Tuesday, July 7, 2015

የሰው ልጅ መብት የት ድረስ ነው?


እግዚአብሔር አምላክ ሰውን ሲፈጥረው አእምሮ የሚባል ዳኛ ህግ የሚባል ልጓም ስጥቶታል። ይህም ያስፈለገበት ምክንያት ሰው ለክብር የተፈጠረ ስለሆነ ስሙን ለመቀደስ ክብሩን ለመውረስ ይችል ዘንድ ነው። ህሊና እና ህግ ያልተሰጣቸው እንስሳት ከሞት በኋላ ያለውን ክብር ስለማይወርሱ እንዲጠብቁ የታዘዙት ህግ የለም። በህግ መመራት በነፍስም በስጋም የሚጠቅመው ሰውን ነው። ያለ ህግ መኖር  እንስሳዊ ባህርይን መላበስ ነው። በህግ ጥላ ስር ስንኖር እግዚአብሔር ከእኛ ጋር ይኖራል። ህግ የተሰራላቸው ህዝበ እግዚአብሔር እስራኤል ከእግዚአብሔር ህግ ፈቀቅ ባሉ ጊዜ ይደርስባቸው የነበረውን መከራና ችግር ቅዱስ መፅሐፍ በሰፊው ይነግረናል። የእግዚአብሔር መንፈስ አድሮበት የተናገረው አዛርያስ እንዲህ ብሏል >> አሳ ይሁዳና ብንያም ሁሉ ሆይ፥ ስሙኝ እናንተ ከእግዚአብሔር ጋር ስትሆኑ እርሱ ከእናንተ ጋር ነው ብትፈልጉትም ይገኝላችኋል ብትተዉት ግን ይተዋችኋል << 2ኛ ዜና 15፥2 ይህን ያላቸው ከህገ እግዚአብሔር ርቀው ስለነበር እግዚአብሔርም ርቋቸው ስለነበር ነው። ይህንንም ከዚሁ ምእራፍና ቁጥር ቀጥሎ እንዲህ ተጽፎ እናነበዋለን  >> እስራኤልም ብዙ ዘመን ያለ እውነተኛ አምላክ፥ ያለ አስተማሪም ካህን፥ ያለ ሕግም ይኖሩ ነበር። በመከራቸውም ወደ እስራኤል አምላክ ወደ እግዚአብሔር ተመልሰው በፈለጉት ጊዜ አገኙት። በዚያም ዘመን ለሚወጣውና ለሚገባው ሰላም አልነበረም፥ በምድርም በሚኖሩት ሁሉ ላይ ታላቅ ድንጋጤ ነበረ <<  ይላል ስለዚህ ሰዎች ከእውነተኛው ከእግዚአብሔር ህግ ከወጡ ፍርሃትና ጭንቀት ችግርና መከራ ያገኛቸዋል። ይህም በመሆኑ የተነሳ እግዚአብሔር በየዘመኑ ህጉን የሚያስፈጽሙ መሪዎችን እና አስተማሪዎችን ከህዝቡ መካከል እያስነሳ ህዝቡን ይመራል ያስተምራል።


ሰው ከእንስሳት የሚለየው ባለአእምሮ በመሆኑ ነው። አእምሮዉን ተጠቅሞ ክፉንና ደጉን በመለየት ህይወቱን መምራት አለበት። ከህጻንነት እስከ ሽምግልና በሚኖረው ህይወት የተዘረጋለት በጎ ስርዓት አለ። ከዚህ ስርዓት ውጭ ከወጣ እንደ ባለ አእምሮ ስለማይቆጠር ጥበቃ ይደረግለታል። ብዙ ሰዎች በኑሯቸው የእለት ተእለት ተግባራቸውን እእምሯቸው በመዛባቱ ምክንያት መከወን ካልቻሉ ከሚፈልጉት ነገር ሊከለከሉ ይችላሉ። የሚፈልጉትን ነገር በዓለም ላይ ተወዳድረው ማድረግ የሚችሉት ባለ ሙሉ አእምሮ መሆን ሲችሉ ብቻ ነው ። ስለዚህ የሰውን ልጅ በየደረጃው መብቱን የሚያስከብሩለት አካላት ይህን እየመዘኑ መሆን ይገባው ነበር ፥ እንደ እንስሳ ልብሱን ጥሎ መሄድ እፈልጋለሁ ቢል መብቱ ነው ሊባል አይገባውም። ይልቁንም አስፈላጊው ጥበቃና ክትትል ያደርጉለታል እንጅ።

በኣእምሮም ሆነ በሰውነት ህጻናት ለሆኑ ልጆች የፈለጉትን እንዲያደርጉ በወላጆቻቸው አይፈቀድላቸውም። ምክንያቱም የሚጠቅማቸውንና የሚጎዳቸውን ነገር ጠንቅቀው ስለማያውቁ ማለት ነው። አብዛኛው ነገር በስሜት የሚደረግ ስለሆነ። በስሜት የሚደረግ ነገር ደግሞ መጨረሻው ፍሬ የለውም። ዛሬ በዓለማችን በልዩ ልዩ ቦታዎች የሚሰማውና የሚታየው ችግር አእምሮ የጎደላቸው ሰዎች ተገቢው ጥበቃና ክትትል ስለማይደረግላቸው ነው።

በአሁኑ ወቅት ዓለማችን በኢኮኖሚውም ሆነ በቴክኖሎጂው ከፍተኛ የእድገት ደረጃ ላይ እንደደረሰች ይታመናል። ይሁን እንጅ እድገት የሚለው ቋንቋ ሲተረጎም በክፉም በደጉም ተመሳሳይ ትርጉም ስለሚኖረው በጥቅሉ እድገት በሚለው እንያዘው።አንዳንድ ጥያቄዎችን በማንሳት ወደዝርዝር ሃሳቤ ልግባ።

 የዓለማችን የኢኮኖሚና  የቴክኖሎጂ እድገት እውነት ለሰው ልጆች ከጉዳቱ ይልቅ ጥቅሙ ያመዝናል? እውነት በዓለማችን ላይ ሌት ከቀን እእምሮዋቸውን አዲስ ነገር በመፍጠር ሲያስጨንቁ  የሚኖሩ ጠቢባን ለዓለማችን በጎ ዉለታ እየዋሉ ነው?

እውነት እግዚአብሔር የሰውን ልጅ ሲፈጥረው አላዋቂና ባዶ አድርጎ ነው የፈጠረው?
ከሁለተኛው ጥያቄ ስነሳ እግዚአብሔር ሰውን የፈጠረው ባለጸጋ አድርጎ ነው። ከሁሉ በፊት ለሰው ልጆች የሚያስፈልገውን ነገር እግዚአብሔር  በልግስና ሰጥቷቸዋል። የሰው ልጆች በራሳቸው ጥበብ የፈለሰፉት ነገር አብዛኛው ጎጂ ነው። አውሮፕላን ከቦታ ቦታ ለመጓጓዝ ቢጠቅምም የብዙ ሰዎችን ህይዎት አጥፍቷል። ሌሎችም እንዲሁ። ያለ እግዚአብሔር ፈቃድ የሚደረግ ነገር በሙሉ ጎጂ እንጅ አንዳች የሚጠቅመው ነገር የለም። ለሰው ልጆች የተሰጠው ጥበብ እግዚአብሔርን አውቀው እሱ በሚመራቸው መንገድ መጓዝ ይችሉ ዘንድ ነው። በራሳቸው ጥበብና ማስተዋል እንጓዛለን ቢሉ ጥበባቸው ሞኝነት ነው። መጨረሻቸውም ጥፋት ነው። ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ  በ1ኛ ቆሮ ም 1፥20 >>  የጥበበኞችን ጥበብ አጠፋለሁ የአስተዋዮችንም ማስተዋል እጥእላለሁ ተብሎ ተጽፎአልና። ጥበበኛ የት አለ? ጻፊስ የት አለ? የዚች ዓለም መርማሪስ የት አለ? እግዚአብሔር የዚችን ዓለም ጥበብ ሞኝነት እንዲሆን አላደረገምን? በእግዚአብሔር ጥበብ ምክንያት ዓለም እግዚአብሔርን በጥበብዋ ስላላወቀች፥ በስብከት ሞኝነት የሚያምኑትን ሊያድን የእግዚአብሔር በጎ ፈቃድ ሆኖአልና << እንዳለው ዓለም ዛሬ በሞኝነት ማእበል ውስጥ እንደተዘፈቀች የምናይበት ብዙ ማስረጃ አለ።

ሰሞኑን የአሜሪካ ከፍተኛው ፍርድ ቤት ግብረሰዶም በምድረ አሜሪካ የተፈቀደ መሆኑን አውጇል። ይሁን እንጅ ብዙ የአሜሪካን ዜጎች በጽኑዕ እየተቃወሙ ነው። እዚህ ላይ ሳላነሳ የማላልፈው የዓለም አብያተክርስቲያናት መሪዎች ይህ አዋጅ ሲታወጅ ምንም ዓይነት መግለጫ መስጠት አለመቻላቸው አሳፋሪ ነው። ከላይ ለመጥቀስ እንደሞከርኩት በኢኮኖሚውም ሆነ በቴክኖሎጂው ዓለምን እየመራች ያለችው ትልቋ ሃገር አሜሪካ በይፋ ይህን አስነዋሪ ተግባር የእድገቷ መገለጫ አድርጋ ማቅረቧ እውነትም የዓለም ጥበብና እውቀት መጨረሻው ሞኝነት መሆኑን ለመረዳት ይቻላል።

ምድረ አሜሪካ ከመላው ዓለም የተሰባሰቡ ህዝቦች የሚኖሩባት ሃገር እንደሆነች ይታወቃል። የእነዚህ ህዝቦች ታሪክ የሚያስረዳው ከተለያዩ ችግሮች ለማምለጥ ነጻነትን ፍለጋ መሆኑ ግልጽ ነው። ምን ዓይነት ነጻነት ስንል ሰብአዊ ነጻነት ማለታችን ነው። ሰብአዊ ነጻነት ማለት ደግሞ ሰውን ከነ ክብሩ ጠብቆ ማኖር ማለት ነው። አሁን እያየን ያለነው ነገር ግን ሰውን ከእንስሳ በታች የሚያደርግ፣ እንስሳት እንኳን የሚጸየፉትን ተግባር ሰዎች በአደባባይ ሲፈጽሙ ማየት ነው።

አንዳንድ አእምሮ የተነሳቸው ሰዎች ኃጢአታቸውን እንደ መብት ቆጥረውት ህጋዊ እውቅና ይሰጠን ስላሉ በመንግስት ደረጃ መብታቸው ነው ተብሎ ፈቃድ ማግኘታቸው እውነትም ይህ ህዝብ እረኛ አልባ መሆኑን ያሳያል። ይህን ያልኩበት ምክንያት እረኛ ወይም ጠባቂ መንጋዎቹን ወደ ፈለጉት ሳይሆን የሚመራቸው ወደ ተሻለ ቦታ ነው መሆን ያለበት። ታዲያ እነዚህ ሰዎች ትውልድን የሚያጠፋ ፣ ታሪክን የሚያበላሽ፣ አእምሮን የሚያቆሽሽ ተግባር ሲፈጽሙ ይበል ብሎ ፈቃድ መስጠት ተገቢ ነው? እንደ እውነቱስ ከሆነ እንዲህ አይነቱ አስነዋሪ ተግባር ከሰው ልጅ መብቶች ውስጥ አለ?  የመጨረሻው ዘመን ላይ እንዳለን በግልጽ የምንረዳበት ሰዓት ላይ መሆናችን ምንም ጥርጥር የለውም።

ዛሬ ለሁላችንም ስጋት የሆነው ጉዳይ ምእራባውያን የጀመሩት ነገር ሁሉ እንደስልጣኔ ስለሚወሰድ ነገ የሃገርና የቤተክርስቲያን ተረካቢ የሚሆነው ትውልድ በዚህ ተታሎ ታሪኩንና ሃይማኖቱን ረስቶ የዚህ ርካሽ ተግባር ባለቤት እንዳይሆን ነው።
ስለዚህ ህዝብና ቤተክርስቲያንን የምትመሩ አካላት በጥልቀት ልታስቡበት ይገባል። ትውልዱ መብቴ ነው ብሎ የሚያቀርበው ጥያቄ መጨረሻው ጥፋት መሆኑን እንዲረዳ ከቀድሞው በበለጠ እቅድና እስትራቴጂ ተነድፎ ተገቢው ትምህርት መሰጠት ይኖርበታል እላለሁ።

 
አምላከ ቅዱሳን ከክፉ ሃሳብ እንድንለይ መለየቱን ይስጠን። 

No comments:

Post a Comment