Wednesday, April 23, 2014

ሳንጀምር የጨረስነው

ጥንት አባቶቻችን አንድ ነገር ለማድረግ ሲነሱ ከመነሻው መድረሻውን የሚያውቁበት ልዩ ጸጋ ነበራቸው። በዚህም የተነሳ ከመጀመራቸው በፊት ፍጻሜው የት ሊደርስ እንደሚችል ይገምታሉ። በመሆኑም በመንገዳቸው ብዙም ፈተና ቢገጥማቸው ማምለጫውን ያዘጋጃሉ። ስለዚህ ብዙ ከባድ ነገሮችን አልፈው ስኬታማ የሆኑባቸው ነገሮች ብዙ ናቸው።

እኛጋ እያስቸገረን ያለው ነገር ይህ ነው። ምንም ነገር ሳንጀምር መጨረስ እንፈልጋለን። ,, የጅብ ችኩል ቀንድ ይነክሳል ,, እንዲሉ ዘለን አናቱ ላይ መውጣት እንፈልጋለን። በዚህም የተነሳ በድካማችን ውስጥ ስኬት አልባ እንሆናለን። ከመጀመር በፊት ፍጻሜውን መገመት ይገባል። ሁሉ ነገር እና እንዳሰብነው ይሆናል ብሎ መገመት ስህተት ነው። በተለይ የብዙኃን የሆነ ነገር ላይ ውሳኔ ስንወስን በአራቱም አቅጣጫ መመልከት ያስፈልጋል። ቤተክርስቲያን የብዙዎች ነች። ይህን የሚገነዘቡ ግን ጥቂቶች ናቸው። አንዳንዶች ብዙ ገንዘብ ስለከፈሉ፣ አንዳንዶች ብዙ ዘመን ስለቆዩ፣ አንዳንዶች ብዙ ቲፎዞ ስላላቸው ለቤተክርስቲያን እራሳቸውን ብቸኛ አካል አድርገው ለማሳየት ይሞክራሉ ይህ ትልቅ ስህተት ነው። ቤተክርስቲያን እንኳን በ40 በ80 ተጠምቆ ልጅነትን ያገኘባት ይቅርና ለአህዛብም እንኳን በተስፋ እናታቸው ናት። አሁን ሁሉም አትኩሮ ሊመለከተው የሚገባ ይህ ጉዳይ ነው። የቤተክርስቲያን ልጆች ከካህናት እስከ ምዕመናን ድረስ እንደ ባይተዋር ምክንያት እየተፈለገ የሚባረሩበት አካሄድ መስተካከል አለበት ። በእናቱ ቤት ባይተዋር እየተደረገ የሚታይ ልጅ መኖር የለበትም። እድሜ ዘመናቸውን መንፈሳዊ ትምህርት ለመቅሰም ከሃገር ሃገር ሲባዝኑ ኑረው በተማሩት ትምህርት ቤተክርስቲያንን ለማገልገል ሲመጡ ተገቢውን ክብር ማግኘት አለባቸው። የምናውቀውን ሁሉን ብናወራው የማያንጽ ስለሆነ ማለፉ ይሻላል።

Saturday, April 19, 2014

የይሁዳ ጸጸት

ለሰው ልጅ ከእግዚአብሔር ከተሰጡት ጸጋዎች አንዱ የህሊና ጸጸት ነው። ሰው ከእንስሳት የሚለየውም የሚጸጸት አእምሮ ስላለው ነው። ይህ ልዩ ጸጋ ከእግዚአብሔር የተሰጠው  እንዲጠቀምበት ነበር። ብዙ የእግዚአብሔር ሰዎች በሰሩት ክፉ ስራ ተጸጽተው ወደ እግዚአብሔር በማልቀሳቸው  ይቅርታንና ምህረትን አግኝተዋል። ምሳ 25፥8

የሰው ልጅ የሚጸጸት አእምሮ የተሰጠውም ከበደል የማይርቅ በመሆኑ ነው። ለእንስሳት የሚጸጸት አእምሮ ያልተሰጣቸው ስለማይበድሉ ነው። ህጻናት አእምሮዋቸው ስላላደገ ክፉውንና ደጉን ለይተው አያውቁም። ነገር ግን የስሜት ህዋሳታቸውን ተጠቅመው ምግባቸውን ይመገባሉ። ዕብ 5፥13 እንስሳት አእምሮ የላቸውም ስንል ክፉንና ደጉን ለይተው የሚያውቁበት ማለታችን ነው ። ይህ ሲባል ግን ከእግዚአብሔርም  ሆነ ከሰው   ጋር ባላቸው ግንኙነት የሚግባቡበት የማስተዋያ መንገድ ተስጥቷቸዋል ።  አንዳንድ ጊዜ የሰው አእምሮ መከወን የተሳነውን ነገር እንስሳት ሲያደርጉ የምናስተውልበት ጊዜ አለ። በክፉ ድርጊቶች የሚያለቅሱ እንስሳት አሉ። የተነገራቸውን መልሰው የሚከውኑ አሉ። እንዲሁም አስቀድሞ የሚመጣውን ነገር በድርጊት የሚጠቁሙም አሉ። ይህ ሁሉ አእምሮ የሌላቸው ከምንላቸው እንስሳት የምናስተውለው ነው። በተቃራኒው ሙሉ አእምሮ የተሰጠው የሰው ልጅ ክፉንና ደጉን ለይቶ እያወቀ ከጸጸት እርቆ ሲኖር እናያለን።

Thursday, March 13, 2014

አሜሪካንን ለማታውቋት

በዓለማችን ብዙ ሰው በተለያየ መንገድ ወደ አሜሪካ ይመጣል። የማያውቁት ሃገር አይናፍቅም የሚለው ተረት ለአሜሪካ አይሰራም። ከሚያውቃት ይልቅ የማያውቃት የሚናፍቃት ሃገር አሜሪካ ነች ቢባል አይጋነንም። የሃገር መሪዎች፣ የሃይማኖት መሪዎች፣    የፖለቲካና የኢኮኖሚ ስደተኞች፣   በልዩ ልዩ መንገድ የሚገቡ ምሁራንና ተማሪዎች፣ እንዲሁም በስራና በንግድ በህክምና በመሳሰለው ምክንያት ወደዚች ምድር ይመጣሉ። በተለይ እኛ ኢትዮጵያውያን ወደ አሜሪካ ለመግባት ስናስብ አስቀድመን ሰፋ ያለ መረጃ ለማግኘት እንቸገራለን። እንድንመጣ የሚረዳን ቤተሰብም ብዙ ገንዘብ ከፍሎ ከሃገራችን እንድንወጣ እንጅ የሚጥረው በሃገራችን ያለ አሜሪካ ውስጥ የሌለ ነገር እንዳለ  አይነግረንም። ሁልጊዜ እኛ እራሳችንን ድሃ ብለን መቁጠር ይቀናናል። እርግጥ ነው በሃገራችን ብዙ ድሆች ይኖሩ ይሆናል፥ ነገር ግን አሜሪካም ጥቂት ድሆች እንዳሉ ልናውቅ ይገባል። ጠንክሮ ካልሰሩ ባግባቡ ኑሮን መምራት ካልቻሉ አሜሪካ ውስጥ ድሃ ብቻ አይደለም የሚኮነው ወንጀለኛም ነው።

Wednesday, February 26, 2014

መጠራታችሁን ተመልከቱ


እግዚአብሔር ፍጥረታትን ሲፈጥር ያለ ዓላማ የፈጠረው ፍጥረት እንደ ሌለ መጽሐፍ ቅዱስ ይነግረናል። የፍጥረት ዓይነቱ ልዩ ልዩ እንደሆነው ሁሉ የተፈጠረለት ዓላማውም ልዩ ልዩ ነው። በተለይ የሰው ልጅ ከፍጥረታት ሁሉ ይለያል። ፍጥረታት በሙሉ የራሳቸውን መልክ ይዘው ሲፈጠሩ ሰው ግን እግዚአብሔርን መስሎ ነው የተፈጠረው። ይህም በመሆኑ ዘላለማዊነትና ገዥነት ተሰጥተውት ነበር። በዚህ ክብርና ልዕልና ጸንቶ የቆየው ግን ለሰባት ዓመታት ብቻ ነበር። በጥንተ ጠላቱ ዲያቢሎስ ተታሎ ከአስተዳዳሪነት ወደ ባርነት ከዘላለማዊነት ወደ ኃላፊነት ከገነት ወደ ምድረ ፋይድ ከተሸጋገረ በኋላ ይገዛቸው ያስተዳድራቸው ዘንድ ሙሉ ስልጣን ሰጥቶት የነበረው እንስሳት እንኳን ሸሹት። ለፈጣሪው ያልታመነ ለኛ የሚራራ ልብ እንዴት ይኖረዋል ያሉ ይመስላል። 

Monday, February 24, 2014

በሁሉ አመስግኑ

በአንድ ወቅት አንድ መልካም ሰው ወንጀል ሰርተሃል ተብሎ ፍርድ ቤት ቀረበ አሉ፤ ታዲያ ይህ ሰው ወንጀሉን የፈጸመው ሆን ብሎ ሳይሆን።በአጋጣሚ ነበር፥ ፍርድ ቤት ቀርቦ ዳኛው የምስክሮች ቃል ከሰሙና የቀረበላቸውን ማስረጃ ከመረመሩ በኋላ በሞት እንዲቀጣ ወሰኑበት። በዚህ ጊዜ በፊቱ ላይ ምንም የመረበሽ ስሜት አልታየበትም ነበር። በሁኔታው የተገረሙት ዳኛውና በዙሪያው ያሉት ሰዎች የመጨረሻ የመሰናበቻ ቃሉን ይጠብቁ ጀመር። እግዚአብሔር ይስጥልኝ ክቡር ዳኛ፣ እድሜ ይስጥልኝ፣ ፍርድ የሚሰጥ ዳኛ አያሳጣን ወ ዘ ተ እያለ ምስጋናውን ያወርደው ጀመር  አግራሞታቸው የጨመረው ዳኛ ግራ ተጋብተው ,, የፍርዱን ውሳኔ የተረዳው አይመስለኝም በሞት እንዲቀጣ ነው የተወሰነበት ምናልባት ውሳኔውን በደንብ ካልሰማ አስረዱት,,  አሉ ። ሰውየውም መለሰ ,, ውሳኔውን በደንብ ተረድቻለሁ ፍርዱም ገብቶኛል የመረዳትም ችግር የለብኝም,, ብሎ መለሰ፤ የዳኛው ጥያቄ ቀጠለ ,, ታዲያ እንዴት ነው የሞት ፍርድ እየተፈረደብህ ፍርድ ቤቱን የምታመሰግነው? አሉ ። ,, ጌታየ ከዚህም የከፋ ፍርድ እኮ አለ መቶ ጅራፍ ተገርፎ ይሙት ቢሉስ ይችሉ አልነበር?  ብሎ መለሰ ይባላል።

Friday, February 14, 2014

እስከ መቼ?

ለሰው ልጆች ከእግዚአብሔር ከተሰጡት ስጦታዎች ትልቁ ሃይማኖት ነው። ሰው ከፍጥረታት ሁሉ የላቀ ክብር እንዳለውም የታወቀው በሃይማኖት ኖሮ ከፈጣሪው ጋር ስለሚገናኝ ነው። ታዲያ ይህን ትልቅ ጸጋ አክብሮና ጠብቆ የመኖር ኃላፊነት አለበት። ቅዱሳን እራሳቸውን ለእግዚአብሔር በማስገዛታቸው በዚህ መንገድ ተጉዘው ወደ ዘለዓለም እረፍት እንዲገቡ እግዚአብሔር ሃይማኖትን ሰጥቷቸዋል። ለዚህም ነው ሐዋርያው ቅዱስ ይሁዳ <<  ወዳጆች ሆይ፥ ስለምንካፈለው ስለ መዳናችን ልጽፍላችሁ እጅግ ተግቼ ሳለሁ፥ ለቅዱሳን አንድ ጊዜ ፈጽሞ ስለ ተሰጠ ሃይማኖት እንድትጋደሉ እየመከርኋችሁ እጽፍላችሁ ዘንድ ግድ ሆነብኝ ይሁዳ 1፥3 >>  ያለው። የሰው ልጆች  በጸጋ የእግዚአብሔር  ልጅነትን ስላገኙ በሃይማኖት ኖረው ያባታቸውን  የእግዚአብሔርን ርስት እንዲወርሱ የእግዚአብሔር ፈቃዱ ነው።
 
ሃገራችን ኢትዮጵያ የቅዱሳን ሃገር በመሆኗ ህዝቦቿም በአምልኮተ እግዚአብሔር ለብዙ ዘመናት ጸንተው የኖሩ በመሆናቸው ብዙ ቅዱሳን በመንፈስ ቅዱስ ተመርተው ወደ ሃገራችን እየፈለሱ እንደመጡ በብዙ ቅዱሳት መጻሕፍት ላይ ተጽፎ እናገኛለን። ዛሬም ቢሆን በዓለም የሚገኙ የታሪክ ተመራማሪዎች ኢትዮጵያ የሰው ዘር መጘኛ፣ የታሪክ ማህደር መሆኗን እየመሰከሩ ነው። ድንቅ ሃይማኖታዊ ስርዓቷንና ትውፊቷን ለማድነቅ በየእለቱ ብዙ የዓለም ህዝቦች እየጎረፉ ነው።  በኢትዮጵያውያን በኩል የሚታየው ግን  ብዙ ደስ የሚል አይደለም። በተለያየ አቅጣጫ ህዝቡ እየተፈተነ  ነው።  በጎ ምግባርንና ሃይማኖትን የተማረው ከሃይማኖት አባቶቹ ነበር ። ዛሬ ላይ በአባቶቹ ተስፋ በመቁረጥ እምነቱ እየተሸረሸረ በመምጣቱ አህዛቡንም ሆነ መናፍቃኑን መቋቋም አቅቶት በእነሱ እየተማረከ የክፉ ስራቸው ተባባሪ በመሆን ቤተክርስቲያኑንና ሃገሩን ታሪክ አልባ እያደረጋት ነው። 

Thursday, February 13, 2014

ከጽኑ ቍጣውም ይመለስ እንደ ሆነ ማን ያውቃል?

በተለያዩ ዘመናት እግዚአብሔር ለሰው ልጆች ያለውን ይቅርታ፣ ቸርነትና ምህረት በቅዱሳኑ በኩል ገልጿል። ከዚህም አንዱ ለሰብአ ነነዌ ያደረገላቸው ምህረትና ይቅርታ ሲነገር ይኖራል። በትንቢተ ዮናስ ተጽፎ እንደምናገኘው የነዚህ ህዝቦች ኃጢዓትና በደል በእግዚአብሔር ፊት ደርሶ ነበር ,,  የእግዚአብሔርም ቃል ወደ አማቴ ልጅ ወደ ዮናስ እንዲህ ሲል መጣ።ተነሥተህ ወደዚያች ወደ ታላቂቱ ከተማ ወደ ነነዌ ሂድ፥ ክፉታቸውም ወደ ፊቴ ወጥቶአልና በእርስዋ ላይ ስበክ ,, ት ዮና 1፥1 ,, በዚህም የተነሳ ነቢዩ ዮናስን ወደ እነርሱ ልኮት ነበር። ነገር ግን ነቢዩ የእግዚአብሔርን ፈቃድ ከመፈጸም ይልቅ በራሱ ሃሳብ ተሸንፎ ከእግዚአብሔር ፊት ለመሸሽ ሞከረ። ብዙውን ጊዜ በራሳችን እውቀትና ጥበብ ከእግዚአብሔር ለመሸሽ የምናደርገው ሙከራ ሰው ምን ያህል በራሱ ሞኝ እንደሆነ የሚገለጥበት ነው። የሚገርመው በእውቀትና በጥበብ የተሻሉ ሆነው በሰው ዘንድ የሚታዩ በእግዚአብሔር ተመርጠው ለህዝቡ እረኛ የሆኑ ሰዎች ከእግዚአብሔር ፊት ለመሸሽ ሲሞክሩ እጅግ ይደንቃል። ዮናስም እንዲሁ ነበር ያደረገው። እግዚአብሔር ደግሞ ከተናገረ ያደርገዋል፣ ከጀመረም ይፈጽማል። ዮናስ በራሱ ጥበብ ከእሱ ለማምለጥ ቢሞክርም በጥበበ እግዚአብሔር ከጥልቁ ባህር እና ከአሳ አንበሪ ሆድ በሰላም እንዲወጣ አድርጎት ለነነዌ ሰዎች የእግዚአብሔርን የንስሃ ጥሪ አድርሶላቸዋል።

Thursday, January 23, 2014

ወደ ጌታህ ደስታ ግባ

ባለንበት ዘመን የብዙዎቻችን ጥረትና ድካም ሰውን ለማስደሰት መሆኑ እሙን ነው። ሰው ከተደሰተ እግዚአብሔር ይደሰታል ብለንም እናምናለን። እውነት ነው ለሌላው በጎ ማሰብ ከዚህ የሚበልጥ በረከት የለም። ነገር ግን የሰው ፍላጎት የማይገታ ስለሆነ ዛሬ ብናስደስተው ነገ ይከፋብናል። ሰው ሲባል ሁሉንም ያጠቃልላል ለምሳሌ ባል ሚስት ልጅ እናት አባት እህት ወንድም ባልንጀራ ወ ዘተ ነገር  ግን እውን ሰውን ደስ ማሰኘት ይቻላል? ሰው ስሜታዊ ነው ስሜት ደግሞ አንድ ጊዜ ይሞቃል አንድ ጊዜ ይቀዘቅዛል።  ብዙ ሰዎች ሰውን ለማስደሰት መልካም ሆኖ መገኘት በቂ መስሏቸው ለሰው ሲሉ የህይዎት መስዋዕትነት እስከ መክፈል ይደርሳሉ ነገር ግን ለሰው ልጅ ዘላቂ ደስታ መስጠት አይችሉም። አንዳንዶች እግዚአብሔርን ፈልገው ሄደው የሰው አገልጋይ የሚሆኑበት ጊዜ አለ። የነዚህ ሰዎች ችግር እግዚአብሄርን መፈለጋቸው ሳይሆን እግዚአብሔርን ፈልጎ ለማግኘት የሚያስፈልገው እምነት እና መንፈሳዊ እውቀት ስለሚጎላቸው ነው። ይህ በመሆኑ ምክንያት ሰዎች ከእግዚአብሔር ጋር እንዳይገናኙ የሚፈልገው ሰይጣን የሰው አገልጋይ ያደርጋቸዋል። ከዚያም ከሰው የሚገጥማቸው ፈተና ደስታቸውን ያርቅባቸዋል። ተስፋ ይቆርጡና እግዚአብሔርን መፈለግ   አቁመው አሰናካይ እስከመሆን ይደርሳሉ። ዛሬ  ከማን ወገን እንደሆኑ በማይታወቁ የበግ ለምድ ለብሰው በመጡ ባህታውያን ነን፣ መነኮሳት ነን ካህናት ነን በሚሉ አስመሳዮች ደስታቸውን ተነጥቀው  በተመሳቀለ መንገድ ላይ የቆሙ ብዙዎች ናቸው። ለሰው ሲሉ ሃይማኖታቸውን የሚቀይሩ፣ ለሰው ሲሉ ከቤተእግዚአብሔር የሚቀሩ፣ ለሰው ሲሉ ከአላማቸው ወደኋላ የሚሉ ወ ዘ ተ ብዙ ናቸው። እነዚህ ሰዎች በራሳቸው መልካም እንዳደረጉ ያስባሉ ። ነገር ግን ለሰው የምናደርገው መልካም ነገር ከእግዚአብሔር ጋር ላለን ግኝኙነት መሰናክል እስካልሆነን ጊዜ ድረስ ብቻ ነው።