Saturday, April 19, 2014

የይሁዳ ጸጸት

ለሰው ልጅ ከእግዚአብሔር ከተሰጡት ጸጋዎች አንዱ የህሊና ጸጸት ነው። ሰው ከእንስሳት የሚለየውም የሚጸጸት አእምሮ ስላለው ነው። ይህ ልዩ ጸጋ ከእግዚአብሔር የተሰጠው  እንዲጠቀምበት ነበር። ብዙ የእግዚአብሔር ሰዎች በሰሩት ክፉ ስራ ተጸጽተው ወደ እግዚአብሔር በማልቀሳቸው  ይቅርታንና ምህረትን አግኝተዋል። ምሳ 25፥8

የሰው ልጅ የሚጸጸት አእምሮ የተሰጠውም ከበደል የማይርቅ በመሆኑ ነው። ለእንስሳት የሚጸጸት አእምሮ ያልተሰጣቸው ስለማይበድሉ ነው። ህጻናት አእምሮዋቸው ስላላደገ ክፉውንና ደጉን ለይተው አያውቁም። ነገር ግን የስሜት ህዋሳታቸውን ተጠቅመው ምግባቸውን ይመገባሉ። ዕብ 5፥13 እንስሳት አእምሮ የላቸውም ስንል ክፉንና ደጉን ለይተው የሚያውቁበት ማለታችን ነው ። ይህ ሲባል ግን ከእግዚአብሔርም  ሆነ ከሰው   ጋር ባላቸው ግንኙነት የሚግባቡበት የማስተዋያ መንገድ ተስጥቷቸዋል ።  አንዳንድ ጊዜ የሰው አእምሮ መከወን የተሳነውን ነገር እንስሳት ሲያደርጉ የምናስተውልበት ጊዜ አለ። በክፉ ድርጊቶች የሚያለቅሱ እንስሳት አሉ። የተነገራቸውን መልሰው የሚከውኑ አሉ። እንዲሁም አስቀድሞ የሚመጣውን ነገር በድርጊት የሚጠቁሙም አሉ። ይህ ሁሉ አእምሮ የሌላቸው ከምንላቸው እንስሳት የምናስተውለው ነው። በተቃራኒው ሙሉ አእምሮ የተሰጠው የሰው ልጅ ክፉንና ደጉን ለይቶ እያወቀ ከጸጸት እርቆ ሲኖር እናያለን።

በዓለም ላይ በጉልህ የሚታዩ ስህተቶችን እየሰሩ ምንም የመጸጸት ምልክት የማይታይባቸው ሰዎች አሉ። ባለፈው ከመጸጸት ይልቅ ሌላ ስህተት ለመስራት ሲደክሙ ይታያሉ። ለዚህ  ነው ቅዱስ ዳዊት ሰው ከንቱ ነገርን ይመስላል ዘመኑም እንደ ጥላ ያልፋል። እንዲሁም ሰውስ ክቡር ሲሆን አላወቀም አእምሮ እንዳልተሰጣቸው እንስሳት ሆነ ያለው። ,, ሰው ግን ክቡር ሆኖ ሳለ አያውቅም እንደሚጠፉ እንስሶች መሰለ መዝ 49፥12 ,,

ይሁዳ ከሰው ልጆች የላቀ እድል የተሰጠው ሰው ነበር። ቅዱስ መጽሐፍ እንደሚነግረን አስቀድሞ ካባቱ የወረሰው ትዕቢትና ተንኮል ተዛምዶት በሰው ዘንድ አስነዋሪ የሚባሉትን ተግባራት የሚፈጽም ሰው  ነበር። እናቱን ከክብር ያሳነሰ በሰውም ሆነ በእግዚአብሔር የተጠላን ተግባር ይፈጽም የነበረ ሰው ነበር። ሁሉን ቻይ የሆነው መድኃኔዓለም ኢየሱስ ክርስቶስ ያንን ሁሉ በደል ሽሮ እሱን ለክብር ከመረጣቸው ከቅዱሳን ሐዋርያት እናቱን ከ 36ቱ ቅዱሳት አንስት ደምሮ በደሉን ያራቀለት ሰው ነበር። እንደ ይሁዳ እድል ያላገኙ በጥረታቸው እግዚአብሔርን ፈልገው ያገኙ ብዙ ቅዱሳን አሉ። ይሁዳ ግን በተመቻቸ ሜዳ ላይ በትክክል መጓዝ ተስኖት ዲያቢሎስ ባዘጋጀው ወጥመድ ውስጥ ገባ። በተጓዘበት መንገድ እጅግ ተጸጽቶ ለንስሃ ጊዜ በማጣቱ ንስሃ ሳይገባ ሞተ። ከጌታ አጠገብ ከተሰቀሉት ወንበዴዎች አንዱ ለንስሃ ጊዜ አግኝቶ አዳምን ቀድሞት ገነት ሲገባ ይሁዳ ግን የተዘጋችውን ሲኦልን ከፍቶ ገብቷል።በዚያን ጊዜ አሳልፎ የሰጠው ይሁዳ እንደ ተፈረደበት አይቶ ተጸጸተ፥ ሠላሳውንም ብር ለካህናት አለቆችና ለሽማግሎች መልሶ፦ ንጹሕ ደም አሳልፌ በመስጠቴ በድያለሁ አለ። እነርሱ ግን። እኛስ ምን አግዶን? አንተው ተጠንቀቅ አሉ። ብሩንም በቤተ መቅደስ ጥሎ ሄደና ታንቆ ሞተ። ማቴ 27፥5

ነገ የምንጸጸትባቸው ዛሬ ላይ እንደቀላል የምናያቸው ብዙ ነገሮች አሉ። ከይሁዳ ምን እንማር ይሆን? በእጃችን ያለውን እድል መጠቀም? ወይስ የእለታዊ ስሜታችንን መጠበቅ፥ ትላንት እንደቀላል የካብነው የመለያየት ግድግዳ ዛሬ ሰማይ ደርሶ እንኳን ልናፈርሰው ልንነቀንቀው ተስኖናል። አባቶቻችን እንደቀላል የፈጠሩት አለመግባባት ከራሳቸው አልፎ ለትውልድ የሚተርፍ ሆኗል። ዛሬ በምድረ አሜሪካ በሰላም መንፈሳዊ አገልግሎት የሚከናወንባቸው አብያተክርስቲያናት ጥቂቶች ናቸው። የትላንትናው ስህተት ጸጽቷቸው ለማስተካከል በሚሞክሩ አባቶች የተነሳ ሁከት በቤተክርስቲያናችን ነግሷል። ዛሬ ላይ መጸጸታቸው መልካም ነበር። ነገር ግን የይሁዳ ጸጸት ሆነና ውጤት አልባ እየሆነ ነው። ጥንቱኑ ለምን ብለው ይህን የስህተት መንገድ እንደ ጀመሩት እግዚአብሔር ይወቀው። መቸም ህዝቡ ዛሬ ላይም ቢሆን ያልተመለሰለት ጥያቄ አለ።
እውነት በትክክል የሚጸጸት ልቦና ካለን ዛሬ ነው ማዘን ያለብን። ይህ የዋህ ምዕመን ትላንትና ያባቶቹን የእግር ጫማ ለመሳም ይጋፋ የነበረ መሆኑ ይታወቃል። ታዲያ ዛሬ ምን ነክቶት ነው አባቶቹን በአስነዋሪ ስድቦች እያጀበ የሚቀበለው? እውነት የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ምዕመን አባቶቹን ባለማክበር ይታማል? ዛሬ መናፍቃን የሚተቹት እኮ የአባቶቹን ክብር አውቆ ተረድቶ ከነሱ የሚገኘውን በረከት ለመሻማት ከእግራቸው ትቢያ ስር ሲወድቅ ሲነሳ በመገኘቱ ነው። ከላጅ አባቶቹ የበለጠ የቤተክርስቲያን አባቶቹን የሚያከብር ህዝብ እንደነበር ታሪክ ይመሰክርለታል። እና ግን ይህን የዋህነቱን ተጠቅመን ወደ ተሳሳተ መንገድ መራነው። የቀደመችይቱን መንገድ ተከትሎ እንዳይሄድ የማሰናከያ ድንጋይ አኖርንበት። በበጎ ነገር ፈንታ  ከእግራችን በታች አስቀምጠን ያስተማርነው ወንጌል ሳይሆን አሳልፎ መሰጣጠትን ነው። ስለዚህ ዛሬ ልንጸጸት ያስፈልጋል።
ትልቋን ቤተክርስቲያን የማይመጥኑ የቤተክርስቲያን ኃላፊዎችን አለቦታቸው በተለያየ መንገድ እያስቀመጥን ለዓለም የሚተርፉ በየአድባራቱና ገዳማቱ አንቱ የተባሉ ሊቃውንትና መምህራን እያሏት ለመንጋው የማይራሩትን ጨካኞቹን ከፊት እያሰለፍን ትውልዱን እያስለቀስን ተስፋ ቆርጦ እቤቱ እንዲቀር እያደረግነው ነው። ምግብና ውሃ በሌለበት በጾምና በጸሎት በየጉባኤ ቤቱ እድሜ ዘመናቸውን ቃለ እግዚአብሔር በመቅሰም የሚያሳልፉ እውነተኛ የቤተክርስቲያን ልጆች እናታቸው የምትሰጣቸው ሳታጣ ነገር ግን በቤቷ የሚያዙት ግድ የሌላቸው በመሆናቸው ጥቂቷን ቀሪ ዘመናቸውን በየመንግስት መስሪያ ቤቱ የባለስልጣንን ጉልበት ሲስሙ ይውላሉ።  

እኛ ማድረግ የነበረብንን እግዚአብሔር በጊዜው አስነስቶ ለወደፊት ለቤተክርስቲያን ተተኪ በማፍራት ላይ የሚገኙትን የቤተክርስቲያን ልጆች መንከባከብና መርዳት ሲገባ ለቤተክርስቲያንና ለሃገር የሚጠቅም ጉልህ ስራ ሲሰሩ እየታየ አንገታቸውን ለማስደፋት የሚደረገው ጥረት መቆም አለበት። ይህን ደግሞ ሊያስቆሙ የሚችሉት የቤተክርስቲያኒቱ የበላይ መሪ አስተዳዳሪ የሆነው የቅዱስ ሲኖዶስ አባላት ሊቃነ ጳጳሳት ናቸው። ስለነገዋ ቤተክርስቲያን እምናስብ ከሆነ ይህን ማድረግ ይጠበቅብናል። አለበለዚያ ዛሬ ላይ እንደቀልድ እያመለጡን የሄዱት እድሎች እንደሚጸጽቱን ሁሉ ነገም የይሁዳን ጸጸት ብንደግመው ዋጋ አይኖረውም።
አንዳድንድ ሰዎች ከማስተዋል እጥረት የተነሳ የኢትዮጵያ እናትነት ለነሱ ብቻ፤ ቤተክርስቲያንንም የእነሱ ብቻ አድርገው የሚያስቡ አሉ። ይህ ስህተት ነው። ሃገራችንም ሆነች ቤተክርስቲያናችን የጋራችን ነች። የሃገራችንም ሆነ የቤተክርስቲያናችን ልጅ የሆነው ሁሉ ወገናችን ነው። አሁን የሚያስፈልገን ይህን የምንረዳበት አእምሮ ነው። አሁን በጭው ዓለም ባሉት አብያተክርስቲያናት ዘንድ አላግባባ እያለያየን ያለው ለወገኖቻችን መጸለይ እንደ አዲስ ነገር ቆጥረነው ነው። ይህ የሚያሳየው ምን ያህል የቤተክርስቲያንን ዓላማ እንደዘነጋነው ነው። የቤተክርስቲያን ዓላማ እኮ እንኳን ለወገን ይቅርና ለመላው ዓለም መጸለይ ነው።

ጌታ ያስተማረን እኮ ለጠላቶቻችን እንድንጸልይ ነው። አባቶቻችን ጽፈው ያስቀመጡልን እኮ ከዚህ የተነሳ ነው። ስለዚህ በዚህ መጣላት የለብንም። በጎ ለምንላቸው ብቻ ሳይሆን ክፉ ለምንላቸውም መጸለይ ይገባናል። ጌታ በወንጌል ,,, እኔ ግን እላችኋለሁ፥ በሰማያት ላለ አባታችሁ ልጆች ትሆኑ ዘንድ ጠላቶቻችሁን ውደዱ፥ የሚረግሙአችሁንም መርቁ፥ ለሚጠሉአችሁም መልካም አድርጉ፥ ስለሚያሳድዱአችሁም ጸልዩ፤ እርሱ በክፎዎችና በበጎዎች ላይ ፀሐይን ያወጣልና፥ በጻድቃንና በኃጢአተኞችም ላይ ዝናቡን ያዘንባልና።የሚወዱአችሁን ብትወዱ ምን ዋጋ አላችሁ? ቀራጮችስ ያንኑ ያደርጉ የለምን?ወንድሞቻችሁንም ብቻ እጅ ብትነሡ ምን ብልጫ ታደርጋላችሁ? አሕዛብስ ያንኑ ያደርጉ የለምን?እንግዲህ የሰማዩ አባታችሁ ፍጹም እንደ ሆነ እናንተ ፍጹማን ሁኑ። ማቴ 5፥44

ሃገራችን ሃገረ እግዚአብሔር እየተባለች ለብዙ ዘመናት የቆየችው በቅዱሳን አባቶቻችን ለትውልድ በተረፈ በጎ ስራና ተጋድሎ መሆኑ ይታወቃል። ለዚያም ነው ህዝቡ ዛሬ ድረስ የረገጡትን አፈር እየላሰ ከደዌው የሚፈወሰው። እንኳን በህይዎት እያሉ ዛሬም ላይ የእነሱን የህይዎት ታሪክ እየሰማ ነው እግዚአብሔርን የሚያመሰግነው። በዘመናቸው የሚያሳዝን ነገር ሳይገጥማቸው ቀርቶ ሳይሆን አስቀድመው ስለሚመጣው ነግር ስለሚጸጸቱ ነበር።

ሰው ክፉ ስራ ሊሰራ ሲነሳ በሌላው ላይ የሚያደርሰውን በደል አስቦ መጸጸት ካልቻለ እሱ የእግዚአብሔር ልጅ ሊባል አይችልም። ወንጌላዊው ቅዱስ ዮሐንስ በመልእክቱ  ,, በብርሃን አለሁ የሚል ወንድሙንም የሚጠላ እስከ አሁን በጨለማ አለ። ወንድሙንም የሚወድ በብርሃን ይኖራል ማሰናከያም የለበትም፤ ወንድሙን የሚጠላ ግን በጨለማ አለ፥ በጨለማም ይመላለሳል፥ የሚሄድበትንም አያውቅም፥ ጨለማው ዓይኖቹን አሳውሮታልና። 1ኛ ዮሐ 2፥9 ይላል ስለዚህ ከፊታችን ያለውን የጨለማ ግድግዳ ልናስወግድ ይገባል። ዛሬ ላይ ሁላችንም ልንታከም የሚገባው እራሳችንን ነው። ሰው አእምሮው በትክክል ሳይሰራ የእግር እባጭ አስወግዳለሁ ቢል ጥቅም የለውም። አሁን እኛ ሁላችን የታመምነው እራሳችንን ነው። አባቶቻችን ለእኛ እራሶቻችን ናችሁ። ያለእናንተ ህልውናችን ዋስትና የለውም።
አባቶቻችን  በየምክንያቱ የውግዘት ደብዳቤ ከመጻፋችሁ በፊት የህዝቡን ጥያቄ መልሱ። ህግ አክብሩ ለማለት እናንተ ህግ አክባሪዎች ሁኑ። እኛ እንድንወዳችሁ እናንተ ተዋደዱ። ስለፍቅር ስታስተምሩን በውግዘት ሰይፍ እያስፈራራችሁ ሳይሆን እንደ ክርስቶስ እግራችንን እያጠባችሁ መሆን አለበት። እግዚአብሔርን በየት በኩል እንየው? ከሐዋርያት የተማርነው,,,  ወዳጆች ሆይ፥ ፍቅር ከእግዚአብሔር ስለ ሆነ፥ የሚወደውም ሁሉ ከእግዚአብሔር ስለ ተወለደ እግዚአብሔርንም ስለሚያውቅ፥ እርስ በርሳችን እንዋደድ።ፍቅር የሌለው እግዚአብሔርን አያውቅም፥ እግዚአብሔር ፍቅር ነውና። 1ኛ ዮሐ 4፥7,,  የሚል ነው ። ታዲያ ተፋቅራችሁ አሳዩና። አሁን ላለንበት ችግር  ምክንያቱ የእናንተ አለመስማማት ነው። በዚህ አካሄድ የምንጓዝ ከሆነ ትልቁን የመንፈስ ቅዱስ መሳሪያ ቃለ ውግዘት አለቦታው በጠቀም አቃለን በኋላ ማጠፊያው እንዳያጥረን።  

አባቶቻችን እስቲ የልጆቻችሁን ልመና ስሙን። ተው በኋላ ይቆጫችኋል ይህች ቤተክርስቲያን በእናንተ ዘመን በተፈጠረ ስህተት የመናፍቃን መሳለቂያ አትሁን፤ ዛሬ እንደ ቀላል የሚታየው ነገር እያደገ ሄዶ ነገ ኦርቶዶክሳዊ ነኝ ማለት የሚያሳፍርበት ዘመን እንዳይመጣ፤ ስለይሁዳ ስናወራ ከይሁዳ ሳንማር ቀርተን አጉል ጸጸት የማይጠቅም ልቅሶ እንዳነለቅስ፤ ዛሬ ላይ ካህኑን በውግዘት ምዕመኑን ከመንፈሳዊ አገልግሎት በማራቅ እያሳደድን ሰላም ለማምጣት የምናደርገው ጥረት የትም አያደርስም።


 የትንሳኤው ጌታ መድኃኔዓለም ኢየሱስ ክርስቶስ ለፍቅር፣ ለሰላም አልነሳ ያለውን ልቦናችንን ያስነሳልን።





No comments:

Post a Comment