ለስደት ስናነሳ ከመሰረቱ ማየት ያስፈልጋል። ከሃይማኖታችን አንጻር ስናየው
ስደት ሁለት ዓይነት ነው። በነፍስ የሚገጥመን ስደትና የስጋ ስደት ማለት ነው። የስደት ጀማሪዎች አባታችን አዳምና እናታችን ሄዋን ናቸው። (ዘፍ 3፥23)
የነሱ ስደት የነፍስና የስጋ ስደት ይባላል። በህይወተ ስጋ ሳሉ ከገነት
ወደ ምድረ ፋይድ ተሰደዋል። ከሞቱም በኋላ በነፍስ ወደ ሲኦል መሰደድ ግድ ሆኖባቸዋል።
ክፉው ስደት የነፍስ ስደት ነው። አባታችን አዳም በምድራዊ ስደት የኖረው
923 ዓመት ሲሆን በገነት ለ7 ዓመታት ብቻ እንደኖረ ቅዱስ መጽሐፍ ይነግረናል። በነፍሱ ደግሞ ከነልጆቹ ለ5500 ዘመናት በስደት
ኖሯል። ለመኖሪያነት ከተሰጠችው ከመጀመሪያ ሃገሩ ከምድረ ገነት ሰይጣን ዲያቢሎስ በሸረበበት ተንኮል ምክንያት ስደት አግኝቶታል።
አስቀድሞ እግዚአብሔር ወደ ቀደመ ርስቱ እንደሚመልሰው ቃል ገብቶለት ስለነበር ጊዜው ሲደርስ ወደ ገነት መልሶታል።
አባታችን አዳም ከገነት ሲወጣ ከነልጆቹ ለመኖሪያነት የተሰጠችው ይህች
አሁን የምንኖርባት ዓለም እንደሆነች እርግጥ ነው። እንዲሁም ምድር
በሞላዋ የእግዚአብሔር እንደሆነች ሁሉ የእግዚአብሔር ፍጥረታት በሙሉ ለኑሯቸው አመች በሆነው አካባቢ ሁሉ ለመኖር መብት ሊኖራቸው
ይገባ ነበር። ነገር ግን የሰው ልጆች አስቀድመው በኃጢአታቸው ብዛት በቋንቋ፣ በዘር፣ በጎሳ፣ በቀለም ወ ዘ ተ ተከፋልለው ስለነበር
ያ ክፉ መንፈስ ከትውልድ ወደ ትውልድ እያደገ መጥቶ ወንድማማቾች በአንድ ቅየ ተሳስቦ መኖር ተስኗቸው አንዱ አንዱን እያሳደደ ለመከራ
ሲዳርግ ይኖራል።
ከላይ ለመግለጽ እንደሞከርኩት የስደትን ታሪክ ስንመለከት በተለይ ቅዱስ
መጽሐፍ እንደሚነግረን በጎ ጎን እንዳለው የተጻፈ ነገር አይገኝም። ምናልባት ሰዎች በግፍ ወይም በችግር እንዲሁም እንጀራ ፍለጋ
ተሰደው እግዚአብሔር እረድቷቸው በስደት በሚኖሩበት ሃገር በርትተው ሰርተው ወይም ባላቸው በጎ ምግባር የሃገሩ ሰው ወዷቸው የተሳካላቸው
ሰዎች ነበሩ። ለምሳሌም አብርሃም ዘፍ 37፥1 ፣ ያዕቆብ 32፥4
፣ ዮሴፍ፣ ዘፍ 39፥1 ሙሴ ዘጸ 3፥15 ወዘተ ማጥቀስ ይቻላል።
ይሁን እንጅ እነዚህ ሰዎች በዘመናቸው ቢመቻቸውም እነሱ ካለፉ በኋላ ወገኖቻቸው የሚቀበሉት መከራ በታሪክ እንደተጻፈው ቀላል አልነበረም።
የመጀመሪያው ስደት የመጣው በኃጢአት ሲሆን ኃጢአት የተባለውም ሰዎች የእግዚአብሔርን
ትእዛዝ በመዘንጋታቸው ያገኛቸው ፍርድ ነው። ያም ፍርድ ርግማን ያለበት፥ ከዘለዓለም ህይዎት የሚያስወጣ፣ ከፍጥረት ወገን በምንም
መልኩ ሊያስተካክለው የማይችለው ፍርድ ነበር። ነገር ግን ቸርነቱ የማያልቅበት አምላክ አስቀድሞ በገባው ቃል መሰረት ያንን ስደት
በስደቱ ያንን ሞት በሞቱ ሽሮ ከሲኦል ወደገነት መልሷቸዋል። በምድር ላይ ያለው ስደትና ሞት ኃላፊ እንዲሆን አድርጓል። ነገር ግን
ሰዎች በተሰጣቸው ነጻ ፈቃድ ከህገ እግዚአብሔር ቢወጡ የዘለዓለም ስደት ይገጥማቸዋል።
ቅዱስ መጽሐፍ
እንደሚነግረን በዓለም ውስጥ በተለያዩ ጊዜያት ስደት የገጠማቸው ህዝቦች አሉ። ብዙ ጊዜም ስለስደት ስናነሳ የሚጠቀሱት እስራኤላውያን ናቸው። ዘፍ 32፥4 የእነዚህን ህዝቦች የስደት
ታሪክ ከእግዚአብሔር ጋር ጥብቅ ግንኙነት ያላቸው ቢሆኑም ነገር ግን ብዙ ጊዜ ትእዛዙን ቸል በማለታቸው ስደት አጋጥሟቸዋል። ሕዝ
12፥11
አሁን ባለንበት
ዘመንም ከሃገራቸው ወደሌሎች ሃገራት የሚሰደዱ ብዙዎች ናቸው። በተለይም የእስልምና አክራሪዎች በየሃገሩ በሚፈጥሩት ሽብር ምክንያት
ብዙ ሰዎች ከቅያቸው እየተሰደዱ ይገኛሉ። የብዙዎችን የስደት ምክንያት ስናነሳ ምክንያታቸው ልዩ ልዩ ነው ከማለት የዘለለ ሁላችንንም
የሚያስማማን ሃሳብ ሲነገር አይሰማማም። ቢሆንም በአንድ ቃል ለመግለጽ
የስደታቸው ምክንያት የተስፋ እጦት ነው። ይህም ድሃ ሃገሮች ብቻ
ሳንሆን በዓለማችን ላይ ብዙ ሰዎች ከሃገር ወደ ሃገር እየተዘዋወሩ የተሻለ ኑሮ ለመኖር ይወስናሉ። በኢኮኖሚ ያደጉ የሚባሉት እነ
አሜሪካና እነ እንግሊዝ ብዙ በሌሎች ሃገሮች በስራ ተሰማርተው የሚነሩ
ዜጎች አሏቸው። ነገር ግን ስደት ልንለው እንችላለን?
አንድ ሰው ወደ አሜሪካ DV ሞልቶ ከመጣ ከሃገሩ ተሰዶ መጣ ልንለው አንችልም
የተሻለ ስራ ፍለጋ እንደሄደ መቆጠር ያለበት ይመስለኛል። ምክንያቱም የስደት ትርጉም አንድ ሰው ሳይወድ በግድ ሁኔታዎች አስገድደውት
ወይም ደግሞ በሃገሩ ላይ ለመኖር የሚያስችል መብት ሳይኖረው ሲቀር የሚደርግ ሽሽት ወይም የሚበላው አጥቶ ምግብ ፍለጋ ወ ዘ ተ
ነው። ለዚህም ምሳሌ የጌታን ስደት ብንወስድ ሄሮድስ ሊገድለው ትእዛዝ በመስጠቱ ከሞት ሊያተርፉት እመቤታችንና ዮሴፍ ወደ ምድረ
ግብጽ ይዘውት ተሰደዱ። ማቴ 2፥13 እንዲሁም አባታችን ያዕቆብ ከነልጆቹ ምግብ ፍለጋ ወደ ምድረ ግብጽ ተሰዷል ዘፍ 46፥5
አንዳንድ ሰው ባለው ነገር እርካታ በማጣት ሃገር የሚቀይር አለ። አንዳንዶች
በሰዎች የተለያየ ችግር ደርሶባቸው ይሰደዳሉ። ታዲያ ችግር አድራሹም ችግረኛውም ከተሰደዱ ችግሩ ያለው የት ነው? ለማንኛውም ከኔ
የተሻለ እውቀት ያላቸው የቋንቋ ምሁራን ስለ ስደት የጻፏቸው መጻህፍት ይኖራሉና ፈልጎ ማንበብ ይበጃል። ከራሳችን ብንነሳ እኔ የሚመስለኝ
በሃገር ላይ ሰርቶ ለማደግ እንቅፋቱ የእርስ በርስ መለያየት ነው ። በሃገሩ ላይ ሰርቶ እንዳያድግ በምቀኝነት በገዛ ወገኑ ተጠልፎ
ያልወደቀ ማን አለ? ይህ የኛ የዛሬው ታሪካችን ነው። ትላንት የነበሩት አባቶቻችን እናቶቻችን እንኳን ለወገናቸው ለሌላው መጠለያ
ሆነው ብዙዎችን ጠቅመዋል። ሃገራችን ኢትዮጵያ የስደተኞች መጠለያ እንደነበረች ታሪክ ምስክር ነው። ለዚያ ደግሞ ምክንያቱ በዘመኑ
የነበሩት ኢትዮጵያውያን ሃይማኖተኞችና ብርቱዎች ስለነበሩ ነው። ለፍልሰት መፍትሔው ተሳስቦ በጋራ ሰርቶ አምርቶ እግዚአብሔርን አመስግኖ
በሃገር መኖር እንዳለበት ማስተማር ነው።
በዘመናችን
ያለው ፍልሰትና ስደት ሃገራቸውን ለማሳደግ የጠቀማቸው ህዝቦች አሉ። በተለይ የእርስ በርስ መለያየት የሌለባቸው ሃገሮች ሃገራቸውን
ለማሳደግ እረድቷቸዋል። ለእኛ ለኢትዮጵያውያንም ጥቅሙ ሰፊ ነው። ይህ ሁልጊዜም የማይካድ ሃቅ ነው።
መቸም ለስደትም ሆነ ለፍልሰት የሚኖሩን ምክንያቶች በቂ ቢሆኑም የምንወስደው
አማራጭ ግን የተሻለ መሆን ይኖርበታል። ብዙ ወጣቶች ወደ ስደት ሲያቀኑ ከተለያየ አቅጣጫ የሚመጣላቸውን ምክር ማስተናገድ አይፈልጉም።
እንደውም አንዳንዶች ከረር ያለ ኃይለ ቃል ሲናገሩ ይሰማሉ። ለምሳሌም መካሪውን ወገን << አንተ የተሻለ ቦታ እየኖርክ
ሌላው ይህን እድል እንዳይጠቀም መከልከል አይገባም >> ብለው ይናገራሉ ይሁን እንጅ ሁሉም ነገር እንደምንገምተውና እንደምናስበው
ይሆናል ማለት አይቻልም። ምናልባት ጥቂቶች ተሳክቶላቸው እራሳቸውንም ወገናቸውንም አልፎም ተርፎም ሃገራቸውን ጠቅመው ይሆናል። ብዙዎች
ግን ያላቸውንም አጥተው ስብእናቸው ተነክቶ ለከፋ ችግር ሲዳረጉ ማየት የተለመደ ነው።
ዛሬ በዓለማችን
ላይ የሰው ሰውነት ክፍል ( ኩላሊት፣ ጉበት ወዘተ) በከፍተኛ ገንዘብ እየተሸጠ ነው። ስደተኞች የዚህ ገንዘብ ማግኛ ዘዴ ተጠቂዎች
እንደሆኑ የታወቀ ነው። በመንገድ ላይ እየተጠለፉ ከፍተኛ ገንዘብ ክፈሉ ካልሆነ አካላችሁ ተቆራርጦ ይሸጣል ተብለው በጭንቅ ላይ
የነበሩ ቤተሰቦችን ሰምተናል። በዚህ ነገር ስንት ሰው ተምሮ እራሱን ከአደጋ ለመጠበቅ ችሏል ስንል መልስ የለም። ሞትን ፈርቶ ወደ
ሞት መሄድ አማራጭ ሊሆን አይችልም። እንደውም በሰው ሃገር ከመሞት
በሃገር ሞቶ በወግ መቀበር ለቋሚ ቤተሰብ ሃዘንን እንደመቀነስ ሊታይ
ይችላል።
ሌላው ልናነሳው የሚገባ ጉዳይ ቢኖር። ከላይ ጠቆም እንዳደረኩት በአሁኑ
ወቅት ስደት እንደ እድል ወይም እንደተሻለ አማራጭ ሆኖ እየተቆጠረ እየመጣ ነው። የውጭ እድል የመጣለት ሰው የ40 ቀን እድሉ የተቃና
እንደሆነ ስለሚታመን ማንም እንደመጥፎ አያየውም። በሃገር ቤት የተሻለ ገቢ ያላቸው ሳይቀር በስደት መከራውን አይቶ ከሚኖር ወገናቸው
ላይ እርዳታ የሚጠብቁ ብዙዎች ናቸው። ወቅትን ወይም በዓላትን ጠብቆ ገንዘብ የማይልክ ስደተኛ እንደዘመድም የማይቆጠርበት ቤተሰብ
አለ። እራሱ በኪራይ ቤት አፓርታማ ላይ ተሰቅሎ እየኖረ በኢትዮጵያ በተንጣለለ ቪላ ቤት ውስጥ ለሚኖር ወገኑ የሚረዳው ስደተኛ ብዙ
ነው።
በተለይ አዲሱ ትውልድ የስደትን አሳፋሪነት ስለማያውቀው ተምሮ ውጭ ለመሄድ
ነው ተስፋ የሚያደርገው። ትላንት አባቶቹ በሰው ሃገር ሄዶ መስራትን እንደ ቅጣት ይቆጥሩት እንደነበር ማን ይንገረው? የስደትን
አስከፊነት ያውቃሉ የሚባሉ የሃይማኖት አባቶች ሳይቀር ከሃገር ኮብልሎ መሄድን እንደአማራጭ ወስደው ሌላውንም በዚሁ መንገድ እንዲጓዝ
ሲያበረታቱ ይታያሉ።
ብዙ ወጣቶች በባህር፣ በዱር በገደል አቋርጠው ወደ ስደት የሚጓዙት በስደት
መኖር እንደነጻነት ተቆጥሮ በኩራት ሲነገር በመስማታቸው ነው። በዚህ ሃሳብ ላይ በሌላ ርእስ ስለምንገናኝ በሰፊው እናየዋለን። ይህ
ለምን ሆነ ስንል ምክንያቱ ከበስተጀርባው ሰፊ ጥቅም የሚያስገኝ መንገድ
ሆኖ በመገኘቱ ነው። ዛሬ በስደተኞች ስም የሚሰበሰብ ገንዘብ የብልጣ ብልጦች ኑሮ ማዳበሪያ ሆኗል። በተለያየ ጊዜ ተፈጠሩ ለተባሉ
ችግሮች ሁሉ ኮሚቴ ተቋቁሞ ገንዘብ ሲሰበሰብ ይታያል።ገንዘቡ የሚሰበሰበውም ከስደተኞች ነው። ነገር ግን የሚሰበሰበው ገንዘብ ባለቤቱ
ማን እንደሆነ ለማወቅ አስቸጋሪ ነው። እንዲሁም ለስደተኞች ተብሎ በተለያየ መንገድ የሚሰበሰበው ገንዘብ ከሁሉ የላቀ ነው። ነገር
ግን ስደተኛ ሲበዛ እንጅ ሲቀነስ ማየት አልቻልንም።
እንደሚታወቀው ዛሬ ዓለምን ለችግር ለመከራ ለስደት እየዳረገ ያለው የገንዘብ
ፍቅር ነው። ከሁሉም ችግሮች በስተጀርባ ገንዘብ አለ። ስለሆነም ገንዘብ ወዳዶች ይህ ችግር መፍትሔ ቢያገኝ ኑሯቸው ይቃወሳል። ስለዚህ
የገንዘብ አሰባሰብ ስልታቸውን ያጠናክራሉ እንጅ ስደት የሚቆምበትን ወይም ስደተኞች ከተረጅነት የሚወጡበትን መፍትሔ አይፈልጉም ቢያውቁትም
አያደርጉትም።
የዓለም ሃብታም ሃገራት ለስደተኞች የሚሰጡትን ጥገኝነት ስንመለከት እንቆቅልሽ
የሚሆንብን ነገር ይገጥመናል። እውነት ስደተኞችን እያስጠጋን ነው ካሉ ዛሬ በሊቢያ በየመን በሳውዝ አፍሪካ ወገኖች ከሃገራቸው ተሰደው
እንጀራ ፍለጋ ሄደው በሰይፍ እየየታረዱ፣ እናቶች ከነልጆቻቸው በእሳት እየተቃጠሉ፣እንጀራ ፍለጋ ብል,ው ቤተሰቦቻቸውን፣ሃገራቸውን
ትተው መጠጊያ የጠየቁ በየእስር ቤቱ እየታጎሩ አይደለምን? ታዲያ እነሱ ስደተኛ እሚሉት ማንን ነው? ግራ ይገባል። ብዙ ስደተኞች
መጠጊያ አጥተው በባህር ሲሰጥሙ በበረሃ የአውሬ እራት ሲሆኑ ነገር ግን ብዙ ሽፍቶች በስደተኛ ስም ተከብረውና ተንደላቀው እንዲኖሩ
ይደረጋል ................................... ይቀጥላል
No comments:
Post a Comment