናከለ ብንል እሷም ሆነች መምህራኗ በቤተክርስቲያናችን ውስጥ የተከሰተውን የአስተዳደር ክፍተት በመጠቀም ከላይ ባለስልጣናት ጋር ባለሟል በመሆን በየአብያተ ክርስቲያናቱ መድረክ ላይ የምንፍቅና ትምህርታቸውን ለማሰራጨት እድል አግንተው ነበር። እውነተኛ የቤተክርስቲያኒቱ ልጆች የቤተክርስቲያናችንን መድረክ አናስደፍርም በማለት ቁርጥ አቋማቸውን ማሳየት ሲጀምሩ ህዝቡን ወደ ባዶ አዳራሽ በመውሰድ ምንፍቅናቸውን ለመዝራት ሞከሩ; ነገር ግን ቀበሮ ከበጎች መካከል ተደብቆ እኖራለሁ ቢል ዓመሉ ያጋልጠዋልና ክፉ ስራቸው ተገልጦ በመውጣቱ የሚከተላቸው ሲያጡ ሀገር በመቀየር በውጭው ዓለም ፖለቲካ የጎዳውን ምእመን ለማታለል ጥቂት ጊዜ ደከሙ አሁንም ተኩላ ከበጎች መካከል ልደበቅ ቢል ባህርይው ያጋልጠዋልና መሪያቸው ሰይጣን ዲያብሎስ ዓይን ያወጣ ዝሙትና ምንፍቅና ውስጥ እንዲዋኙ ሲያደርጋቸው እራሳቸውን ገልጠው ሊወጡ ችለዋል።
ስለዚህ ሐዋርያው ቅዱስ ዮሐንስ በመልእክቱ ከእኛ ዘንድ ወጡ፥ ዳሩ ግን ከእኛ ወገን አልነበሩም፤ ከእኛ ወገንስ ቢሆኑ ከእኛ ጋር ጸንተው በኖሩ ነበር፤ ነገር ግን ሁሉ ከእኛ ወገን እንዳልሆኑ ይገለጡ ዘንድ ወጡ። 1ኛ ዮሐ 2፥19 እንዳለው ዘርፌም ሀነች አስተማሪዎቿ መቼም የኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ልጆች አልነበሩም። የኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ልጅ ለመሆን መስፈርት አለው። እንኳን ዘማሪ ለመባል የእምነቱ አካል ለመሆን የተዘረጋ ስርዓት አለ ያንን መፈጸም ያልቻለ የኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ልጅ መሆን አይችልም። ምናልባት የቤተክርስቲያኒቱን ልእልና በማየት በስሟ ሊነግድ ይችላል ነገር ግን ማስመሰል እና ሆኖ መገኘት የተለያዩ ናቸው። እነዚህ ሰዎች ወይ እንደ አገልጋይ በአብነት ትምህርት ቤቶች ገብተው ተምረው የአንድ አጥቢያ ቤተክርስቲያን አገልጋይ ተብለው አልተመደቡ ወይም ደግሞ እንደሌሎች ዘማርያን በሰንበት ትምህርት ቤት አድገው በአጥቢያቸው ተመስክሮላቸው ቤተክርስቲያንን አላገለገሉ ታዲያ እንዴት የኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ልጆች ሊባሉ ይችላሉ? እርግጥ ነው ቤተክርስቲያኒቱን ለማዳከም ከመንግስት አካላት ጀምሮ በተነደፈው እቅድ መሰረት ብዙ መናፍቃን ሰርገው ገብተዋል። ይሁን እንጅ እውነተኛ የቤተክርስቲያኒቱ አባቶችና ልጆች በጋራ በመሆን እያጋለጡ እያወጡዋቸው ነው። ሁላችንም ልናውቃቸው ይገባል። እንደነዚህ ያሉት የኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ልጆች ሳይሆኑ ጥፋቷን የሚመኙ የሰይጣን ማደሪያዎች ናቸው። ስለዚህ ከእንደነዚህ ዓይነቶች ጋር ምንም ዓይነት ህብረት ሊኖረን አይገባም። ክፉ ሥራቸውንም ለሌሎች መሰናክል እንዳይሆን share ማድረግ የለብንም። እንዲህ ተብሎ እንደተጻፈ። ከማያምኑ ጋር በማይመች አካሄድ አትጠመዱ፤ ጽድቅ ከዓመፅ ጋር ምን ተካፋይነት አለውና? ብርሃንም ከጨለማ ጋር ምን ኅብረት አለው?ክርስቶስስ ከቤልሆር ጋር ምን መስማማት አለው? ወይስ የሚያምን ከማያምን ጋር ምን ክፍል አለው?
በትክክል ገልፀውታል
ReplyDeleteቃለ ሕይወት ያሰማልን መጋቢ ኃይማኖት
ReplyDelete