Wednesday, April 6, 2016

ደብረ ዘይትን ስናስብ ከእሥራኤል መንግሥትና ህዝብ ምን እንማራለን

ኢትዮጵያ ሀገራችን ለክርስቶስ እና ለእናቱ ለቅድስት ድንግል ማርያም ካላት ፍቅር የተነሳ ክርስቶስ የተወለደበትን፣ ያደገበትን፣ ያስተማረበትን ተአምራት ያደረገባቸውን ቦታዎች አክብሮት ሰጥታ ህዝቡ ፈጣሪውን እንዲያስታውስ በማለት የቅዱሳን መካናቱን ስም ወደ ኢትዮጵያ በማምጣት እንዲሰየሙ አድርጋለች። ለምሳሌ ደብረ ዘይት፣ ደብረ ታቦር፣ ደብር ሲና፣ ናዝሬት፣ ቤተልሄም ቀራንዮ ጌቴሴማኒ ወ ዘ ተ የሚባሉ ቦታዎች በኢትዮጵያ ይገኛሉ። እነዚህ ሁሉ በምድረ እሥራኤል ታላላቅ ተአምራት የተደረጉባቸው ቦታዎች ናቸው። ለምሳሌ ባለፈው ሰንበት አስበነው የዋልነውን ደብረዘይትን ማየት እንችላለን።


ደብረ ዘይት ማለት የወይራ ዛፍ የበዛበት ተራራ ነው። በመጽሐፍ ቅዱስ ከተጠቀሱት ቅዱሳን ቦታዎች (ተራራዎች) አንዱ ነው። በዚሁ ተራራ ላይ ሐዋርያት ጌታችንን የመምጣትህ ነገር እንዴት ነው ብለው ጠይቀውታል እሱም የሚመጣበትን ከእርሱ ብቻ በቀር ሊያውቅ የሚችል እንደሌለ እና የሚመጣበት ቀኑና ሰዓቱ ስለማይታወቅ ዘወትር ተዘጋጅተው ሊኖሩ እንደሚገባቸው አስተምሯቸዋል  የመምጫውም ምልክቶች ዛሬ በዓለማችን ላይ እያየናቸው ያሉ ችግሮች እንደሆኑ አስረድቷቸዋል። ማቴ 24፥1 ጌታ ሲያስተምር ውሎ ያድርበት የነበረው ስፍራ በዚያው ይገኛል። ከሙታን ከተነሣ በ40ኛው ቀን ያረገውም ከዚሁ ቦታ ነው።
 የደብረ ዘይት ታሪኩ ብዙ ነው በብሉይ ዘመን ቅዱስ ዳዊት ልጁ አቤሴሎም በጠላትነት በተነሳበት ጊዜ ወደዚሁ ተራራ እንደሸሸ ተጽፏል ከትራራው ወረድ ብሎ የአቤሴሎም (በመጥፎ ጎን ቢሆንም) የመታሰቢያ ሃውልት ይገኛል።

እንደሚታወቀው አሁን እሥራኤል ተብላ የምትጠራው ሀገር ከተቋቋመች 60 ዓመታት አካባቢ የሆናት ሲሆን ነገር ግን በታሪክ ብዙ ሽ ዓመታትን አስቆጥረናል ከሚሉት ሀገራት በላቀ ሁኔታ የዓለምን ታሪክ በተገቢው ቦታና ለጎብኚዎች ምቹ ሁኔታን በመፍጠር የዓለም ህዝብ የሚጎርፍባት ሀገር ለመሆን ችላለች። በተለይ እንደ ኢትዮጵያ ላሉ ሀገራት ትልቅ ማሳያ ነው። እርግጥ ነው በምድር ላይ በምድረ እሥራኤል የተሰራውን ታሪክ የሚተካከል በየትም ሊኖር አይችልም። የእሥራኤል መንግስት የሚደነቀው የራሳቸውንም የታሪክ ስህተቶች በማሳያነት ለሌላው ዓለም ህብረተሰብ ለጎብኚዎች ክፍት ማድረጋቸው ነው። በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ያሉት ታሪኮች የሀገራቸው ታሪኮች በመሆናቸው አክብረው ይዘዋቸዋል። የኛም የቀድሞ ደጋግ ነገስታትና ንግስታት እንዲሁም ደጋግ ክርስቲያኖች ያሳነጿቸው ከሰባት በላይ የሚሆኑ አብያተክርስቲያናትና ገዳማት በምድረ እሥራኤል ይገኛሉ። ከዚህም በተጨማሪ ከላይ የጠቀስኳቸው ከንግስት ሳባ ጀምሮ ያሉ ኢትዮጵያውያን በገዳማቱ ለሚያገለግሉ አባቶችና እናቶች መደጎሚያ ይሆኑ ዘንድ ህንፃዎችና ቤቶችን አሰርተዋል።

አይሁድ አዲስ ኪዳንን አይቀበሉም ነገር ግን በምድረ እሥራኤል የተፈጸመ ታሪክ በመሆኑ አክብረው ይዘውታል። በመሆኑም በየእለቱ ከጎብኝዎች ከፍተኛ ገቢ ያገኙበታል። ይህ ለኛ ትልቅ ትምህርት የሚሰጥ ነው። ደብረ ዘይት፣ ደብረ ታቦር ፣ ጎልጎታ ወዘተ ለአይሁድ ስለማያምኑበት ምናቸውም አይደል። ነገር ግን ታሪክ ነውና ተከብሮ ይኖራል።  የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ቅርሶች ወደድንም ጠላንም የኢትዮጵያ ሀብቶች ናቸው ብናከብራቸው እንከብርባቸዋለን ዛሬ ኢትዮጵያ ሀገራችን በዓለም ህብረተሰብ ዘንድ ታሪካዊት ተብላ የምትደነቀው ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን በፈጸመቻቸው አኩሪ ተግባራት ነው። ስለዚህ ኢትዮጵያዊ የሆነ ሁሉ ይህን እውነት አምኖ ሊቀበል ይገባዋል። ቅዱሳን መካናቷ ገዳማቷ በአግባቡ ተይዘው በዓለም ህዝብ ዘንድ እንዲታወቁ ቢደረጉ ያለብንን የውጭ ምንዛሪ ችግር መፍታት እንችል ነበር። በኛ ዘንድ ያለው ችግር የማይቀረፈው ችግሩን። ሆነ ብለን ስለምንፈጥረው ነው። ስለዚህ እንደ እሥራኤል መንግስትና ህዝብ ሁሉም ብሄሮችና ሃይማኖቶች እንዲሁም መንግሥት የኢትዮጵያን ታሪካዊ ቦታዎች መጠበቅ አለባቸው። ይኽ የነገሌ ነው ይጥፋ ማለት ድህነትን (ችግርን) እንጅ እድገትን አላመጣልንም። የቆጡን አወርድ ብላ የብብቷን ጣለች እንደሚባለው የምንከበርበትና የምንከብርበት ታሪክ እያለን የሰው በመመኘት ትውልዱን ከሁለት ያጣ እንዳናደርገው ልንጠነቀቅ ይገባል።

ሌላው በመጽሐፍ ቅዱስ እንደተጻፈው እሥራኤላውያን ብዙ ጊዜ ለእግዚአብሔር  ባለመታዘዛቸው ምክንያት ርሃብ፣ ስደት፣ ጦርነት ወዘተ መከራና ችግር አይተዋል። ከዚህም በላይ ዓለምን ለማዳን ከእነርሱ ወገን በስጋ የተወለደውን መድኃኔ ዓለም ኢየሱስ ክርስቶስን ሰቅለው በመግደላቸው ጭካኔያቸውን አሳይተዋል።

 አንድ የአይሁድ የልጆች አስተማሪ የኢየሱስ ክርስቶስን መወለድ ታምናላችሁ? ብየ ላቀረብኩለት ጥያቄ እንዲህ በማለት ነበር የመለሰልኝ "  ኢየሱስ ክርስቶስ መወለዱን እናውቃለን ነገር ግን እናንተ እንደምትሉት አምላክ አይደለም እናቱም ማርያም የተወደደች መልካም ሰው ነበረች አባቱም ዮሴፍ ይባላል የናዝሬት ነዋሪዎች ነበሩ ኢየሱስ ክርስቶስም በልጅነቱ እጅግ ጥበበኛ ነበር አስደናቂ ነገሮችን በማድረግ የሰውን ሁሉ ቀልብ የሳበ ነበር በኋላ ግን አምላክ ነኝ በማለቱ እኛ ሳንሆን ሮማውያን ሰቅለውታል። እናንተ ግን ኛ እንደሰቀልነው አድርጋችሁ ትናገራላችሁ " ብሎ ነበር ሊመልስልኝ የሞከረው የሰውየው ንግግሮች በወንጌሉ ላይ ቃል በቃል ከተጻፉት ጋር የተመሳሰሉ በመሆናቸው አላስደነቀኝም። የአይሁድ ትልቁ ስህተታቸው ጌታን ሰቅለው ከገደሉ በኋላ እንኳን ባዩዋቸው ተአምራት የጌታን አምላክነት አለማመናቸው ነው። ይሁን እንጅ ዛሬ በምድረ እሥራኤል የሚገኙ ቅዱሳን መካናትን መጓብኘት የቻለ ሰው የክርስትናው ታሪክ የክርስቲያን ጠላት በሚባሉት አይሁድ ዘንድ ታሪኩ ተጠብቆ እየኖረ እንደሆነ መመስከር ይችላል።

ይህን ታሪካቸውን ባለመደበቅ ለዓለም ህዝብ በማሳየታቸው ዛሬ ከፍተኛ የገቢ ምንጭ ሊኖራቸው ችሏል። እንግዱህ እነሱ አባቶቻቸው ያጠፉትን ጥፋትና ስህተት በመመስከር ባለጸጋ ከሆኑ እንዴት እኛ ብዙ መልካም የሰሩ አባቶቻችንን ታሪክ ተናግረን መበልጸግ አቃተን?

በኢትዮጵያ ውስጥ ከሰው ህሊና በላይ የሆኑ ሥራዎች የተሰሩባቸው ቅዱሳን መካናት አሉ። ታሪካቸውን ጽፈው ያስቀመጡልን አባቶቻችን እንደነገሩን እነሱ ይጀምራሉ እግዚአብሔር ይፈጽመው ነበር። ይህንም ለማመን የተሰሩትን ሥራዎች ብቻ ማየት በቂ ነው። እነቅዱስ ላሊበላ ያነጹት ቤተመቅደስ ዛሬ ዓለም በቴክኖሎጅ ጣራ ላይ በደረሰበት ዘመን እንኳን ሊሰራ እንደማይችል በጠቢባን ተረጋግጧል። ሰለዚህ በደብረ ዘይት ሆኖ ያስተማረው ጌታ በኢትዮጵያውያ ደግሞ የሚመለክበትን ቤት ሰርቷል ማለት ነው። ለዚያም ነው ብዙ ቅዱሳን ሀገራቸውን እየተው ኑሮዋቸውን በኢትዮጵያ ገዳማት ያደርጉ የነበረው። እነ ጻድቁ አቡነ ገብረ መንፈስ ቅዱስ በቀላሉ ሲናይን ተሻግረው እሥራኤል መግባት ሲችሉ ከባዱን ቀይ ባህርን አቋርጠው ወደ ኢትዮጵያ የመጡበት በቂ ምክንያት ነበራቸው። ተሰዓቱ ቅዱሳን ከሀገራቸው ከወገናቸው ተለይተው ኢትዮጵያን የሙጥኝ ማለታቸው ከሁሉ አብልጠው በማየታቸው አይደለምን? ሰለዚህ እኛም ከእሥራኤሎች ተምረን በታሪክ የበለጸገች ሀገራችንን ልንከባከባትና ልንጠብቃት ይገባል።

No comments:

Post a Comment