Wednesday, April 23, 2014

ሳንጀምር የጨረስነው

ጥንት አባቶቻችን አንድ ነገር ለማድረግ ሲነሱ ከመነሻው መድረሻውን የሚያውቁበት ልዩ ጸጋ ነበራቸው። በዚህም የተነሳ ከመጀመራቸው በፊት ፍጻሜው የት ሊደርስ እንደሚችል ይገምታሉ። በመሆኑም በመንገዳቸው ብዙም ፈተና ቢገጥማቸው ማምለጫውን ያዘጋጃሉ። ስለዚህ ብዙ ከባድ ነገሮችን አልፈው ስኬታማ የሆኑባቸው ነገሮች ብዙ ናቸው።

እኛጋ እያስቸገረን ያለው ነገር ይህ ነው። ምንም ነገር ሳንጀምር መጨረስ እንፈልጋለን። ,, የጅብ ችኩል ቀንድ ይነክሳል ,, እንዲሉ ዘለን አናቱ ላይ መውጣት እንፈልጋለን። በዚህም የተነሳ በድካማችን ውስጥ ስኬት አልባ እንሆናለን። ከመጀመር በፊት ፍጻሜውን መገመት ይገባል። ሁሉ ነገር እና እንዳሰብነው ይሆናል ብሎ መገመት ስህተት ነው። በተለይ የብዙኃን የሆነ ነገር ላይ ውሳኔ ስንወስን በአራቱም አቅጣጫ መመልከት ያስፈልጋል። ቤተክርስቲያን የብዙዎች ነች። ይህን የሚገነዘቡ ግን ጥቂቶች ናቸው። አንዳንዶች ብዙ ገንዘብ ስለከፈሉ፣ አንዳንዶች ብዙ ዘመን ስለቆዩ፣ አንዳንዶች ብዙ ቲፎዞ ስላላቸው ለቤተክርስቲያን እራሳቸውን ብቸኛ አካል አድርገው ለማሳየት ይሞክራሉ ይህ ትልቅ ስህተት ነው። ቤተክርስቲያን እንኳን በ40 በ80 ተጠምቆ ልጅነትን ያገኘባት ይቅርና ለአህዛብም እንኳን በተስፋ እናታቸው ናት። አሁን ሁሉም አትኩሮ ሊመለከተው የሚገባ ይህ ጉዳይ ነው። የቤተክርስቲያን ልጆች ከካህናት እስከ ምዕመናን ድረስ እንደ ባይተዋር ምክንያት እየተፈለገ የሚባረሩበት አካሄድ መስተካከል አለበት ። በእናቱ ቤት ባይተዋር እየተደረገ የሚታይ ልጅ መኖር የለበትም። እድሜ ዘመናቸውን መንፈሳዊ ትምህርት ለመቅሰም ከሃገር ሃገር ሲባዝኑ ኑረው በተማሩት ትምህርት ቤተክርስቲያንን ለማገልገል ሲመጡ ተገቢውን ክብር ማግኘት አለባቸው። የምናውቀውን ሁሉን ብናወራው የማያንጽ ስለሆነ ማለፉ ይሻላል።


በምንኖርበት ሃገር በምድረ አሜሪካ ባሉት የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ አብያተክርስቲያናት የሚታዩት አለመግባባቶች አብዛኞቹ ተመሳሳይነት አላቸው። መነሻቸው አለመደማመጥ ይሆንና መጨረሻቸው መለያየት ነው። ከዚህ የተለየ ችግር ብዙም የለም። የሁሉም ሰው ስሜት ኣና ፍላጎት ተመሳሳይነት አላው። ተቀምጦ መወያየት ስለሌለ ፍላጎትን ማጣጣም አልተቻለም። እንደምንሰማው ሁሉም ለቤተክርስቲያን ተቆርቋሪ ነን ሲሉ ይሰማሉ ነገር ግን የቤተክርስቲያንን ገበና ለመሸፈን ጥረት የሚያደርግ የለም።

የጠላነውን ሁሉ ማጥፋት እንጅ መጀመሪያ ለምን እንደጠላነው፣ በምን እንደጠላነው፣ ቢጠፋ ጉዳቱ ለማን ነው? በመጥፋቱ እኔ ምን እጠቀማለሁ? መኖሩ እኔን ይጎዳኛል? ወ ዘ ተ የሚሉትን ከበጎ ህሊና የሚመነጩ ጥበቦችን አንጠቀምም። በተለይ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የተዛመደን ክፉ መንፈስ ,, የጠላቴ ጠላት ወዳጄ እንደሚባለው ,, የኛ የሆነውን ነገር  የኛ ባልሆነ ነገር  ለመለወጥ  ጥረት ስናደርግ ይታያል። በዚህም የተነሳ እየተጓተትን አንዱ አንዱን ወደ ኋላ እየሳበ አለም በብዙ ነገር ወደፊት ሲጓዝ እኛ ባለንበት እንሮጣለን።

ቅዱስ መጽሐፍ እንደሚነግረን ከማውገዝ በፊት ማስተማር፣ መምከር፣ ማስመከር፣ መገሰጽ የሚቀድሙ ነገሮች ናቸው። እኛ ግን አንድ እርምጃም ቢሆን መጓዝ አንፈልግም በቀጥታ አናቱ ላይ ጉብ ማለት ነው የምንፈልገው። ምክንያቱም እንዚህ ነገሮች በመንፈሳዊ ህይዎት የጠነከረ ስብዕና ለሌለው ሰው እንደ ስምኦን ቀሬናዊ ዓይነት የመስቀል ጉዞ ነው የሚሆኑት። መንፈሳዊ ኃይል ካልተላበሱ መስቀል ተሸክሞ ዳገት መውጣት የማውራት ያህል ቀላል አይደለም።

ብፁዓን አባቶቻችን ከመጀመር ይልቅ መጨረስ የሚለውን መርህ በመከተላቸው በውግዘት ከእግዚአብሔር መንግስት ለይተውን እርስበርሳችን ስንበላላ እንኖራለን ። ,,ያዳቆነ ,,,,,, ሳያቀስ አይተውም,, እንደተባለው ይኸው እስከዛሬ የውግዘት ቀንበር ተጭኖን በጎ እንዳናስብ መልካሙን ነገር ከፊታችን እያሳየ እንዳንሰራው አቅም ያሳጣናል። ታዲያ እንዴት አድርገን በጎውን እንመልከት?  መዝሙረኛው ቅዱስ ዳዊት ,, በጎውን ማን ያሳየናል? የሚሉ ብዙ ናቸው ,, መዝ 4፥6 ።  ብሎ እንደተናገረው በጎ ነገር ጀምሮ መጨረስን ማስተማር የሚገባቸው አባቶች ከአንድነትና ከፍቅር ሽሽት በያዙበት ዘመን እንዴት መልካም ፍሬ ማፍራት ይቻላል? የቤተክርስቲያን ተቀዳሚ ዓላማ ስለ ሁሉ መጸለይ እንደሆነ ቅዱስ መጽሐፍ ይነግረናል።

  እስቲ ከመጨረሳችን በፊት መጀመር እንሞክር፥ ካልጀመርን እያስተካከልን መጓዝ አንችልም። መቸም ሳትጀምሩ ጨርሱ የሚል አስገዳጅ ህግ የወጣብን አይመስለኝም። ሳትፋቀሩ ተጣሉ፣ ሳትነጋገሩ ተለያዩ፣ ሳትማማሩ ተወጋገዙ የሚል ህግ ለኛ ለኢትዮጵያውያን ብቻ ወጣ እንዴ? በጸብ፣ በክርክር፣ በአሉባልታ፣ በጦርነት፣ በመወጋገዝ፣ ወዘተ ያልሞከርነው የዲያቢሎስ ጥበብ የለም። ኪሳራ እንጅ ጥቅም አላገኘንበትም። እስቲ ደግሞ በፍቅር፣ በመወያየት፣ በመተዛዘን፣በመከባበር፣በመተሳሰብ እንሞክረው።

አሁን እየጎዳን ያለው አባቶቻችን የተጓዙበትን በጎ ጎዳና መከተል አለመቻላችን  ነው። ,, አባቶችህ የሠሩትን የቀድሞውን የድንበር ምልክት አታፍልስ,, ምሳ 22፥28  ተብሎ እንደተጻፈው አባቶቻችን ያቆዩልንን የመከባበርና የመተዛዘን መንፈስ ማምጣት አለብን። አንዱ ስለሌላው ይጸልይ ተብሎ እንደተጻፈው ስለ ሁሉ ሳናቋርጥ መጸለይ ይገባናል።

የቤተክርስቲያን ተቀዳሚ ዓላማ ስለ ዓለም በጸሎት በእግዚአብሔር ፊት መቆም ነው። እኛ ግን እያደረግነው አይደለም። እንደውም እያለያየን ያለውn ጉዳይ ይህ ነው። አንዱ ስለሌላው እንጸልይ ይላል, ሌላው አይሆንም ይላል እውነታው ግን ስለ ፍጥረታት በሙሉ መጸለይ እንዳለብን ነው የሚያስረዳን። ስለሌላው ይጸለይ ሲባል። በጎ ስለሚያደርጉ ወይንም እግዚአብሔርን ስለሚያዉቁ ብቻ አይደለም። ክፉ የሚያደርገው ከክፋቱ እንዲመለስ። እግዚአብሔርን የማያውቀው እግዚአብሔርን እንዲያውቅ ልቦና እንዲሰጠው መጸለይ ያስፈልጋል። ለጣኦት ሲያሰግዱ የነበሩት እነናቡከደነጾር በነዳንኤል ጸሎት እግዚአብሔርን ሊያመሰግኑ በቅተዋል። ከዚህ ልንማረው የምንችለው ብዙ ነገር አለ። ለሃይማኖት አባቶችም ሆነ ለሃገር መሪዎች ጸሎት እንዲደረግ አባቶቻችን ያዘዙት። ለሚመሩት ህዝብ ቅን አስተሳሰብ እንዲኖራቸው በጸሎት ለማገዝ ነው። ይህን በማድረጋቸው ለብዙ ዘመናት ሃገራቸውንና ህዝባቸውን አስከብረው ለመኖር በቅተዋል። በውጭው ዓለም ባሉት ምዕመናንና ካህናት ዘንድ የሚታየው ስርዓት እውነተኛዋ ቤተክርስቲያንን የሚወክል ነው ለማለት ያስቸግራል። መቸም ለሁሉም ነገር ገደብ አለው። የሰው እድሜም ይገደባል። የእኛም ስርዓት አልባነት ገደብ ሊኖረው ያስፈልጋል።

ቤተክርስቲያን የክርስቶስ እንደመሆኗ ክርስቶስን መከተል አለባት።i ይህም ማለት የሚወዷትን የሚያከብሯትን ብቻ ሳይሆን የሚያሳድዷትንም ቢሆን በጸሎት ማሰብ አለባት። ጌታ እንዲህ ብሎ እንዳስተማረን ,,, እኔ ግን እላችኋለሁ፥ በሰማያት ላለ አባታችሁ ልጆች ትሆኑ ዘንድ ጠላቶቻችሁን ውደዱ፥ የሚረግሙአችሁንም መርቁ፥ ለሚጠሉአችሁም መልካም አድርጉ፥ ስለሚያሳድዱአችሁም ጸልዩ፤ እርሱ በክፎዎችና በበጎዎች ላይ ፀሐይን ያወጣልና፥ በጻድቃንና በኃጢአተኞችም ላይ ዝናቡን ያዘንባልና። የሚወዱአችሁን ብትወዱ ምን ዋጋ አላችሁ? ቀራጮችስ ያንኑ ያደርጉ የለምን? ወንድሞቻችሁንም ብቻ እጅ ብትነሡ ምን ብልጫ ታደርጋላችሁ? አሕዛብስ ያንኑ ያደርጉ የለምን?እንግዲህ የሰማዩ አባታችሁ ፍጹም እንደ ሆነ እናንተ ፍጹማን ሁኑ,, ማቴ 5፥44 ይህ ለክርስቲያኖች የታዘዘ ማንም የማይሽረው የጌታ ትዕዛዝ ነው። ለጳጳሱም ፣ለካህኑም፣ ለዲያቆኑም፣ ለምዕመኑም የታዘዘ ማለት ነው። ሁላችን ልንጠብቀው እንጅ ልናሻሽለው አንዳች ስልጣን አልተሰጠንም። ታዲያ እኛ ከየት አምጥተነው ነው ለሚወዱን የምንጸልይ ለሚጠሉን የማንጸልይ? ጌታ ለድህነተ ዓለም መስቀል ላይ በዋለበት ሰዓት የተናገረውን እናስብ። ለነማን ይቅርታ እንደጠየቀላቸውም ሲያስተምረን እንዲህ ብሏል ,,  ኢየሱስም፦ አባት ሆይ፥ የሚያደርጉትን አያውቁምና ይቅር በላቸው አለ። ልብሱንም ተካፍለው ዕጣ ተጣጣሉበት። ሕዝቡም ቆመው ይመለከቱ ነበር። መኳንንቱም ደግሞ። ሌሎችን አዳነ፤ እርሱ በእግዚአብሔር የተመረጠው ክርስቶስ ከሆነ፥ ራሱን ያድን እያሉ ያፌዙበት ነበር። ጭፍሮችም ደግሞ ወደ እርሱ ቀርበው ሆምጣጤም አምጥተው። አንተስ የአሁድ ንጉሥ ከሆንህ፥ ራስህን አድን እያሉ ይዘብቱበት ነበር  ሉቃ 23፥34
 
እንደምናምነው ሁላችንም የአንድ እናት ልጆች ነን። ይህን አስፍተን ስንመለከተው መለያየታችን መነቃቀፋችን ስህተት ሆኖ እናገኘዋለን። የስህተታችን መሰረቱ ደግሞ እራስ ወዳድነት ነው። እኔን ብቻ ይድላኝ ማለት ነው። ሌላው ካልጠፋ መኖር የማንችል አድርገን የምናስብ አለን። ይህን ማስወገድ አለብን። ሁሉ እራሱን ለሁሉ ነገር ብቸኛ አድርጎ ይቆጥራል። በኃላፊነት ስንቀመጥ በቅንነት ልናገለግል እንጅ ሁሉን መብት አልባ አድርገን የግል ህይዎታችንን ልናደላድልበት አይደለም። ለእኔ ብቻ የሚለው አባዜ ከኛ መወገድ አለበት። ክፉም ሆነ በጎ ሁሉም ለእናቱ ልጅ ነው። ስለዚህ ሁላችንም ለበቀልንባት ሃገራችን ልጆች ነን።
 
ይህን ለማሰብ ይቅር ባይ ልቦና ሊኖረን ያስፈልጋል። በይቅርታ ካልሆነ በሌላ መንገድ መፍትሔ እናመጣለን ብሎ መድከሙ ከንቱ ነው።
 
መቸም በዓለም ውስጥ እየኖርን ለዓለም የተገለጠውን አላየሁም አልሰማሁም ቢባል ውሸት ነው የሚሆነው። በፖለቲካው ቢሆን፣ በሃይማኖት ቢሆን እንደምንሰማው በሁሉም መልኩ እንደኛ የሚለፋ እንደሌለ እናያለን ።ነገር ግን አስደሳች ነገር ማየት አልቻልንም። ምክንያቱም ደስታን የሚፈጥሩት በጎ አስተሳሰቦች ስለሚጎድሉን ነው። አሁን አሁንማ አዲስ ነገር መፍጠር ትተን አባቶቻችን ለብዙ ዘመን ጠብቀው ያኖሩትን የፍቅር የመከባበር የመደጋገፍ ሰንሰለት ለመበጠስ መታገል ጀምረናል። ዓለም በየጊዜው በሚፈጥረው ቴክኖሎጅ ረሃብን ችግርን ለማጥፋት ደፋ ቀና በሚልበት ወቅት እኛ መፍጠር ቢያቅተን ሌላው በደከመበት እንኳን በፍቅር በአግባቡ መጠቀም ተሳነን።




 

No comments:

Post a Comment