Monday, July 20, 2015

ስደት በኛ ዘመን _ _ _ ክፍል 2 ካለፈው የቀጠለ


ሃብታም ሃገራት ስደተኞችን የሚቀበሉበት መስፈርት በራሱ ፖለቲካዊ ብቻ ነው። አንድ ሰው ተርቦ እሚበላው አጥቶ ከሃገር ቢሰደድ መስፈርቱን አላሟላህም ተብሎ ተቀባይነት አያገኝም። ነገር ግን ሌላው በሃገሩ ላይ ወንጀል ሰርቶ ወይንም በመንግስት ላይ አምጾ ከቀረበ የስደተኛ መብት ያገኛል። የሚቀርበው ምክንያት ደግሞ ሃገሩ ቢመለስ ሊታሰር ይችላል የሚል ነው፤ ይህ መሆኑ ባልከፋ ነገር ግን ረሃብ ለስደት በቂ ምክንያት አይደለም መባሉ ሊፈተሽ የሚገባው ጉዳይ ነው። ረሃብ የሚመጣው ከበስተጀርባው ባሉ ብዙ ወንጀሎች ምክንያት ነው።ለኢኮኖሚ ስደተኞች መጠጊያ የለንም የሚሉ ሃገራት ብዙ ናቸው።  ይህ ስደት የሚለውን ትርጉም ያዛባ ውሳኔ መሆኑን ለመረዳት ስደት ማለት ምን ማለት እንደሆነ ማወቅን ይጠይቃል።

ሌላው አሳሳቢ ጉዳይ ስደትን ለማስቀረት ስደተኞች እራሳቸው መፍትሔ ለመፈለግ ጥረት አለማድረጋቸው ነው። ምክንያቱም የስደቱ መንስኤ በግልጽ ይታወቃል። ነገር ግን ከችግሩ ተነስቶ የችግሩን ምንጭ ከማድረቅ ይልቅ በተለያየ ሃሳብ በመራኮት ጊዜያቸውን ሲያሳልፉ ይታያሉ። መለያየት ደግሞ ለሰው ልጆች ትልቁ የችግር መነሻ ነው። በተለይ እኛ ኢትዮጵያውያን ስለ ስደት አሁን ካለን አመለካከት መውጣት ካልቻልን ለዘመናት ይህን ከባድ ችግር መፍታት አንችልም። ጳጳሱ የሃገር መሪው ከትልቁ እስከትንሹ  የስደት ተስፈኛ ነው።  ለዚህ ሁሉ ምክንያቱ ደግሞ ፍቅር ማጣታችን ነው።
ሃገራችን ሃገረ እግዚአብሔር መባሏ ታሪክ ሊሆን ጥቂት የቀረ ይመስላል። ትላንት ተፋቅረን ተዋደን በሃገራችን ስንኖር የማንሰማቸው ነገሮች ዛሬ በሰው ሃገር እንጀራ ፍለጋ ብለን ወጥተን ባንደበታችን የሚነገረው አጽያፊ ነገር ከኢትዮጵያዊ የሚጠበቅ አይደለም። አንተ አማራ፣ አንተ ኦሮሞ፣ አንተ ትግሬ፣ አንተ ጉራጌ ወ ዘ ተ እየተባባሉ ጎራ ፈጥሮ መናቆር የኛ ዘመን ትውልድ ከክፉ ልቦናው ያመነጨው ክፉ ሃሳብ ነው። ይህ ትውልድ የራሱ ሳያንስ ትላንትና ኢትዮጵያውያንን አንድ አድርገው ሲመሩ የነበሩ አባቶቻችንን ያለእፍረት የሚሳደብ ሆኗል። ታዲያ ይህ ሁሉ ክፋትና በደል እየተሰራ እግዚአብሔር እንዴት በኛ መካከል በጎ ነገር ሊያደርግ ይችላል?

በአንድ ወቅት እስራኤል ሃገር በምኖርበት ጊዜ አየው የነበረው አሳፋሪ ነገር ይታወሰኛል። በተለያየ መንገድ ወደ እስራኤል ሃገር የሄዱ ኢትዮጵያውያንና ኤርትራውያን ይገኛሉ። የጉዟቸው መንስኤ የተለያየ ይሁን እንጅ ነገር ግን በአብዛኛው በአንድ ቋንቋ የሚናገሩ፣ተመሳሳይ ቀለም ያላቸው እና በእስራኤላውያን ዘንድ ሃበሽ ወይም አበሻ ተብለው በአንድ ስም የሚጠሩ ናቸው። በሌላ በኩል ቤተእስራኤላውያን ተብለው ብዙ ኢትዮጵያውያን ወደ ምድረ እስራኤል ፈልሰዋል። ይሁን እንጅ በዚህ አጋጣሚ ሌሎችም ብዙዎች የእድሉ ተጠቃሚ ለመሆን ችለዋል ተብሎ ይነገራል። የእድሉ ተጠቃሚ መሆናቸው መልካም መሆኑ አይጠረጠርም። ነገር ግን ትላንት እንደ እናት ጉያዋ አድርጋ ያላትን እያካፈለች ያቆየች እናት ኢትዮጵያን ነጻነት አገኘን በሚል ሰበብ ሚዲያ ከፍቶ ማጥላላት ከሰብአዊነት አንጻር አሳፋሪ ነው።
በተለይ የኢትዮጵያን ባህልና አኗኗር ያየ ሰው እንዲህ ዓይነቱን ተግባር ለመፈጸም ህሊናውን ለማዘዝ ይቸገራል። ብዙ ሲናገሩ እንሰማ ነበር። የሚገርመው ደግሞ ያ ሁሉ ውርጅብኝ የሚነገረው በኢትዮጵያ ቋንቋ በአማርኛ ነበር። በኢትዮጵያ ምድር ሳሉ ከፍተኛ ስቃይና እንግልት ህብረተሰቡ ያደርስባቸው እንደነበር ባልተቋረጠ መልኩ እለት እለት በሬዲዮናቸው ያጥላሉ ነበር። የእስራኤል መንግስት በኢትዮጵያውያን ላይ እስርና ማንገላታት ሲፈጽም ጥቆማ በመስጠት ትልቁን ሚና የሚጫወቱ እነርሱ ነበሩ። ያ ሁሉ ወቀሳና ውንጀላ ሳያበቃ ያልጠበቁት መከራና ፈተና እየገጠማቸው ይገኛል። የእስራኤል ህዝብ ለሁለት ጎራ ተከፍሎ በእነሱ ጉዳይ በየእለቱ ይነታረካል። ግማሹ ህዝብ እንደወገን መብት ይኑራቸው ሲል አብዛኛው ህዝብ ግን ማግለልና መድልዎ እየፈጸመባቸው ይገኛል። አንዳንዶች እናት ሃገራቸውን ኢትዮጵያን በመናፈቅ ሁሉም ይቅርብኝ ብለው ወደ ሃገራቸው የተመለሱም አሉ። ይህ ለሁላችንም አስተማሪ ሊሆን ይገባዋል።   አሁንም ሃገራችን ሰፊ ነች። ከትውልድ እስከ ትውልድ የማይነጥፍ አኩሪ የሆነ በጎ ባህል አላት። ፍቅር ብንሆን ሁላችንም ተደስተን ልንኖርባት እንችላለን። ስለዚህ ሁላችንም በጎ ህሊናን ገንዘብ እናድርግ።  

 

ቀሲስ ዘለዓለም ጽጌ ሴንት ሉዊስ ሚዙሪ

No comments:

Post a Comment